የደስተኝነት መንገድ . . የሰው ልጅ ከራሱ፣ከሕይወትና ከፍጥረተ ዓለሙም ጋር የሚያደርገው እርቅ ነው፦

የደስተኝነት መንገድ . . የሰው ልጅ ከራሱ፣ከሕይወትና ከፍጥረተ ዓለሙም ጋር የሚያደርገው እርቅ ነው፦

1-የሰው ልጅ

ከምን ተፈጠረ?!

አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱ ያ ከዐፈር፣ከዚያም ከፍትወት ጠብታ፣ከዚያም ከረጋ ደም፣የፈጠራችሁ ነው። ከዚያም ሕጻናት አድርጎ ያወጣችኋል፤ከዚያም ጥንካሬያችሁን ትደርሱ ዘንድ፤ከዚም ሽማግሌዎች ትኾኑ ዘንድ፣(ያቆያችኋል)፤ከናንተም ውስጥ ከዚህ በፊት የሚሞት አለ፤(ይህንንም ያደረገው ልትኖሩና) የተወሰነ ጊዜንም ልትደርሱ፣ታውቁም ዘንድ ነው። }[አል ሙእሚን፡67]

አዎ . . የተፈጠረው ከአፈርና ከጠብታ ውሃ ሲሆን መጨረሻው በድን ሬሳ መሆን ነው። በውስጡ ቆሻሻ ተሸክሞ ይሄዳል፤ከአካላቱ የሚወጡ ነገሮችን ሁሉ ይጸየፋል። ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ፈጣሪ ጌታውን ተሟጋች ይሆናል፤ሰው ከሓዲነቱም ከፋ!! አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሰው ተረገመ፤ምን ከሓዲ አደረገው? (ጌታው) ከምን ነገር ፈጠረው? (አያስብምን?) ከፍትወት ጠብታ ፈጠረው፤መጠነውም። ከዚያም (መውጫ) መንገዱን አገራው። ከዚያም ገደለው፤እንዲቀበርም አደረገው። ከዚያም (ማንሳቱን) በሻ ጊዜ ያስነሳዋል።}[ዐበሰ፡17-22]

ከዚህ ሁሉ ጋር ግን ከተቀሩት ፍጥረታት ሁሉ ክቡር ፍጡር ተደርጓል። አላህ (ሱ.ወ.) መላእኮችን ለአባቱ ለኣደም እንዲሰግዱ አዟል። ምድሪቱና እንስሳትን ለርሱ አገልግሎት የተገሩ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ተአምር መስራት የሚችል አእምሮም ለግሶታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የኣደምንም ልጆች በእርግጥ (ከሌላው ፍጡር) አከበርናቸው፤በየብስና በባሕርም አሳፈርናቸው፤ከመልካሞችም (ሲሳዮች ሰጠናቸው)፤ከፈጠርናቸውም ፍጡሮች በብዙዎቹ ላይ ማብለጥን አበለጥናቸው።}[አል እስራእ፡70]

እናም የሰውን ልጅ ስረ መሠረት መረዳት የሚቻለው እነዚህን ሁለት እውነታዎች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው። በዚህ ግንዛቤ መሰረትም የሰው ልጅ የሚያስመዘግበው ድል፣ክብር፣ዕድገት፣ሀብት፣ዕውቀትና ሌላውም ስኬት አላህ (ሱ.ወ.) ከቸረው ጸጋ ብቻ የተገኘ መሆኑን በማመን ላይ የሚመሰረተው ምዘና ትክክለኛው ምዘና ይሆናል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ማንኛውም በናንተ ላይ ያለው ጸጋ ከአላህ ነው፤ከዚያም ችግር በደረሰባችሁ ጊዜ፣ወደርሱ ብቻ ትጮኻላችሁ።}[አል ነሕል፡53]

የሰው ልጅ በራሱ የሥጋና የአጥንት ክምር እንጂ ሌላ ምንም አይደለም። ምጥቀቱ የሚመጣው በጠቃሚ ዕውቀትና በመልካም ሥራ የማነጽና የማሰልጠን ግዴታ ባለበት ነፍሱ በኩል ነው። ሰው ደካማና አቅም የለሽ ከመሆኑም ጋር አላህ (ሱ.ወ.) ግን ለተቀሩት ሌሎች ፍጥረታት አቅርቦ መሸከም ያልቻሉትን አማና (ኃላፊነት) መቀበልና መሸከም የሚያስችሉ ባሕርያትን አጎናጽፎታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እኛ አደራን በሰማያትና በምድር፣በተራራዎችም ላይ አቀረብናት፤መሸከሟንም እንቢ አሉ፤ከርሷም ፈሩ፤ሰውም ተሸከማት፤እርሱ በጣም በደለኛ ተሳሳች ነውና።}[አል አሕዛብ፡72]

የሰው ልጅ በእምነቱ እነዚህን ሁለት እውነታዎች የማመጣጠንና የማመዛዘን መስፈርት ካጓደለ፣ትኩረቱ በሙሉ ወደ መጀመሪያው እውነታ ብቻ ይሆንና ራሱን እንደ እንስሳት ሆዱንና ሥጋዊ ፍላጎቶቹን ብቻ ከማርካት ያለፈ ሌላ ዓለማ የሌለው ፍጡር አድርጎ በመውሰድ ሰብእናውን ያዋርዳል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያም የካዱት፣(በቅርቢቱ ዓለም) ይጣቀማሉ፤እንስሳዎች እንደሚበሉ ይበላሉ፤እሳትም ለነርሱ መኖሪያቸው ናት።}[ሙሐመድ፡12]

ወይ ደግሞ ሁለተኛው እውነታ አእምሮውን አሸንፎ ወደ መኩራራት ወደ እብሪትና ልኩን ወደ ማለፍ ይወስደውና ወደ ፈጣሪ ጌታው ተመላሽ መሆኑን ያዘናገዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በውነቱ ሰው ወሰንን ያልፋል፤ራሱን የተብቃቃ (ባለ ሀብት) ኾኖ ለማየቱ። መመለሻው ወደ ጌታህ ብቻ ነው።}[አል ዐለቅ፡6-8]

ስለዚህም የሰው ልጅ የራሱን ደረጃ አውቆ ከራሱ ጋር መታረቅ ይኖርበታል። በዚህ የተነሳ ከሰው ልጅ የደስተኝነት እጦት ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ራሱን አለማግኘቱና በሕብረተሰቡ ውስጥ ቦታው የት እንደሆነ አለማወቁ ነው። በመሆኑም ማንነቱን፣ሚናውን ስፍራውንና ምን ማበርከት እንደሚችል አያውቅም። (5)

ለምን ዓላማ ተፈጠረ?!

አላህ (ሱ.ወ.) ፍጥረታትን ሁሉ ፈጥሯል። የፈጠራቸውም ፈጽሞ እንዲሁ ለከንቱ አይደለም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የፈጠርናችሁ ለከንቱ መኾኑን እናንተም ወደኛ የማትመለሱ መኾናችሁን ጠረጠራችሁን? (ለከንቱ የፈጠርናችሁ መሰላችሁን?)።}[አል ሙእምኑን፡24]

የፈጠራቸው፣በጸሎት ስነ ሥርዓቶች ብቻ ሳይወሰን፤የሰውን ሥራ፣ጨዋታውንና ቀልዱን ሳይቀር ሙሉ ሕይወቱን በሚሸፍነው፣ በተሟላው አጠቃላይ የአምልኮተ አላህ (ዕባዳ) ትርጓሜ መሰረት፣እርሱን እንዲያመልኩና እርሱን ብቻ እንድግገዙት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ጋኔንና ሰውንም፣ሊገዝዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።}[አል ዛሪያት፡56]

ይህን የማያውቅ ሰው ግን በዚህ አለማወቅ እንደተሰቃየ፣ሕይወቱንም በጥርጣሬና በግራ መጋባት ጽልመት እንዳደበዘዘ መኖሩን ይቀጥላል። ለርሱ ዕባዳና ደስተኝነት የተነጣጠሉ፣ዕባዳ ከዓለማዊ ሕይወቱ ጉዳዮች ጋር፣የዛሬው ዓለም ሕይወትም ከወዲያኛው ሕይወት (ከኣኽራ) ጋር ያልተያያዘ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) በሰማያትና በምድርም ያሉትን ሁሉ ለሰው ልጆች የተገሩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለናንተም በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ በመላ ከርሱ ሲኾን የገራላችሁ ነው፤በዚህ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ታምራት አለበት።}[አል ጃሢያህ፡13]

የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ ከምድሪቱና ከራሱ ከሰው እውነተኛ ባለንብረት በኩል፣ለመፈተኛና ለሙከራ ተተኪና ተጠሪው (ኸሊፋ) ተደርጎ ተሹሟል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱም ያ በምድር ምትኮች ያደረጋችሁ፣በሰጣችሁም ጸጋ ሊፈትናችሁ ከፊሉን በከፊሉ ላይ በደረጃዎች ከፍ ደረገ ነው፤ጌታህ ቅጣቱ ፈጣን ነው፤እርሱም እጅግ መሓሪ ርኅሩህ ነው።}[አል አንዓም፡165]

2-ሕይወት፦

የሰው ልጅ የተፈጠረበትን እውነታ ከተረዳ በኋላ፣ከርሱ ጋር ተፈጥሯዊ ቁርኝ ያላት ሕይወት ምንነቷን ለማወቅ ነፍሱ ትቋምጣለች። ሕይወት የዓለማዊ ደስታዎችና መደሰቻዎች ሁሉ መሰረት እንደ መሆኗ፣ነፍስ የምትፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ የማግኘት ተስፋ የተንጠለጠለው በርሷ ላይ ነው። ለመሆኑ የሕይወት ዓለማ ምንድን ነው?! ሕይወትና ሞት የተፈጠሩበት ዓለማ ማንኛው ሰው የተሻለ መልካም ሥራ እንደሚሠራ ለመፈተን ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መኾኑን ሊሞክራችሁ፣ሞትንና ሕይወትን የፈጠረ ነው፤እርሱም አሸናፊው መሓሪው ነው።}[አል ሙልክ፡2]

ይህ እውነታው ነው፤ብዙ ሰዎች ግን አያውቁትም!! አዎ፣ይህ ይህች ዱንያ የተፈጠረችበት ምስጢርና ጥበብ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የቅርቢቱ ሕይወት ምሳሌ (ጊዜዋ በማጠርና በመጥፋት) ከሰማይ እንዳወረድነው ውሃ፣በርሱም ሰውና እንስሳዎች ከሚበሉት የምድር በቃይ ተቀላቅሎበት (እንደ ፋፋ)፣ምድርም ውበትዋን በያዘችና ባጌጠች ጊዜ፣ባለቤቶቿም በርሷ ላይ እነርሱ ቻዮች መኾናቸውን ባሰቡ ጊዜ፣ትእዛዛችን ሌሊት ወይም ቀን መጥቶባት፣ትላንት እንዳልነበረች የታጨደች፣እንዳደረግናት ብጤ ነው፤እንደዚሁም ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች አንቀጾችን እናብራራለን።}[ዩኑስ፡24]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

የቅርቢቱን ሕይወት ምሳሌ አውሳላቸው፤(እርሷ) ከሰማይ እንዳወረድነው ውሃ፣በርሱም የምድር በቃይ እንደ ተቀላቀለበት፣(ከተዋበ በኋላ ደርቆ) ነፋሶችም የሚያበኑት ደቃቅ እንደ ኾነ ብጤ ናት፤አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው።}[አል ከህፍ፡45]

ዛሬ የምንኖረው ሕይወታችን መተላለፊያ እንጂ ቋሚ የመኖሪያ ስፍራችን አይደለም። ወደ ወዲያኛው የኣኽራ ዘላለማዊ ሕይወት የምታደርሰን መሸጋገሪያ ድልድይ ናት። በመሆኑም ሕይወት በዚህች ዓለም ፍጻሜ አታበቃም፤እውነተኛው የኣኽራ ዘላለማዊ መጭ ሕይወት አለ። የቅርቢቱ ዓለማዊ ሕይወት አላህ (ሱ.ወ.) እንዳለው ሁሉ ጨዋታና ዛዛታ፣ማጌጫና እርስበርስ መፎካከሪያ ብቻ ናት። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ቅርቢቱ ሕይወት፣ጨዋታና ዛዛታ፣ማጌጫም፣በመካከላችሁም መፎካከሪያ፣በገንዘቦችና በልጆችም ብዛት መበላለጫ ብቻ መኾንዋን ዕወቁ፤(እርሷ) በቃዩ ገበሬዎችን እንደሚያስደስት ዝናም፣ከዚያም በቃዩ እንደሚደርቅና ገርጥቶ እንደሚታየው፣ከዚያም የተሰባበረ እንደሚኾን ብጤ ናት፤በመጨረሻይቱም ዓለም፣ብርቱ ቅጣት፣ከአላህም ምሕረትና ውዴታ አልለ፤የቅርቢቱም ሕይወት መታለያ ጥቅም እንጅ ሌላ አይደለችም።}[አል ሐዲድ፡20]

ይህ ቁርኣናዊ አንቀጽ የቅርቢቱን ዓለም ሕይወት በጥቅሉ ደረጃዋን በሚያጣጥል፣በሰው አእምሮ ውስጥ ቦታ በሚያሳጣት አገላለጽ፣የሰው ልጅን ከኣኽራ ሕይወትና ከፋይዳዎቹ ጋር ራሱን እንዲያስተሳስር በሚያደርግ ሁኔታ ያቀርባል። የቅርቢቱ ሕይወት በራሷ ሚዛን ስትለካ ለዓይንና ለእይታ እጅግ የገዘፈ ታላቅ ነገር ሆና ትታያለች። በግዙፉ ዩኒቨርስ ውስጥ ካላት ቦታ አንጻር ስትለካና በኣኽራ ሚዛን ስትመዘን ግን እዚህ ግቢ የማትባል አልባለ ተራ ነገር፣ጨዋታና ዛዛታ፣ማጌጫና በሰዎች መካከል መፎካከሪያ ብቻ ነች። በቁም ነገር የተሞላች፣ትኩረትና ቀልብን በእጅጉ የምትስብ የምር ነገር መስላ ከመታየቷ ጀርባ ያለው እውነታ ግን ይኸው ነው። አዎ . . ይህ የቅርቢቱ ዓለም ሕይወት እውነታ ነው . . እውነታን ለመፈለግ በጥልቀት ሲጓዝ አእምሮ የሚደርስበት እውነታ ነው። ቁርኣን ይህን ሲል ከዓለማዊ ምድራዊ ሕይወት መገለልን፣ምድርን ለሰው ልጆች አገልግሎት መግራትንና ማልማትን፣ወይም የሰው ልጅ የምድር ተጠሪነት ግዴታውን ችላ ብሎ እንዲተው መፈለጉ አይደለም። በዚህ አገላለጹ የሚያነጣጥረው፣የስሜታዊና ስነልቦናዊ እሴቶችን መስፈርቶች በማረም፣በአላፊ ጊዜያዊ ደስታዎች ከመሸንገልና ከመንፈሳዊ ምጥቀት አስሮ ከሚያስቀረው መስሕብነታቸው በማስጠንቀቅ ላይ ነው። ይህች ሕይወት ፍጥረታት ወደ ወዲያኛው የኣኽራ ዘላለማዊ ሕይወት በሚያደርጉት ጉዞ የሚሸጋገሩበት ድልድይ ብቻ ናት። የዚህች ዓለም ሕይወት አጭር ዕድሜና በፍጥነት ማለፍ ቀጥሎ ከሚመጣው ዘላለማዊነት ጋር ሲነጻጸር ከምንም የሚቆጠር አይደለም። የወዲያኛው ዓለም ሕይወትም በበኩሉ አንድ ሰው በዚህች የመጀመሪያ ሕይወቱ በሚያሳልፈው ሁኔታ ላይ የተሞረኮዘ ነው። እናም ዓለማዊ ሕይወቱን የሚያሳልፈው በማያቋርጥ የመፈተኛ ሂደት ውስጥ ነው ማለት ነው። በዙሪያው የሚመለከታቸው መደሰቻዎች፣አዝናኝና አርኪ ነገሮችም ሆኑ አሳዛኝ፣አሰቃቂና አስጨናቂ ነገሮች ሁሉ ቋሚነት የሌላቸው ቶሎ የሚያበቁ አላፊ ነገሮች እንጂ ሌላ አይደሉም። ነገ ሁሉም ከነዝርዝር ይዘቶቻቸው ተመዝነው የፈጻሚ እጆችን የመጨረሻ ዕድል ይወስናሉ። የሥራዎች ዋጋ እንጂ አብሮ ወደ መቃብር የሚወርድ ሌላ ምንም ነገር የለም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{መጀመሪያም ጊዜ እንደ ፈጠርናችሁ ኾናችሁ፣የሰጠናችሁን ሁሉ በጀርባዎቻቸው ኋላ የተዋችሁ ስትኾኑ፣ለየብቻችሁ ኾናችሁ በእርግጥ መጣችሁን፤እነዚያንም እነሱ በናንተ ውስጥ (ለአላህ) ተጋሪዎች ናቸው የምትሉዋቸውን አማላጆቻችሁን፣ከናንተ ጋር አናይም፤ግንኙነታችሁ፣በእርግጥ ተቋረጠ፤ከናንተም ያ (ያማልደናል) የምትሉት ጠፋ፣(ይባላሉ)።}[አል አንዓም፡94]

አብዛኞቹ ሰዎች ግን ከዚህ እውነታ የተዘናጉ ናቸው። ይህንኑ በማስመልከት አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከቅርቢቱ ሕይውት ግልጹን ብቻ ያውቃሉ፤እነርሱም ከኋላኛይቱ ዓለም እነርሱ ዘንጊዎች ናቸው።}[አል ሩም፡7]

በዚህች አላፊ ሕይወት ረክቶና ወዶ ከፈጣሪ ጌታ ጋር መገናኘትን የማይፈራ ሰው እንዴት ይሆን?! አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያ መገናኘታችንን የማይፈሩ፣ቅርቢቱንም ሕይወት የወደዱ፣በሷም የረኩ፣እነዚያ እነሱ ከአንቀጾቻችን ዘንጊዎች የኾኑ፣እነዚያ ይሠሩት በነበሩት ምክንያት መኖሪያቸው በእሳት ውስጥ ነው።}[ዩኑስ፡7-8]

ኣኽራን ትቶ ቅርቢቱንም ሕይወት የመረጠ ሰውስ ምን ይዋጠው?! አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የካዳ ሰውማ፣ቅርቢቱንም ሕይወት የመረጠ፣ገሀነም እርሷ በእርግጥ መኖሪያው ናት። በጌታው ፊት መቆምን የፈራ ሰውማ፣ነፍሱንም ከዝንባሌዋ የከለከለ፣ገነት እርሷ በእርግጥ መኖሪያው ናት።}[አል ናዝዓት፡37-41]

አዎ፣ሃይማኖታቸውን መሳለቂያና መጫወቻ አድርገው የያዙና በቅርቢቱ ሕይወት የተሸነገሉ ናቸውና አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያ ሃይማኖታቸውን መሳለቂያና መጫወቻ አድርገው የያዙ፣የቅርቢቱም ሕይወት ያታለለቻቸው፣ይህንን ቀናቸውን መገናኘትን እንደረሱ፣በተአምራታችንም ይክዱ እንደ ነበሩ፣ዛሬ እንረሳቸዋለን።}[አል አዕራፍ፡51]

አዎ፣የአላህ መንገድ መጥመሙንም የሚፈልጉ ናቸውና። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያ የቅርቢቱን ሕይወት ከመጨረሻይቱ ሕይወት ይበልጥ የሚወዱ፣ከአላህም መንገድ የሚያግዱ፣መጥመሙዋንም የሚፈልጉ ናቸው፤እነዚያ በሩቅ ስሕተት ውስጥ ናቸው።}[ኢብራሂም፡3]

ይህ ሁሉ ሲባል ግን የሰው ልጅ ሕይወትን በንቀት ዓይን ይመልከት፣በዕውቀትና በሥራ ምድርን ከማልማት ተቆጥቦ በችጋር እንደ ተቆራመደ ሞቱን ይጠብቅ ማለት አይደለም። ፈጽሞ እንዲህ ማለት አይደለም። ተፈላጊው ነገር የዓለማዊ ሕይወት አነዋዋርን አላህ ባስቀመጠው መንገድ ብቻ ማስኬድ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም በሰጠህ ሀብት የመጨረሻይቱን አገር ፈልግ፤ከቅርቢቱም ዓለም ፋንታህን አትርሳ፤አላህም ወደ አንተ መልካምን እንዳደረገልህ (ለሰዎች) መልካምን አድርግ፤በምድርም ውስጥ ማጥፋትን አትፈልግ፤አላህ አጥፊዎችን አይወድምና፣(አሉት)።}[አል ቀሶስ፡77]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከማንኛውም ነገር የተሰጣችሁት፤የቅርቢቱ ሕይወት ጥቅምና፣ጌጧ ነው፤አላህ ዘንድ ያለውም (ምንዳ) በጣም በላጭና ዘውታሪ ነው፤አታውቁምን?}[አል ቀሶስ፡60]

በዚህ የተሟላ እሳቤ መሰረት የሰው ልጅ ዓለማዊ ሕይወትን ሊጠቀምበት የሚገባው፣እንደ ውድ መገልገያ መሳሪያ ብቻ ይሆናል። በትክክለኛ መሰረታዊ ምንነቷ ግን ለዘላለማዊው ተድላ የመሸጋገሪያ ድልድይ ከመሆን ያለፍፈ ትኩረት ሊሰጣት አይገባም። በዚህ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙት አላፊ ዓለማዊ ደስታዎች፣ብልልጭ ጊዜያዊ የእርካታ መጠቀሚያዎችና ጌጦች ብቻ ናቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከሴቶችና ከወንዶች ልጆችም፣ከወርቅና ከብር፣ከተከማቹ ገንዘቦችም፣ከተሰማሩ ፈረሶችም፣ከግመል፣ከከብትና ከፍየልም፣ከአዝመራም የኾኑ ፍላጎቶችን መውደድ፣ለሰዎች ተሸለመ፤ይህ ሁሉ የቅርቢቱ ሕይወት መጠቀሚያ ነው፤አላህም እርሱ ዘንድ መልካም መመለሻ (ገነት) አለ።}[ኣሊ ዒምራን፡14]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ገንዘብና ወንዶች ልጆች፣የቅርቢቱ ሕይወት ጌጦች ናቸው፤መልካሞቹም ቀሪዎች (ሥራዎች)፣እጌታህ ዘንድ በምንዳ በላጭ ናቸው፤በተስፋም በላጭ ናቸው።}[አል ከህፍ፡46]

ዓለማዊ መጠቀሚያዎችም በታዘዘው ተገቢ መንገድ አገልግሎት ላይ እስከ ዋሉ ድረስ በራሳቸው የተጠሉ አይደሉም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{፦ የአላህን ጌጥ፣ያችን ለባሮቹ የፈጠራትን፣ከሲሳይም ጥሩዎቹን፣እርም ያደረገው ማን ነው? በላቸው፤እርሷ በትንሣኤ ቀን ለነዚያ ላመኑት ብቻ ስትኾን፣በቅርቢቱ ሕይወት፣ተገቢያቸው ናት በላቸው፤እንደዚሁ አንቀጾችን እናብራራለን።}[አል አዕራፍ፡32]

አንድ ሙስሊም በዚህች ዓለም ላይ ያገኘው ሀብትና ንብረት፣ያጋጠመው ደስታና ሀዘንም ቋሚ አለመሆኑን በእርግጠኝነት ካረጋገጠ በኋላ፣በዚህ እሳቤና በዚህ ግንዛቤ ነው በዓለማዊ ሕይወትና በመደሰቻዎቿ ውስጥ በአስተማማኝ እርምጃ የሚጓዘው። በመሆኑም ያፈራው ሀብት እጁ ላይ እንጂ ልቡ ውስጥ ገብቶ የተደላደለ አለመሆኑን፣ያመለጠውም ሆነ ያገኘው ዓለማዊ ደስታ የማይጎዳው መሆኑን በተመለከተ ውስጣዊ እምነት ከመቋጠር ጋር፣ ከገደቡ ሳያሳልፍ በልኩ ለመደሰትና ለመጠቀም በማያቋርጥ ጥረት ውስጥ ይኖራል ማለት ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በምድርም፣በነፍሶቻችሁም፣መከራ (ማንንም) አትነካም፣ሳንፈጥራት በፊት በመጽሐፍ የተመዘገበች ብትኾን እንጅ፤ይህ በአላህ ላይ ገር ነው። (ይህ ማሳወቃችን) ባመለጣችሁ ጸጋ ላይ እንዳታዝኑ፣አላህም በሰጣችሁ ነገር (በትዕቢት) እንዳትደሰቱ ነው፤አላህም ኩራተኛን፣ጉረኛን ሁሉ አይወድም።}[አል ሐዲድ፡22-23]

በዚህም በመደሰቻዎች፣በመጠቀሚዎችና በፍላጎት ማርኪዎች ይጠቀምና ከአላህ (ሱ.ወ.) ምንዳ ያገኝበታል። ዓለማዊ ሕይወትና የወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት፣አካላዊና ሥጋዊ ደስታ ከመንፈሳዊና ሕሊናዊ ደስታ ጋር፣ደስተኝነትና መታደል ከዓለማዊ መደሰቻዎች ጋር፣ደስተኛነትና ውስጣዊ እፎይታም እርሱ ዘንድ እርስ በርስ የተሳሰሩ ይሆናሉ።

3- ዩኒቨርስ

ሙስሊም ሰው በዩኒቨርስ ግንዛቤ አስተውሎው ወደ ሦስተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ የሚሸጋገር ሲሆን፣ይህም በዚሪያው ያለው መላው ፍጥረተ ዓለምና ሕላዌ ነው። የሚቀጥለውን የአላህ (ሱ.ወ.) ቃል በማስተዋልና በመስተንንም ይጀምረል፦

{፦ በሰማያትና በምድር ያለውን (ታምር) ተመልከቱ፣በላቸው፤ታምራቶችና አስፈራሪዎችም፣ለማያምኑ ሕዝቦች አይጠቅሙም።}[ዩኑስ፡101]

በማስከተልም ቀደም ሲል ባደረገው አስተውሎና ማስተንተን፣የተፈጠረበትን ዓለማና የመኖሩን እውነታ አስመልክቶ ከደረሰበት ውጤት ጋር ተመሳሳይ ወደ ሆነ ውጤት ይደርስ ዘንድ የአላህን (ሱ.ወ.) ፍጥረታትና ድንቅ ሥራዎቹን እንዲያስተውልና እንዲያስተነትን ጥሪ የሚያደርጉ በአስርቶች የሚቆጠሩ ቁርኣናዊ አንቀጾችን ማጥናት ይቀጥላል። ስለ ዩኒቨርስ የሚኖረው ግንዛቤም ሁለት የተሟሉ እውነታዎችን ከመረዳት መንደርደር እንዳለበትም ግልጽ ይሆንለታል። እነሱም፦

አንደኛው እውነታ፦ አላህ (ሱ.ወ.) በአካባቢው የሚገኙ አብዛኞቹን ነገሮች ለርሱ ግልጋሎት የገራለት የመሆኑ እውነታ ነው። ስለሆነም ለርሱ የተሰጠው ብልጫ በአንዳንድ ልዩ መለዮዎቹ ብቻ ላይ የተወሰነ ሳይሆን፣እነዚህን ፍጥረታት ለርሱ ጥቅም፣ብልጽግናውንና እድገቱን እውን ለማድረግ ለግልጋሎቱ የተገሩለት ወደማድረግም የሚሸጋገር ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ፣ለናንተ ያገራላችሁ፣ጸጋዎቹንም ግልጽም ድብቅም ሲኾኑ የሞላላችሁ፣መኾኑን አታዩምን? ከሰዎችም ያለ ዕውቀትና ያለ መሪ፣ያለ ግልጽ መጽሐፍም በአላህ የሚከራከር አልለ።}[ሉቅማን፡20]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለናንተም ሌሊትንና ቀንን፣ፀሐይና ጨረቃንም፣ገራላችሁ፤ከዋክብትም በፈቃዱ የተገሩ ናቸው፤በዚህ ውስጥ ለሚያውቁ ሕዝቦች በእርግጥ ታምራቶች አልሉ።}[አል ነሕል፡12]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱ ያ ምድርን ለናንተ የተገራች ያደረገላችሁ ነው፤በጋራዎችና በመንገዶችዋም ኺዱ፣ከሲሳዩም ብሉ፤(ኋላ) መመለሻውም ወደርሱ ብቻ ነው።}[አል ሙልክ፡15]

ሙስሊሙ በብዙ ቁርኣናዊ አንቀጾች ውስጥ ይህ ዩኒቨርስና ያጠቃለላቸው ነገሮች ሁሉ ለርሱ ጥቅም የተገሩ መሆናቸውን የሚያመለክቱ አንጸባራቂ ማስረጃዎችን ያገኛል። ይህም ዩኒቨርስን መላመድና ለጥቅሙ መግራት ለሰው ልጅ የግድ አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁም ሲሆን፣በውስጡ ሊደርሱ በሚችሉ አደጋዎችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተስፋ መቁረጥ የተከለከለ መሆኑንም በውስጡ ይዟል። እናም ተፈጥሮ ለደካማው የሰው ልጅ የማያቋርጥ ፈታኝ ባለጋራ አይደለችም፤ሰውም በፊናው ተፈጥሮን ለጥቅሙ በመግራት ላይ እንጂ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥሩ ስር ለማዋል የማያቋርጥ ትግል በማድረግ ላይ አይደለም።

ሁለተኛው እውነታ፦ ዩኒቨርስ ምስጢራቱን ሙሉ በሙሉ ለሰው ልጅ ገና ያልገለጠ የመሆኑ እውነታ ነው። የተገሩለትና ያሳካቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም የዩኒቨርሱ ሌሎች አያሌ ጎኖች ከሰው ልጆች ግንዛቤ ከዕውቀቱና ከቁጥጥሩ ውጭ ናቸው። ፍጥረተ ዓለም በመላእክትና በጋኔኖች (በጅንን) የተሞላ ነው። የሰው ልጅ ትክክለኛ ምንነታቸውን ብቻ ሳይሆን መኖራቸውንም ጭምር ለማወቅ ከግንዛቤው ውጭ የሆኑ ሌሎች ፍጥረታትም ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚህ ዩኒቨርስ ታላቅ ግዝፈት አንጻር የሰው ልጅ በውስጡ የሚይዘው ቦታ ይህ ነው ሊባል ከማይችል አንዲት የአቶም ቅንጣት የሚያክል አይደለም።

በነዚህ ሁለት እውነታዎችም ሙስሊሙ በዙሪያው ስላለው ዩኒቨርስ ያለው እይታ የተሟላ ይሆናል። ከተቀሩት ፍጥረታት መካከል የተሰጠውን ልዩ ቦታም በሚገባ ይገነዘባል። አላህ (ሱ.ወ.) ሰውን፣በውስጡ የሚገኙ አብዛኞቹ ፍጥረታትን ለርሱ የተገሩ ያደረገው ዩኒቨርስና የመላው ፍጥረተ ዓለም ማዕከል አድርጎታል። በተመሳሳይ መልኩም በዩኒቨርሱ ውስጥ አንዳንዶቹ በሮች ለርሱ ዝግ የመደረጋቸውን፣እጹብ ድንቅ ተሰጥኦውና ድንቅ ችሎታው የፈለገውን ያህል ቢመጥቅ እነዚያን በሮች ማንኳኳት ፈጽሞ የማይችል የመሆኑን እውነታም ይገነዘባል።

የሰው ልጅ በዙሪያው ከሚገኙት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በላቀ የጨዋነት ባሕርይና ምሉእ በሆኑ ስነምግባሮች የሚመራ መሆን አለበት። ግንኙነቶቻቸውን በሥርዓተ አልበኝነት የሚመሩ ግለሰቦች፣ለደንብና ለመመሪያ የማይገዛ ሚዘናዊ ያልሆነ ግንኙነት ስለሚኖራቸው ሁሌም የችግር፣የስቃይና ያልተገራ ሻካራ ሕይወት ይመራሉ። ከሌሎች ጋር ያላቸው ትስስር በራስ ወዳድነት፣በምቀኝነት፣በክፉ ጥርጣሬ፣በሴረኝነትና በመጠላለፍ . . ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ሁሉ የሰውን ልጅ ደስተኝነትና እፎይታን የሚነሳው ሲሆን፣ሁሌም በማያቋርጥ የጭንቀት፣የድብርት፣የውጥረት ሁኔታ ውስጥ እየተሰቃየ እንዲኖር ያደርገዋል። እናም እፎይታና ደስተኝነት ከወዴት አባቱ?! አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{መልካሚቱና ክፉይቱም (ጠባይ) አይተካከሉም፤በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው ጠባይ (መጥፎይቱን) ገፍትር፤ያን ጊዜ ያ ባንተና በርሱ መካከል ጠብ ያለው ሰው፣እርሱ ልክ እንደ አዛኝ ዘመድ ይኾናል።}[ሓ.ሚም አልሰጅዳህ፡34-35]

ሕይወቱንና ግንኙነቶቹን በመብትና ግዴታ መርሕ ላይ ያደራጀው ሰው ግን ግዴታዎቹን እየፈጸመና፣መብቶቹን በገዛ ፈቃዱ ለቀቅ እያደረገ፣ያጠፉበትንም በይቅርታ እያለፈ ኑሮውን ይመራል። ይህን በማድረጉም ያለጥርጥር ደስተኛ ሰው ይሆናል። ውዴታ ከመሰል ሰብአዊ ፍጡራን ጋር በሚኖረው በይነሰባዊ ግንኙነት ውስጥ በሚኖሩት ደረጃዎች ቁንጮ ደረጃ ይይዛል። ውዴታ፡- ፍቅር፣መግባባት፣አብሮነትና መተሳሰብ ማለት ነውና። የሰው ልጅ የተስተካከለ ሚዘናዊ ተፈጥሮም ይህ ነው።

የደስተኝነት መንገድ . . የሰው ልጅ ከራሱ፣ከሕይወትና ከፍጥረተ ዓለሙም ጋር የሚያደርገው እርቅ ነው፦

የሰው ልጅ በዚህ እምነቱ ከፈጣሪው፣ከገዛ ራሱና በዙሪያው ካለው ፍጥረተ ዓለም ጋር ይታረቃል። በቅድሚያ ለአላህ (ሱ.ወ.) አገልጋይ ባሪያ የመሆኑን እውነታ የሚገነዘብና ተገቢ ግዴታዎቹን በመፈጸም ላይ የተሰማራ ነው። ሁለተኛም የተቀሩ ፍጥረታትን ለርሱ ጥቅም የተገሩ በማድረግ አላህ (ሱ.ወ.) ያከበረው ፍጡር የመሆኑን እውነታ በማወቁ የራሱን ልክና ደረጃ የሚረዳ፣ለርሱ ወደ ተፈጠረው ጀነት ከመመለሱ በፊት ይፈተን ዘንድ ወደ መሬት የወረደ መሆኑን፣ይህችን ምድር የማልማትና ለሰው ልጆች ኑሮ ገር የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑንም የሚገነዘብ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱ ከምድር ፈጠራችሁ፤በውስጧ እንድታለሙዋትም አደረጋችሁ፤ምሕረቱንም ለምኑት፤ከዚህም ወደርሱ ተመለሱ፤ጌታዬ ቅርብ፣(ለለመነው) ተቀባይ ነውና አላቸው።}[ሁድ፡61]

በተጨማሪም ሥጋዊ ፍላጎቶቹን ሸሪዓው ባስቀመጠው ገደብና አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ መጠቀምን ራሱን እንዲያለማምድና እንዲያሰለጥንም ኃላፊነት ተጥሎበታል። ፈጣሪ አምላክን፣ነፍስንና ፍጥረተ ዓለምን በተመለከተ ወደዚህ የተሟላ ግንዛቤ ከደረስን ዘንዳ፣ይህንን ግንዛቤ በተግባር በመተርጎም ልንደርስበት የምንችለው ውጤት ምን እንደሚሆን መጠየቅ አሁን ተገቢያችን ይሆናል። የሰው ልጅ ይህንን እውነታ ከተገነዘበ በኋላ ደስተኝነት በሁለቱም ሕይወቶች ማለትም በዱንያና በኣኽራም፣ከአላህ (ሱ.ወ.) ውዴታ፣ትእዛዛቱን ከመፈጸምና እርሱ ባስቀመጠው ገደብ ውስጥ ከመወሰን . . ጋር የተቆራኘ ነው። የአካልና የነፍስ ፍላጎቶችን፣የግለሰብና የማሕበረሰብ ፍላጎቶችንም፣የዱንያ ሕይወት ግንባታንና የኣኽራ ሕይወት ግንባታንም ሚዘናዊና ተመጣጣኝ በማድረግ ብቻ ይደረስበታል። ዱንያ የትግል፣የሥራና የመፈተኛ አገር በመሆኗ በዚህች ዓለም ላይ ሊገኝ የሚችለው ተድላና ደስተኝነት ደረጃው ያሻውን ያህል ቢሆን ጎደሎ መሆኑን፣የወዲያኛው የኣኽራ ሕይወት የምርመራ አገር በመሆኑ ምርመራውን በስኬት ያለፈ ሰው ዘላለማዊውንና ምሉእ የሆነውን ተድላና ደስተኝነት የሚጎናጸፍ መሆኑን ወደሚያረጋግጥ ድምዳሜ መድረሱ የግድ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ጌታቸው ከርሱ በኾነው እዝነትና ውዴታ በገነቶችም ለነሱ በውስጥዋ የማያቋርጥ መጠቀሚያ ያለባት ስትኾን ያበስራቸዋል።}[አል ተውበህ፡21-22]

የሰው ልጅ እርጋታና እርካታ ይሰማው ዘንድ፣በዱንያና በኣኽራም ጥሩ ሕይወት ለመኖር፣ኢማንና መልካም ሥራ የግድ አስፈላጊ ይሆናሉ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከወንድ ወይም ከሴት፣እርሱ አማኝ ኾኖ በጎን የሠራ፣መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።}[አል ነሕል፡97]