እስላም ለሁሉም ጊዜና ቦታ ምቹ፣ከሰው ልጆች ተፈጥሮ ጋር የሚጣጣም፣የሕይወትን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ የሚያስገባ፣ከሰው ልጅ ሥልጣኔና ዕድጋት ጋር የሚራመድ፣ለዓለም ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ፣ማሕበራዊና ሌሎችም ችግሮች መፍትሔ ሰጭ ሆኖ ነው ከአላህ (ሱ.ወ.) የተላለፈው። ይሁን እንጂ በዙ ሰዎች ከዚህ ብሩህ ጎዳና ሲያፈነግጡ፣ሌሎች ደግሞ ሰዎችን ከርሱ ለማራቅ ገጽታውን የማበላሸት ጦርነት ከፍተውበታል። ይህም ብዙውን የዓለም ሕዝብ ለከፋ ችግር አጋልጧል። አላህ (ሱ.ወ.) መመሪያውን ለተከተለና በሕጎቹ ለተመራ ሁሉ በዛሬዋ ዓለም ሕይወቱና በወዲያኛው ዓለም ደስተኝነትንና መታደልን ሊያጎናጽፈው ዋስትና ሲሰጥ፣ከርሱ ባፈነገጠና በተኩራራ ላይ ደግሞ ውርደትንና ዕድለ ቢስነትን ወስኖበታል።
አላህ (ሱ.ወ.) ይህን እስላም ለሰው ልጆች የሰጠው ሕይወታቸው የተስተካከለ፣ኑሯቸውም ያማረ፣በዛሬው የመጀመሪያ ሕይወታቸውም ሆነ በመጪው ዘላለማዊ ሕይወታቸው መታደልን እንዲያገኙና ከመከራም ይድኑ ዘንድ ነው። የሰው ልጅ ነፍስ ግን በተፈጥሯ ስሜታዊ ዝንባሌዎቿንና ሥጋዊ ፍላጎቶቿን የሚገድቡ ግዴታዎችን - ግዴታዎቹ ለራሷ የሚበጁ ቢሆኑ እንኳ - አትፈልግም። በዚህም ምክንያት እውነታን የሚያውቁ ደጋግ ሰዎች እነሱ ወደ ደረሱበት እውነትና ቅን መንገድ ይመጡ ዘንድ ሰዎችን ወደ እውነትና ወደ በጎ ነገር የመጥራትና የማስተማር (የደዕዋ) ግዴታ አላህ (ሱ.ወ.) ጥሎባቸዋል። ደዕዋውንም ለዓለማት ሁሉ እንዲያደርሱ አዟቸዋል። የአላህ መልክተኛም የተላኩት ለመታደልና ከርሳቸው ጋር ያሉት፣ሕዝባቸውና መላው የሰው ዘርም አብሯቸው እንዲታደል ለማድረግ ዓለማ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ቁርኣንን፣ባንተ ላይ እንድትቸገር አላወረድንም።}[ጣሃ፡2]
በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም።}[አል አንቢያ፡107]
በመሆኑም ነቢዩን መከተል፣በፈለጋቸው መጓዝ፣መንገዳቸውን አጥብቆ መያዝ የደስተኝነትና የመታደል ምንጭ ነው። የመድህን ዋስትና ነው። ትእዛዛቱን በመፈጸምና ከእገዳዎቹ በመራቅ ክልል ውስጥ አላህ (ሱ.ወ.) እንድንመራው ያዘዘን የአነዋነዋር መንገድ ነው። ውጤቱም የዛሬውና የነገው ሕይወት ተድላና ደስታ ብቻ ነው። ከዚህ ነቢያዊ ፈለግ ማፈንገጥ ግን ውጤቱ የዛሬውና የነገው ዘላለማዊ ሕይወት ውድቀትና ዕድለ ቢስነት ብቻ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ከግሣጼየም የዞረ ሰው፣ለርሱ ጠባብ ኑሮ አልለው፤በትንሣኤም ቀን ዕውር ኾኖ እንቀሰቅሰዋለን። ፦ ጌታዬ ሆይ! ለምን ዕውር አድርገህ አስነሳኸኝ? በእርግጥ የማይ የነበርኩ ስኾን ይላል። (ነገሩ) እንደዚሁ ነው፤ታምራታችን መጣችልህ፤ተውካትም፤እንደዚሁም ዛሬ ትትተዋለህ፤ይለዋል።} [ጣሃ፡124-126]
አላህ (ሱ.ወ.)፦
{መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤}[አል ነሕል፡97]
በማለት በገለጸው አማኝና ቀጥሎ በተገለጸው ከአላህ ውዳሴ ፊቱን ባዞረው ሰው መካከል ያለው ልዩነትም የሰፋ ነው፦
{ለርሱ ጠባብ ኑሮ አልለው፤} [ጣሃ፡124]
መልካም ሕይወትን መታደል የሚቻለው፣በግልጽና በስውርም የአላህን ትእዛዛት በመፈጸምና ከእገዳዎቹ በመራቅ፣የምንኖረው በርሱ ጥበቃና እንክብካቤ ስር በመሆኑ የአላህን (ሱ.ወ.) ውሳኔ በጸጋና በእርካታ በመቀበል ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{(እነሱም) እነዚያ ያመኑ፣ልቦቻቸውም አላህን በማውሳት የሚረኩ ናቸው፤ንቁ አላህን በማውሳት ልቦች ይረካሉ።}[አል ረዕድ፡28]
የልቦና መረጋጋትና ውስጣዊ እርካታ የሰው ልጅ በሚፈጽማቸው ተግባራት ሁሉ ይንጸባረቃል። በተቃራኒው ጭንቀትና ውስጣዊ ውጥረትም ውጡቱ አስከፊ ይሆናል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ሊያጠመውም የሚሻውን ሰው፣ደረቱን ጠባብ፣ቸጋራ፣ወደ ሰማይ ለመውጣት እንደሚታገል፣ያደርገዋል። እንደዚሁ አላህ በነዚያ በማያምኑት ላይ ርክሰትን ያደርጋል።}[አል አንዓም፡125]
ጥበቱ፣ቸጋራነቱና አስከፊ ኑሮው በድህነትና በበሽታ ምክንያት የመጣ ሳይሆን፣በሁሉም ተግባሩ ወይም በሁሉም ነገሩ ውስጥ ከሚንጸባረቀው ውስጣዊ ውጥረትና አለመረጋጋት ሁኔታ የሚመነጭ ነው። ያልታደለን ሰው ሀብት ማግኘትም ሆነ ማጣት ከዚህ ክልል አያስወጣውም፤የአለመታደሉ መንስኤ ይህ አይደለምና። መንስኤው አመለካከትና የእሳቤ መንገዱ ነው። የሀብቱ መጨመር ወይም መቀነስ፣መታመሙ ወይም ጤነኛ መሆኑ ጭንቀትና አለመታደሉ እንዲባባስ ምክንያት ሊሆንም ይችላል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ገንዘቦቻቸውና ልጆቻቸውም አይድነቁህ፤አላህ የሚሻው በቅርቢቱ ሕይወት በነርሱ (በገንዘቦቻቸውና በልጆቻቸው) ሊቀጣቸው፣ነፍሶቻቸውም እነሱ ከሓዲዎች ኾነው ነፍሶቻቸው እንዲወጡ ብቻ ነው።}[አል ተውበህ፡55]
በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ገንዘቦቻችውና ልጆቻቸውም አይድነቁህ፤አላህ የሚሻው፣በቅርቢቱ ዓለም በነሱ ሊቀጣቸውና፣ከሓዲዎችም ኾነው ነፍሶቻቸው እንዲወጡ ብቻ ነው።}[አል ተውበህ፡85]
የሰው ልጆችን በተመለከተ አለመታደልና ደስተኝነትን ማጣት ሀብታም ወይም ደሃ ከመሆን ጋር አይያያዝም። ከበሽታ ወይም ከፈታኝ ነገር ጋርም አይገናኝም። አለመታደል ማለት ከአላህ (ሱ.ወ.) መራቅ፣ከርሱ መንገድ ማፈንገጥ፣ከፈጣሪ ጌታ ጋር ግንኙነት አልባ መሆን ነው። ዘከሪያ በጸሎታቸው አላህን (ሱ.ወ.) ሲማጸኑ እንዲህ ብለዋል፦
{አንተንም በመለመኔ ጌታዬ ሆይ! (ምንጊዜም) ዕድለ ቢስ አልኾንም።}[መርየም፡4]
ባለፉት ጊዜያት ለጸሎቴ ምላሽ በመስጠትና ልመናዬን በመቀበል አክብረኸኛል፤አሁንም ልመናዬን በመስማት ዕድለኛ አድርገኝ፣ነበር ያሉት። ይህ በዘከሪያ ላይ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ጌታችን አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሎናልና፦
{ባሮቼ ስለኔ በጠየቁህ ጊዜ፣እኔ ቅርብ ነኝ፤የለማኝን ጸሎት በለመነኝ ጊዜ፣እቀበለዋለሁ፤ስለዚህም ወደ ቅኑ መንገድ ይመሩ ዘንድ በኔ ይመኑ።}[አል በቀራህ፡186]
በአገልጋይ ባሪያውና በፈጣሪ አምላኩ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነትና ትስስሩ እስካለ ድረስ፣መታደልን የማግኘት ዕድል የተረጋገጠ ነው። ዕድለ ቢስነት የሚያጋጥመው ይህ ትስስር ሲቋረጥ ነው። አንድ ሰው ራሱን ለዚህ ሃይማኖት ተገዥ ማድረጉን በአጓደለ መጠን በራሱና በሕይወቱ ላይ እንከንና አለመረጋጋት ይፈጠራል።
ለዚህ ነው አላህ (ሱ.ወ.) ቅን መመሪያን ከእዝነትና ከጸጋው ጋር፣ጥመትን ደግሞ ከዕድለ ቢስነት ጋር የሚያስተሳስረው። የመጀመሪያውን አስመልክቶ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{እነዚያ ከጌታቸው በመመራት ላይ ላይ ናቸው፤እነዚያም እነርሱ ፍላጎታቸውን ያገኙ ናቸው።}[አል በቀራህ፡5]
በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{እነዚያ ከጌታቸው የኾኑ ምሕረቶችንና ችሮታንም የሚቀበሉ ናቸው፤እነርሱም የተመሩት እነርሱ ናቸው።}[አል በቀራህ፡157]
በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ከኔም የኾነ መሪ ቢመጣላችሁ፣መሪየን የተከተለ፣አይሳሳትም፤አይቸገርምም።}[ጣሃ፡123]
ከርሱ ዘንድ የሆነ መመሪያ (አልሁዳ) ከጥመት ማዳኑ ሲሆን፣እዝነት (ረሕመት) ደግሞ ከዕድለ ቢስነት መታደጉ ነው። በጣሃ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ ያወሳው እውነታም ይኸው ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ጠ.ሀ. (ጣሃ) [አንተ ሰው] ቁርኣንን፣ባንተ ላይ እንድትቸገር አላወረድንም።}[ጣሃ፡1-2]
ከላይ ቁርኣንን በነቢዩ ላይ ማውረድንና ዕድለ ቢስነትን ከርሳቸው ማራቅን ሲያጣምር፣በምዕራፉ መጨረሻ ላይ ደግሞ ተከታዮቻቸውን አስመልክቶ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{አይሳሳትም፤አይቸገርምም።}[ጣሃ፡123]
ወደ ቅኑ መንገድ መመራት፣ችሮታ፣ጸጋና እዝነት እርስ በርሳቸው የተያያዙና የማይነጣጠሉ ሲሆኑ፤ጥመትና አለመታደልም እንደዚሁ የተያያዙና የማይነጣጠሉ ናቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{አመጠኞች በስሕተትና በእሳቶች ውስጥ ናቸው።}[አል ቀመር፡47]
ከመንገዱ ያፈነገጡ አመጸኞች መጨረሻ አስከፊውና መራሩ የገሀነም እሳት ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ አላህን (ሱ.ወ.) የሚፈሩ ትጉህ ታዛዥ አገልጋዮቹ መጨረሻን አስመልክቶ አላህ (ሱ.ወ.) በዚሁ ተመሳሳይ ምዕራፍ ውስጥ እንዲህ ብሏል፦
{አላህን ፈሪዎቹ በአትክልቶችና በወንዞች ውስጥ ናቸው። (እነሱም ውድቅ ቃልና መውወንጀል በሌለበት) በውነት መቀመጫ ውስጥ፣ቻይ እኾነው ንጉሥ ዘንድ ናቸው።}[አል ቀመር፡54-55]
ማግኘት ለሚፈልግ ሰው የደስተኝነት መንገድና የመታደል ጎዳናው ይህ ነው። መንገዱን ከተያያዝከው በአፈታሪኮች በመንፈሳዊም ሆነ ርእዮታዊ ባዶ መናፊቅነት ላይ ያልተመሰረተ መንገድ ነው። የደስተኝነት መንገድ፣የመታደል ጎዳና ነው። በተጨማሪም የዕውቀትና የሥልጣኔ መንገድ ነው።