በአላህ (ሱ.ወ.) የማመን መንገድ የሆነውን እውነተኛውን የደስተኝነት መንገድ እስኪ እንተዋወቅ። በጉዞው ወቅት የተረጋጋንና ኃያል ወኔ የሰነቅን እንሆን ዘንድ፣የዚህ መንገድ አቅጣጫ አመላካች የሆኑ አንዳንድ ጠቋሚ ምልክቶችን ማብራራት ተገቢ ይሆናል፦
አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ይህም ቀጥተኛ ሲኾን መንገዴ ነው፤ተከተሉትም፤(የጥመት) መንገዶችንም አትከተሉ፤ከ(ቀጥተኛው) መንገዱ እናንተን ይለያዩዋችኋልና። ይኻችሁ ትጠነቀቁ ዘንድ በርሱ አዘዛችሁ።}[አል አንዓም፡153]
እናም የደስተኝነትና የመታደል መንገድ የአላህ (ሱ.ወ.) መንገድ፣ለፍጡራን አገልጋዮቹ ያስተላለፋቸው - እርሱ የሚበጃቸውን ከሁሉም በላይ ዐዋቂ ነና - መመሪያዎቹ ነው። የአላህን መንገድ የሚተውና በተለያዩ ሰው ሠራሽ መንገዶች ደስተኝነትንና መታደልን የሚመኝ ሰው፣ያልታደለ መናጢ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ከርሱ መንገድ ውጭ በምንም ዓይነት ተድላና ደስተኝነት ሊሞኖር አይችልም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ከኔም የኾነ መሪ ቢመጣላችሁ፣መሪየን የተከተለ አይሳሳትም፤አይቸገርምም። ከግሣጼየም የዞረ ሰው፣ለርሱ ጠባብ ኑሮ አልለው፤በትንሣኤም ቀን ዕውር ኾኖ እንቀሰቅሰዋለን።}[አል ጣሃ፡123-124]
ደስተኝነትና መታደል የርሱን መንገድ ለያዘና መመሪያውን ለተከተለ ሰው ብቻ ነው። ዘላለማዊ ዕድለ ቢስነትና ስቃይ ደግሞ ከስመ ገናና ታዋቂ ከዋክብት አንዱ ተደርጎ ቢታይ እንኳ፣ከመንገዱ ፊቱን ያዞረና ከርሱ ያፈነገጠ ሰው ዕጣ ፈንታ ነው።
ሰው የሥጋና የነፍስ ውሑድ መሆኑ ይታወቃል። ሁለቱም የየራሳቸው የሆነ ቀለብ አላቸው። አንዳንድ መንገዶችና ፍልስፍናዎች ለነፍስ ፍላጎቶች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሥጋዊ ፍላጎቶችን በከፍተኛ ደረጃ ያጣጥላሉ። ይህም ታላቅ አደጋን አስከትሏል። ዘመናዊው ቁስ አካላዊነት ደግሞ በተቃራኒው የመንፈስና የነፍስ ፍላጎቶችን ከነአካቴው ውድቅ አድርጎ ለሥጋ ወይ ለገላ ብቻ የሚፈልገውን ሁሉ ሰጠ። በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰብአዊ ፍጡራን ለሥጋዊ ፍላጎቶችና ለአካላዊ መደሰቻዎች ብቻ ወደ ተፈጠሩ እንስሳት ደረጃ እንዲዘቅጡ ተደረጉ! ወይም ወደ ግኡዝ ቁሳቁስነት ተቀየሩ። የእስላም መንገድ ግን ነፍስና መንፈስን በመለኮታዊ ብርሃን ይቀልባል፤አካልንም ይንከባከባል፤ፍላጎቶቹን ጥሩና ሐላል በሆነ ማርኪያ ያጠግባል፦
{አላህም በሰጠህ ሀብት የመጨረሻይቱን አገር ፈልግ፤ከቅርቢቱም ዓለም ፋንታህን አትርሳ፤አላህም ወደ አንተ መልካምን እንዳደረገልህ (ለሰዎች) መልካምን አድርግ፤}[አል ቀሶስ፡77]
ነቢዩ ፣ሰልማን አልፋሪሲ (ረ.ዐ.)፦ {ለፈጣሪ ጌታህ ግዴታ አለብህ፤ለራስህ ነፍስም ግዴታ አለብህ፣ለቤተሰብህም ግዴታ አለብህ፣እናም ለሁሉም ባለመብት ተገቢውን ፈጽም።} [በቡኻሪ የተዘገበ] ያሉትን አባባል ተቀብለው አጽድቀዋል።
የኢማንን ጥፍጥና የቀመሰ ሰው፣አንገቱ ላይ ጎራዴ ቢደረግ እንኳ ፈጽሞ ሊተወው አይችልም። የፈርዖን ድግምተኞች አምነው የመታደለን መንገድ ሲይዙ ፈርዖን እንዴት እንደዛተባቸው ተመልከቱ፤ቁርኣን ውስጥ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
{እጆቻችሁንና እግሮቻችሁን በማናጋት (ግራና ቀኝን በማፈራረቅ) እቆርጣችኋለሁ፤በዘምባባም ግንዶች ላይ እሰቅላችኋለሁ፤ማንኛችንም ቅጣቱ በጣም ብርቱ፣የሚቆይም መኾኑን ታውቃላችሁ አላቸው።}[ጣሃ፡71]
ምላሸቸው ግን በጽናት የተሞላ ነበር፦
{ከመጡልን ታምራቶችና ከዚያም ከፈጠረን (አምላክ)፣ፈጽሞ አንመርጥህም፤አንተም የምትፈርደውን ፍረድ፤የምትፈርደው በዚች በአነስተኛይቱ ሕይወት ብቻ ነው አሉ።}[ጣሃ፡72]
የደስተኝነትን መንገድ መርጠው ከያዙ ከአጭር ጊዜ በኋላ ይህን የመሰለ ጽናት የተላበሱት፣የዚህን ኢማን ጥፍጥና ስለቀመሱና በአመለካከታቸውና በውሳኔያቸውም ግልጽ የሞት ዛቻና አደጋ በታጋረጠባቸው ሁኔታ ውስጥ እንኳ ይበልጥ ጽኑና እርግጠኞች እንዲሆኑ ስለ አደረጋቸው ነው።
ያለ ሕሊና ዕረፍት፣ያለ ውስጣዊ መረጋጋትና እፎታ ደስተኝነት አይኖርም። እነዚህ ደግሞ ኢማን በሌለበት የሚታሰቡ አይደሉም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{እርሱ በምእመናን ልቦች ውስጥ ከእምነታቸው ጋር እምነትን ይጨምሩ ዘንድ፣እርዳታን ያወረደ ነው፤ለአላህም የሰማያትና የምድር ሰራዊቶች አልሉት፤አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው።}[አል ፈትሕ፡4]
እምነት በሁለት በኩል ደስተኝነትን ያስገኛል። አንደኛ፦ የዕድለ ቢስነትና የመናጢነት አደገኛ መንስኤዎች በሆኑት በኃጢኣትና በወንጀል አረንቋ ውስጥ ከመዘፈቅ ይጠብቃል። አንድ ሰው ልቡ በፈጣሪ አምላኩ ከማመን የተራቆተ እስከሆነ ድረስ፣አንድን ሰው ሥጋዊ ፍላጎቶቹና እኩይ ዝንባሌዎቹ ወደ አደጋ የማይጎትቱት ስለመሆኑ ዋስትና የሚሰጥ ምንም ነገር የለም። ሁለተኛ፦ ኢማን ከደስተኝነት አበይት መስፈርቶች ሁለቱን ማለትም ውስጣዊ መረጋጋትና የልብ እፎይታን የሚሰጥ መሆኑ ነው። በችግሮችና በቀውሶች ማዕበል ሲናወጡ መዳኛና መጠጊያው ኢማን ብቻ ነው። ኢማን በሌለበት የፍርሃትና የጭንቀት መንስኤዎች እየጨመሩ ይሄዳሉ። ከኢማን ጋር ግን ከአላህ (ሱ.ወ.) በስተቀር ሊፈሩት የሚገባ አንዳች ነገር አይኖርም።
አማኝ የሆነ ልብ፣በአላህ ላይ የሚተማመን በመሆኑ ማንኛውንም አስቸጋሪ ሁኔታ አቅልሎ ይመለከታል። ከኢማን የተራቆተ ልብ ግን ከዛፉ እንደ ረገፈ ቅጠል በነፋስ ወዲያና ወዲህ የሚላጋ ይሆናል። ከሞትና ይህችን ዓለም ለቆ ከመሰናበት ይበልጥ ሰውን የሚያስፈራ ምን ነገር ይኖራል?! በአማኝ ሰው ዘንድ ግን ሞት የመረጋጋት መንስኤ እንጂ የፍርሃት መነሻ አይደለም። ልቡ በኢማንና በአላህ ፍራቻ (በተቅዋ) ለተሞላ ሰው ሞት ምኑም አይደለም!!
ኢማን በሰው ልጅ የሰራ አካላት የሰላም የደህንነትና የመረጋጋት ስሜትን ይዘራል። አማኝ ሰው፣እውነተኛ እምነቱ የአላህን ረድኤት፣ጥበቃውንና እንክብካቤውን በተስፋ የመጠበቅ የማያቋርጥ ስንቅ ስለሚያቀርብለት፣ደህንነት የሚሰማውና የተረጋጋ ሆኖ ነው በአላህ መንገድ የሚጓዘው። ምንጊዜም አላህ (ሱ.ወ.) በረድኤቱና በእገዛው ከርሱ መሆኑ ይሰማዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{አላህም ከምእመናን ጋር ነው።}[አል አንፋል፡19]
አማኝ ሰው የፈለገ ዓይነት ችግር ቢደርስበት፣የፈለገ ፈተና ቢያጋጥመው፣በአንጸባራቂ ብርሃን ያሸበረቁ የአላህ መጽሐፍና ቃሎቹ፣የነፍስያውን ጉትጎታና የአካላቱን ሕመም ለማስወገድ ዋስትናው ናቸው። እናም ፍርሃትና ስጋቱ በሰላምና መረጋጋት ይለወጣል። ዕድለ ቢስነትና ጭንቀቱ በተድላና በደስተኝነት ይቀየራል። በመሆኑም የምድር ሀብት በሙሉ ቢሰጠው እንኳ ሊያገኝ የማይችለውን ስነልቦናዊና መንፈሳዊ ደስተኝነት ወደሚያጎናጽፈው እፎይታ ይመራዋል። (13)
የሰዎች ሕይወት ሦስት እርከኖች እንዳሉት ይታወቃል። አንደኛው የዱንያ ሕይወቱ፣ሁለተኛው ከሞተ በኋላ የሚጀምረው የመቃብር ሕይወቱ፣ሦስተኛው የትንሳኤ ቀን ሕይወቱ ናቸው። የደስተኝነትና የመታደል መንገድም በነዚህ ሁሉ እርከኖች ውስጥ ያልፋል። የዱንያውን አስመልክቶ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ከወንድ ወይም ከሴት፣እርሱ አማኝ ኾኖ በጎን የሠራ፣መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።}[አል ነሕል፡97]
ይህም ሀብትና ንብረቱ ትንሽ ቢሆን እንኳ፣በመንፈስ እርካታ፣በሕሊና እፎይታ፣በውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት፣በአላህ ላይ በሚኖረው መተማመንና በእርግጠኝነቱ አማካይነት፣ በዚህች ዓለም ሕይወቱ ደስተኛ የሆነ የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖር እናደርጋለን ማለት ነው። አማኙ በመቃብር ሕይወቱ የሚያገኘውን ደስተኝነት በተመለከተ ደግሞ አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ.) ከአላህ መልክተኛ በስተላለፉት ተከታዩ ሐዲስ ውስጥ እናገኛለን፦ { ሙእምን ሰው መቃብሩ ውስጥ በእርግጥ ለምለም ጨፌ ውስጥ ነው፤በመቃብሩ ውስጥ ሰባ ክንድ ይሰፋለታል፤እንደ ሙሉ ጨረቃም ይበራለታል።} [አልባኒ ‹ሐስን› ብሎታል]
በወዲያኛው የኣኽራ ዘላለማዊ ሕይወቱ የሚጠብቀውን መታደልና ደስተኝነት በተመለከተ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{እነዚያም ዕድለኞቹማ ጌታህ ከሻው (ጭማሬ) ሌላ፣ሰማያትና ምድር እስከ ዘወተሩ ድረስ፣በውስጧ ዘውታሪዎች ኾነው በገነት ውስጥ ይኖራሉ፤የማይቋረጥ ስጦታን ተሰጡ።}[ሁድ፡108]
በዚህች ዓለማዊ ሕይወት ደስተኝነትን ሲታደሉ፣በመጭው የኣኽራ ዘላለማዊ ሕይወት ደግሞ መታደልን ተቀዳጅተዋል።
ስለዚህም እስላም ለሰው ልጅ ዘላለማዊ የሆነ ደስተኝነትንና መታደልን፣ዛሬ ለሚኖረው ሕይወቱ ደስተኝነትን፣በወዲያኛው የኣኽራ ሕወቱም መታደልን ይዞለት ነው የመጣው። አላህ ዘንድ ያለው በላጭና ዘላለማዊ ነውና። ይህም ብቻ ሳይሆን አላህ (ሱ.ወ.) የዱንያንና የኣኽራን ደስተኝነትና መታደል፣በመካከላቸው ግጭትና ቅራኔ ሳይኖር የተሳሰሩና የተቆራኙ አድርጓቸዋል። ይህች የዱንያ ሕይወት ወደ ኣኽራና በትንሣኤው ቀንም ወደ ታላቁ መታደልና ደስታ የምታደርስ መንገድ ነች። የዘላለማዊ መታደልና የደስተኝነት መንገድ በዱንያም ሆነ በኣኽራ አንድ መንገድ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{የቅርቢቱን ዓለም ምንዳ የሚፈልግ የኾነ ሰው፣አላህ ዘንድ የቅርቢቱና የመጨረሻይቱ ምንዳ አልለ። አላህም ሰሚ ተመልካች ነው።}[አል ኒሳእ፡134]