የመርየም [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁን] አባት ዒምራን ከእስራኤላውያን መካከል አላህን (ሱ.ወ.) አብዝተው በመግገዛት የሚታወቅ ጻድቅ ሰው ነበር። የዘር ሐረጉ ከተከበረ ነቢያዊ ቤተሰብ ከዳዉድ ቤት የሚመዘዝ ሲሆን፣ባለቤቱ የመርየም እናት ልጅ ለመውለድ ያልታደለች ነበረች። ልጅ የመውለድ ፍላጎቷን ያሳካላት ዘንድም ልጅ ከወለደች ለቤተመቅደስ አገልግሎት ብቻ የተሰጠ እንዲሆን ለማድረግ ለአላህ ተሳለች።
{የዒምራን ባለቤት (ሐና)፦ ጌታ ሆይ! እኔ በሆዴ ውስጥ ያለውን (ጽንስ፣ከሥራ) ነጻ የተደረገ ሲኾን ለአንተ ተሳልኩ፤ከኔም ተቀበል፤አንተ ሰሚው፣ዐዋቂው ነህና ባለች ጊዜ (አስታውስ)። በወለደቻትም ጊዜ፦ ጌታዬ ሆይ! እኔ ሴት ኾና ወለድኋት፤አላህም የወለደችውን ዐዋቂ ነው፤ወንድም እንደ ሴት አይደለም፤እኔም መርየም ብዬ ስም አወጣሁላት፣እኔም እስዋንም ዝርያዋንም ከተረገመው ሰይጣን በአንተ እጠብቃቸዋለሁ፣አለች።}[አሊ ዒምራን፡35-36]
አላህም (ሱ.ወ.) የእናቷን ስለት ሞላላት፦
{ጌታዋም በደህና አቀባበል ተቀበላት፤በመልካም አስተዳደግም አፋፋት፤}[ኣሊ ዒምራን፡37]
አስተዳደጓም ውብና መልካም በሆነ የደጋግ የአላህ አገልጋዮች የመታደል መንገድ ላይ የታነጸ ነበር። ለዚህም ነው አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ያለው፦
{ዘከሪያም አሳደጋት፤}[ኣሊ ዒምራን፡37]
የአክስቷ ወይም የእህቷ ባል የሆነው አሳዳጊዋ የአላህ (ሱ.ወ.) ነቢይ መሆኑ የተቸረችው የአላህ (ሱ.ወ.) ታላቅ ጸጋ ነበር።
{ዘከሪያ በርሷ ላይ በምኩራቧ (በመጸለያ ስፍራዋ) በገባ ቁጥር፣እርሷ ዘንድ ሲሳይን አገኘ፤፦ መርየም ሆይ! ይህ ለአንቺ ከየት ነው? አላት፤- እርሱ ከአላህ ዘንድ ነው፤አላህ ለሚሻው ሰወ ሲሳዩን ያለ ድካም ይሰጣል አለችው።} [ኣሊዒምራን፡37]
ይህም ከአላህ (ሱ.ወ.) የተሰጣት የመከበሪያና የባለሟልነት ደረጃ ነበር። አላህም (ሱ.ወ.) ምርጥና የተከበረች አድርጓት በአምልኮው አዟታል፦
{መላእክትም ያሉትን (አስታውስ)፦ መርየም ሆይ! አላህ በእርግጥ መረጠሸ፣አነጻሽም፣በዓለማት ሴቶችም ላይ መረጠሸ። መርየም ሆይ! ለጌታሽ ታዘዢ፤ስገጂም፤ከአጎንባሾቹም ጋር አጎንብሺ።}[ኣሊ ዒምራን፡42-43]
ከዚያም ዒሳ u እንዲወለዱ የአላህ (ሱ.ወ.) ፈቃድ ሲሆንም መርየም u ከቤተሰቦቿ ገለል ብላ ሄደች፦
{በመጽሐፉ ውስጥ መርየምንም ከቤተሰቧ ወደ ምሥራቃዊ ስፍራ በተለየች ጊዜ (የኾነውን ታሪኳን) አውሳ። ከነሱም መጋረጃን አደረገች፣መንፈሳችንንም (ጂብሪልን) ወደርሷ ላክን፤ለርሷም ትክክለኛ ሰው ኾኖ ተመሰለላት።}[መርየም፡16-17]
ክፉ የሚሠራባት አድርጋ ስለጠረጠረችው መርየም መልአኩን ፈራች፦
{፦ እኔ ከአንተ በአልረሕማን እጠበቃለሁ፤ጌታህን ፈሪ እንደ ኾንክ፣(አትቅረበኝ) አለች። ፦ እኔ ንጹሕን ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ፣የጌታሽ መልክተኛ ነኝ አላት። }[መርየም፡18-19]
ድንግሏ መርየም በነገሩ እጅግ ተገረመች፦
{(በጋብቻ) ሰው ያልነካኝ ኾኜ፣አመንዝራም ሳልኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል! አለች።}[መርየም፡20]
መልአኩም ይህ የአላህ (ሱ.ወ.) ፍርድና የርሱ ውሳኔ መሆኑን፣የሚወለደው ልጅም የርሱ ታምር መሆኑንና ይህን ማድረግም ለአላህ (ሱ.ወ.) በጣም ቀላል መሆኑን ነገራት።
{አላት፦ (ነገሩ) እንደዚህሽ ነው፤ጌታሽ ፦ እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው፤ለሰዎችም ታምር፣ከኛም ችሮታ ልናደርገው (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነው፣አለ፤(ነፋባትም)።}[መርየም፡21]
ንጹሕና የጠራች፣ከዝሙትም ሆነ ከማንኛውም ዝንፈት የጸዳች ከሆነች ድንግል እናት ዒሳ u ያለ አባት እንዲወለድ የአላህ (ሱ.ወ.) ፈቃድ ነበር። ይህም በችሮታውና ቃሉን ለመፈጸም ሲሆን የነቢዩ ዒሳ u በዚህ ሁኔታ መወለድም ከአላህ (ሱ.ወ.) ተአምራት አንዱ ተአምር ነው። ምሳሌውም ያለ አባትና ያለ እናት ከዐፈር እንደ ተፈጠረው አዳም ምሳሌ ነው። ህን በማስመልከት አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ፣እንደ አዳም ብጤ ነው፤ከዐፈር ፈጠረው፤ከዚያም ለርሱ (ሰው) ኹን አለው፣ኾነም። ይህ ከጌታህ ዘንድ የኾነ እውነት ነው፤ከተጠራጣሪዎቹም አትኹን።}[ኣሊ ዒምራን፡59-60]
በጸነሰች ጊዜም ከማሕበረሰቡ ገለል አለች፦
{ወዲያውኑም አረገዘችው፤በርሱም (በሆድዋ ይዛው) ወደ ሩቅ ስፍራ ገለል አለች።}[መርየም፡22]
የመውለጃ ጊዜዋም ደረሰ፦
{ምጡም፣ወደ ዘንባባይቱ ግንድ አስጠጋት፤ዋ ምኞቴ! ምነው ከዚህ በፊት በሞትኩ፤ተረስቼም የቀረሁ በኾንኩ፤አለች።}[መርየም፡23]
እዚህ ላይም ሌላ ተአምር ለነቢዩ ዒሳ u ተከሰተ፦
{ከበታቿም እንዲህ ሲል ጠራት፦ አትዘኝ፤ጌታሽ ከበታችሽ ትንሽን ወንዝ በእርግጥ አድርጓል።የዘምባባይቱንም ግንድ፣ወዳንቺ ወዝውዧት፤ባንቺ ላይ የበሰለን የተምር እሸት ታራግፍልሻለችና። ብይም፣ጠጭም፤ተደሰችም፤ከሰዎችም አንድን ብታይ፦ እኔ ለአልረሕማን ዝምታን ተስያለሁ፤ዛሬም ሰውን በፍጹም አላነጋግርም፣በይ።}[መርየም፡24-26]
ወልዳ ወደ ማሕበረሰቡ ስትመለስም ንጹይቱን ድንግል የጠበቃት አቀባባል በጣም አስጨናቂ ነበር፦
{በርሱም የተሸከመችው ኾና ወደ ዘመዶቿ መጣች፤- መርም ሆይ! ከባድን ነገር በእርግጥ ሠራሽ አሉዋት። የሃሩን እኅት ሆይ! አባትሽ መጥፎ ሰው አልነበረም፤እናትሽም አመንዝራ አልነበረችም፣አሉዋት።}[መርየም፡27-28]
መልስ ሳትሰጥ፦
{ወደርሱም ጠቀሰች፤}[መርየም፡29]
እንዴት ይሆናል ብለው ተቃወሙና፦
{በአንቀልባ ያለን ሕጻን እንዴት እናናግራለን! አሉ።}[መርየም፡29] {(ሕጻኑም) አለ፦ እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ፤መጽሐፍን ሰጥቶኛል፣ነቢይም አድርጎኛል። በየትም ስፍራ ብኾን ብሩክ አድርጎኛል፤በሕይወትም እስካለሁ ሶላትን በመስገድ፣ዘካንም በመስጠት አዞኛል። ለእናቴም ታዛዥ፣(አድርጎኛል)፤ትእቢተኛ እምቢተኛም አላደረገኝም።› ሰላምም በኔ ላይ ነው፣በተወለድሁ ቀን፣በምሞትበትም ቀን፣ሕያው ኾኘ በምቀሰቀስበትም ቀን፤}[መርየም፡30-33]
ከአይሁድ ከፊሉ እውነት አይደለም ብለው አስተባበሉ፤አላህ (ሱ.ወ.) የጠራትንና ያነጻትን ድንግል በከባድ ኀጢአት ወነጀሉ።
{በመካዳቸውም፣በመርየም ላይ ከባድ ቅጥፈትን በመናገራቸውም ምክንያት፣(ረገምናቸው)።}[አል ኒሳእ፡156]
ድንግሏን በዝሙት ሲወነጅሉም አላህ (ሱ.ወ.) ንጽሕናዋንና ቅድስናዋን እንዲህ ሲል አረጋገጠ፦
{እናቱም በጣም እውነተኛ ናት፤}[አል ማእዳህ፡75]
አላህ (ሱ.ወ.) በዒሳ u ነቢይነትና በመልክታቸው ያመነች መሆኗን አረጋገጠ። ጸጋውንም ለአገልጋዩና ለመልክተኛው ዒሳና ለድንግል እናቱ ዘረጋ።
{አላህ በሚል ጊዜ (አስታውስ)፦ የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! በአንተና በእናትህ ላይ (የዋልኩላችሁን) ጸጋዬን አስታውስ፤በሕጻንነትና በከፈኒሳነት (የበሰለ ሰው ኾነህ) ሰዎችን የምታናግር ስትኾን፣በቅዱሱ መንፈስ (በገብርኤል) ባበረታሁህ ጊዜ፣ጽሕፈትንና ጥበብንም፣ተውራትንና እንጂልንም፣ባስተማርኩህ ጊዜ፣›[አል ማእዳህ፡110]
በታኣምራትና በተለያዩ ምልክቶችም አገዘው፦
{ከጭቃም የወፍ ቅርጽ ብጤ በፈቃዴ በምትሠራና በውስጧ በምትነፋ፣በፈቃዴም ወፍ በምትኾን ጊዜ፣ዕውርም ኾኖ የተወለደንና ለምጻምንም በፈቃዴ በምታሽር ጊዜ፣ሙታንንም በፈቃዴ (ከመቃብራቸው) በምታወጣ ጊዜ፣የእስራኤልንም ልጆች በተአምራት በመጣህባቸውና ከነሱ እነዚያ የካዱት ይህ ግልጽ ድግምት እንጅ ሌላ አይደለም ባሉ ጊዜ፣(ሊገድሉህ ሲያስቡህ) ከአንተ ላይ በከለከልኩልህም ጊዜ፣(ያደረግሁልህን ውለታ አስታውስ)። ወደ ሐዋርያትም በኔና በመልክተኛዬ እመኑ፣በማለት ባዘዝኩ ጊዜ፣(አስታውስ)፤አመንን፤እኛም ሙስሊሞች መኾናችንን፣መስክር አሉ።}[አልማእዳህ፡110]
በኋላ ላይም ሐዋርያት ማእድ ከሰማይ ያወርድላቸው ዘንድ ለጌታቸው ለአላህ እንዲጸልዩ ነቢዩ ዒሳን u ጠየቁ። ይህን በማስመልከት አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ሐዋርያት፦ የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! ጌታህ በኛ ላይ ከሰማይ ማእድን ሊያወርድልን ይችላልን? ባሉ ጊዜ (አስታውስ)፤}[አል ማእዳህ፡112]
ነቢዩ ዒሳ u ግን ሐዋርያቱ ለጸጋው ተገቢውን ተግባራዊ ምስገና አያደርሱ ይሆናል ብለው ሰጉ፦
{ምእመናን እንደ ኾናችሁ አላህን ፍሩ አላቸው።}[አል ማእዳህ፡112-113]
ነቢዩም ጌታቸውን ለመኑም፦
{የመርም ልጅ ዒሳ አለ፦ ጌታችን አላህ ሆይ! ለኛ ለመጀመሪያዎቻችንና ለመጨረሻዎቻችን ባዕል (መደሰቻ) የምትኾንን፣ከአንተም ተአምር የኾነችን ማእድ፣ከሰማይ በኛ ላይ አውርድ፤ስጠንም፤አንተ ከሰጪዎች ሁሉ በላጭ ነህና። አላህ፦ እኔ (ማእድዋን) በናንተ ላይ አውራጅዋ ነኝ፤በኋላም ከናንተ የሚክድ ሰው፣እኔ ከዓለማት አንድንም የማልቀጣውን ቅጣት እቀጣዋለሁ አለ።}[አል ማእዳህ፡114-115]
ማእዱ ከወረደላቸውና ከተቋደሱት መካከል ከፊሉ ከሓዲ ሆነ።
የአላህን ነቢይ ዒሳን u ያስተባበሉት አይሁዶች ክደታቸውና በዒሳ u ላይ የሚሸርቡት ሴራቸው እንደቀጠለ ዘለቀ፦
{(አይሁዶችም) አደሙ፤አላህም አድማቸውን መለሰባቸው፤አላህም ከአድመኞች ሁሉ በላጭ ነው።}[ኣሊ ዒምራን፡54]
አላህ (ሱ.ወ.) ግን አድማቸውን ለነቢዩ ዒሳ u አጋልጦ እንዴት ከተንኮላቸው እንደሚያድናቸውም ነገራቸው፦
{አላህም ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤ዒሳ ሆይ! እኔ ወሳጅህ፣ወደ እኔም አንሺህ ነኝ፤ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህም (ከጉርብትናቸው አራቂህ) ነኝ፤እነዚያንም የተከተሉህን እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ፣ከነዚያ ከካዱት በላይ አድራጊ ነኝ፤ከዚያም መመለሻችሁ ወደኔ ነው፤በርሱ ትለያዩበት በነበራችሁት ነገር በመካከላችሁ እፈርዳለሁ።}[ኣሊ ዒምራን፡55]
ቃል ኪዳን ማፍረሳቸውን፣ሴራ መጎንጎናቸውን፣ክህደታቸውን፣የአላህን ነቢያት ለመግደል መሞከራቸውን፣ክብርቷን ቅድስት ድንግል መርየምን በሐሰት መወንጀላቸውን ሲገፉበት አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ አለ፦
{ቃል ኪዳናቸውንም በማፍረሳቸው፣በአላህም አንቀጾች በመካዳቸው፣ነቢያትንም ያለ አግባብ በመግደላቸውና ልቦቻችን ሽፍኖች ናቸው በማለታቸው ምክንያት፣(ረገምናቸው)፤በውነቱ በክህደታቸው ምክንያት አላህ በርሷ ላይ አተመ፤ስለዚህ ጥቂትን እንጅ አያምኑም። በመካዳቸውም፣በመርየም ላይ ከባድ ቅጥፈትን በመናገራቸውም ምክንያት፣(ረገምናቸው)። ፦ እኛ የአላህን መልክተኛ፣የመርምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን በማለታቸውም፣(ረገምናቸው)፤}[አል ኒሳእ፡155-157]
አላህ (ሱ.ወ.) ግን ከመግደል ሙከራቸው ነቢዩ ዒሳን u አዳነ፦
{አልገደሉትም፤አልሰቀሉትምም፤›[አል ኒሳእ፡157]
የገደሉት ግን በዒሳ የተመሰለላቸውን ሰው ነበር፦
{ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ፤እነዚያም በርሱ ነገር የተለያዩት፣ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፤ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም፤በእርግጥም አልገደሉትም። ይልቁንስ አላህ ወደርሱ አነሳው፤አላህም አሸናፊ፣ጥበበኛ ነው።}[አል ኒሳእ፡157-158]
አላህ (ሱ.ወ.) አገልጋዩንና መልክተኛውን ዒሳ u ከተንኮላቸው አድኖ ወደራሱ ከፍ አደረጋቸው፦
{ከመጽሐፉም ሰዎች ከመሞቱ በፊት፣በርሱ (በዒሳ) በእርግጥ የሚያምን እንጅ (አንድም) የለም፤በትንሣኤም ቀን በነሱ ላይ መስካሪ ይኾናል።}[አል ኒሳእ፡159]
እናም ይህ የመርየም ልጅ የዒሳ [የአላህ ሰላም በሁለቱም ላይ ይሁን] ታሪክ እውነታ ነው፦
{ይህ የመርየም ልጅ ዒሳ ነው፤ያ በርሱ የሚጠራጠሩበት እውነተኛ ቃል ነው። ለአላህ ልጅን መያዝ አይገባውም፤(ከጉድለት ሁሉ) ጠራ፤ነገርን በሻ ጊዜ ለርሱ የሚለው ኹን ነው፣ወዲያውም ይኾናል።}[መርየም፡35]
አላህ (ሱ.ወ.) የሁሉም ነገር ፈጣሪና ገዥ ጌታ በመሆኑ ልጅ መውለድ ለርሱ ተገቢው አለመሆኑን፣እርሱ ከምንምና ከማንም የተብቃቃ ሲሆን ሁሉም ሁሉንም ነገር ከርሱ ፈላጊዎችና ከጃዮች፣ለርሱም ታዛዦችና ተገዥዎች መሆናቸውን፣በሰማያትና በምድር የሚገኙ ሁሉ አገልጋይ ባሮቹ ሲሆኑ እርሱ ግን ብቸኛው አንድ አምላካቸውና ጌታቸው መሆኑን አላህ (ሱ.ወ.) አብራርቷል።