ሰዎች መጀመሪያ ላይ በንጹሕ ተፈጥሯቸው በትክክለኛው መንገድ ላይ የነበሩ ሲሆን፣በኋላ ተለያዩና ያስተምሯቸውና ያሰጠነቅቋቸው ዘንድ አላህ መልክተኞቹን ላከላቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{እርሱ ያ በመሃይሞች ውስጥ አንቀጾቹን (ቁርአንን)፣በነርሱ ላይ የሚያነብላቸው፣(ከማጋራት) የሚያጠራቸውም፣መጽሐፍንና ጥበብን የሚያስተምራቸው የኾነን መልክተኛ (ሙሐመድን) ከነሱው ውስጥ የላከ ነው፤እነርሱም ከርሱ በፊት በግልጽ ስሕተት ውስጥ ነበሩ።}[አል ጁሙዓ፡2]
አንደኛው ጎራ መልክተኞቹን አምኖ ሲቀበላቸው፣ሌላኛው ጎራ ደግሞ መልክተኞቹን አስተባብሎ በነርሱና ይዘውት በመጡት ጥሪም ካደ። አላህ (ሱ.ወ.) ይህን በማስመልከት እንዲህ ብሏል፦
{ሰዎች ሁሉ አንድ ሕዝብ ነበሩ፤(ተለያዩ)፤አላህም ነቢያትን አብሳሪዎችና አስጠንቃቂዎች አድርጎ ላከ፤ከነርሱም ጋር መጻሕፍትን በሰዎች መካከል በዚያ በተለያዩበት ነገር ይፈርድ ዘንድ በእውነት አወረደ፤በርሱም (በሃይማኖት) ግልጽ አስረጂዎች ከመጡላቸው በኋላ በመካከላቸው ለኾነው ምቀኝነት እነዚያው የተሰጡት እንጅ አልተለያዩበትም፤አላህም እነዚያን ያመኑትን ሰዎች፣ለዚያ ከውነት በርሱ ለተለያዩበት በፈቃዱ መራቸው፤አላህም የሚሻውን ሰው ወደ ቀጥተኛው መንገድ ይመራል።}[አል በቀራህ፡213]
ያስተባበሏቸውና የካዱትም በትዕቢትና ዝንባሌዎቻቸውን በመከተል ነበር። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ነፍሶቻችሁ በማትወደው ነገር መልክተኛ በመጣላችሁ ቁጥር (ከመከተል) ትኮራላችሁን? ከፊሉን አስተባበላችሁ፤ከፊሉንም ትገድላላችሁ።}[አል በቀራህ፡87]
{በአላህና ወደኛ በተወረደው (ቁርኣን)፣ወደ ኢብራሂምም፣ወደ እስማዒልና ወደ ኢስሐቅም፣ወደ ያዕቁብና ወደ ነገዶቹም በተወረደው፣በዚያም ሙሳና ዒሳ በተሰጡት፣በዚያም ነቢያት ሁሉ ከጌታቸው በተሰጡት፣ከነርሱ በአንድም መካከል የማንለይ ስንኾን አመንን፤እኛም ለርሱ (ለአላህ) ታዛዦች ነን በሉ።}[አል በቀራህ፡136]
በመልክተኞች ላመኑት በዛሬዋ ዓለማዊ ሕይወትና በወዲያኛው ዘላለማዊ ሕይወት ተድላና ድልን ሊያጎናጽፍ አላህ ቃል ገብቷል። ስለ አመኑ ሰዎች ሲናገርም እንዲህ ብሏል፦
{አላህንና መልክተኛውን፣እነዚያንም ያመኑትን የሚወዳጅ ሰው፣(ከአላህ ጭፍሮች ይኾናል)፤የአላህም ጭፍሮች እነርሱ አሸናፊዎች ናቸው።} [አል ማእዳህ፡56]
በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{(እነሱም) እነዚያ ያመኑ፣ልቦቻቸውም አላህን በማውሳት የሚረኩ ናቸው፤ንቁ! አላህን በማውሳት ልቦች ይረካሉ። እነዚያ ያመኑትና መልካም ሥራዎችን የሠሩት፣ለነሱ ደግ ኑሮ መልካም መመለሻም አላቸው።}[አል ረዕድ፡28]
በመልክተኞቹ የካዱትን አስመልክቶም እንዲህ ብሏል፦
{እነዚያን የካዱትን በምድር ውስጥ የሚያቅቱ አድርገህ አታስብ፤መኖሪያቸውም እሳት ናት፤በእርግጥም የከፋች መመለሻ ናት።}[አል ኑር፡57]
እያንዳንዱ ነቢይም ጠላቶች ነበሩት። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{እንደዚሁም ለነቢዩ ሁሉ ከሰውና ከጋኔን የኾኑን ሰይጣናት ጠላት አደረግን፤ከፊላቸው ወደ ከፊሉ ለማታለል ልብስብስን ቃል ይጥላሉ፤ጌታህም በሻ ኖሮ ባልሠሩት ነበር። ከቅጥፈታቸውም ጋር ተዋቸው።}[አል አንዓም፡112]
በተጨማሪም ከሓዲዎቹ አስተባባዮች በነቢዮቻቸው ላይ ድንበር አለፉ፤ጥቃት ሰነዘሩባቸው፤ተሳለቁባቸው፣መዘባበቻም አደረጓቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ማንኛውም መልክተኛ በርሱ የሚያላግጡበት ኾነው እንጅ አይመጣቸውም ነበር።}[አል ሕጅር፡11]
በተጨማሪም አላህ እንዲህ ብሏል፦
{ከነቢይም አንድም የሚመጣላቸው አልነበረም፣በርሱ ይሳለቁበት የነበሩ ቢኾን እንጅ።}[አል ዙኽሩፍ፡7]
በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦
{ካንተ በፊትም በመልክተኞች በእርግጥ ተላግጧል፤በነዚያም ከነሱ ባላገጡት ላይ በርሱ ያላግጡ የነበሩት ነገር (ቅጣት) ወረደባቸው።}[አል አንዓም፡10]
ሃማኖታቸውን እንዲተው ካልተው ግን ከአገር ለማስወጣትም ዛቱባቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{እነዚም የካዱት፣ለመለክተኞቻቸው፦ ከምድራችን በእርግጥ እናወጣችኋለን፤ወይም ወደ ሃማኖታችን በእርግጥ ትመለሳላችሁ፣አሉ፤ወደነርሱም ጌታቸው እንዲህ ሲል ላከ፦ ከሓዲዎችን በእርግጥ እናጠፋለን። }[ኢብራሂም፡13]
ማስጠንቀቂያው እስከ የመግደል ሙከራ ደርሷል፦
{ሕዝቦችም ሁሉ መልክተኛቸውን ልይዙ አሰቡ}[አል ሙእሚ፡5]
ይህም መልክተኞቻቸውንና ነቢዮቻቸውን ለመግደል አሰቡ ማለት ሲሆን፣ነቢዮችን የገደሉ ሕዝቦችም ይገኛሉ፦
{ነፍሶቻችሁ በማትወደው ነገር መልክተኛ በመጣላችሁ ቁጥር (ከመከተል) ትኮራላችሁን? ከፊሉን አስተባበላችሁ፤ከፊሉንም ትገድላላችሁ።}[አልበቀራህ፡87]
ከዚያ በኋላ ግን አላህ አስተባባዮቹን ከሓዲዎች አጠፋ። የመልክተኞቹን ጥሪም ይፋ አደረገ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{አላህ ፦ እኔ በእርግጥ አሸንፋለሁ፤መልክተኞቹም (ያሸንፋሉ ሲል) ጽፏል። አላህ ብርቱ፣አሸናፊ ነውና።}[አል ሙጃደላህ፡21]
በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{(የርዳታ) ቃላችንም፣መልክተኞች ለኾኑት ባሮቻችን በውነት አልፋለች። እነርሱ ተረጂዎቹ እነርሱ ናቸው።}[አል ሷፋት፡171-172]
አላህም መልክተኞቹንና ነቢዮቹን [የአላህ ሰላም በሁሉም ላይ ይሁን] ከከሓዲዎች ተንኮል አዳናቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{እነዚያንም ያመኑትንና ከክሕደት ይጠነቀቁ የነበሩትን አዳን።}[አል ነምል፡53]
በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦
{እነዚያንም ያመኑትንና ይጠነቀቁ የነበሩትን አዳንናቸው።}[ሓ ሚም አልሰጅዳህ፡18]
እያንዳንዱ ነቢይ የተላከው ለራሱ ሕዝብና ለራሱ ዘመን፣ሕይወታቸውን ለመግራትና ባህርቸውን ለማረቅ ተስማሚ የሆነ መልክት ይዞ ነው። በአንድ መልክተኛ የካደ ሰው በሁሉም የአላህ መልክተኞች እንደ ካደና እንዳስተባበለ ይቆጠራል። በዒሳ [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁን] የካደ ሰው፣በእርግጥ በሙሳም [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁን] አላመነም። የሙሐመድ መልክት የዒሳን መልክት ሽሯል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ወደ አንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና በርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲኾን በውነት አወረድን፤በመካከላቸውም፣አላህ ባወረደው ሕግ ፍረድ፤እውነቱም ከመጣልህ በኋላ ዝንባሌዎቻቸውን አትከተል።}[አል ማእዳህ፡48]
በሙሐመድ ያላመነ ሰውም በዒሳ መልክት በትክክል አላመነም።
የነቢያትና የመልክተኞች የመደምደሚያ መልክትና ጥሪ፣ለሁሉም ሕዝቦችና ለሁሉም ዘመን እንጅ ለተወሰነ ዘመን ወይም ለተለየ አንድ ሕዝብ አለመሆኑ ግድ ነው። ያ ባይሆን ኖሮ የሰው ልጅ ከሰማያትና ምድር ፈጣሪ የሚተላለፍለትን የመለኮታዊ ራእይ ትሩፋት ባጣ ነበር። ሙሐመድም የነቢያትና የመልክተኞች መደምደሚያና የመቋጫ ጉልላት ናቸው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ሙሐመድ፣ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም፤ግን የአላህ መልክተኛና የነቢዮች መደምደሚያ ነው፤አላህም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው።}[አል አሕዛብ፡40] (11)
አላህ (ሱ.ወ.) ሰውን መፍጠር ከፈለገበት ጊዜ ጀምሮ ኣደምን ከጀነት እስከ አወጣበትና ወደ መሬት እስከ አወረደበት ባለው እንጀምራለን። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{(ሙሐመድ ሆይ!) ጌታህ ለመላእክት ፦ እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ፤ ባለ ጊዜ፣(የኾነውን አስታውስ፤እነርሱም) እኛ ከማመስገን ጋር የምናጠራህ፣ላንተም የምንቀድስ ስንኾን በርሷ ውስጥ የሚያጠፋንና ደሞችንም የሚያፈስን ታደርጋለህን? አሉ፤(አላህ) እኔ የማታውቁትን ነገር ዐውቃለሁ አላቸው። አደምንም ስሞችን ሁሏንም አስተማረው፤ከዚያም በመላእክት ላይ (ተጠሪዎቹን) አቀረባቸው፤እውነተኞችም እንደ ኾናችሁ የነዚህን (ተጠሪዎች) ስሞች ንገሩኝ፣ አላቸው። ጥራት ይገባህ፤ከአስተማርከን ነገር በስተቀር ለኛ ዕውቀት የለንም፤አንተ ዐዋቂው ጥበበኛው አንተ ብቻ ነህና (አሉ)። ፦ አደም ሆይ! ስሞቻቸውን ንገራቸው አለው፤ስሞቻቸውን በነገራቸውም ጊዜ፣እኔ የሰማያትንና የምድርን ሩቅ ምስጢር ዐውቃለሁ፤የምትገልጹትንና ያንንም ትደብቁት የነበራችሁትን ዐውቃለሁ አላልኳችሁምን? አላቸው። ለመላእክትም፣ለአደም ስገዱ፣ባልን ጊዜ (አስታውስ)፤ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፤ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር፣እምቢ አለ፤ኮራም፣ከከሓዲዎቹም ኾነ። አደም ሆይ! አንተ ከነሚስትህ በገነት ተቀመጥ፤ከርሷም በፈለጋችሁት ስፍራ በሰፊው ተመገቡ፤ግን ይህችን ዛፍ አትቅረቡ፤ከበደለኞች ትኾናላችሁና አልንም። ከርሷም ሰይጣን እንዳለጣቸው፤በውስጡም ከነበሩበት (ድሎት) አወጣቸው፤ከፊላችሁም ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ፤ለናንተም በምድር ላይ እስከ ጊዜ (ሞታችሁ) ድረስ መርጊያና መጣቀሚያ አላችሁ፤አልናቸው። አደምም ከጌታው ቃላትን ተቀበለ፤ከርሱ ላይም (ጌታው ጸተትን በመቀበል) ተመለሰለት፤እነሆ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና። ሁላችሁም ኾናችሁ ከርሷ ውረዱ፤ከኔም የኾነ መምሪያ ቢመጣላችሁ፣ወዲያውኑ መምሪያዬን የተከተለ ሰው፣በነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤እነሱም አያዝኑም፣አልናቸው። እነዚያም (በመልክተኞቻችን) የካዱ፣በአንቀጾቻችንም ያስተባበሉ፣እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፤እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው።}[አል በቀራህ፡30-39]
ኋላ ላይ ሰዎች ሲለያዩና ከቀጥተኛው መንገድና ከእውነት ሲርቁ፣አላህ መልክተኞችን ላከ።የየራሳቸውን ሕግጋት የያዙ መልክተኞችም በተከታታይ ወደ ሰው ልጆች ተላኩ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{ለናንተ ከሃይማኖት ያንን ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ፤ያንንም ወደ አንተ ያወረድነውን፣ያንንም በርሱ ኢብራሂምን፣ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን፣ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ፣በርሱም አትለያዩ፣ማለትን (ደነገግን)፤}[አል ሹራ፡13]
የአላህ ነቢያትና መልክተኞች ከእድሪስ፣ከኑሕና ከኢብራሂም ጀምሮ እስከ እስማዒል፣ሙሳ፣ዒሳና ሙሐመድ [የአላህ ሰላም በሁሉም ላይ ይሁን] ድረስ ተከታትለው መጡ።
አላህ (ሱ.ወ.) ስለነሱ ተርኮልን፣ዜናቸውንም ነግሮናል። እዚህ ላይ ስለ አንዳንዶቻቸው ታሪክ ጥቂቱን እንመለከታለን። ታሪካቸው ለሚያስተውሉ ሰዎች በትምህርትና በግሳጼ የተሞላ ነውና። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦
{በታሪካቸው ውስጥ፣ለአእምሮ ባለቤቶች በእርግጥ መገሠጫ ነበረ፤(ይህ ቁርኣን) የሚቀጣጠፍ ወሬ አይደለም፤ግን ያንን በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ፣ለነገርም ሁሉ ገላጭ፣ለሚያምኑ ሕዝቦችም መሪና ችሮታ ነው።}[ዩሱፍ፡111]