ኢብራሂም የነቢያት አባትና የተውሒድ ነቢይ ናቸው። ይህም በሁሉም የሕይወት ታሪካቸው ውስጥ በግልጽ የተንጸባረቀ ነው። ለዚህም ነው አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ሲል የገለጻቸው፦
{ኢብራሂም ለአላህ ታዛዥ፣ወደ ቀጥተኛ ሃይማኖት ተዘንባይ፣ሕዝብ ነበር፤ከአጋሪዎቹም አልነበረም።}[አል ነሕል፡120]
ነቢዩ ኢብራሂም ያደጉት በጣዖታውያን ሕዝቦች ውስጥ ነበር። ይልቅዬም አባታቸው ከጣዖት አምላኪዎች አንዱ ብቻ ሳይሆን የጣዖታቱ አንዱ ጠራቢ አዘጋጅና አገልጋይም ነበር። ኢብራሂም በዚህ ጉዳይ ላይ አባታቸውንና ሕዝባቸውን አወያዩ፦
{ኢብራሂምም ለአባቱ ለአዘር ጣዖታትን አማልክት አድርገህ ትይዛለህን? እኔ፤አንተንም ሕዝቦችህንም በግልጽ መሳሳት ውስጥ ኾናችሁ አያችኋለሁ ባለ ጊዜ (አስታውስ)።}[አል አንዓም፡74]
የሕዝባቸውን ጣዖት አምልኮ አሳማኝ ማስረጃዎችን በመደርደር ተቃወሙ። የአላህን (ሱ.ወ.) አንድነት የሚያሳዩ ምልክቶችንም ተመልክተው ያስተነትኑ ነበር፦
{ሌሊቱም በርሱ ላይ ባጨለመ ጊዜ ኮከብን አየ፤ይህ ጌታዬ ነው አለ፤በጠለቀም ጊዜ፦ }[አል አንዓም፡76]
ኮከቡ ከእይታ በተሰወረ ጊዜም ፦
{ጠላቂዎችን አልወድም አለ። ጨረቃንም ወጪ ኾኖ ባየ ጊዜ፦}[አል አንዓም፡76-77]
ጨረቃን ወጥታ አድማሱ ላይ ሲመለከቱ አንዳንድ ሰዎች ሲያመልኳት አስተዋሉና፦
{ይህ ጌታዬ ነው አለ፤}[አል አንዓም፡77]
ይህም አባባላቸው የሰዎቹን ሥራ በማብጠልጠልና በአምልኳቸውም በመገረም ድምጸት ነበር።
{በገባም ጊዜ።}[አል አንዓም፡77]
ጨረቃዋ ጠልቃ ስታልፍም ለሕዝቡ እንዲህ አሉ፦
{፦ ጌታዬ (ቅኑን መንገድ) ባይመራኝ በእርግጥ ከተሳሳቱት ሕዝቦች እኾናለሁ አለ። ፀሐይንም ጮራዋን ዘርግታ ባየ ጊዜ፦ }[አል አንዓም፡77-78]
ሕዝቡን ለፀሐይቱ ሲሰግድ ተመለከቱና፦
{ይህ ጌታዬ ነው፤ይህ በጣም ትልቅ ነው አለ፤}[አል አንዓም፡78]
ይህም ድርጊታቸውን በማብጠልጠልና ወጥታ የምትጠልቅ ፀሐይ እንዴት አምላክ አድርጎ ይይዛሉ?! ብሎ በመሳለቅ መንፈስ ነበር።
{በገባችም ጊዜ፦ }[አል አንዓም፡78]
ፀሐይዋ ጠልቃ ከዓይን ስትሰወርም ሲያመልኩባት ወደነበሩ ሰዎች ፊታቸውን አዞና፦
{ወገኖቼ ሆይ! እኔ ከምታጋሩ ሁሉ ንጹሕ ነኝ አለ። እኔ ለዚያ ሰማያትንና ምድርን ለፈጠረው (አምላክ) ቀጥተኛ ስኾን ፊቴን አዞርኩ፤እኔም ከአጋሪዎቹ አይደለሁም (አለ)።}[አል አንዓም፡78-79]
ነቢዩ ኢብራሂም አባታቸውን ከጠዖት አምልኮና ከሽርክ ለመከልከል በተለሳለሰና ምክንያታዊነትን በተላበሰ አቀራረብ ብዙ ይመክሩ ነበር፦
{፦ አባቴ ሆይ! የማይሰማንና የማያይን፣ከአንተም ምንንም የማይጠቅምህን (ጣዖት) ለምን ትገዛለህ? አባቴ ሆይ! እኔ ከዕውቀት ያልመጣልህ ነገር በእርግጥ መጥቶልኛልና ተከተለኝ፤ቀጥተኛውን መንገድ እመራሃለሁና። አባቴ ሆይ! ሰይጣንን አትግገዛ፤ሰይጣን ለአልረሕማን አመጠኛ ነውና። አባቴ ሆይ! እኔ ከአልረሕማን ቅጣት ሊያገኝህ፣ለሰይጣንም ጓደኛ ልትኾን እፈራለሁ።}[መርየም፡42-45]
የሚያሳዝነው ግን የአባታቸው ምላሽ ከእምቢታም ያላለፈ መሆኑ ነበር፦
{(አባቱም)፦ ኢብራሂም ሆይ! አንተ ከአምላኮቼ ትተህ የምትዞር ነህን? ባትከለከል፣በእርግጥ እወግረሃለሁ፤ረዢም ጊዜንም ተዎኝ አለ።}[መርየም፡42]
ለዚህ ማስፈራሪያ ኢብራሂም u የሰጡት መልስ በመልካም ስነምግባር በእዝነትና በርህራሄ የታጀበ ነበር፦
{፦ ደህና ኹን፤ወደፊት ከጌታዬ ምሕረትን እለምንልሃለሁ፤እርሱ ለኔ በጣም ርኅሩኅ ነውና አለ፤እናንተንም፣ከአላህ ሌላ የምትግገዙትንም ፣እርቃለሁ፤ጌታየን በመገዛት የማፍር አለመኾኔን እከጅላለሁ።}[መርየም፡47-45]
ኢብራሂም u ለአባታቸውና ለሕዝባቸው ጣዖታትን ማምለክና በአላህ ማጋራትን ትተው አንድ አላህን (ሱ.ወ.) ብቻ እንዲያመልኩ ወደ ተውሒድ የሚያደርጉትን ጥሪ አለመታከት ቀጠሉበት። ሕዝቡ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ በሽርኩ ገፋበት፦
{ወገኖቹም ተከራከሩት፤በአላህ (አንድነት) በእርግጥ የመራኝ ሲኾን፣ትከራከሩኛላችሁን? በርሱም የምታጋሩትን ነገር አልፈራም፤ግን ጌታዬ ነገርን ቢሻ (ያገኘኛል)፤ጌታዬም ነገሩን ሁሉ ዕውቀቱ ሰፋ፤አትገነዘቡምን? አላቸው። በናንተ ላይ በርሱ ማስረጃን ያላወረደበትን፣እናንተ ማጋራታችሁን የማትፈሩ ስትኾኑ፣የምታጋሩትን (ጣዖታት) እንዴት እፈራለሁ! የምታውቁም ብትኾኑ ከሁለቱ ክፍሎች (በአንድ አምላክ ከሚያምኑና ከሚያጋሩ) በጸጥታ ይበልጥ ተገቢው ማንኛው ነው? (አለ)።}[አል አንዓም፡80-81]
በድጋሜም ለአባታቸውና ለሕዝቡ እንዲህ አሏቸው፦
{ለአባቱና ለሕዝቦቹ ምንን ትገግገዛላችሁ ባለ ጊዜ፣}[አል ሹዐራ፡70]
የተሰጣቸው መልስ ግን አሸፈረን ጣዖታቱን መግገዛት እንቀጥልበታለን የሚል ነበር፦
{ጣዖታትን እንግገዛለን፤እርሷንም በመግገዛት ላይ እንቆያለን፤አሉ።}[አል ሹዐራ፡71] {(እርሱም) አለ፦ በጠራችኋቸው ጊዜ ይሰሟችኋልን? ወይስ ይጠቅሟችኋልን? ወይስ ይጎዷችኋልን?}[አል ሹዐራ፡73]
ምላሹ በእርግጥ አዙሮ ማየትን የማያውቅ፣ሰብአዊ አእምሮን አውልቆ የሚያስቀምጥ፣አመንክዮን የሚጻረርና ሲሰሩ አይተን ተከተልን በሚል በጭፍን ተከታይነት ላይ የተመሰረተ ጅላጅል ምላሽ ነበር።
{የለም፣አባቶቻችን እንደዚሁ ሲሠሩ አገኘን አሉት።}[አል ሹዐራ፡74]
ኢብራሂም በማስረጃዎችና በአመንክዮና በአስተዋይ አእምሮ በተደገፈ የጠራ ተውሒድ መልስ ሰጧቸው፦
{እናንተም የቀድሞዎቹ አባቶቻችሁም፣(የተገዛችሁትን)፤እነሱም (ጣዖቶቹ) ለኔ ጠላቶች ናቸው፤ግን የዓለማት ጌታ ሲቀር፣(እርሱ ወዳጄ ነው)። (እርሰሱ) ያ የፈጠረኝ ነው፤እርሱም ይመራኛል። ያም እርሱ የሚያበላኝና፣የሚያጠጣኝ ነው። በታመምኩም ጊዜ፣እርሱ ያሽረኛል። ያም የሚገድለኝ፣ከዚያም ሕያው የሚያደርገኝ፣ነው። ያም በፍርዱ ቀን ኀጢአቴን ለኔ ሊምር የምከጅለው ነው።ጌታዬ ሆይ! ዕውቀትን ስጠኝ፤በደጋጎቹም ሰዎች አስጠጋኝ። በኋለኞቹም ሕዝቦች ውስጥ ለኔ መልካም ዝናን አድርግልኝ። የጸጋይቱን ገነት ከሚወርሱትም አድርገኝ። ለአባቴም ማር፤እርሱ ከተሳሳቱት ነበረና።}[አል ሹዐራ፡75-86]
ሕዝቡና ንጉሣቸው በዓላቸውን ለማክበር ወደ በረሃ ሲወጡ ኢብራሂም አብሯቸው ሳይወጡ ቀሩ።
{ከርሱም የሸሹ ኾነው ኼዱ። ወደ አማልክቶቻቸውም ተዘነበለ፤አለም፦ አትበሉምን? የማትናገሩት ለናንተ ምን አላችሁ? በኀይል የሚመታቸውም ኾኖ በነርሱ ላይ በድብቅ ተዘነበለ።}[አል ሷፍፋት፡90-93]
ከበዓሉ ስነ ሥርዓት ፍጻሜ በኋላ ሲመለሱ የሚያመልኩባቸው ጣዖቶቻቸውን ተሰባብረው አገኙ። ራሳቸውን እንኳ ከጥቃት ለመከላከል አቅም የሌላቸው ጣዖታት እንዴት አማልክት መሆን ይችላሉ! እናም እየተጣደፉ መጡና፦
{፦ በአማልክቶቻችን ይህንን የሠራ ማነው? እርሱ በእርግጥ ከበደለኞቹ ነው አሉ። ኢብራሂም የሚባል ጎበዝ፣(በመጥፎ) ሲያነሳቸው ሰምተናል፣ተባባሉ። ይመሰክሩበት ዘንድ፣በሰዎቹ ዓይን (ፊት) ላይ አምጡት አሉ። ኢብራሂም ሆይ! በአማልክቶቻችን ይህንን የሠራህ አንተ ነህን? አሉት። }[አል አንቢያ፡59-62]
ኢብራሂንምም u ማፈናፈኛ የማይሰጥ መልስ ሰጧቸው፦
{አይደለም፣ይህ ትልቃቸው ሠራው፤ይናገሩም እንደ ኾነ ጠይቋቸው፣አለ።}[አል አንቢያ፡63]
በምላሹ ምክንያታዊነትና በአስረጅነቱ፣በሙግቱም ጥንካሬ ፊት የተዋራጅነት ስሜት ተሰማቸው።
{ወደ ነፍሶቻቸውም ተመለሱ። እናንተ (በመጠየቃችሁ) በዳዮች ናችሁም ተባባሉ። ከዚያም በራሶቻቸው ላይ ተገለበጡ (ወደ መጥፎ ሁኔታቸው ተመለሱ)፤እነዚህ የሚናገሩ አለመኾናቸውን በእርግጥ ዐውቀሃል፤(አሉ)።}[አል አንቢያ፡64-65]
ኢብራሂምም በማያፈናፍን ብርቱ አስረጅ ጠየቋቸው፦
{ታዲያ ለናንተ ምንም የማይጠቅማችሁንና የማይጎዳችሁን ነገር፣ከአላህ ሌላ ትግገዛላችሁን? አላቸው።}[አል አንቢያ፡66]
አስተዋይ አእምሮ፣አሳማኝ ማስረጃና ምክንያታዊ መከራከሪያ እንደራቃቸው ሲረዱ ኢብራሂምን ለመበቀል አሰቡ።
{፦ ሠሪዎች እንደ ኾናችሁ አቃጥሉት፣አማልክቶቻችሁንም እርዱ አሉ። (በእሳት ላይ ጣሉትም)።}[አል አንቢያ፡68]
አላህ (ሱ.ወ.) ግን ነቢዩን አዳናቸው፦
{፦ እሳት ሆይ! በኢብራሂም ላይ ቀዝቃዛ፤ሰላም ኹኚ፣አልን። በርሱም ተንኮልን አሰቡ፤በጣም ከሳሪዎችም አደረግናቸው።}[አል አንቢያ፡69-70]
አላህ (ሱ.ወ.) ከጥቃቱ ካዳናቸው በኋላ ኢብራሂም ተመልሰው ከንጉሡ ጋር ተከራከሩ፦
{ወደዚያ አላህ ንግሥናን ስለ ሰጠው ኢብራሂምን በጌታው ነገር ወደ ተከራከረው አላየህምን? ኢብራሂም፦ ጌታዬ ያ ሕያው የሚያደርግና የሚገድልነው ባለ ጊዜ፣}[አል በቀራህ፡258]
ለዚህ ግልጽና አሳማኝ ማስረጃ ጅላጅል ምላሽ ተሰጠ፦
{እኔ ሕያው አደርጋለሁ፣እገድላለሁም አለ፤}[አል በቀራህ፡258]
የፈለገውን ሰው መግደልና የፈለገውንም መተው ለሚለው ለዚህ ጅል የሽሽት ክርክር ኢብራሂም መልስ አልሰጡም።
{ኢብራሂም፦ አላህ ፀሐይን ከምሥራቅ በኩል ያመጣል፣(አንተ) ከምዕራብ በኩል አምጣት አለው፤ያም የካደው ሰው ዋለለ (መልስ አጣ)፤ አላህም በዳዮች ሕዝቦችን አይመራም።}[አል በቀራህ፡258]
በዚህም የከሓዲዎቹ አስረጅና አመንክዮ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ተጋለጠ። ከክርክሩ በኋላም አላህ (ሱ.ወ.) እንዴት አንደሚፈጥርና እንዴት ሕያው እንደሚያደርግ ኢብራሂም በገዛ ዓይናቸው ለማየት ፈለጉ።
{ኢብራሂምም ጌታዬ ሆይ! ሙታንን እንዴት ሕያው እንደምታደርግ አሳየኝ ባለ ጊዜ፣(አስታውስ፤አላህ)፦ አላመንክምን? አለው፤አይደለም (አምኛለሁ)፤ግን ልቤ እንዲረጋ ነው አለ፤(አላህም)፦ ከበራሪዎች (ከወፎች) አራትን ያዝ፤ወደ አንተም ሰብስባቸው፤(ቆራርጣቸውም)፤ከዚያም በየኮረብታው ሁሉ ላይ ከነርሱ ቁራጭን አድርግ፤ከዚያም ጥራቸው፤ፈጥነው ይመጡሃልና፤አላህም አሸናፊ ጥበበኛ መኾኑን ዕወቅ አለው።}[አል በቀራህ፡260]
አላህ (ሱ.ወ.) ኢብራሂምንና ልጃቸው እስማዒልን መካ የሚገኘውን የአላህ ማምለኪያ ቤት ከባእድ አምልኮና ከጣዖታት ነጻ እንዲያደርጉ አዘዛቸው።
{ቤቱንም (የአላህን መገዣ ቤት ከዕባን) ለሰዎች መመለሻና ጸጥተኛ ባደረግን ጊዜ (አስታውስ)፤ከኢብራሂምም መቆሚያ መስገጃን አድርጉ፤ወደ ኢብራሂምና ወደ ኢስማዒልም ቤቴን ለዘዋሪዎቹና ለተቀማጮቹም፣ለአጎንባሽ ሰጋጆችም፣አጥሩ ስንል ቃል ኪዳን ያዝን። ኢብራሂም ባለ ጊዜ (አስታውስ)፤ጌታዬ ሆይ! ይህንን ጸጥተኛ አገር አድርግ፤ቤተሰቦቹንም ከነሱ በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነውን ሰው ከፍሬዎች ስጠው፤(አላህም) ፦ የካደውንም ሰው (እሰጠዋለሁ)፤ጥቂትም እጠቅመዋለሁ፤ከዚያም ወደ እሳት ቅጣት አስጠጋዋለሁ፤ምን ትከፋም መመለሻ! (አለ)። ኢብራሂምና ኢስማዒልም ጌታችን ሆይ! ከኛ ተቀበል፤አንተ ሰሚው፣ዐዋቂው አንተ ነህና የሚሉ ሲኾኑ፣ከቤቱ መሠረቶቹን ከፍ ባደረጉ ጊዜ፣(አስታውስ)። ጌታችን ሆይ! ላንተ ታዛዦችም አድርገን፤ከዘሮቻችንም ላንተ ታዛዦች ሕዝቦችን (አድርግ)፤ሕግጋታችንንም አሳየን (አሳውቀን)፤በኛም ላይ ተመለስልን፤አንተ ጸጸትን ተቀባዩ፣ርኅሩኁ አንተ ብቻ ነህና።}[አል በቀራህ፡125-128]