‹‹በዚህ አንድ ዓለም ውስጥ፣ዛሬ ሙስሊምና ክርስቲያን ዐረቦች ከአውሮፓውያን ጋር ያላቸው ትስስር እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት፣እስላም በአውሮፓ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖና የተዋቸውን አሻራዎች የሚመለከት ጥናት ይፋ መደረጉ በጣም ተገቢ ነው። አንድ ወቅት ላይ በመካከለኞቹ ክፍለ ዘመናት የአውሮፓ ክርስቲያን ጸሐፍት በተለያዩ ጎኖች የእስላምን ገጽታ አበላሽተው ማቅረባቸው የሚታወቅ ነው። በተገባደደው ክፍለ ዘመን ግን ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥረት የበለጠ ተጨባጭነትና ሚዘናዊነት ያለው የእስላም ምስል በምዕራባውያን አእምሮ ውስጥ መቀረጽ ጀምሯል። ከዐረቦችና ከሙስሊሞች ጋር መልካም ግንኙነት ይኖረን ዘንድ፣ሙስሊሞች በኛ ላይ ያላቸውን ትሩፋት ሁሉ አምነን መቀበል ይኖርብናል። ያንን ለመካድ የምናደርጋቸው ጥረቶች ግን ራስን በውሸት ከማሞካሽትና ከግብዝነት ምልክቶች አንዱ ከመሆን አያልፍም።››