-ይህን ግዙፍ ዩኒቨርስና በውስጡ ያቀፋቸውን ሰማያት ምድሮችና ጠፈራዊ አካላት አታዩምን?!
-ስለ ሰማያት አፈጣጠር፣ስለ ከዋክብትና ስለ ጋላክሲዎች አስበውና አስተንትነው ያውቃሉ?!
-ስለዚች ምድራችንና ስላቀፈቻቸው ወንዞች፣ባሕሮች፣ተራሮችና ሸለቆዎችስ አስበው አስተንትነው ያውቃሉ?!
-የሚስተዋልባቸው እጹብ ድንቅ አፈጣጠር፣ቅንብርና ቅንጅት አያስደምምዎትም?!
ለመሆኑ ይህን ድንቅ ዩኒቨርስ ያስገኘው፣የፈጠረውና በዚህ ተኣምራዊ አኳኋን ያሳመረው፣ያለ ምንም የቀደመ አምሳያ በዚህ ታላቅ ምሉእነት ከምንም ጀምሮ የሠራው ማነው?!
ራሱን በራሱ ፈጠረ ብለው ይገምታሉ?! ወይስ ይህ ዩኒቨርስ ኃያል ችሎታ ያለው ፈጣሪ ጌታ አለው ብለው ያስባሉ?
አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦
{ሰማያትንና ምድርን በመፍጠር፣ሌሊትና ቀንም በመተካካት፣ለባለ አእምሮዎች ምልክቶች አሉ። (እነርሱም) እነዚያ ቆመው ተቀምጠውም፣በጎኖቻቸው ተጋድመውም፣አላህን የሚያወሱ፣በሰማያትና በምድር አፈጣጠርም የሚያስተነትኑ ፦› ጌታችን ሆይ! ይኸን በከንቱ አልፈጠርከውም፤ጥራት ይገባህ፤ከእሳትም ቅጣት ጠብቀን የሚሉ ናቸው።}[ኣል ዒምራን:190-191]
ስለ ራስዎት አፈጣጠርና ምንነት በአእምሮ አሰላስለው አያውቁም? አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦
{በነፍሶቻችሁም ውስጥ (ምልክቶች አልሉ)፤ታዲያ አትመለከቱምን? ።} [አልዛሪያት፡24]
የሰው ልጅ እንዴት ተፈጠረ? አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦
{ወይስ ያለ አንዳች (ፈጣሪ) ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን? ወይስ ሰማያትንና ምድርን ፈጠሩን? አይደለም አያረጋግጡም።}[አል ጡር፡35-36]
ከምንም ያልተፈጠሩ ከሆኑና ራሳቸውንም ያልፈጠሩ፣ሰማያትና ምድርንም ያልፈጠሩ እስከሆኑ ድረስ ይህን ዩኒቨርስና ያቀፋቸውን ፍጥረታት በመላ ያስገኘና የፈጠረ ፈጣሪ መኖሩ ጥርጥር የለውም፤እርሱም አላህ (ሱ.ወ) ነው። ከዚህ ሁሉ አመላካች ማስረጃዎች በኋላ፣መጥኔ አቅዶና ቀርጾ የፈጠራቸውን ፈጣሪ አምላክ የአላህን መኖር ለሚክዱ ወገኖች!!
የሰው ልጆች ያለ ጥርጥር ፈጣሪ አምላክ መኖሩን አምነው የመቀበል ተፈጥሮ ይዘው ይወለዳሉ። መልካሙን መውደድና ክፉን መጥላትም የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ማስረጃ እንኳ በማያሻው ሁኔታ ፈጣሪ መኖሩን አምኖ መቀበል ከምንም በላይ በሰው ልጅ ውስጥ ሰርጾ የጸና ተፈጥሮው ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦
{ወደ እውነት ተዘንባይ ኾነህ ፊትህን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ፤የአላህን ፍጥረት ያችን አላህ ሰዎችን በርስዋ ላይ የፈጠረባትን (ሃማኖት ያዙዋት)፤የአላህን ፍጥረት መለወጥ የለም፤ይህ ቀጥተኛ ሃይማኖት ነው፤ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም።}[አል ሩም፡30]
ነብዩም እንዲህ ብለዋል፦ «ማንኛውም ሕጻን በተፈጥሮ ላይ ሆኖ እንጅ አይወለድም።»
ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ የዩኒቨርሱ ፈጣሪ አምላክ አላህ በመሆኑ ላይ ስምምነት አላቸው። በመሆኑም አላህ (ሱ.ወ) ያለ ተፎካካሪና ያለ ምንም ሸሪክ የፍጥረተ ዓለሙ ፈጣሪ ጌታ የመሆኑ እውነታ የጸና መሰረት ያለው የጋራ አቋም ሊሆን ችሏል። የትኛውም ሕዝብ ከአላህ በስተቀር ሌላ የሰማያትና የምድር ፈጣሪ፣ሌላ ሲሳይ ሰጭና መጋቢ አምላክ ፈጽሞ አለ አይልም። በአላህ (ሱ.ወ) ብቸኛ ጌትነት ሌሎች ባእድ አማልክትን ቢያጋሩም፣ስለፈጣሪነቱ በሚጠየቁበት ጊዜ ግን ፈጣሪነቱን ያረጋግጡለታል። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦
{ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ፀሐይንና ጨረቃንም የገራ ማን እንደኾነ ብትጠይቃቸው በእርግጥ አላህ ነው፣ይሉሃል፤ታዲያ እንዴት ይመለሳሉ።}[አል ዐንከቡት፡61-63]
በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦
{ሰማያትንና ምድርንም ማን ፈጠራቸው? ብለህ ብትጠይቃቸው አሸናፊው ዐዋቂው (አላህ) በእርግጥ ፈጠራቸው ይላሉ።}[አልዙኽሩፍ፡9]
ኤቲዝምና የአላህን (ሱ.ወ) መኖር መካድ፣ከአርቆ አስተዋዮች ጉዞ የተንጠባጠቡና የተንሻፈፈ እይታ ያላቸው ጥቂቶች ብቻ የሚያራምዱት፣በተጨባጭ ውድቀቱና ምክነቱ የተጋለጠ ክስተት እንጂ ሌላ ምንም አይደለም።
የአላህን መኖርና ጌትነቱን አስመልክተው ከላይ ከቀረቡት ማስረጃዎች በተጨማሪ፣በዩኒቨርስ ውስጥ የሚስተዋለው ይህ ድንቅና የጸና ቅንብር ራሱን በራሱ ያልፈጠረ ስለመሆኑ ሰብአዊ አእምሮ ከዋነኛ አስረጅዎች አንዱ ነው። ራሱን በራሱ ያልፈጠረና ያላስገኝ እስከሆነ ድረስም ያልነበረና አዲስ የተገኘ ነው፤አዲስ የተገገኘ ነገር ደግሞ ያለ አንዳች ጥርጥር ያስገኘውና የጀመረው ፈጣሪ የግድ ይኖረዋል ማለት ነው።
እዚህ የሚነሳው ጥያቄ ፦ ስንት ጭንቅ ስንት መከራና ስንት አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሞን ወደ ማነው የወተወትነው? ማንን ነው የተማጸነው? ከጭንቅ እንዲገላግለን፣ከከመከራ እንዲታደገንና ከስቃይ እንዲያድነን ማንን ነው የለመነው? ወደማነው የወተወትነው? የሚለው ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦
{ሰውንም ጉዳት ባገኘው ጊዜ፣ጌታውን ወደርሱ ተመላሽ ኾኖ ይጠራል። ከዚያም ከርሱ ዘንድ ጸጋን በሰጠው ጊዜ ያንን ከዚያ በፊት ወደርሱ ይጸልይበት የነበረውን (መከራ) ይረሳል፤ከመንገዱ ለማሳሳትም ለአላህ ባላንጣዎችን ያደርጋል፤በክሕደት ጥቂትን ተጣቀም፤አንተ በእርግጥ ከእሳት ጓዶች ነህ በለው።}[አል ዙመር፡8]
በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦
{እርሱ (አላህ) ያ በየብስና በባሕር የሚያስኼዳችሁ ነው፤በመርከቦችም ውስጥ በኾናችሁና በነርሱም (በተሳፋሪዎቹ) በመልካም ነፋስ የተደሰቱ ኾነው (መርከቦቹ) በተንሻለሉ ጊዜ፣ኀይለኛ ነፋስ ትመጣበታለች፤ከየስፍራውም ማዕበል ይመጣባቸዋል፤እነሱም (ለጥፋት) የተከበቡ መኾናቸውን ያረጋግጣሉ፤(ያን ጊዜ) አላህን ከዚች (ጭንቅ) ብታድነን በእርግጥ ከአመስጋኞቹ እንኾናለን ሲሉ ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ ያጠሩ ኾነው ይለምኑታል። በአዳናቸውም ጊዜ እነሱ ወዲያውኑ ያለ አግባብ በምድር ላይ ወሰን ያልፋሉ፤እላንተ ሰዎች ሆይ! ወሰን ማለፋችሁ (ጥፋቱ) በነፍሶቻችሁ ላይ ብቻ ነው፤(እርሱም) የቅርቢቱ ሕይወት መጠቀሚያ ነው፤ከዚያም መመለሻችሁ ወደኛ ነው፣ትሠሩት የነበራችሁትንም ሁሉ እንነግራችኋለን።}[ዩኑስ፡22-23]
አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፦
{እንደ ጥላዎችም የኾነ ማዕበል በሸፈናቸው ጊዜ፣አላህን ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ ያጠሩ ኾነው ይጠሩታል፤ወደ የብስም ባዳናቸው ጊዜ፣ከነሱም ትክክለኛም አልለ፤(ከነሱም የሚክድ አልለ)፤በአንቀጾቻችንም አታላይ ከዳተኛ ሁሉ እንጅ ሌላው አይክድም።}[ሉቅማን፡32]