በዚህ ዓለም ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ደስተኝነትን ለማግኘት ይጥራል። ሰዎች በአመለካከታቸው፣በዘር ግንዳቸው፣በዝንባሌ እና በመርሆዎቻቸው፣በዓላማቸውና በግባቸው የሚለያዩ ቢሆኑም በአንድ ዓለማ ላይ ግን ይስማማሉ፤እሱም ሁሉም ደስተኝነትንና እርጋታን ፈላጊ መሆናቸው ነው።
ይህን ለምን ታደርጋለህ? ያንን ለምን ትሠራለህ? ብለን ማንኛውንም ሰው ብንጠይቅ፣በቃላትም ይሁን በይዘቱ በቀጥተኛ አነጋገርም ይሁን በተዘዋዋሪ ትርጉሙ ደስተኝነትን ስለምፈልግ ነው ማለቱ አይቀርም።
ደስተኝነት ቀጣይነት ያለው የእርካታ፣የመረጋጋት፣የመታደል፣የሐሴትና የምቾት ስሜት ነው። ይህ አስደሳች ስሜት የሚመጣው ሦስት ነገሮችን በቋሚነት በመገንዘብ ነው፤እነሱም፦ የራስን ጥሩነት፣የሕይወትን በጎነትና የመጨረሻ ግብን ጥሩነት መገንዘብ ናቸው።
በነዚህ ሦስት ጉዳዮች ዙሪያ ነው የሰው ልጅ ለገዛ ራሱ የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች የሚጀምሩትና አብረውት እያደጉ የሚመጡት። ሰው በአእምሮው ውስጥ ለሚመላለሱ ጎትጓች ጥያቄዎች ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ደስተኝነትን አያገኝም። ከጥያቄዎቹ መካከልም፦
-የዚህ ዩኒቨርስ ባለቤትና አስተዳዳሪው ማነው?
-እኔንና በዙሪያዬ ያለውን ፍጥረት የፈጠረው ማነው?
-እኔ ማነኝ? ከየት መጣሁ? ለምንስ ዓላማ ተፈጠርኩ? መጨረሻዬና መመለሻዬስ ወዴት ነው?
የሚሉት ይገኛሉ። የሰው ልጅ ስለራሱና ስለ ሕይወቱ ያለው ንቃተ ሕሊና እና ግንዛቤ በጨመረ ቁጥር፣የነዚህ ጥያቄዎች ጉትጎታና ጫና በአእምሮው፣በአስተሳሰቡና በመንፈሱ ላይ እየጨመረ ይሄዳል። ነፍሱ ለጥያቄዎቹ አርኪ የሆነ አሳማኝ ምላሽ እስካላገኘች ድረስ እርጋታና ደስተኝነትን አያገኝም።