ኑሕ

ኑሕ

ኑሕ  ፦ የኑሕ ሕዝቦች ቀደም ሲል አንድ አላህን ብቻ የሚያመልኩ፣ከሞት በኋላ ዳግም መቀስቀስና መጠየቅ መኖሩን የሚያምኑ፣መልካም ሥራዎችንም የሚሠሩ ሕዝቦች ነበሩ። እነዚያ ሰዎች በሞት ሲያልፉ ቀሪዎቹ ለነዚያ ደጋግ ጻድቃን ሰዎችና ለውብ ስነምግባራቸው በጣም ስላዘኑ የመታሰቢያ ቅርጻ ቅርጽና ሐውልቶች አቆሙላቸው። እነዚያን ነገሮችም {ወድ፣ሱዋዕ፣የጉሥ፣የዑቅ፣ነስር} ብለው ሰየሟቸው። እነዚህን ምስሎችና ቅርጻቅርጾች መላመድና የነዚያ የሞቱባቸው ደጋግ ሰዎች መለያ ምልክትና ተምሳሌት አድርገው መውሰድ ጀመሩ። ለሙታኑ የነበራቸውን አክብሮት ለመግለጽም ቀስ በቀስ እነዚህን ምስሎችና ቅርጻቅርጾች ማክበር ያዙ። እንዲህ እያሉ ዘመን አልፎ ዘመን ተተካ። አባቶች ሞተው ልጆች ጎለመሱ። ተተኪው ትውልድ አባቶቹ የጀመሩትን የምስሎቹንና የቅርጻቅርጾቹን አክብሮት በይበልጥ በመጨመር ከፊታቸው ማጎንበስና መስገድ ጀመሩ። ቅርጻቅርጾቹ በሰዎቹ ልብ ውስጥ ጠልቀው እየገቡና ከፍተኛ ቦታ እየያዙ መጡ። ቀጣዩ ትውልድም በቅርጻቅርጾቹንና ምስሎቹን የሚሰገድላቸውና የሚሳልላቸው አማልክት አድርጓ በመያዙ ብዙ ሕዝብ ለጥመት ተጋለጠ።

በዚህን ጊዜ ነው አላህ (ሱ.ወ.) ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመራቸው፣ከጣዖታት አምልኮ እንዲከለክላቸውና አላህን ብቻ እንዲገዙ ጥሪ እንዲያደርጉላቸው ነቢዩ ኑሕን  ወደነዚህ ሕዝቦች የላከው። . .

{፦ ሕዝቦቼ ሆይ! አላህን ተገዙ፤ከርሱ ሌላ ምንም አምላክ የላችሁም . . አላቸው።}[አል ሙእሚኑን፡23]

አስተባበሉት እንጂ አልተቀበሉትም። ከአላህ ቅጣትና ከቁጣው በማስጠነቀቅም እንዲህ አላቸው፦

{እኔ በናንተ ላይ የታላቅን ቀን ቅጣት እፈራለሁና።}[አል ሹዐራ፡135]

እንዲህም መለሱለት፦

{ከሕዝቦቹ (የካዱት) መሪዎቹ፦ እኛ በግልጽ መሳሳት ውስጥ ኾነህ በእርግጥ እናይሃለን አሉት።}[አል አዕራፍ፡60]

ኑሕም  መለሱላቸው፦

{አላቸው፦ ወገኖቼ ሆይ! ምንም መሳሳት የለብኝም፤ግን እኔ ከዓለማት ጌታ መልክተኛ ነኝ። የጌታዬን መልክቶች አደርስላችኋለሁ፤ለናንተም እመክራችኋለሁ፤ከአላህም በኩል የማታውቁትን ዐቃለሁ።}[አል አዕራፍ፡61-62]

ሕዝቡቦቹም በኑሕ አነጋገር ተገረሙ። አንተ እንደኛው ያለ ሰው ሆነህ እንዴት የአላህ መልክተኛ ትሆናለህ?! አንተን አምነው የተከተሉህም ግምት የማይሰጣቸው ተራ ሰዎች ናቸው፤ . . እናም በገንዘብም ሆነ በክብር ከኛ የተሻላችሁ አይደላችሁምና ውሸታሞች ናችሁ የሚል ጥርጣሬ አለን፣አሉ። እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦

{፦ ይህ ብጤያችሁ ሰው እንጅ ሌላ አይደለም፤በናንተ ላይ መብለጥን ይፈልጋል፤አላህም በሻ ኖሮ መላእክትን ባወረደ ነበር፤ይህንንም (የሚለውን) በመጀመሪያዎቹ አባቶቻችን አልሰማንም። እርሱ፣በርሱ ዕብደት ያለበት ሰው እንጅ ሌላ አይደለም፤}[አል ሙእሚኑን፡24-25]

ከፊላቸው ከፊሉን በጣዖታቱ አምልኮ ላይ አበረታታ፦

{አሉም፦ አምላኮቻችሁን አትተዉ፤ወድንም፣ሱዋዕንም፣የጉሥንም፣የዑቅንም፣ነስርንም (እነዚህ የአማልክቶቻቸው ስሞች ናቸው) አትተዉ።}[ኑሕ፡23]

ኑሕም  እንዲህ አሏቸው፦

{አላህን ልትፈሩና ይታዘንላችሁም ዘንድ ከናንተው (ጎሳ) በኾነ ሰው ላይ እንዲያስጠነቅቃችሁ ከጌታችሁ ግሣጼ ቢመጣላችሁ ትደነቃላችሁን?(አላቸው)።}[አል አዕራፍ፡63]

በጥሪው ኑሕ  ለስለስ ያለ አግባቢ አቀራረብ ቢከተሉም ሰዎቹ ግን እምቢታና ትእቢትን ብቻ ጨመሩ። ነቢዩ ሳይሰለቹ አዘውትረው ጥሪያቸውን ቀጠሉ። እንዲህ እስከማለት ደረጃ ድረስም ለፉ፦

{(ስለተቃወሙትም) አለ፦ ሕዝቦቼ ሆይ! እኔ ለናንተ ገላጭ የኾንኩ አስጠንቃቂ ነኝ። አላህን ተገዙት፤ፍሩትም፤ታዘዙኝም በማለት (አስጠንቃቂ ነኝ)። ለናንተ ከኀጢአቶቻችሁ ይምራልና፤ወደ ተወሰነው ጊዜም ያቆያችኋል፤የአላህ (የወሰነው) ጊዜ፣በመጣ ወቅት አይቅቆይም። የምታውቁ ብትኾኑ ኖሮ (በታዘዛችሁ ነበር)። (ስለ ተቃወሙትም) አለ፦ ጌታዬ ሆየ! እኔ ሌሊትም ቀንም ሕዝቦቼን ጠራሁ። ጥሪየም መሸሽን እንጅ ሌላ አልጨመረላቸውም። እኔም ለነርሱ ትምር ዘንድ (ወደ እምነት) በጠራኋቸው ቁጥር፣ጣቶቻቸውን በጆሮቻቸው ውስጥ አደረጉ፤ልብሶቻቸውንም ተከናነቡ፤(በመጥፎ ሥራቸው ላይ) ዘወተሩም። (ያለ ልክ) መኩራትንም ኮሩ።}[ኑሕ፡5-7]

ነቢዩ  አመቺ ሆኖ በተገኘ ስልት ሁሉ ጥሪ አደረጉ፦

{ከዚያም እኔ ለነሱ ገለጽኩ፣ለነሱም መመስጠርን መሰጠርኩ (በግልጽም በምስጢርም ወደ እምነት ጠራኋቸው)፣አልኳቸውም፦ ጌታችሁን ምሕረትን ለምኑት፤እርሱ በጣም መሓሪ ነውና።}[ኑሕ፡9-10]

አንዳንዶቻቸው ውሃ የማይቋጥር ምክንያት መደርደር ያዙ። እንዲህም አሉ፦

{(እነርሱም)፣ወራዶቹ የተከተሉህ ኾነህ ለአንተ እናምናለን? አሉት።}[አል ሹዐራ፡111]

የኑሕ  ምላሽ ግን ሙሉ በሙሉ በለሰለሰ ለዘብተኛ መካሪ አነጋገር ነበር፦

{(እርሱም) አላቸው፦ ይሠሩት በነበሩት ነገር ምን ዕውቀት አለኝ፤}[አል ሹዐራ፡112]

እንዲህም አሏቸው፦

{ምርመራቸው በጌታዬ ላይ እንጅ በሌላ ላይ አይደለም፤ብታውቁ ኖሮ፣(ይህንን ትረዱ ነበር)፤}[አል ሹዐራ፡113]

በተጨማሪም እንዲህ አሏቸው፦

{እኔም አማኞችን አባራሪ አይደለሁም፤}[አል ሹዐራ፡114]

{እኔም እነዚያን ያመኑትን አባራሪ አይደለሁም፤}[ሁድ፡29]

በኔ ያመኑ፣ከኔ ጋር የቆሙና ያገዙኝን ሰዎች እንዴት አባርራለሁ?! በማለት ጠየቁ፦

{ሕዝቦቼም ሆይ! ባባርራቸው፣ከአላህ (ቅጣት) የሚያድነኝ ማን ነው? አትገሠጹምን?}[ሁድ፡30]

{እኔ ግልጽ አስፈራሪ እንጅ ሌላ አይደለሁም።}[አል ሹዐራ፡115]

ጨዋና ተራ፣ሀብታምና ደሃ፣ትልቅና ትንሽ፣ነጭና ጥቁር ሳይሉ ሰዎችን ሁሉ በእኩል አስተማሩ፤ አስጠነቀቁ። . . ሰዎቹ ግን በኑሕ የቀረበላቸውን ማስረጃ መካድ ሲያቅተታቸውና መሞገት ሲሳናቸው፣ነቢዩን በድንጋይ ለመውገር መዛት ጀመሩ፦

{፦ ኑሕ ሆይ! (ከምትለው) ባትከለከል፣በእርግጥ ከሚወገሩት ትኾናለህ አሉት።}[አል ሹዐራ፡116]

ኑሕ ፣ሰዎቹ ምንም ዓይነት ምክንያታዊ አስተሳሰብ እንደማይቀበሉና እንደማይመሩ እርግጠኛ በሆኑ ጊዜ፣ከነዚህ ትእቢተኞች እንዲያድናቸው አላህን ለመኑ፦

{(እርሱም) አለ፦ ጌታዬ ሆይ! ሕዝቦቼ አስተባበሉኝ፤}[አል ሹዐራ፡117] {በኔና በነርሱም መካከል (ተገቢን) ፍርድ ፍረድ፤አድነኝም፤ከኔ ጋር ያሉትንም ምእመናን።}[አል ሹዐራ፡118]

ኑሕ ፣ሰዎቹ በክህደታቸው ከቀጠሉ የአላህ ቅጣት እንሚወርድባቸው በሚያስጠነቅቁበት ጊዜ፣አንዳንዶቹ በመሳለቅ እንዲህ አሏቸው፦፦

{ከእውነተኞቹም አንደ ኾንክ የምታስፈራራብንን ቅጣት አምጣው አሉ።}[ሁድ፡32]

ኑሕ ግን ውሳኔው በኔ እጅ አይደለም አሏቸው፦

{፦ እርሱን የሚያመጣባችሁ የሻ እንደኾነ አላህ ብቻ ነው፤}[ሁድ፡33] {ለናንተም ልመክራችሁ ብሻ አላህ ሊያጠማችሁ ሽቶ እንደኾነ ምክሬ አይጠቅማችሁም፤}[ሁድ፡34]

አላህም (ሱ.ወ.) እንዲህ ሲል ወደ ነቢዩ ላከ፦

{ከሕዝቦችህ በእርግጥ ካመኑት በስተቀር (ወደፊት) አያምኑም፤ይሠሩትም በነበሩት (ክህደት) አትዘን . . }[ሁድ፡36]

ማስረጃው ተጠናቆ ቀርቧል፤የማመካኛ ቀዳዳ ሁሉ ተዘግቷል፤ጥሪውም ለዐሥር ምእተ ዓመታት ያህል ተራዝሟል። ነቢዩ ኑሕም  ከዚህ ሁሉ ረዥም ዘመናት ጥረት በኋላ ከሕዝባቸው ተስፋ ቆርጠዋል። በመሆኑም እንዲህ ሲሉ አላህን (ሱ.ወ.) ለመኑ፦

{ኑሕም አለ፦ ጌታዬ ሆይ! ከከሃዲዎቹ በምድር ላይ አንድንም አትተው። አንተ ብትተዋቸው ባሮችህን ያሳስታሉና፤ኀጢአተኛና ከሓዲንም እንጅ ሌላን አይወልዱም።}[ኑሕ፡26-27]

መርከብ እንዲሰሩም አላህ ላከባቸው፦

{ወደርሱም (እንዲህ ስንል) ላክን፦ በተመልካችነታችንና በትእዛዛችን፣ታንኳን ሥራ፤}[አል ሙእሚኑን፡27]

መርከቡንም መስራት ጀመሩ፦

{ከወገኖቹም መሪዎቹ በርሱ አጠገብ ባለፉ ቁጥር ከርሱ እየተሳለቁ መርከቢቱን ይሠራል።}[ሁድ፡38]

ኑሕም  በመልካም ስነምግባርና በተለሳለሰ አነጋገር መልስ ሰጧቸው፦

{ከኛ ብትሳለቁ እኛም እንደ ተሳለቃችሁብን ከእናንተ እንሳለቅባችኋለን አላቸው።}[ሁድ፡38]

ከዚያም ሕዝቡን አስጠነቀቁ፤በአላህም ቅጣት አስፈራሩ፦

{የሚያዋርደው ቅጣት የሚመጣበትን፣በርሱም ላይ ዘውታሪ ቅጣት የሚሰፍርበትን ሰው፣(ማን እንደ ኾነ) ወደፊት ታውቃላችሁ (አላቸው)።}[ሁድ፡39]

መርከቡ ተሰርቶ እስኪያበቃ ድረስ ሥራውን በትጋት አከናወኑ። ከዚያም ከርሳቸው ጋር ያመኑትን ሰዎችና ሕይወት ካላቸው ነገሮች ሁሉ ጥንድ ጥንድ በመርከቢቱ እንዲያሳፍሩ አላህ (ሱ.ወ.) ኑሕን አዘዛቸው፦

{ትእዛዛችን በመጣና እቶኑም በገነፈለ ጊዜ፣በርሷ ውስጥ ከየዓይነቱ ሁሉ ሁለት ሁለት፣(ወንድና ሴት)፤ቤተሰቦችህንም፣ቃል ያለፈበት ሲቀር፣ያመነንም ሰው ሁሉ ጫን አልነው፤ከርሱም ጋር ጥቂቶች እንጅ አላመኑም።}[ሁድ፡40]

አምነው የተከተሏቸውን ሰዎችና ጥንድ ጥንዶቹንም እንስሳት አሳፈሩ፦

{፦ መኼዷም መቆሟም በአላህ ስም ነው፣እያላችሁም በውስጧ ተሳፈሩ፤ጌታዬ መሓሪ አዛኝ ነውና ?አላቸው።}[ሁድ፡41]

ኑሕና ከርሳቸው ጋር ያመኑ ሰዎች፣ከጥንድ ጥንዶቹ እንስሳት ጋር በመርከቡ ተሳፍረው ቦታ ቦታቸውን ሲይዙ፣ሰማዩ ከባድና የማያቋርጥ ዝናም ማንቆርቆር ጀመረ። ወንዞችና ምንጮች በውሃ ገነፈሉ፦

{ወዲያውም የሰማይን ደጃፎች በሚንቧቧ ውሃ ከፈትን። የምድርንም ምንጮች አፈነዳን፤ውሃውም (የሰማዩና የምድሩ) በእርግጥ በተወሰነ ኹነታ ላይ ተገናኘ። ባለ ሳንቃዎችና ባለ ሚስማሮች በኾነችም ታንኳ ላይ ጫነው። በጥበቃችን ሥር ኾና ትንሻለላለች፤ተክዶ ለነበረው ሰው ምንዳ (ይህንን ሠራን)።}[አል ቀመር፡11-14]

ኑሕ  ያላመነውን ልጃቸውን ከውሃ ማጥለቅለቁ ለመሸሽ ሲሞክር ያዩትና እንዲህ ሲሉ ይጠሩታል፦

{ልጄ ሆይ! ከኛ ጋር ተሳፈር፣ከከሓዲዎቹም አትኹን ሲል ጠራው።}[ሁድ፡42]

ልጁ ግና አላምን ይላል፤የአባቱን ምክር አሻፈረኝ ብሎ ለኑሕ እንዲህ ሲል ይመልሳል፦

{(ልጁም)፦ ከውሃው ወደሚጠብቀኝ ተራራ እጠጋለሁ አለ፤}[ሁድ፡43]

ኑሕ  ልጃቸውን በእዝነትና በርህራሄ ተመለከቱና እንዲህ አሉት፦

{(አባቱም)፦ ዛሬ ከአላህ ትእዛዝ ምንም ጠባቂ የለም፤(እርሱ) ያዘነለት ካልኾነ በቀር አለው፤}[ሁድ፡43]

{ማዕበሉም በመካከላቸው ጋረደ፤ከሰጣሚዎቹም ኾነ።}[ሁድ፡43]

ቀደም ብሎ ቤተሰባቸው ለማዳን አላህ ቃል የገባላቸው ኑሕ ፣ሆዳቸው ለአብራካቸው ክፋይ ይራራና ያድነው ዘንድ ወደ አላህ (ሱ.ወ.) ይማጸናሉ። እንዲህ ሲሉም ለመኑ፦

{፦ ጌታዬ ሆይ! ልጄ ከቤተሰቤ ነው፤ኪዳንህም እውነት ነው፤አንተም ከፈራጆቹ ሁሉ ይበልጥ ዐዋቂ ነህ።}[ሁድ፡45]

በጎ ሠሪ ምእመናን የሆኑ ቤተሰቦቻቸውን ለማዳን ቃል የገባላቸው አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦

{(አላህም)፦ ኑሕ ሆይ! እርሱ ከቤተሰብህ አይደለም፤እርሱ መልካም ያልኾነ ሥራ ነው፤ . . . አለው።}[ሁድ፡46]

በሃይማኖት ውስጥ አማላጅ ጉዳይ አስፈጻሚ የለም፤እርሱ ቤተሰብህ አይደለም። በአላህ አንድነት ካላመነና እርሱን ብቻ ካልተገዛ ያንተ የነቢዩ ልጅ መሆኑ ምንም አይጠቅመውም።

ውሃው ምድሪቱን ሙሉ በሙሉ ካጥለቀለቀና ከሓዲዎቹን ሙሉ በሙሉ ካጠፋ በኋላም ለምድሪቱ እንዲህ ተባለ፦

{ተባለም፦ ምድር ሆይ! ውሃሽን ዋጪ፤44]

ከምድር የፈለቀው ውሃ ወደ ምድር ገባ፤ለሰማይም ጥሪ ተላለፈ፦

{ሰማይም ሆይ! (ዝናምሽን) ያዢ።}[ሁድ፡44]

ከሰማይ የሚንቆረቆረው ውሃ ጋብ አለ፤ዝናሙም አቆመ፦

{ጁዲይ በሚባልም ተራራ ላይ (መርከቢቱ) ተደላደለች፤}[ሁድ፡44]

ጁዲይ መርከቢቱ የቆመችበት ተራራ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) ወደ ኑሕ  እንዲህ ሲል ላከ፦

{፦ ኑሕ ሆይ! ከኛ በኾነ ሰላም፣ባንተ ላይና አንተም ጋር ባሉት ሕዝቦች (ትውልድ) ላይ በኾኑ በረከቶችም፣የተጎናጸፍክ ኾነህ ውረድ፤}[ሁድ፡48]

ኑሕ ከመርከቧ ወረዱ። ከርሳቸው ጋር የነበሩ ምእመናንም ወረዱ። መንደርም መሰረቱ። እጽዋት ተከሉ። አብሯቸው የነበሩ የእንስሳት ዝርያዎችንም ጥይራቡ ዘንድ አውጥተው ለቀቁ። በምድር ላይ ግንባታ ተጀመረ። ሰዎችም መዋለድና መራባት ቀጠሉ።