የሦስቱ ጓደኛሞች የቀጠሮ ሰዓት ከመድረሱ በፊት ራሽድ ኮምፒውተሩ ላይ ሆኖ የራጂቭንና የማይክልን መግባት እየጠበቀ ነበር። ከአፍታ በኋላ ሁለቱ በተከታታይ ብቅ አሉ። ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ራሽድ ተናገረ፦
ራጂቭ፣ባለፈው ውይይታችን መጨረሻ ላይ፣ከቀጠሮ አለማክበር በተጨማሪ የአንዳንድ ሙስሊሞችን ስነምግባር በተመለከተ የምትለው ነገር እንዳለህ ጠቅሰህ ነበር።
ራጂቭ፦ ልክ ነው፤ከሌሎች ጋር በሚኖራችሁ በይነሰባዊ ግንኙነቶች ውስጥ ትኩረት የማትሰጡት ለቀጠሮው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የሰው ለሰው መግባቢያ ጥበብ ገጽታዎችም ጭምር መሆኑ ይስተዋላል።
ራሽድ፦ እንዴት ማለት? በአያያዜና በምግባሬ ተገቢ ያልሆነ ነገር ወይም ከአደብ ያፈነገጠ ነገር አየኽብኝ'ንዴ?!
ራጂቭ፦ የለም፣በፍጹም . . ይቅርታ አድርግልኝና አንተን በግልህ ማለቴ ሳሆን፣በሙስሊሞች ዘንድ በጥቅሉ የሚስተዋለውን ሁኔታ ማለቴ ነው። አንድ ሬስቶራንት ገብቼ መግቢያው ላይ "ለውሾችና ለዐረቦች መግባት የተከለከለ ነው!" የሚል የተጻፈበት ሰሌዳ አየሁ። በዚህ ተከፍቼ የሬስቶራንቱን ባለቤት ለምን እንደተጻፈ ምክንያቱን ጠየቅኹት . . ኩራትና ትእቢት ከገጽታው እየተነበበም ቢሆን ለዚህ አድራጎቱ ማለፊያ ምክንያቶችን ደረደረ። ሬስቶራንቱ የላቀ ደረጃ ስላለው ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ሚኒስትሮችና ታላላቅ ሰዎች የሚጎበኙት መሆኑን ነገረኝ . . በአንድ ወቅት ወደ ሬስቶራንቱ የመጡ የዐረብ ወጣቶች ሬስቶራንቱንና ደንበኞቹን የሚጎዳ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ፈጸሙ።
- ወጣቶቹ አንዴ ጠረጴዛዎቹን ሠራተኞች እየከለከሏቸው እንዳሻቸው ከቦታቸው አንስተው ወደሚፈልጉት ቦታ በመውሰድ የሬስቶራንቱን ሰላምና ጸጥታ ያደፈርሳሉ፤ደንበኞችን በዚህ አድራጎታቸው ያስከፋሉ . .
- ሌላ ጊዜ ደግሞ በመካከላቸው የሆነ ልዩነት ይፈጠርፈና በጣም ከፍ ባለ ድምጽ በመጯጯህ ሬስቶራንቱን ሰላም ይነሳሉ፤ይበጠብጣሉ . .
- አንዳንዶቻቸው ደግሞ በሚያስቀይም ሁኔታ ጣቶቻቸውን ወደ ምግብ ሳህኖች ይዘፍቃሉ፤በዚህም ሌሎች ደንበኞችን ያስከፋሉ።
- ከዚህም አልፎ አንዳቸው በሹካ ወይም በብላዋ ጀርባውን ሲያክክ ነበር . .
በዚህ ተገቢ ያልሆነ ስነምግባር ምክንያት ብዙ ታላላቅ ደንበኞቹን ያሳጡት በመሆናቸው ዐረቦች ወደ ሬስቶራንቱ እንዳይገቡ የከለከለ መጎኑን ነገረኝ።
ራሽድ፦ ከተናገርካቸው ውስጥ ብዙዎቹ ትክክል ናቸው። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩላችሁ እኛው ራሳችን በአድራጎታችን በራሳችን ላይ ጥፋት ሠርተን ሌሎች ስለኛ ጥሩ አመለካከት እንዳይኖራቸው ያደረግነው እኛው ነን . . ግና እነዚህን የተሳሳቱ የግለሰቦች አድራጎቶችን ከእስላም ጋር ማያያዝ ስህተት በመሆኑ ሊታረም የሚገባ መሆኑን አሁንም ደግሜ ማስታወስ እፈልጋለሁ።
ማይክል፦ እነዚህን አድራጎቶችም ምናልባት ከአካባቢ ተጽእኖ ጋር ተያይዘው ይሆን?!
ራሽድ፦ በትክክል፤የጠቀስካቸው ወጣቶች ከታነጹበት የአስተዳደግ ሁኔታ በተጨማሪ፣የአካባቢን ተጽእኖ ችላ ማለት አልችልም።
ማይክል፦ የተሳሳተ የአስተዳደግ ሁኔታን ተጽእኖ እረዳለሁ፤እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ አካባቢ የሚያሳድረው ተጽእኖ ግን አይገባኝም!
ራሽድ፦ ይህን ተጽእኖ እንድትረዳ ምሳሌ ልስጥህ፦ እናንተ በዓለም ላይ በጣም ቀዝቃዛ በሆነ የአየር ንብረት ውስጥ በሚገኝ የምድር ክፍል እንደምትኖሩ ይታወቃል። በዚህ የዓለም ክፍል ያለው የክረምት ወቅት ረዥም፣ቅዝቃዜው የከፋ፣በዝናም በበረዶና በቀዝቃዛ ንፋስ የታጀበ አስቸጋሪ ወቅት ነው። በዚህ ዓይነቱ ምቹ ያልሆነ የአየር ንብረት ውስጥ የሚኖር ሰው ይህን ሁሉ ግምት ውስጥ ሳያስገባና ችግሩን ለመቋቋም አስፈላጊውን ጥንቃቄና ዝግጅት ሳያደርግ መኖር አይችልም። ለምሳሌ ያህል፣መኖሪያ ቤቶችንና ተቋማትን ሲሠሩ ይህን የአየር ንብረት ሁኔታ ግምት ውስጥ በሚያስገባ መልኩ መቀየስ የግድ ነው። ሥራውንም በጥንቃቄ በጥራትና በብቃት መፈጸም የግድ ነው። ጣሪያዎች፣በሮችና መስኮቶች፣ . . ፈሳሽና ቀዝቃዛ አየር እንዳያስገቡ በከፍተኛ ጥንቃቄ መሠራት ይኖርባቸዋል። ለዚህ ሁኔታ ተስማሚ የሆነ የማሞቂያ ስልትና ለወቅቱ ፍላጎት በቂ የሆነ ነዳጅና ማገዶ ማዘጋጀትም የማይታለፍ ግዴታ ነው . . እነዚህ ሁሉ ተደማምረው በጥንቃቄ፣በብቃት፣በጥብቅነትና በእቅድ በመመራት ወደሚገለጹ የአፈጻጸም ስነምግባራት ይለወጣል።
በኛ አገር ግን ይህን የመሰለ አስቸጋሪ የአየር ንብረት የለም። በመሆኑም ሰው በሕይወት ለመቆየት እነዚህ የአፈጻጸም እሴቶችና ስነምግባሮች አያስፈልጉትም። በዚህ ሁኔታ ለአካባቢ ተጽእኖ ሲጋለጥ የብዙዎች የአኗኗር ዘይቤ ሥርዓተ አልበኝነትን የተላበሰ ይሆናል። በአብላጫው በራሃማ የሆነው የኛ አካባቢ የድርቀት ሁኔታ ወደ ስሜተ ሸካራነት የመለወጥ እድልም ሊኖረው እንደሚችል አትዘንጋ።
ራጂቭ፦ ታድያ ይህን ሰው ለአካባቢው ተጽእኖ ሰለባ እንደሆነ፣ስነምግባራዊ እነጻም ሆነ ለአነዋነዋሩ ሥርዓት ሳናበጅለት፣ከሌሎች ጋር ያለው በይነሰባዊ ግንኙነቱ ሥርዓት ሳይዝና ሳይገራ በሥርዓተ አልበኝነት እንዲኖር ምክንያት ልንሰጠው ይገባልን?
ራሽድ፦ እንደዚያ አይደለም። ይህ የኔ ትንተና አሁን ለምናስተውለው ሁኔታ እውነተኛው መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ የተደረገ ሙከራ ነው።
ራጂቭ፦ በምዕራቡ ዓለም ሕዝቦችና በምሥራቁ ወይም በሙስሊሙ ዓለም ሕዝቦች መካከል በአየር ንብረት ሁኔታ ልዩነት የምንመለከት ከሆን፣የሁለቱ ዓለም አብዛኞቹ ሕዝቦች በሚከተሏቸው ሃይማኖቶች መካከልም ልዩነት እናያለን። ታድያ ለምናነሳቸው ሁኔታዎች እስላም መንስኤ የማይሆንበት ምን ምክንያት አለ?!
ራሽድ፦ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ሰፋ ባለው የዕባዳ (አምልኮተ አላህ) ጽንሰ ሀሳብ፣ሥራዎቹን ሁሉ ዕባዳ ለማድረግ እስላም የሙስሊሙን ሕይወትና ጊዜ አደራጅቶለታል። ከሌሎች ጋር በሚኖረንን ግንኙነት የሚመሩ የስነምግባር (etiquette) ወይም የኣዳብ ጥበብ ንድፈ ሀሳቦች አብዛኞቹ እንደሚያረጋግጡት፣ይህ ጥበብ ምንጩ እስላማዊው ሃይማኖት መሆኑንና በሙስሊሞች አማካይነት ወደ አንዱሉስ (እስፔይን) የደረሰ መሆኑን ብዙዎች አያውቁ ይሆናል። ከአንዱሉስ ውድቀት በኋላ ብዙ አገሮች ከነዚህም መካከል ፈረንሳይ፣እስፔይንና እንግሊዝ ይህን ዕውቀት ከሙስሊሞች ወስደው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት አዳብረውታል፤ዛሬ ባለው መልኩ ለኛ እስኪደርስ ድረስ ሌሎች ዝርዝር ነገሮችንም አክለውበት አደራጅተውታል።
ማይክል (እየሳቀ)፦ እናንተ ሙስሊሞች‘ኮ ለሃይማኖታችሁ ካላችሁ ድንበረ የጣሰ ወገንተኝነት የተነሳ ማንኛውንም መልካም ነገር ከርሱ ጋር ማስተሳሰር ትወዳላችሁ . . ያን ማድረግ ሰፊ ጥናት እንደሚሻ አውቃለሁና ለምትናገረው ነገር ማረጋገጫ አምጣ አልልም፤‘ምጠይቅህ ነገር ቢኖር እነዚህ የስነምግባር መርሆዎች እስላም ውስጥ መኖራቸውን እንድታረጋግጥልኝ ብቻ ነው።
ራሽድ፦ እስላም የግለሰብን ስነምግባርና ፀባዩን በሁሉም የሕይወቱ ዘርፎች ውስጥ ያሻሻለ ሲሆን፣በቅዱስ ቁርኣንና በነቢያዊ ሱንና ውስጥ በስነምግባር (etiquette) ወይም በኣዳብ ጥበብ ስር የሚመደቡ ብዙ መሰረታዊ መርሆዎች ይገኛሉ።
ማይክል፦ ወዳጄ ይህ ድፍን አነጋገር ነው። የምትለው ነገር አሳማኝ እንዲሆን ምሳሌዎችን እንድታቀርብ እፈልጋለሁ።
ራሽድ፦ ‘ምናገረውን ለማብራራት አንዳንድ ምሳሌዎችን አቀርብላችኋለሁ። ለምሳሌ ያህል ነቢዩ ﷺ ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ውስጥ የነበራቸውን ስነምግባር እንመልከት፦
ወርዶ ለባለቤቱ የመኪና በር የሚከፍት ወንድ ስናይ እንዴት ያለ ትሁትና በመልካም ስነምግባር የታነጸ ሰው ነው! እንላለን። ረሱል ﷺ ግን መሬት ቁጭ ብለው ባለቤታቸው በእጃቸው ላይ ሆነው ግመል ላይ እንዲቀመጡ ያደርጉ ነበር ።
ረሱልﷺ ከባለቤቶቻቸው፣ከልጆቻቸውና ከአገልጋዮቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ውስጥ የነበራቸው ስነምግባር ፍጹም የሆነ ርህራሄን፣ትዕግስትንና ይቅርባይነትን የተላበሰ ነበር። አንድ ጊዜ ነቢዩ ﷺ ሙስሊሞችን በኢማምነት መርተው እያሰገዱ ሱጁድ ላይ በነበሩበት ሁኔታ፣ከልጅ ልጆቻቸው መካከል አንደኛው ሕጻን ይመጣና ጀርባቸው ላይ ይወጣል። ነቢዩ ግን ለሕጻኑ በመራራት ከጀርባቸው ላይ እስኪወርድ ድረስ አልተንቀሳቀሱም ነበር።
እስላም ለተገራ ስነምግባር፣ለትሁትነትና ለውብ ጸባያት ሁሉ ጥሪ ያደርጋል። የእስላም ረሱል ﷺ ይህን ሁሉ በተግባር ተላብሰዋል። ረሱል ﷺ በሶሓቦቻቸው ዘንድ የተከበሩ ነቢይና የእስላማዊው መንግስት ርእሰ ብሔር ከመሆናቸውም ጋር፣እጅግ በጣም ትሁት የሆኑ ሰው ነበሩ። ከትሕትናቸው ብዛት ልብሳቸውን ለራሳቸው ያጥቡ ነበር። የሚያገለግላቸውን ሰው ከአቅሙ በላይ እንዲሠራ አያዙም ነበር። አገልጋያቸውን አንድ ነገር እንዲሠራ ከጠየቁ አብረውት በመሥራት ያግዙታል። ሙስሊም ካልሆኑት ወገኖች ጋር እንኳ ድንቅ የሆነ ሰብአዊ ስነምግባራዊ አቋም ነበራቸው። አንድ ወቅት የአይሁዳዊ ሰው አስከሬን የተሸከሙ ሰዎች በአጠገባቸው ሲያልፉ ነቢዩ ﷺ ተነስተው ቆሙለት። በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎች በአድራጎታቸው ሲገረሙ፣ነቢዩ ﷺ ሁሉም ነፍስ ነውና ለሰው ልጅ አስከሬን ከበሬታ በመስጠት ረገድ በሰዎች መካከል ልዩነት እንደማይደረግ አብራሩላቸው።
ሌላው ቀርቶ እስላም የሰውን አካሄድ ከስነምግባራዊ ጸባዩ ጋር አስተሳስሯል። ቁርኣን የአካሄድን ስነምግባራዊ መሰረት ያስቀመጠ ሲሆን፣አንገትን በጣም ቀና በማድረግ በኩራት ከሰዎች በላይ የመሆን ስሜትን አለማንጸባረቅ፣አንገትን በማዘቀዘቅም ተዋራጅ አለመምሰልን ደንግጓል። አላህ ﷻ እንዲህ ይላል፦
{ጉንጭህንም (በኩራት) ከሰዎች አታዙር፤በምድርም ላይ ተንበጣርረህ አትኺድ፤አላህ ተንበጣራሪን፣ጉረኛን ሁሉ አይወድምና። በአካኼድህም፣መካከለኛ ኹን፤ከድምጽህም ዝቅ አድርግ፤ከድምጾች ሁሉ አስከፊው የአህዮች ድምጽ ነውና።} [ሉቅማን፡18-19]
ራጂቭ፦ ከዚያ ሬስቶራንት ባለቤት ጋር ብገናኝ፣በዓይኑ ካየው ከነዚያ ወጣቶች ድርጊት ተቃራኒ የሆነ ሌላ ገጽታ ላስተላልፍለት እችላለሁ?
ራሽድ፦ በዚያ ቦታም ሆነ በሌለው ቦታ ከጠቀስካቸው ወጣቶችና ከሌሎቹም ኢ-ስነምግባራዊ ድርጊቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አንዳንድ እስላማዊ ስነምግባራት እጠቅስልሃለሁ።
ከነዚህ ኣዳብ መካከል፣እስላም ለሌሎች ሠላምታ ማቅረብን ማዘዙ፣በሕብረተሰቡ ውስጥ ሠላምታ መንዛትን ማበረታታቱ፣ይህን ማድረግ ፍቅርና መዋደድ እንዲሰፍን የሚያደርግ መሆኑን ማስገንዘቡ፣ለሠላምታ ምላሽ መስጠትን ማሕበራዊ ስነምግባር ብቻ ሳይሆን፣ሃይማኖታዊ ግዴታ ማድረጉ ይገኙበታል። በመመገብ ላይ ለሚገኝ ሰው ምግቡ በአፉ ውስጥ ካለ ሠላምታ ማቅረብን፣ገና እንቅልፍ እየወሰደው ላለው ሰውም ሠላምታ መስጠትን የከለከለ ሲሆን፣የተኙ ሰዎች ባሉበት ቦታ ድምጽ መቀነስንም ደንግጓል።
የግድ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ድምጽን ከፍ ማድረግ ቁርኣን አጥላልቶታል። አላህ ﷻ እንዲህ ይላል፦
{በአካኼድህም፣መካከለኛ ኹን፤ከድምጽህም ዝቅ አድርግ፤ከድምጾች ሁሉ አስከፊው የአህዮች ድምጽ ነውና።} [ሉቅማን፡19] ከዚህ አልፎ ከቤቱ ውጭ ቆሞ የቤቱን ባለቤት በከፍተኛ ድምጽ የሚጣራውን ሰው በአለዐዋቂነት ገልጾታል። አላህ ﷻ እንዲህ ይላል፦
{እነዚያ ከክፍሎቹ ውጭ ኾነው የሚጠሩህ፣አብዛኞቻቸው አያውቁም።}[አልሑጁራት፡4]ነቢዩ ﷺ በማንም ግለሰብ ላይ ጮኸው አያውቁም፤ድምጻቸው በጩኸት ከፍ ብሎ ፈጽሞ አያውቅም።
እስላም በሁሉም ቦታ፣በጉባኤ፣በመመገቢያ ቦታ፣በመኖርያ ቤት፣ከቤት ውጭ፣ቀጣይነት ባለው መልኩ ለንጽሕና ጥሪ አድርጓል። በመብላትና በመጣጣት ላይ ሊከተሉት የሚገባውን ስነምግባርም አስቀምጧል። የሰው ልጆች እንደ ማንኪያ፣ሹካና ሳህን የመሳሰሉ የመመገቢያ ቁሳቁሶችን ገና ባላወቁበት ጊዜ፣ረሱል ﷺ ከሦስት በበለጡ ጣቶች መብላትን ከልክሏል . . ሲመገቡ እጅ ማእዱ ላይ እዚያ እዚህ እንዳይልና ይበልጥ ከሚቀርበው በኩል መብላትን፣ሲጠጡ ውሃን በአንድ ትንፋሽ መጨለጥ ሳይሆን በሦስት ትንፋሾች እንዲሆን ማድረግን፣ሆድን በምግብና በመጠጥ አለመወጠርን . . እስላም መክሯል። በምግብ ወቅት ሊመሰረት ለሚችል ማሕበራዊና ስሜታዊ ገጽታም ትኩረት በመስጠት፣የመመገቢያ አጋጣሚን በህብረተሰቡ አባላት መካከል ቅርርብና ውዴታን ለመፍጠር መግቢያ በር አድርጓል። እንዳይቦዝን ወይም ሐፍረት እንዳይሰማው ሲባል፣ ሲመገቡ ከእንግዳ ጋር መጫወትንም አበረታቷል። ታላቁ ነቢያችን ﷺ ባለቤታቸውን በእጃቸው ይመግቡ የነበረ ሲሆን፣«በላጩ ምጽዋት ባል በሚስቱ አፍ ውስጥ የሚያደርገው ጉርሻ ነው» ብለዋል። ረሱልﷺ ራሳቸው በጠጡበት መጠጫ ከንፈራቸው ባረፈበት ቦታ ባለቤታቸውን ዓእሻን (ረዐ) ያጠጡ ነበር . . እስላም ምግብን ለአላህ ﷻ ተገዥ ከመሆን ጋር ያስተሳሰረ ሲሆን፣ከምግብ በፊት የአላህን ስም ማውሳት፣ከተበላ በኋላ ደግሞ አላህን ማመሰገን አዟል።
ማይክል፦ ራሽድ ይቅርታ አድርግልኝና . . በሃይማኖታችሁና በናንተ ድርጊቶች መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን ልንገርህ። በዚህ መስክ ከናንተ ይልቅ ለሃይማኖታችሁ አስተምሮ የምንቀርበው እኛ ነን።
ራሽድ፦ በጣም አዝናለሁ፣ያልከው እውነት ነው።