ራሽድ እንደተቀመጠ ላፕቶፑን ከሻንጣው አወጣ፤በመክፈት ላይ እያለ ማይክል እንዲህ ሲል አቋረጠው፦
ዛሬ የተለየ የቪዲዩ ትእይንት አሳየሃለሁ፤ትእይንቱ ከግማሽ ደቂቃ ትንሽ የሚያልፍ ሲሆን ያልተለመደ ዓይነት ነው፤አንድ መቶ ዓመት ወደ ኋላ የሚወስደን ታሪካዊ የምስል ሰነድ ነው።
ማይክልና ራሽድ ወደ ኮምፒውተሩ ቀረብ ብለው በከፍተኛ ትኩረት ዓይኖቻቸውን ወደ እስክሪኑ አነጣጠሩ።
ማይክል፦ ዋው፣እንዴት ያስደስታል! ከአንድ መቶ ዓመት በፊት አካባቢ በአገሬ በእንግሊዝ የነበረው የአኗኗር ሁኔታ እንዴት እንደ ነበረ በማየቴ በጣም ደስተኛ ነኝ . . በተላላፊ መንገደኞች ፊት ላይ የሚነበበውን ደስተኝነት ተመልከት . . የዚህን ሕጻን ደስ ደስ እስኪ ተመለከት! . . ሕይወት ለተፈጥሮ ይበልጥ የቀረበችና እንደ ወረደ ነበረች ማለት ነው . . ለነፍስ በጣም ቅርብ የሆነች ሕይወት ነበረች።
ራሽድ፦ ትኩረትህን ወደ ሌላ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ለመሳብ ትእይንቱን እንደገና እመልሰዋለሁ።
ራሽድ ምስሉን እንደገና እያጫወተ ከማይክል ጋር ጭውውቱን ቀጠለ፦
ተመልከት! . . ይህችን ሴት ናት . . ሁለት . . አምስት ሴቶች ናቸው፤አስተውለህ እያቸውማ . . በባርኔጣ ከተሸፈነው ራሳቸውና ከመዳፋቸው በስተቀር ሙሉ በሙሉ ተሸፋፍነዋል . . ልብሶቻቸው ለቀቅ ያሉና የገላቸውን ቅርጽ የማያስነብቡ ናቸው . .
ማይክል፦ ትክክል ነው!
ራሽድ፦ ታዲያ ምንድነው የተፈጠረው?!
ማይክል፦ በምኑ?
ራሽድ፦ በምዕራቡ ዓለም ሕብረተሰባችሁ ውስጥ . .
ማይክል፦ ገላን ገላልጦ እርቃን መሄዱን ማለትህ ነው?!
ራሽድ፦ በትክክል፣ይህ አጠቃላዩ የስነምግባር እሴቶች ይዘት መንኮታኮቱን የሚጠቁም ትእይንት ነው ባይ ነኝ።
ማይክል፦ ይህማ የግለሰባዊ ነጻነቶች ጉዳይ ነው፤እኛ ዛሬ ነጻነትን አብዝቶ የሚያከብር ሕብረተሰቦች ነን። እያንዳንዱ ግለሰብ የፈለገውን ዓይነት የአኑዋኑዋር ስልት የመከተልና ያሸውን ፋሽን የመምረጥ መብት አለው።
ራሽድ፦ በእርግጥ ያንን እገነዘባለሁ፤ግና በጥንቃቄ ለመመርመር ራሳቸውን የቻሉ የውይይት ዙሮች የሚያስፈልጉት ጉዳይ ነው። ትኩረት የሚስበው ነገር፣የስነምግባር እሴቶቹን መቀየር በሚመለከት ሁሉም የሕብረተሰቡ አባላት በምርጫ በአንድ መርህና ምንጭ ላይ የሚመረኮዙ ይመስል፣ሕብረተሰባዊ ይሁንታና ስምምነት የተሰጠው መሆኑ ነው።
ማይክል፦ ማህበራዊ ንቃተ ሕሊና እና የወል ግንዛቤ የሚባል ነገር መኖሩ ካንተ የተሰወረ አይደለም። ግለሰቦች ይህን ይዘው የሚያድጉ በመሆኑ እያንዳንዱ ሰው መርሕና ማጣቀሻ ሳያስፈልገው፣ከሕብረተሰቡ ምንም ዓይነት ተቃውሞም ሆነ ቅሬታ ሳይቀርብበት ወደ እያንዳንዱ ሰው መደበኛ ድርጊትነት ይለወጣሉ። በዚህ የጋራ ግንዛቤ ማእቀፍ ውስጥ ግን በግለሰቦች ምርጫዎች ዓይነት መካከል ልዩነት ሊኖር ይችላል።
ራሽድ፦ በጣም ጥሩ ነው፤ይህን ክስተት ይዘን ትክክልና ስህተቱን ከፈተሸን፣ቅዱስ መጽሐፋችሁ ለጨዋ አለባበስና ውበትን በእርቃን ላለማሳየት ጥሪ የሚያደርግ መሆኑን እንረዳለን። ጳውሎስ በመጀመሪያው የጢሞቴዎስ መልእክቱ እንዲህ ይላል፦ ‹‹እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፣መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።›› (2፣9-10)
ማይክል፦ የኔ ጌታ ይህ የቤተክርስቲያን አባላት ለሆኑ ሴቶች ብቻ የሚስማማ ነው። እኛ ግን ከቤተክርስቲያን ውጭ ባለው ሕይወታችን ውስጥ፣ቀደም ሲል እንደነገርኩህ ከዘመነ ሕዳሴ ወዲህ ሃይማኖትን በኛ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ ወደ ጎን ብለነዋል።
ራሽድ፦ ወዳጄ አሁን በተመለከትነው ተንቀሳቃሽ የቪዲዮ ምስል ላይ በጨዋ አለባበስ ያየናቸው ሴቶች ጎዳና ላይ የሚጓዙ እንጂ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚጸልዩ ሴቶች አይደሉም። ይህም የብርሃን ዘመን ከምትሉት ዘመን ብዙ ምእተ ዓመታት በኋላ ነበር . . ሃይማኖት ከመሪ እሴቶቻችሁ መስራችነት ለቆ የወጣ መሆኑን አምነህ ከተቀበልክ ዘንዳ፣አሁንም ደግሜ ምንድነው የተፈጠረው?! ብዬ እጠይቃለሁ። ሴቶቻችሁን ወደዚህ ርካሽ የመራቆት ሁኔታ የለወጣቸው ምንድን ነው?!
ማይክል፦ በአንተ ዓይን ውርደት ነው፤እኔ ግን የተለመደ ተራና መደበኛ ነገር አድርጌ ነው የማየው። በምስሉ ላይ ያስተዋልኩትን ልንገርህና ጊዜው ክረምት ወይም ቢያንስ የቅዝቃዜ ወቅት ነው። ይህ ደግሞ ወንዶችና ሕጻናት ከለበሱት አልባሳት ዓይነትና ከቀለማቸው ደብዛዛነት በግልጽ የሚታይ ነው . . እንዲህ የተከናነቡት በአየሩ ቅዝቃዜ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ግን በዚያን ጊዜና ሩቅ ባልሆኑ ዘመናት ሴቶች ይበልጥ ጨዋነት ያለው ልብስ ይለብሱ የነበረ የመሆኑን ሁላችንም የምናውቀውን እውነታ የሚያስተባብል አይደለም። ምን ተፈጠረ? የሚለውን በተመለከተ መልሱ በቀላሉ የሕብረተሰብ ዕድገትን ተከትሎ እሴቶችና ግንዛቤዎች ተለዋወጡ ነው።
ራሽድ፦ ይህ የራሱ የሆነ ጊዜ ሰጥተነው ልንወያይበት የምንችል ሌላ ጉዳይ ነው። ነገሩ የስነምግባርን አንጻራዊነት የሚመለከት ጉዳይ ሲሆን፣የሳይንስና ቴክኖሎጂን ዕድገት አስፈላጊነት እረዳለሁ፤ስነምግባርና እሴቶችን ለዚህ ዕድገትና መሻሻል ማስገዛት ግን አይታየኝም።
ማይክል፦ ችግር የለውም፣ወደፊት እንወያይበታለን። ራሽድ ፍቀድልኝና ሴትን ሁሌ እንደ መደሰቻ እቃ የምትመለከቷት ለምንድነው?! ይህ ነገር ለምን እንዲህ ያሳስባችኋል?!
ራሽድ፦ በእስላም አመለካከት ሴትም ሆነች ወንድ ሁለቱም ሰዎች ሲሆኑ፣ሰብአዊ ፍጡር ደግሞ ከገላ ከነፍስና ከአእምሮ የተዋቀረ ፍጡር ነው። ሥጋዊነቱን ብቻ ሳይሆን እንስሳዊነቱንም ጨምሮ ከነዚህ አንዱንም ችላ ማለት አንችልም። ይህ ተናጋሪ እንስሳ ወደ ሰብአዊ ፍጡርነት ደረጃ ለመድረስ ከፍ ማለት የሚችለው በስነምግባር እነጻ፣በመንፈስ ምጥቀትና ማህበራዊና ሕጋዊ ቅንጅትን ባካተተ የተሟላ ሥርዓት አማካይነት ብቻ ነው። እናንተ ግን የሰለጠናችሁና የመጠቃችሁ አድርጋችሁ ራሳችሁን ገምታችሁ ቤተክርስቲያንን (ይበልጥ ትክክለኛ ለመሆን) ሃይማኖትን ከሕይወት በነጠላችሁ ጊዜ፣ቤተክርስቲያን በመንፈሳዊ ጉዳዮች ክልል ውስጥ ብቻ እንድትወሰንና በሥጋዊ ገላ ያሻችሁን ማድረግ ትችሉ ዘንድ፣አእምሮ ከሃይማኖት ማእቀፍ ውጭ በነጻ መንደርደሩን ወዳችሁ ተቀብላችኋል። በዚህ ምክንያትም የቁሳዊ ሥልጣኔ ሰይጣናት ከሞራላዊና ሃይማኖታዊ ማእቀፍ ውጭ በእንስሳዊ ሥጋዊ ፍላጎቶች ያለገደብ ይደሰቱ ዘንድ መረን ተለቀቁ። እንስሳዊ ሥጋዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማርካት ሲሉም ሴት ልጅ ፈታኝ ገላዋንና ውበቷን በሁሉም መንገድና በሁሉም ሁኔታዎች ለእይታ እንድታቀርብ አበረታቷት፤ይህንንም በመብትና በነጻነት ስም አጸኑት።
ማይክል፦ እኛ ግን የሴቶችን እርቃነ ገላ ጧትና ማታ ዘውትር እንመለከታለን፤እንስሳዊ ብለህ የምትጠራው ሥጋዊ ፍላጎትን ቀስቅሶብን አያውቅም።
ራሽድ፦ ይኸ ትሩፋት ወይም መልካም ስነምግባር ነው ብለህ ታስባለህ? የተራቆተ ገላን ማየትን ወይም ስሜት ቀስቃሽ ትእይንቶችን መመልከት መላመድ በጣም አነስተኛ እኩይ ውጤቱ የወሲባዊ ፍላጎት መቀዝቀዝ ሰለባ መሆን ነው። ከዚህ የሚቀጥለው ሌላ አስከፊ ጉዳቱ ደግሞ ከተለመደው የተለየና ወጣ ያለ ስሜት ቀስቃሽ ነገሮችን ወደ መፈለግ መሸጋገር ነው። ይህ ደግሞ አፈንጋጭ ወደ ሆኑ ያልተለመዱ የስጋዊ ፍላጎት ማርኪያ ዓይነቶች መዝቀጥን ሊያስከትል ይችላል።
ማይክል፦ ራሽድ አንተ ዘንድ እኩይ ውጤቶች በየዓይነቱ ናቸው፤የቅርብ የሩቁ፣እኩይ በጣም እኩይ . .
ራሽድ፦ አዎ፣ከነዚህ ክስተቶች ውስጥ ከፊሎቹ በወንጀሎች ክልል ውስጥ የሚወድቁ ሲሆን፣በአካላዊና ማህበራዊ ወይም ስነምግባራዊ ሁኔታዎች ምክንያት ወደ ወሲብ ስሜት መቀዛቀዝ ያልደረሰ ሰው፣ገደብ ባለፈ የወሲብ ስሜት ይጠመድና አስገድዶ መድፈር እንዲስፋፋ ምክንያት ይሆናል። ይህም የአስገድዶ መድፈር አኃዛዊ መረጃዎች የሚያረጋግጡት እውነታ ነው። ጥቂቱን ብቻ ላስታውስህ፦
የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አኃዛዊ መረጃ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ፈረንሳይ ውስጥ 4412 የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች መፈጸማቸውን ያመለክታል። ይህም ከሞላ ጎደል በአማካይ በየሁለት ሰዓቱ አንድ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ይፈጸማል ማለት ነው።
በአገረ እንግሊዝ ፦ የዋና ከተማው የለንደን ፖሊስ፣ሴቶች ከወንዶች ጾታዊ ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችላቸውን ስልጠና ይወስዱ ዘንድ ለማበረታታት የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ አካሂዷል። ይህም በለንደን አውራ ጎዳናዎች ላይ የሚፈጸመው ጾታዊ ጥቃትና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ወደ 11% ከፍ ማለቱ ከተነገረ በኋላ ነበር።
በአገረ አሜሪካ ፦ የኃይልና የጥቃት እርምጃ ወንጀል ሰለባዎች መብት ተሟጋች የሆነው ብሔራዊ የሰለባዎች ማእከል፣በአሜሪካ ያለው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በአማካይ በአንዲት ደቂቃ ውስጥ በ1.3 ዐዋቂ ሴት ላይ የሚፈጸም መሆኑን አስታውቋል። በ1991 ዓመተ ልደት ከስምንት ዐዋቂ ሴቶች መካከል አንዱዋ ለአስገድዶ መድፈር ወንጀል መጋለጧን ማእከሉ አረጋግጧል።
በ2009 ዓል ደግሞ ከአሜሪካውያት ሴቶች ከሦስት አንዷ በ14 ዓመት ዕድሜዋ ለአስገድዶ መደፈር እንደምትጋለጥ፣በአገሪቱ በየዓመቱ ግማሽ ሚሊዮን የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደሚፈጸምና 61% የሚሆኑ አሜሪካውያት ልጃገረዶች ክብረ ንጽሕናቸውን የሚገሰሱት 12 ዓመት ሳይሞላቸው መሆኑን አኃዛዊ መረጃዎቹ ያረጋግጣሉ።
በዝምታ የሚታለፍ ወንጀል በመባል የሚታወቅ ሌላ ዓይነት ወንጀልም አለ። እሱም አሠሪዎች ወይም ሥራ አመራሮች በሥልጣናቸው ስር በሚገኙት ሴት ሠራተኞች ላይ የሚፈጽሙት ጾታዊ ትንኮሳ ሲሆን፣ልማድ ሆኖ ሴቲቱ ሥራዋን እንዳታጣ ስለምትፈራ ወይም ለመካካሻ ስለምትጓጓ፣አለዚያም በማስረጃ ማረጋገጥ አስቸጋሪ ስለሚሆን እነዚህ ወንጀሎች አይመዘገቡም።
የሴቶች ፀረ አስገድዶ መድፈር ማህበር ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት መሰረት ከሚከሰቱት የአስገድዶ መደፈር ሁኔታዎች ከ35ቱ አንዱ ብቻ የሚመዘገብ ሲሆን ቀሪዎቹ የማይገለጹ በመሆናቸው፣እነዚህ አኃዞች በትክክል ሁኔታውን የሚያንጸባርቁ አይደሉም።
ማይክል፦ የአስገድዶ መድፈር ችግር ውስብስብ ችግር ነው። ብዙ ስነልቦናዊ፣ስነምግባራዊና ማህበራዊ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ መነሻዎች የሚደበላለቁበት የተወሳሰበ ችግር ነው።
ራሽድ፦ ትክክል ነው፤ነገር ግን ከዋነኞቹ መነሻ ምክንያቶች አንዱ በዓይን እይታም ቢሆን የወንዱን ስሜት የሚቀሰቅሱ ነገሮች ናቸው። ትኩረት የሚስበው ጉዳይ አሜሪካ ውስጥ በተካሄደ አንድ ጥናት እንደ ተመለከተው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በክረምት ወቅት የሚያንስ መሆኑና ይህም በሴቶች አለባበስ ምክንያት እርቃን የሚታየው የገላ ክፍል የሚቀንስ በመሆኑ ወይም ሰዎች ክረምት ውስጥ ብዙ ጊዜ የማይወጡ በመሆኑ የመገናኘት ዕድሉ አነስተኛ በመሆኑ ሊሆን እንደሚችል መጠቆሙ ነው። ሁለቱም ግምቶች ያንኑ ተመሳሳይ መነሻ ምክንያት ያረጋግጣሉ።
ማይክል፦ ነገር ግን ያንን በገዛ ፍላጎታቸው የመረጡት ሴቶቹ ራሳቸው ናቸው። እንዳልኩህ ሁሉ ይህ የግለሰብ ነጻነት ጉዳይ ነውና ልንከለክላቸው አንችልም።
ራሽድ፦ ላይ-ላዩን ሲታይ እንደዚያ ይመስላል። እውነቱ ግን ያለ ገደብና በልቅነት በሴቷ ገላ ለመደሰት ሲሉ፣ለእርቃነ ገላ ባህል ስርጸት የሠሩት፣ያሰማመሩትና ደጋፊ አከባቢያዊ ሁኔታዎችን ያመቻቹለት፣እንዲስፋፋና እንዲሰራጭ ቀላል ስልቶችን የፈጠሩለት፣የምዕራቡ ዓለም የሕብረተሰብ መሪዎችና በቀዳሚነትም ወንዶች ናቸው። ከዚህም አልፈው የሴቲቱን ክቡር ሰበእና እና መልካም ስነምግባር የሚጻረሩ ሕጎችን ደነገጉ። በምዕራቡ ዓለም ያሉ ሰው ሰራሽ ሕጎች ከተደፈረችው ሴት ይልቅ ለደፋሪው ወንድ የሚራሩ ሲሆኑ፣ይህም አስገድዶ መድፈር እንዲበራከት አግዟል። ይባስ ብሎም አንዳንድ የምዕራብ አገሮች አስገድዶ መድፈርን የመልካም ስነምግባር ጥሰት እንጂ የጥቃት ወንጀል አድርገው አይቆጥሩም።
ይህን ተግባራዊ ምሳሌ ውሰድ ፦ ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ረገድ ቀዳሚ ተደርጋ በምትወሰደው ፊንላንድ ውስጥ፣አንድ ወንድ አንዲት ሴትን በአንድ የመኪኖች ማቆያ ላይ ለአካል ጉዳተኞች በተዘጋጀ መጸዳጃ ቤት ውስጥ፣ራሷን ከግርግዳው ጋር በማጋጨትና እጆቿን ወደ ኋላ በመጠምዘዝ አብራው ወሲብ እንድትፈጽም አስገደዳት። በአቃበ ሕጉ አመለካከት ግን ሰውየው የተጠቀመው የኃይል እርምጃ በአነስተኛነት የሚመደብ በመሆኑ ድርጊቱ አስገድዶ መድፈር ተደርጎ አልተወሰደም!! እናም ወሲባዊ ግንኙነት እንድትፈጽም ሰለባዋን በማስገደድ ጥፋተኝነት ተወስኖበት የሰባት ወር እስራት በገደብ ተፈርዶበታል!!
ወዳጄ! ከስነምግባር አንጻር ከሁለቱ ሕብረሰቦች የትኛው ነው ይበልጥ ሰላማዊና አስተማማኙ? የዛሬው ሕብረተሰብ ወይስ ከምዕተ ዓመት በፊት የነበረው ሕብረተሰብ?! የቪዲዩ ምስሉን በድጋሜ በማየት መዝናናት ትፈልጋለህ?!
ማይክል፦ ራሽድ፣ነገሩ ግልጽ ነው። ለመሆኑ ከእስላማዊ አመለካከት አኳያ ይህን ጉዳይ እንዴት ነው የምታዩት?
ራሽድ፦ ነገሩን ለመመርመር ሌላ ዙር እንዲያውም ብዙ ዙር ውይይቶች ያስፈልጉናል።