የእስላማዊ ድንጋጌ መለያ ባሕርያት

የእስላማዊ ድንጋጌ መለያ ባሕርያት

አንደኛ - የምንጩ መለኮታዊነት፦

የእስላማዊው ሃይማኖት ምንጭ ሰዎችንና ፍጥረተ ዓለሙን በመላ የፈጠረው ኃያል ፈጣሪ አምላክ ነው። የመሰረቱና የምንጩ መለኮታዊ መሆን ብዙ መለያ ባሕርያትን የሚያሰጠው ሲሆን፣ከነዚህ መካከል አላህ (ሱ.ወ.) ፈጣሪና መጋቢ አምላክ መሆኑ፣ሕግ የመስጠትና የመደንገግ መብት የርሱ ብቻ መሆኑ ይገኙበታል። ነቢያትና መልክተኞች ተከታዮቻቸውም ሕግ ማውጣትንና መደንገግን ለአላህ (ሱ.ወ.) ብቻ የተሰጠ መብት ያደርጉ የነበረ ሲሆን ከርሱ ውጭ ያለውን ሁሉ ውድቅ ያደርጉ ነበር። ሸሪዓውን አስመልክቶ የነቢዮቹና የመልክተኞቹ መደምደሚያ ያሉትን ሲያወሳ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከመልክተኞች ብጤ የሌለኝ አይደለሁም፤በኔም በናንተም ምን እንደሚሠራም አላውቅም፤ወደኔ የሚወረደውን እንጅ ሌላን አልከተልም፤እኔም ግልጽ አስፈራሪ [አስጠንቃቂ] እንጅ ሌላ አይደለሁም በላቸው።}[አልአሕቃፍ፡9]

የአላህ መልክተኛ - አላህ ዘንድ ካላቸው ደረጃና የላቀ ከበሬታ ጋር - ወደርሳቸው የተላለፈው የአላህ (ሱ.ወ.) ሸሪዓ ተከታይ፣ለርሱ መርሕ ተመሪ እንጂ ከራሳቸው አዲስ የፈጠሩትን የሚከተሉ አይደሉም። አላህ (ሱ.ወ.) ፈጣሪ አምላክ በመሆኑ ለፍጥረታቱ የሚበጀውን ከርሱ ይበልጥ የሚያውቅ ማንም የለም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀተ ረቂቁ፣ውስጥ አዋቂው ሲኾን (ምስጢርን ሁሉ) አያውቅምን።}[አል ሙልክ፡14]

ስለ ፍጡራኑ ባሕርይና ስለፍጥረታቸው፣ስለሚጠቅማቸውና ስለሚጎዳቸው፣ስለሚበጃቸውና ስለማይበጃቸው ነገር ከማንም በላይ የሚያውቅ እርሱ ብቻ ነው። ከሠሪው ይበልጥ ስለሠራው ነገር የሚያውቅ ማንም አይኖርምና። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እናንተ ታውቃላችሁን? ወይንስ አላህ? በላቸው፤።}[አልበቀራህ፡140]

ሕግ አውጭና ሰጭው አላህ (ሱ.ወ.) ለሕጉ ፍጹማዊ የሆነ ፍትሕና እውነትን ያጎናጽፋል። አላህ (ሱ.ወ.) ሰብአዊ ፍጡራኑን በአድልኦ ከማየት የራቀ ፍትሐዊ ፈጣሪ ጌታ ነውና። የእስላም መቀጫዎችም በዛሬው ዓለማዊ ሕይወትና በመችጭው ዘላለማዊ ሕይወት የሚፈጸሙ ሲሆኑ፣በአንዱ ወይም በሌላው ምክንያት በዚህ ዓለም ላይ መብቱ ያልተከበረለትና ፍትሕ ያላገኘ ሰው ወይም በእኩይ ተግባሩ ዛሬ ያልተቀጣ ሰው፣ብድራቱን በወዲያኛው ዘላለማዊ ሕይወት ያገኛል። (39)

ሁለተኛ - ሕግጋትን ከስነምግባር ጋር ማስተሳሰሩ፦

ሕግ በመታወጁ ብቻ ዓላማው እውን እንደማሆንና ይህን ለማድረግ የሰዎች አምነውበት መቀበልና ለተግባራዊነቱ መተባበር አስፈላጊ መሆኑ የታመነ ነው። ሕግ እውን እንዲያደርግ የሚጠበቀው ዓላማና ግብ በአቀራረጹና በድንጋጌዎቹ ጥሩነት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ሕጉ የተደነገገላቸው ሰዎች ከውስጣቸው በመጣ ልባዊ ግፊት ሲተገብሩት ጭምር ነው። ይህ ውስጣዊ ግፊት የሚመጣው ለሕጉ ፍትሐዊነት ካላቸው እምነት፣ወደው ከመቀበላቸውና ሕጉን ከደነገገው ወገን ድንጋጌዎቹንና ውሳኔዎቹን ወደው በመተግበራቸው ሽልማት እንዳላቸው ከማመናቸው የተነሳ ነው። የእስላም ሕግጋት የተመሰረቱት በፍላጎትና በእምነት ወዶ በመቀበል ላይ ሲሆን አላህ (ሱ.ወ.) በእስላም ትምሕርትቶች ውስጥ ሙስሊሞች ይህንን እንዲያደርጉ አዟል፦

{በነፍሶቻቸው ውስጥ ስሜት ያለው [የሚያጭር] ቃል ተናገራቸው።}[አልኒሳእ፡63]

 

{[ለሌሎች] አስታውስም፤አንተ አስታዋሽ ብቻ ነህና። በነሱ ላይ ተሿሚ (አስገዳጅ) አይደለህም፤}[አልጋሽያህ፡21-22]

ለዚህም ነው የነቢዩ ሙሐመድን  ተልእኮ አላህ (ሱ.ወ.) በዚህ ክልል ውስጥ የወሰነው። ነቢዩ  ፦ {የተላክሁት መልካም ስነምግባራትን ምሉእ ለማድረግ ነው።} ብለዋል።

ሦስተኛ - የሰው ልጆችን ጥቅሞች ግንዛቤ ውስጥ ማስገባቱ፦

እስላማዊ ሕግን ከተቀሩት ሰው ሰራሽ ምድራዊ ሕጎች የተለየ የሚያደርገው፣በዚህች ዓለማዊ ሕይወትና በወዲያኛው ዘላለማዊ ሕይወትም የሚያሸልምና የሚያስቀጣ መሆኑ ነው። የወዲያኛው ዓለም ምንዳም ሆነ ቅጣት ሁሌም ከዛሬዋ ሕይወት ምንዳና ቅጣት በእጅጉ የላቀ ነው። በመሆኑም አንድ አማኝ ሰው ሁሌ የአላህን ሕግጋት የመተግበር፣ያዘዘውን የመፈፈጸምና ከከለከለው የመታቀብን አስፈላጊነት የሚያስገነዝብ ብርቱ ውስጣዊ ግፊትና ስሜት ይሰማዋል። በዚህ ዓለም ላይ ለፈጸመው ነገር ከቅጣት ማምለጥ ቢችል እንኳ አላህ (ሱ.ወ.) የሚያየውና የሚቆጣጠረው መሆኑን፣ሰዎች በዚህ ዓለም የሕይወት ዘመናቸው ለፈጸሙት ሁሉ አላህ (ሱ.ወ.) ፊት ነገ ተጠያቂዎች መሆናቸውን በእርግጠኝነት ያውቃል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በርሱ ላይ አንድም የማይችል መኾኑን ይጠረጥራልን?}[አልበለድ፡5]

በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አንድም ያላየው መኾኑን ያስባልን?}[አልበለድ፡7]

አራተኛ - የሕግጋቱ ማሕበራዊ ገጽታ፦

እስላማዊው ሕግ የአንዱን ጥቅም ከሌላው ጥቅም አያበላልጥም፤በሌላው ሰው ሒሳብ ለማንም አይወግንም። እስላምን የሕይወት መመሪያና የአነዋነዋር ሥርዓት አድርገው ያልያዙ ብዙ ሕብረተሰቦችን ወጥሮ ከያዘውና በግለሰብ ጥቅምና በሕብረተሰብ የጋራ ጥቅም መካከል ያለውን ቅራኔ እስላም ፈቶታል። አንዳንድ ማሕበረሰቦች ግን በካፒታሊስት ሥርዓት ውስጥ እንደሚስተዋለው ለግለሰባዊ ጥቅሞች ብልጫ በመስጠት የሚወግኑ ሲሆን፣የሶሸደሊስቱ ሥርዓት ደግሞ ሚዛኑን ወደ ሕብረተሰባዊ ጥቅም በማጋደል የግለሰብን መብት ይደፍቃል። ከሰው ልጅ ተፈጥሮ በተጻራሪ ግላዊ ነጻነትንና ሀብት የማፍራት መብትን ነፍጎ ግለሰባዊ ማንነትንና ተሰጥኦን በማኮስመን፣ብቃትና ክህሎቱን ብኩን ያደርጋል። እስላማዊው ሕግ ግን በሚመሰርተው ሕብረተሰብ ውስጥ ሥርዓቱን የሚያንጸው ሚዘናዊ በሆነ ሁኔታ እነዚህን መብቶች በሚያስተናግድ መሰረት ላይ ነው። ለሙስሊሙ ሕብረተሰብ የጋራ ማሕበራዊ ጥቅሞች ትኩረት የሚሰጥ ቢሆንም የሙስሊም ግለሰብን መብትና ፍላጎቶችም ችላ አይልም። በፖለቲካው መስክ የአገር መሪ መብት ዜጎች ለሕግና ሥርዓቱ እንዲታዘዙ ማድረግ ሲሆን የዜጎች የመታዘዝ ግዴታ ግን መሪው በአመራሩ የሕግ የበላይነትን የሚያሰፍን፣ለጋራ ጥቅሞች ትኩረት የሚሰጥ በመሆን ግዴታ የተገደበ ነው። ይህን የማያሟላ ከሆነ ግን እስላም ይህን መብት ይነጥቀዋል። መሪውን የመታዘዝ ግዴታ የሚጸናውም የአላህን ትእዛዝ መጣስ በሌለበባቸው ነገሮች ላይ ብቻ ይሆናል።

አምስተኛ - በመርሕ ላይ መጽናትና የትግበራ ገርነት፦

እስላም ከመጀመሪያ ምንጩና መሰረቱ ከሆነው፣የአላህ (ሱ.ወ.) ጥበቃ ከሚደረግለት ቁርኣን በመነጩ የማይለወጡ ጽኑና ቋሚ መደላድሎች ላይ ይቆማል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፤እኛም ለርሱ ጠባቂዎቹ ነን።}[አል ሕጅር፡9]

ከኋላውም ሆነ ከፊቱ ውሸት በማይመጣበት ሕያው መጽሐፍ ላይ ይሞረኮዛል፦

{ከኋላውም ከፊቱም ውሸት አይመጣበትም፤ጥበበኛ ምስጉኑ ከኾነው ጌታ የተወረደ [የተላለፈ] ነው።}[ሓ.ሚም አልሰጅዳህ፡42]

ወደር በማይገኝለት ከፍተኛ ጥንቃቄና በተራቀቀ ስልት የተጠናቀረው የነቢያዊው ሱንና (ፈለግ) ብዙዎቹ ዘገባዎችም ለሕግ አወጣጥ መሰረት የሆኑ አጠቃላይ ድንጋጌዎችን ያካተቱ ናቸው። እንደ ጊዜና ሁኔታዎች መለዋወጥ ተመጣጣኝ የሆኑ ዝርዝር የአፈጻጸም ደንቦችና መመሪያዎችን ከአጠቃላይ ሕግጋቱ ለሚያመነጩ የሃይማኖቱ ሊቃውንት ሰፊ ክፍተት በመለቀቁ ለትግበራ ምቹና ገር የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ዝርዝር የአፈጻጸም ጉዳዮቹ ከመሰረታዊ ሕግጋት አንቀጾች ጋር እስካልተጋጩ ድረስ የእስላማዊውን ሸሪዓን አጠቃላይ ግብና ዓላማዎች (አልመቃስድ) እውን ለማድረግ የሚመነጩ የትግበራና የአፈጻጸም ደንቦች በከፍተኛ ደረጃ የመለወጥ የማደግና የልስላሴ ባሕርያትን የተላበሱ ናቸው። በመሆኑም ፊት ያልነበሩና አዳዲስ ለተፈጠሩ ተጨባጭ ሁኔታዎች መፍትሔ የሚሰጡ አዳዲስ ዝርዝር ሕጎችን በዚህ መሰረት ላይ በመሞርከዝ ማመንጨትን የሚከለክል ነገር የለም።