ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ፣ራጂቭና ራሽድ ማይክል የውይይቱ ጀማሪ ለመሆን እንደጓጓ አስተዋሉና ራሽድ አንዲህ ሲል ቀለደበት፦
ማይክል በል ቀጥል፣ለዚህ ውይይት የምታስፈነጥራቸውን ቀስቶች አዘጋጅተህ የለም? እንዳያገኙኝ ከእስክሪኑ ፊት ገለል ልበል መሰለኝ!!
ማይክል፦ በፍጹም፣ምንም አልተኩስም፣ተረጋጋ . . ያለ ስጋት እስክሪንህ ላይ ማፍጠጥ ትችላለህ . . ። እውነቱን ለመናገር ያለፈው ውይይት ባህልና ስልጣኔዎችን ይበልጥ እንድፈትሽና ሙስሊሞች ለሰው ልጆች ምን እንዳበረከቱ ለማወቅ ጥረት እንዳደርግ አድርጎኛል። በዚህም ‹‹አንድ ሺህ አንድ ፈጠራና የምስጢራት ቤተመጽሐፍ›› በሚል ርእስ የተዘጋጀ ፊልም አግኝቻለሁ። ፊልሙ የሚወስደው ጊዜ አጭር ሲሆን 13 ደቂቃብቻ ነው። በይዘቱ ግን በርእሰ ጉዳዩ ላይ አርኪና ማራኪ ነው . . እስላማዊው ስልጣኔ በዘመናዊው የሰው ልጆች እድገት ውስጥ ያለውን አበርክቶ የሚተርክ ሲሆን፣ከሃያ የሚበልጡ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያሸነፈ ፊልም ነው።
ፊልሙ በአቀራረቡ የአጭር ትረካን ስልት የተከተለ ሆኖ በአንድ ቤተ መጽሐፍት በትምሕርታዊ ሽርሽር ላይ የነበሩ ሕጻናት ተማሪዎች በኃላፊው እየተመሩ ጉብኝት ሲያደርጉ፣የጨለማው ዘመን በመባል የሚታወቅ ዘመን በአውሮፓ እንደነበረ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሰማሉ። የእስክሪኑ መሪ ተዋናይ የቤተ መጽሐፉን ኃላፊ ገጸባሕሪ ተላብሶ የሚጫወተው ‹‹ሴር ብን ኪንግዝሊ›› ሲሆን ቀጥሎም ሙስሊሙን ሊቅ አልጀዘሪን መስሎ ይተውናል። በዚያ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሙስሊም ሊቃውንትን ለተማሪዎቹ ያስተዋውቃል። በወቅቱ ሙስሊሞች የደረሱበትን ከፍተኛ የሳይንስና የዕውቀት ደረጃ፣ከሰባተኛው እስከ አስራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ ፈጠራዎቻቸውንና ለዓለም ያበረከቱትን ሳይንሳዊ ግኝቶች እየዘረዘረ ያስረዳቸዋል።ይህ ዘመን ከታሪክ አኳያ በጣም አስደናቂ ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን ተገቢ የሆነ ትኩረትና ክብር ግን አልተሰጠውም።
ራሽድ፦ የፊልሙ ዓለማ ምንድነው?
ማይክል፦ የፊልሙ ዓላማ በአውሮፓ ለሕዳሴው ዘመን መጀመር ዋነኛ መንስኤና ምክንያት የሆነው፣በሙስሊሙ ዓለም የተፈጠረውና የተለያየ ሃይማኖት በነበራቸው ሳይንቲስቶችና የፈጠራ ሰዎች አማካይነት እውን የተደረጉ ሳይንሳዊና ቴክኒካዊ ግኝትቶች መሆናቸውንማረጋገጥ ነው። ይህ ግንዛቤ በከፍተኛ ደረጃ የተዘነጋ ታሪካዊ እውነታ መሆኑን ፊልሙ ይጠቁማል።
ራጂቭ፦ ማይክል የምትናገረውን ነገር በዝርዝር እንዳውቀው የበለጠ አጓግተኸኛል።
ማይክል፦ በዚህ ረገድ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች ሲኖሩ ጥቂቶቹን እነሆ፦ አልጀዘሪ በታሪክ ውስጥ ከታላላቅ መሐንዲሶች፣ኬሚስቶችና የፈጠራ ባለቤቶች አንዱ ሲሆን፣እንደ ትንግርት የሚጠቀሰውን የዝሆን ሰዓት ፈጥሯል። በመላው ዓለም ላይ ሰዎች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚጠቀሙባቸውን አያሌ የመገልገያ መሳሪያዎችንምሰርቷል። በጥንቶቹ ዝርዝር አሰራራቸው መሰረት የተሰሩ ሜካኒካል መሳሪያዎች፣ የነፋስና የውሃን ኃይል መጠቀም በእርሻ መስክ ስርነቀል ለውጥ እንዴት ማስገኘት እንዳስቻለ ያብራራሉ . . በተጨማሪም አንዱሉሳዊው ሐኪም አዝዘህራዊ ለቀዶ ጥገና ሕክምና የሚውሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ መሳሪያዎችንና መገልገያ እቃዎችን ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ለመፍጠር ችሏል። ፈጠራዎቹ አንዳንድ ቀዶ ጥገናዊ ነገሮችን ግንዛቤ ውስጥ ከማድረግ ጋር ዛሬም ድረስ በዘመናዊ ሆስፒታሎች ውስጥ የሕሙማንን ሕይወት በመታደግ ላይ ይገኛሉ . . ሌላው ሳይንቲስት ሐሰን ብን አልሀይሠም፣ዐይን እንዴት እንደሚሠራ ያብራራ ሰው ነው። የምስል ቀረጻና አፈጻጸሙን እብን አልሀይሠም እንዴት እንዳስቀመጠ እንድናውቅ ትንሽዬ ቀዳዳ ያለው ግዙፍ የካሜራ ሞዴል ፊልሙ ላይ እንመለከታለን።
ራጂቭ፦ ማይክል በጣም ጠቃሚ የሆነ መረጃ ነው ያመጣኸው፤ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገህ ፍተሻ ያካሄድክ አንተ ብቻ አይደለህም። እኔም የበኩሌን ጥረት አድርጌ አንዳንድ ነገሮችን አግኝቻለሁ። ዘግሪድ ሆንከህ በተባለች ጀርመናዊት ጸሐፊ ‹‹የእግዚአብሔር ሐፀሐይ ለምዕራቡ ዓለም ስትፈነጥቅ›› በሚል ርእስ የተዘጋጀ አስደናቂ መጽሐፍ አጋጥሞኛል።
ማይክል፦ ምን አዲስ ነገር አገኘህበት?
ራጂቭ፦ ያልጠበቅኳቸው ብዙ ነገሮች ትኩረቴን ስበዋል። በአውሮፓ ቋንቋዎች ውስጥ የሚገኙ ብዙ የተውሶ ቃላት መሰረታቸው ዐረብኛ መሆኑን ታውቃለህ?!
ማይክል፦ በእርግጥ የሚገርም ነው! የምርህን ነው?!
ራጂቭ፦ የምሬን ነው።ለምሳሌ(Coffee)የሚለውን የእንግሊዝኛና የሌሎች የአውሮፓ ቋንቋዎች ቃል ውሰድ፤‹‹ቀህዋህ›› ከሚለው የዐረብኛ ቃል የተዋሱት ነው። ካፌ የሚለው ቡና የሚጠጣበት ቦታም ከዚሁ የወጣ ነው . . (Rice) የሚለው ቃልም ‹‹አሩዝ›› ከሚለው የተወረሰ ነው። (Sofa) የሚለው ቃልም እንዲሁ ከዐረብኛ የተወሰደ ነው . . (Alcohol) የሚለውን የመሳሰሉ ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸውን አያሌ ቃላትም ከዐረብኛው ንበት ጋር የሚጣጣሙ ሆነው አግኝቻለሁ . .
መጽሐፉ ብዙ የማላውቃቸውን እውነታዎች አሳውቆኛል። ጸሐፊዋ ይህንኑ ጠቅለል አድርጋ ስታስቀምጥ እንዲህ ትላለች ፦ ‹‹አውሮፓ ለዐረቦችና ለዐረብ ስልጣኔ ባለዕዳ ነች። በአውሮፓና በሌሎቹም ክፍለ አሕጉራት ጫንቃ ላይ ያለው የዐረቦች ብድራት እጅግ የበዛ ነው። አውሮፓ ለዚህ ከባድ ውለታ ከረዥም ጊዜ በፊት እውቅና መስጠት ይገባት ነበር። ይሁን እንጂ ጭፍን ወገንተኝነትና የእምነቶች መለያየት ዐይኖቻችንን አሳውረው ጋርደውብናል።››
ራሽድ፦ ራጂቭ ትኩረትህን የሳቡ እነዚህን እውነታዎች የበለጠ ለማወቅ እኔንም በጣም አጓግተኸኛል።
ራጂቭ፦ ከዚህ መካከል ለማሳሌ ያህል የሚከተለውን እናገኛለን፦ የጋሊኖስን (Galen) ስሕተቶች መጀመሪያ ያስተዋለውና የደም ዝውውር ሥርዓትን ያስተዋወቀው የእስፔኑ ሳርቪቶስም ሆነ እንግሊዛዊው ሃርቬይ ሳይሆን፣በአስራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረው ዐረባዊው እብን አንነፊስ መሆኑን አላውቅም ነበር።እብን አንነፊስ በሰው ልጅ ታሪክና በሕክምና ጥበብ ታሪክ ውስጥ የሚይዘውን ይህን ታላቅ ግኝት ያስመዘገበው ከሃርቬይ በፊት አራት መቶ ከሳርቪቶስ ደግሞ ሦስት መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ነበር . .የእቅሊዶስንና የበጥሊሞስን (Patolmy) ስሕተት በቅድሚያ ያስተዋለው ዐረባዊው ሙስሊም ሊቅ እብን አልሀይሠም መሆኑንም አላውቅም ነበር። ዐይን ማየት ወደሚፈልገው ነገር ጨረር ይልክና ነጥሮ የሚመለሰውን ነጸብራቅ ይመለከታል፣የሚለው የሁለቱ ግሪካውያን እሳቤ ከዐይን የሚወጣ ጨረር አለመኖሩን በማረጋገጥና በተቃራኒው ዐይን ከነገሮች የሚንጸባረቀውን በሌንሱ አማካይነት የሚመለከት መሆኑን እብን አልሀይሠም ደርሶበታል . . በተጨማሪም መሬት በፀሐይና በራሷ ዙሪያ የምትሽከረከር መሆኗን ያገኘው በስፋት እንደሚነገረው ኮፐርኒከስም ሆነ ሌላ ሳይሆን፣ዐረባዊው ሙስሊም ሳይንቲስት አልበይሩኒ መሆኑንም አላውቅም ነበር . . ይህች አስደናቂ ኦሪየንታሊስት እንደገለጸችው ሙስሊሙ የሕክምና ሊቅ አልራዚ በሁሉም ታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ በሁሉም ዘመናት ከታላላቆቹ የሕክምና ጠበብቶች አንዱ ሲሆን፣በፈንጣጣና በኩፍኝ ላይ የተጻፉ መጣጥፎቹ ተላላፊ በሽታዎችን የሚመለከቱ የመጀመሪያዎቹ ሁነኛ ሥራዎች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው። ጽሑፎቹ በአስተውሎ፣በበሽታዎች ምርመራና ትንተና ልዩ አቅም ያለቸው ሲሆኑ ከ1489 ዓል እስከ 1866 ዓል ድረስ አውሮፓ ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አርባ ጊዜ ታትመዋል . . በአውሮፓ የጨለማው ዘመን በመባል በሚታወቀው በዚህ ዘመን ዐረቦች የቅርብ ዘመን ፈጠራ ተደርጎ የሚገመተውን የሕክምና ማደንዘዣን ያውቁ እንደነበረም ጸሐፊዋ ገልጻለች። እውነታው እንደሚናገረውና ታሪክ እንደሚመሰክረው የእስፖንጅ ማደንዘዣ ጥበብ ማንም ያልቀደማቸው አንጡራ ግኝታቸው ነው . . እንዲህ ባለው አጭር ውይይት ላይ ማቅረብ የሚያስቸግሩ ሌሎች በጣም ብዙ ዝርዝር ነገሮችም ይገኛሉ።
ራሽድ፦ አሁን የጠቀስካቸው ነጥቦች ዐረቦችና ሙስሊሞች፣ለሰው ልጆች በተለይም በተግባራዊ ሳይንስ መስክ የጨመሩት አዲስ ነገር የለም ለሚሉና የታሪክን እውነታዎች ለማያውቁ ወይም ለሚያስተባብሉ አንዳንድ ወገኖች አሉባልታ አጥጋቢ ምላሽ ነው። እንደ እውነታው ከሆነ ግን የሰው ልጆች ተግባራዊና ሙከራዊ ስልትን በዐረቦችና በሙስሊሞች አማካይነት እንጂ አላወቀም። በዚህ ረገድ የአንዳንድ ምዕራባውያን ሳይንቲስቶችን ቃል እንድጠቅስላችሁ ፍቀዱልኝ።
ፈረንሳዊው ኦሪየንታሊስት ክሎድ ካህን እንዲህ ይላል፦ ‹‹ . . ሙስሊም ሊቃውንት -ርእዮታዊ ዝንባሌያቸው እንዳለም ሆኖ - በረቂቃዊነት ኃይል ከግሪኮች አነስ ያሉ ሲሆን፣ይህንን ያካካሱት ግን ለተግባራዊነት ባላቸው ብርቱ ዝንባሌያቸው ነው። ቀጥሎ የመጣው ሳይንሳዊ እድገት የዚህን ዝንባሌ አስፈላጊነትና ፋይዳውን አሳይቷል።ዐረቦች ያበረከቱት ዕውቀት በዕለታዊ ሕይወታቸው ውስጥ የተገበሩት ዕውቀት ነው። ለዚህም ነው መኖር የቀጠለውና ቀጣይነትን ማረጋገጥ የቻለው። አልራዚ (ከታላላቅ ሊቃውንት አንዱ ነው)፣ሳይንሳዊ እድገት ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል በጣም ግልጽ በሆነ አባባል ተናግሯል። ይህ በብዙኃኑ የመካከሎኛው ዘመን ሊቃውንት ዘንድ እንግዳ የሆነ መርህ ነው . . ›› ጣልያናዊቷ ተመራማሪ ሎራ ቪሽያ ቫግሌሪ ደግሞ እንዲህ ትጠይቃለች፦ ‹‹ . . ቤይከን አስፈላጊነቱን ከማወጁ ከረጅም ዘመን በፊት የትግበራና የሙከራ ስልቶችን ያስገኙት ዐረቦች አልነበሩምን?! የኬሚስትሪና የስነፈለክ እመርታ፣የግሪኮች ዕውቀት ስርጭት፣የሕክምና ሳይንስ መጎልበት፣የተለያዩ የፊዚክስ ሕጎች ግኝት፣ . . እነዚህ ሁሉ ዐረቦች ከተውልን የተገኙ አይደሉምን?›› . . አሜሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ዎል ዲዮራንት ደግሞ እንዲህ ይላል፦ ‹‹ . . ዐረባዊ ዕውቀት በኬሚስትሪ ሳይንስ ውስጥ ሳይንሳዊው የሙከራ ስልት እንዲያቆጠቁጥ አድርጓል፤ይህም የዘመኑ አእምሮ አንዱ ዐቢይ መሳሪያና ታላቅ መመኪያው ነው . . ስልቱን ጃብር ]እብን ሐያን[ካስተዋወቀው ከአምስት መቶ ዓመት በኋላ ሮዠር ቤይከን ለአውሮፓ ወደዚያ የመራው ከአንዱሉስ ዐረቦች የፈነጠቀለት ብርሃን መንገዱን ያበራለት በመሆኑ ነበር። ይህ የብርሃን ወገግታ ራሱም ቢሆን በምሥራቁ ዓለም ከሚገኙ ሙስሊሞች የተወሰደ እንጂ ሌላ አልነበረም››።
ይህ ዐረባዊ እስላማዊ ስልጣኔ በፈጠራ መስክ ለሰው ልጆች ካበረከታቸው አስተዋጽኦዎች ኢምንቱ ብቻ ነው።
ማይክል፦ በእርግጥ ይህ ሊስተባበል የማይችል ትልቅ አበርክቶ ነው። ግና ይህ ስልጣኔም እንደ ግሪክ ስልጣኔ ካሉ የቀደሙ ስልጣኔዎች የተጠቀመ መሆኑን መካድ አይቻልም።
ራሽድ፦ ወዳጄ፣ይህ የሳይንሳዊ እድገት ባሕሪ ነው። ሳይንስ በጥቅሉ ሲታይ በባሕሪው የሰው ልጅ ስኬቶች የተያያዘ ሰንሰለት ሲሆን፣ይህም የስልጣኔ ዑደቶች በመባል የሚታወቀው ነው። ፈረንሳዊው ኦሪየንታሊስት አልዶ ሜይሊ፦ ‹‹ . . ይህ የዐረቦች ሳይንስ ጥንታዊውን ስልጣኔ ከአዲሱ ዓለም ጋር የሚያስተሳስረውን የግንኙነትና የቀጣይነት ቀለበት የሚመሰርት ነው።ያንን ዐረባዊ ዕውቀት ካላገኘነውና ካልተገነዘብነው በስተቀር ምንነቱን ለመተንተን አስቸጋሪ የሚሆን ከፍተት በቀድሞዎቹ ስልጣኔዎችና በዘመናዊው ስልጣኔያችን መካከል ያጋጥመናል።››
‹‹የዘመናዊ ሳይንስ ጎሕ . . እስላም - ቻይና - ምዕራቡ ዓለም›› የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲ በሆኑት የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲው የታሪክ ፕሮፌሰርበዶክተር ቶቢ ሃፍ አመለካከት፣በዐረባዊ እስላማዊ ስልጣኔ ውስጥ የተነባበረውና የተከማቸው ሳይንሳዊና ፍስፍናዊ ዕውቀት፣የመካከለኞቹ ክፍለ ዘመናት አውሮፓውያን ባከናወኑት ታላቅ የትርጉም ሥራ አማካይነት ወደ ምዕራቡ ዓለም መሸጋገር፣ለምዕራቡ ዓለም የእሳቤ እድገት አካሄድ ላይ ትልቅ አሻራ ነበረው።
የዐረባዊ እስላማዊ ስልጣኔ ስኬቶች ግን የትኛውም ሌላ ስልጣኔ የሌለው ልዩ ባሕርያት አሉት። ከነዚህም ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፦
እስላማዊው ዕውቀት ከሃይማኖት ፈጽሞ ተለይቶ አያውቅም። ይልቅዬ ሃይማኖት ዋነኛ መጋቢውና አነቃቂ ኃይሉ ነው።
የሙስሊሞች ዕውቀትም እንደ ምስጢራት ተቆጥሮ አያውቅም። ይልቁንም እንደየትስስራቸው በመላው የሰው ዘር መካከል ለማሰራጨት ይጓጉም ነበር። የሙስሊም ዩኒቨርሲቲዎችም ዕውቀት ፍለጋ ወደነሱ ለሚሰደዱ አውሮፓውያን ተማሪዎች ክፍት ነበሩ . .
እናም እኔ በዚያ ስልጣኔ እምኮራ ነኝ።