የመልክተኞች ጥሪ መሰረታዊ መርሕ

የመልክተኞች ጥሪ መሰረታዊ መርሕ
5
22856

የሁሉም ነቢያትና መልክተኞች ጥሪ በአንድ መሰረታዊ መርሕ ላይ የተመሰረተና የተስማማ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ለናንተ ከሃይማኖት ያንን ኑሕን ያዘዘበትን ደነገገላችሁ፤ያንንም ወደ አንተ ያወረድነውን፣ያንንም በርሱ ኢብራሂምን፣ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን፣ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ፣በርሱም አትለያዩ፣ማለትን (ደነገግን)፤በአጋሪዎቹ ላይ ያ ወደርሱ የምትጠራቸው ነገር ከበዳቸው፤አላህ የሚሻውን ሰው ወደርሱ (እምነት) ይመርጣል፤የሚመለስንም ሰው ወደርሱ ይመራል።}[አል ሹራ፡13]

ለዚህም ነው የሁሉም ነቢያት ሃይማኖት አንድ የሆነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እላንተ መልክተኞች ሆይ! ከተፈቀዱት ምግቦች ብሉ፤በጎ ሥራንም ሥሩ፤እኔ የምትሠሩትን ሁሉ ዐዋቂ ነኝ። ይህችም፣(በአንድ አምላክ የማመን ሕግጋት)፣አንድ መንገድ ስትኾን፣ሃይማኖታችሁ ናት፤እኔም ጌታችሁ ነኝና ፍሩኝ፤}[አል ሙእሚኑን፡51-52]

በዝርዝር ንዑሳን ሕግጋት ግን ሊለያዩ ይችላሉ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከናንተ ለሁሉም ሕግንና መንገድን አደረግን፤} [አል ማእዳህ፡48]

ዝርዝር ሕግጋቱ ከዚያ የጋራ መሰረታዊ መርሕ ጋር የሚጻረር ቢሆን ኖሮ ከጥበብ ከጠቀሜታና ከርህራሄ የራቀ በሆነ ነበር። ይህ ግን ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህም ዝንባሌዎቻቸውን በተከተለ ኖሮ፣ሰማያትና ምድር፣በውስጣቸውም ያለው ሁሉ፣በእርግጥ በተበላሸ ነበር፤}[አል ሙእሚኑን፡71]

በመልክተኞችና በትምሕርቶቻቸው ላይ የጋራ ስምምነት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል፦

በአላህ፣በመላእክቱ፣በመጽሐፎቹ፣በመልክተኞቹ፣በመጨረሻው ቀንና፣ደጉና ክፉውም በአላህ ዕውቀትና በርሱ ቅድመ ውሳኔ የሚከሰት መሆኑን ማመን ይገኙባቸዋል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{መልክተኛው፣ከጌታው ወደርሱ በተወረደው አመነ፤ምእመኖችም (እንደዚሁ)፤ሁሉም በአላህ፣በመላእክቱም፣በመጻሕፍቱም፣በመልክተኞቹም፣ከመልክተኞቹ በአንድም መካከል አንለይም፣(የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ፤ሰማን፤ታዘዝንም፤ጌታችን ሆይ! ምሕረትህን (እንሻለን)፤መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው አሉም።}[አል በቀራህ፡285]

ሌላው ያለ ምንም ማጋራት አንድ አላህን ብቻ እንዲገዙ ሰዎችን ማዘዝ፣ወዳጅም ሆነ ልጅ ከመያዝ፣ከባላንጣ፣ከአምሳያና ከተጋሪ ሸሪክ እርሱን ማጥራት፤ከጣዖታትና ቅርጻ ቅርጽ አምልኮ መራቅ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከአንተ በፊትም፣እነሆ ከኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።}[አል አንቢያ፡25]

እንደዚሁም የአላህን መንገድ ብቻ መከተል፣ከርሱ የሚጻረሩ መንገዶችን አለመከተል፣ቃል ኪዳንን ማክበር፣መስፈሪያና ሚዛንን አለማጉደል፣ለወላጆች ደግ መሆን፣ለሰዎች ሁሉ ፍትሐዊ መሆን፣በቃልና በተግባርም እውነተኛ መሆን፣ግልጹንም ሆነ ስውሩን ዝሙት እርም ማድረግ፣ሕጻናትን መግደልና ነፍስን ያለ ሕግ አግባብ ማጥፋትን እርም ማድረግ፣አራጣና የየቲሞችን (ወላጅ አልባዎች) ገንዘብ መብላትን መከልከል፣ማባከንን፣መኩራትንና የሰውን ገንዘብ በሐሰት መብላትን መከልከል ይገኙበታል።

በመጨረሻው ቀን ማመን፤እያንዳንዱ ሰው ከዕለታት አንድ ቀን እንደሚሞት በእርግጠኝነት ያውቃል። ይሁንና ከሞት በኋላ መጨረሻው ምን ይሆናል? ጽድቅ ወይስ ኩነኔ? ከሞት ተቀስቅሰው የየሥራቸውን ዋጋ በጎ ከሆነ በጎ፣ክፉ ከሆነ ክፉ ዋጋ እንደሚቀበሉ፣ሁሉም መልክተኞችና ነቢያት ለሕዝቦቻቸው አስተምረዋል። ይህን ጉዳይ - ከሞት በኋላ መቀስቀስና በሠሩት ሥራ መጠየቅን - አመዛዛኝ አእምሮ የሚያረጋግጠውና መለኮታዊ ሃይማኖቶች ያጸኑት እውነታ ነው። ኃያሉ ጥበበኛው ዐዋቂው ፈጣሪ ይህን ፍጥረት እንዳው ለከንቱ ፈጥሮ ከመተው የላቀና የጠራ አምላክ ነውና። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ሰማይንና ምድርን፣በመካከላቸውም ያለውን ሁሉ፣ለከንቱ አልፈጠርንም፤ይህ የነዚያ የካዱት ሰዎች ጥርጣሬ ነው፤ለነዚያም ለካዱት ሰዎች ከእሳት ወየውላቸው።}[ሷድ፡27]

ይልቅዬ ይህን ድንቅ ፍጥረት የፈጠረው ለታላቅ ጥበብና ለክቡር ዓላማ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።}[አል ዛርያት፡56]

ታዛዡንና አመጸኛውን እኩል ማስተናገድም ለዚህ ጥበበኛ ኃያል አምላክ የተገባ አይደለም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{በውነቱ እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችን የሠሩትን፣በምድር ውስጥ እንደሚያጠፉት እናደርጋለን?! ወይስ አላህን ፈሪዎቹን እንደ ከሓዲዎቹ እናደርጋለን?}[ሷድ፡28]

ስለዚህም ፍጥረታትን በትንሣኤ ቀን ከሞት ቀስቅሶ ለያንዳንን ሰው እንደሥራው በመስጠት በጎ ሠሪውን መሸለምና ክፉ ሠሪውን መቅጣት፣የጥበቡ ምሉእነትና የችሎታው ኃያልነት መገለጫ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ከዚያም እነዚያን ያመኑትንና መልካም የሠሩትን በትክክል ይመነዳ ዘንድ ይመልሰዋል፤እነዚያ የካዱትም፣ይክዱት በነበሩት ነገር ለነርሱ ከፈላ ውሃ የኾነ መጠጥና አሳማሚ ቅጣት አላቸው።} [ዩኑስ፡4]

እናም ከሞቱ በኋላ ሰዎችን ዳግም መቀስቀስ ለርሱ እጅግ ቀላል ነው። ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ እርሱ አይደለምን? ዩኒቨርሱን በመላ ያለ ምንም ቅድመ አምሳያ ከምንም ከፈጠረ፣ይህንኑ መልሶ እንደገና ማምጣት ከዚያ የቀለለ መሆኑ አያጠያይቅም! አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ፣እነርሱንም በመፍጠሩ ያልደከመው አላህ፣ሙታንን ሕያው በማድረግ ላይ ቻይ መኾኑን አላስተዋሉምን? (በማስነሳት) ቻይ ነው። እርሱ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና።}[አል አሕቃፍ፡33]

በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦

{ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ፣ብጤያቸውን በመፍጠር ላይ ቻይ አይደለምን? ነው እንጅ፤እርሱም በብዙ ፈጣሪው፣ዐዋቂው ነው።}[ያሲን፡81]

ያልነበረውን ማስገኘት የሚችል የነበረውን መልሶ ማስገኘቱ ለርሱ በጣም ቀላል ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{እርሱም ያ መፍጠርንየሚጀምር፣ከዚያም የሚመልሰው ነው፤(መመለሱ) (7)በርሱ ላይ በጣም ገር ነው፤ለርሱም በሰማያትም በምድርም ከፍተኛ ባሕርይ (አንደነትና ለርሱ ብጤ የሌለው መኾን) አልለው፤እርሱም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።}[አል ሩም፡27]

ይልቅዬም በዚችው ዓለማዊ ሕይወት በነቢዩ ኢብራሂም [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁን] ፊት በአላህ ፈቃድ ሙታንን ከሞት ማስነሳት ተፈጽሟል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{ኢብራሂምም ጌታዬ ሆይ! ሙታንን እንዴት ሕያው እንደምታደርግ አሳየኝ ባለ ጊዜ፣(አስታውስ፤አላህ)፦ አላመንክምን? አለው፤አይደለም (አምኛለሁ)፤ግን ልቤ እንዲረጋ ነው አለ፤(አላህም)፦ ከበራሪዎች (ከወፎች) አራትን ያዝ፤ወደ አንተም ሰብስባቸው፤(ቆራርጣቸውም)፤ከዚያም በየኮረብታው ሁሉ ላይ ከነርሱ ቁራጭን አድርግ፤ከዚያም ጥራቸው፤ፈጥነው ይመጡሃልና፤አላህም አሸናፊ፣ጥበበኛ መኾኑን ዕወቅ አለው።}[አል በቀራህ፡260]

በአልመሲሕ ዒሳ [የአላህ ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁን] እጅም እንደዚሁ በአላህ ፈቃድ ተፈጽሟል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብሏል፦

{አላህ በሚል ጊዜ (አስታውስ)፦ የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! በአንተና በእናትህ ላይ (የዋልኩላችሁን) ጸጋዬን አስታውስ፤በሕፃንነትና በከፈኒሳነት (የበሰለ ሰው ኾነህ) ሰዎችን የምትናገር ስትኾን፣በቅዱሱ መንፈስ (በገብርኤል) ባበረታሁህ ጊዜ፣ጽሕፈትንና ጥበብንም፣ተውራትንና ኢንጂልንም፣ባስተማርኩህ ጊዜ፣ከጭቃም የወፍ ቅርጽ ብጤ በፈቃዴ በምትሠራና በውስጧ በምትነፋ፣በፈቃዴም ወፍ በምትኾን ጊዜ፣ዕውርም ኾኖ የተወለደንና ለምጻምንም በፈቃዴ በምታሽር ጊዜ፣ሙታንንም በፈቃዴ (ከመቃብራቸው) በምታወጣ ጊዜ፣የእስራኤልንም ልጆች በተአምራት በመጣህባቸውና ከነሱ እነዚያ የካዱት ይህ ግልጽ ድግምት እንጅ ሌላ አይደለም ባሉ ጊዜ፣(ሊገድሉህ ሲያስቡህ) ከአንተ ላይ በከለከልኩልህም ጊዜ፣(ያደረግሁልህን ውለታ አስታውስ)።}[አልማእዳህ፡110]