ሁለቱ ወዳጆች ፓሪስ ከደረሱ በኋላ የቀኑን ቀሪ ጊዜ ያሳላፉት ተስማሚ ሆቴል በማፈላለግ ላይ ነበር። በመጨረሻም ፓሪስ የሚገኘውን የወጣቶች ማእከል እንግዳ ቤት ለማረፊያነት መረጡ። በቂ ዕረፍት መውሰድ እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነበርና ሌሊቱን በእንቅልፍ አሳለፉ። በቀጣዩ ቀን ጓደኛሞቹ ከተማዋን ለማየት ወወጡ፤በዙረት ላይ እንዳሉ አንድ ካፌ አጠገብ ደረሱ።
ማይክል፦ ራሽድ፣እዚህ ካፌ ገብተን ሻይ ብንጠጣና ዕረፍት ብንወስድ ምን ይመስለሃል?
ራሽድ፦ ጥሩ ነው፣እንዳውም አጭር ዕረፍት ማግኘት እያስፈለገኝ ነበር።
ማይክል፦ ታዋቂው የስነልቦና ሊቅ ሲግመንድ ፍሮይድ ይህን ካፌ ያዘወትር ነበር፤ስለርሱ ሰምተህ ታውቃለህ?
ራሽድ፦ አዎ፣በስነልቦና ሳይንስ ውስጥ ስሙ ከስነልቦና ትንተና አስተሳሰብ ጎራ ጋር የተያያዘውና በተጨማሪም ከስነምግባር ልጓሞች ነጻ ለመሆንና ለወሲባዊ ልቅ ነጻነት ጥሪ በማድረጉ የሚታወቀው ነው።
ማይክል፦ ከጠቀስካቸው ነገሮች ጋር ተያይዞ ስሙ የሚነሳ ቢሆንም፣እኛ ዘንድ ግን አክብሮት የሚቸረው ሳይንቲስት ነው።
ራሽድ፦ ዘመናዊውን የምዕራቡን ዓለም ህብረተሰቦች ስልጣኔ የቀረጸው እሳቤ የቆመባቸውና ከነ ዳርዊን፣ካንት፣ማርክስ፣ ዶርካይምና ሳርተር ጋር አንደኛው የማእዘን ድንጋይ ነው የሚል እምነት አለኝ። እነዚህ እያንዳንዳቸው የምዕራቡን ዓለም አስተሳሰብ በማናጋት አዲሱን የምዕራባውያን የተቀደሱ እሴቶችን . . አስፈላጊ በሆነ መልኩ እንደገና በመቅረጽ ረገድ የየራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል። ሁሉም በየፊናው ሃይማኖትን፣ወግና ሞራላዊ ስነምግባርን አፈረካክሶ ለማውደም የድርሻቸውን ተወጥተዋል።
የዳርዊን የኢቮሉሽን ንድፈ ሀሳብ፣ከርሱ በኋላ የመጡት በዘመኑ ሰፍኖ የቆየውን የአስተሳሰብ መሰረት ለመናድ ለተገለገሉባቸው ሁለት አደገኛ የአስተሳሰብ ሕጎች መነሻ ነበር። የመጀመሪያው ሕግ፦ ጸንቶ የመቆየትን እሳቤ የሚጻረረውን የማያቋርጥ ለውጥና ዕድተት እሳቤን ማሰራጨት ነው። ከዚህም በመነሳት ሁሉም ሞራላዊ ስነምግባሮችና እሴቶች እንደዚሁም አመለካከቶች ተለዋዋጭና አንጻራዊ ናቸው የሚል ነው። ሁለተኛው ሕግ፦ የሰውን ልጅ መንፈሳዊና ሕሊናዊ ጎኖች ሙሉ በሙሉ ችላ በማለት እንስሳዊና ቁሳዊ ጎኑን ብቻ ማጉላት፣ተጽእኖ የሚያሳድሩበት ነገሮችም እንዲሁ ቁሳዊ መሆናቸውን ማሳየት፣የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ ወይም በዕድገት ሂደቱ የአላህ ፍጡር መሆኑን ማስተባበል ነው። በዚህም “አምላክ - ሰው - ዩኒቨርስ - መመለሻ” የሚሉ ታላላቅ የፍልስፍና ጥያቄዎችን የሚመለከቱ የጸኑ ጽንሰ ሀሳቦች ፈረካክሰው የሚወድሙበት አደገኛ ሁኔታ ተጀመረ።
የፍሮይድ ሚና ሰብአዊ ፍጡርን ወደ ወሲባዊ ቋጠሮዎች ስብስብ መለወጥ ሲሆን፣የሰውን ልጅ ባህሪና ድርጊት የሚመራው በአእምሮ መሆኑን ያስተባብላል። በርሱ እምነት የሰው ልጅ ሕይወት ዕለታዊ እንቅስቃሴ መሰረታዊ አንቀሳቃሽ ደስታና እርካታ ነው። በዚህም ምክንያት የመልካም ስነምግባርና የሞራላዊ እሴቶች ሥርዓት ተንኮታኩቶ በኢተጨባጭነትና በኢሳይንሳዊነት የተፈረጀ አድኃሪነትና ኋላቀርነት ተደረገ።
ማይክል፦ በኔ እምነት ሁሉም የሰው ልጆች ስልጣኔዎች የሚጋሯቸው ጽንሰ ሀሳቦች ያሏቸው ሲሆን፣እያንዳንዱ ስልጣኔም ከሌላው የሚለየው የራሱ የሆኑ ጽንሰ ሀሳቦች አሉት። “አምላክ - ሰው - ዩኒቨርስ” የመሳሰሉ ጽንሰ ሀሳቦች ሁሉም ስልጣኔዎች የሚጋሯቸው ጽንሰ ሀሳቦች ናቸው። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ስልጣኔ የጽንሰ ሀሳቦቹን ቅደም ተከተል በተመለከተ ከሌላው የሚለይ ሲሆን፣አንዱ ስልጣኔ አንደኛውን ጽንሰ ሀሳብ በተቀሩት ሁለቱ ጽንሰ ሀሳቦች ገዥ በማድረግ በመጀመሪያው ጽንሰ ሀሳብ ውስጥ ይመለከተዋል።
ከዘመነ ሕዳሴ በኋላ ባለው ዘመናዊው የአውሮፓ ስልጣኔ ውስጥ፣ዩኒቨርስ ገዥ ጽንሰ ሀሳብ ሆኖ ወጥቷል። ሳይንሳዊ እሳቤ ሲሰራጭም አምላክ ሰውን የፈጠረው መሆኑን ውድቅ የሚያደርግ አዲስ አስተሳሰብ መስፈን ጀምሮ የማቴሪያሊዝምን ርእዮተ ዓለም ይዞ መጣ። በዚህም በሰው ልጅ ውስጥ ያለው መንፈሳዊ ጎን ሞት ተፈረደበት። በእርግጥም ዳርዊን ይህን አካሄድ ከመሰረቱት ታላላቅ ቀማሪዎች አንዱ ነበር።
ራሽድ፦ በዚህ ላይ ሙሉ በሙሉ ከአንተ ጋር እስማማለሁ። ግና በተናገርከው ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን በአጽንኦት ማከል እፈልጋለሁ፦
አንደኛ፦ እነዚህን አመለካከቶች ወደ እውነተኛ አብዮቶች እንዲለወጡ ያደረገው ዋነኛው ምክንያት፣በዘመኑ በምዕራቡ ዓለም ሕብረተሰብ ውስጥ የነበረው የመንፈስ ባዶነት ሁኔታ ሲሆን፣በተጨማሪም የቤተክርስቲያን አምባገነንነትና ፍጥረትንና ሕይወትን አስመልክቶ ታራምድ የነበረውን የተሳሳተ ግንዛቤ የሙጥኝ ማለቷ ብቻ ሳይሆን አመለካከቶቿን አምኖ መቀበል ግዴታ ማድረጓ ነበር።
ሁለተኛ፦ የምዕራቡ ዓለም ዕድገትና ስልጣኔ መነሻው፣በሕዳሴው ዘመን መጀመሪያና መካካሉ ላይ በተሰራጩት እነዚያ አስተሳሰቦችና ርእዮቶች ላይ መመርኮዙ ነው የሚለው እምነት በስፋት የተሰራጨ የተሳሳተ እምነት ነው።
ሦስተኛ፦ የነዚያ አቀንቃኞችና ፈላስፎች እሳቤና አመለካከት ከእውነተኛው የሳይንስና የዕውቀት አብዮት በኋላ፣አንዱ ንድፈ ሀሳብ ሌላውን እየተከተለ መፈረካከስና መሰነጣጠቅ ያዘ። ይሁን እንጂ ዕውቀትና ግንዛቤያቸው ውስን የሆኑ ብዙ ሰዎች በምዕራብም ሆነ በምስራቁ ዓለም ዛሬም ድረስ እነዚያን አመለካከቶች በሚደግፈው ብርቱ ፕሮፓጋንዳ ተጽእኖ ስር እንደወደቁ ናቸው።
ሁሉም ስልጣኔዎች የሚጋሯቸው ጽንሰ ሀሳቦች መኖራቸውን አስመልክተህ የተናገርከው ነገር አንድ አስገራሚ ንጽጽሮሽ አስታውሶኛል። ፍሮይድ ስለ ሰው ልጅ ባሕሪ የሚሰጠው ትንተና እና ከሙስሊም ሊቃውንቶች አንዱ የሆኑ ሰው የዛሬ ሰባት መቶ ዓመት አካባቢ የጸፉትን ማነጻጸር ፈልጌ ነው።
ማይክል፦ በፍሮይድ አመለካከትና በዚያ ዘመን በኖረ ሙስሊም ሊቅ እስላማዊ ግንዛቤዎች መካከል ተመሳስሎ መኖሩ በእርግጥም አስገራሚ ነው።
ራሽድ፦ የግንዛቤ ተመሳስሎ ሳይሆን የማእቀፍ መመሳሰል ልንለው የምንችል ተመሳስሎ ነው። ይበልጥ እንዳብራራልህ በፍሮይድ አመለካከት የስነልቦና ሥርዓት አወቃቀር እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?
ማይክል፦ አዎ፣በሚገባ አውቃለሁ። በአጭሩ ለማስቀመጥ የምግብ መሰልቀጫና የደም ዝውውር . . የመሳሰሉና ስነሕይወታዊ ተግባሮችን የሚያከናውኑ ባዮሎጂያዊ ሥርዓትቶች እንዳሉት ሁሉ፣የሰው ልጅ እርስ በርስ ከሚተሳሰሩ ክፍሎች የተዋቀረ የስነልቦና ሥርዓት አለው ብሎ ያስባል - ፍሮይድ።
ይህ የስነልቦና ሥርዓት “እርሱ”፣”ከፍተኛው እኔ” እና “እኔ” ብሎ ከሚጠራቸው አሃዶች የተዋቀረ ነው።
“እርሱ” ከግላዊ ፍላጎቶችና ጎትጓች ስሜቶች፣ከእምቅ ልማዶች፣በእርካታ መርህ መሰረት ፍላጎቶቹን እውን ለማድረግ በንቃተ ስሜት ክልል ለመገኘት ቀጣይነት ባለውና በጭፍኑ ከሚገፋፋ ያልተገራ ዝንባሌ የተዋቀረ ክልል ነው። “እርሱ” በአፈጣጠር የስነልቦና ሥርዓቱን ከሚመሰርቱ ከሁሉም አሃዶች ቀዳሚው ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን፣የሰው ልጅ ይዞት ከሚለወለደውና ልዩ ተፈጥሮው ከሚወስናቸው የተዋቀረ ነው። “እርሱ” ጄነቲክ (ውርስ) አሻራን ይወክላል።
“ከፍተኛው እኔ” የማሕበራዊ እሴቶች፣መርሆዎች፣ ለእላይ ተምሳሌቶችና አብነት ስብስብ ማለትም ሰው ከሌሎች የሚያገኛቸውን አሻራ የሚወክል ነው። ይህም ሕጸኑ ከወላጆቹ ከትምህርት ቤቱና ከማሕበረሰቡ የገበያቸውን እነጻ አስተዳደግና ስነምግባራዊ እሴቶች የሚያጠቃልል ሲሆን፣የቤተሰቡን የጎሳውን የብሔረሰቡንና የሃይማኖቱን ወግና ልማዶችና እነዚህ የሚወክሉትን የቀጥተኛ ማህበራዊ አካባቢ ተጽእኖዎችንም ያካትታል። በሕጻን ልጅ “ከፍተኛው እኔ” ላይ፣የቤተሰብ ተተኪዎችና ተለዋጮች ማለትም ሞግዚቶችና በሕብረተሰቡ ውስጥ ተምሳሌት ተደርገው የሚወሰዱና የሚከበሩ . . አንዳንድ ግለሰቦች ተጽእኖ ያሳድራሉ። “ከፍተኛው እኔ” ውስጥ ከቁሳዊ ፍላጎትና ከስሜታዊ ዝንባሌ ተግባሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ የመራቅ አዝማሚያ አለበት። “ከፍተኛው እኔ” ሕሊናን የሚወክል እንደ መሆኑ ከተጨባጭነት የራቀ የአብነትና የተምሳሌት ክልል ነው። “ከፍተኛው እኔ” ፍሮይድ እንደሚለው ወደ ተራ ደስታና እርካታ ሳይሆን ሁሌም ወደ ምሉእነት ደረጃ መድረስን የሚፈልግ ነው።
“እኔ” ደግሞ በ”እርሱ” እና በ”ከፍተኛው እኔ” መካከል የሚደረግ ትግል፣ስምምነት ወይም መስተጋቢር ውጤት ነው። በእርካታ መርህ ላይ በተመሰረቱ ፍላጎቶችና በቁጥጥርና ገደብ ላይ በቆሙት አብነቶችና መርሆዎች መካከል ያለው ትግል ውጤት ነው። “እኔ” የሰብእናን ሚዛን ለመጠበቅ በተጨባጭ ያሉትን ቀውሶች ወይም በፍላጎቶች መካከል የሚገኙትን ግጭቶች ለመፍታት የሚሠራ ንቁ ስሜት ነው። “እኔ” ሲጠቃለል ጅምሩ የሰው ልጅ ሰብእና ውጫዊ ገቢር ውጤት ነው።
“ከፍተኛው እኔ” በ”እኔ” ላይ የተቆጣጣሪነትን ሚና ለመጫወት ከ”እኔ” የተነጠለው ጎን ነው። “እኔ” ለ”እርሱ” ተንበርካኪ እንዳይሆንና ለታፈኑ ፍላጎቶች እጅ እንዳይሰጥ የማስጠንቀቅ ተግባር ያከናውናል።
ራሽድ፦ ዋው፣ማይክል ድንቅ ማብራሪያ ነው። ፍሮይድ እዚህ ካፌ ውስጥ ቁጭ ብሎ ሻይ ፉት እያለ የሚናገር ነው ያስመሰልከው . .
ይሁንና ይህን ድንቅ ማብራሪያ ፍሮይድ “እኔ” በስነልቦና ሥርዓቱ ውስጥ የሚፈጽመውን ተልእኮ አስቸጋሪነት አምኖ የሚቀበል መሆኑን በመግለጽ የተሟላ ላድርገው። ይህ የማይቻል ነው ባይባል እንኳ በጣም አስቸጋሪ የሆነ ተልእኮ፣ተጻራሪ የሆኑ ፍላጎቶችን በማስማማትና በማቻቻል የሚገለጽ ነው። በዚህም “እኔ” የ”እርሱ”ን ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ተቀብሎ ማስተናገድ ይኖርበታል። ፍላጎቶቹም በዋነኝነት ወሲባዊ ሲሆኑ፣የውጭውን ከባቢያዊ ፍላጎቶችን “ከፍተኛው እኔ”ንም በተመሳሳይ ወቅት ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይጠበቅበታል። ስለዚህም እነዚህን የማጣጣምና የማስማማት ሂደቱ አስቸጋሪ ሆኖ ይታያል። በመሆኑም “እኔ” ከ”እርሱ” ጋር የተግባቦትና የስምምነት ግንኙነት ለመፍጠርና ለፍላጎቶቹ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ያደርግና ከ”ከፍተኛው እኔ”፣አብዛኛውን ጊዜ ወሲባዊ ፍላጎቶችን ወደ ማፈንና ወደማቀብ በሚያደርሱ የተወሰኑ መስፈርቶች መሰረት ወሲባዊ ግንኙነቶችን ከሚያደራጅ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ይጋፈጣል። “እኔ” “እርሱ”ን፣”ከፍተኛው እኔ”ንና ተጨባጩን ሁኔታ ማጣጣምና ማመዛዘን ከቻለ ግለሰቡ ከራሱ ጋር የተጣጣመ ሆኖ ይኖራል። “እርሱ” ወይም “ከፍተኛው እኔ” የበላይነትን ከያዘ ግን የግለሰቡ ሰብእና የተናጋና ያልተረጋጋ ይሆናል። የ”እኔ” በነዚህ ተጻራሪ ፍላጎቶች መካከል መጣጣምና ሚዘናዊነትን ማስገኘት አለመቻል ደግሞ ወደ ሕመምነት ሁኔታዎች ያደርሳል።
እዚህ ላይ አደገኛው ሁኔታ፦ የስነልቦና ጤንነት በዚህ ግንዛቤው የ”እኔ” ከ”እርሱ” . . ማለትም ሥጋዊ ፍላጎቶችና ስሜታዊ ዝንባሌዎች፣ከ”ከፍተኛው እኔ› ማለትም ከእሴቶች፣ከመርሆዎችና ከአብነታዊ ተምሳሌቶች ጋር መጣጣም ነው ካልን፣”እርሱ”ን መለወጥ የማንችል መሆናችንን ግምት ውስጥ በማስገባት ለ”እርሱ” ፍላጎቶች ምላሽ አለመስጠት ወደ ፍላጎት እመቃ የሚወስድ ከሆነ . . ወደዚህ መጣጣም ለመድረስ “ከፍተኛው እኔ”ን ከመለወጥና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ከማውደም ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም ማለት ነው። ስለዚህም ሃይማኖትን፣ምጡቅ ስነምግባራዊና ሞራላዊ ተምሳሌቶችን ከሕይወታችን አስወጥተን፣”እርሱ” እውን በሚያደርጋቸው የሰው ልጅ ሥጋዊ ዝንባሌዎች፣ወሲባዊ ፍላጎቶችና በአድርባይ ራስ ወዳድነት . . መቀየር ግድ ይላል። ሃይማኖትንና ሞራላዊ እሴቶችን ከሕይወቱ በማራቅ ላልተገሩ ሥጋዊ ፍላጎቶች፣የስነምግባር ልጓም ለሌላቸው ልቅ ወሲባዊ ግንኙነቶች ያልተገደበ ነጻነት በታወጀበት ጊዜ በምዕራቡ ዓለም በትክክል የተከሰተው ይኸው ነበር። ሥልጣኔውንም በዚህ ላይ ያነጸ በመሆኑ ቤተሰባዊ ሕይወት ከመናዱም በላይ፣ከደመ ነፍስ ተፈጥሯዊ ስሜቱ ማእቀፍ ውጭ ስነምግባራዊ ገደቦችን ከማያውቀው የማያስብ የእንስሳት ዓለም የሚለየው ነገር ባለ መኖሩ የሰው ልጅ ሰብእናም ባከነ . . ወደ ጀመርነው የዳርዊን ጉዳይ እንመለስ መሰለኝ!!
ማይክል፦ የታፈኑ ፍላጎቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሁሌም እርካታ የሚያስገኝላቸውን ነገር የሚፈትሹ እስከሆኑ ድረስ፣አንተ ፍሮይድንና አካሄዱን በምትረዳበት ግንዛቤ መሰረት፣ይህ በፍሮይድ እምነት በመርህ በተምሳሌታዊ አብነትና በሞራላዊ እሴቶች ላይ የሚታነጽ ስልጣኔንን እመቃ-ወለድ ሥልጣኔ አድርጎ እንዲወሰድ ያደርጋል ማለትህ ነው።
ራሽድ፦ ልክ ነህ፣ምዕራባዊው ሥልጣኔ ሞራላዊ እሴቶችን የሚያፈራው የአምላክን ቅድስና ከግምቱ ውስጥ በማስወጣት ነው። በሙስሊሞች ዘንድ ግን በሰው ልጆች ሕብረተሰብ ውስጥ ሞራላዊ ስነምግባሮች ምንጫቸው ሰብአዊ አእምሮ ሳይሆን የግዴታ መለኮታዊ ሸሪዓ (ሕግ) መሆን ይኖርበታል። አእምሮ ብቻውን ከሆነ መዛነፉ አይቀሬ ሲሆን፣በመለኮታዊ ሸሪዓ ማእቀፍ ውስጥ ከሆኑ ግን ሞራላዊ ስነምግባሮቹ ምሉእና ምጡቅ ይሆናሉ።
ማይክል፦ ራሽድ፣ቅድም የጠቀስከው የሃይማኖታችሁ ሊቅ የተናገረውን አልነገርከኝም። የተናገረው ከዚህ ጋር የሚስማማ ነው ወይስ የሚጻረር ነው?
ራሽድ፦ የተናገረው ነገር በእሴቶችና በጽንሰ ሀሳቦች ግንዛቤ መዋቅር ማእቀፍ ውስጥ የሚካተት ነው። ይህን መዋቅር በዝርዝር በማቅረብ ይዘቱን በአግባቡ ለመመልከት ረዥም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ለቀጣዩ ውይይት ብናቆየው ይሻላል ባይ ነኝ።