(1)
ለብዙ ጊዜ አብሮት የቆየው ከባድ ጭንቀትና መደበት ከጎበኘው በኋላ ለመወሰን ቆረጠና ወረቀት አውጥቶ የሚከተለውን ማስታወሻ ጻፈ ፡-
‹‹ካትሪና የኔ ፍቅር መሄዴ ነው አልመለስም፡፡ አብሮኝ የኖረው ዕድለ ቢስነትን እንዲያበቃ አደርጋለሁ፡፡ እቅጩን ልናገርና መኖሬን አበቃለሁ፤ራሴን አጠፋለሁ፡፡ አንቺም ይቅርታ አድርጊልኝ፣ ልጆቼም ይቅርታ ያደርጉልኝ››፡፡
መንገዱን ቀጠለ . .
ከራሱ ጋር ደጋግሞ የመከረ ቢሆንም እያመነታ ነበር፡፡ ካለበት ስቃይ ለመገላገል ሕይወቱን ከማጥፋት ውጭ ሌላ መፍትሔ አልታየውም፡፡ ‹እውን እኔ ሕመምተኛ ነኝ ማለት ነው?
ካትሪናማ ዘውትር እንደዚያ ነው የምትለው! ሁሌም እምነትና እርግጠኝነት እንዲኖረኝ ስትጎተጉተኝ ነው የኖረችው፣ አዘውትራም ፡-
አንተ ጆርጅ፣ጥርጣሬ'ኮ በሽታ ነው፣ፈጽሞ እጅ አትስጠው፡፡ ትለኛለች› እያለ ከራሱ ጋር እያወራ በአዝጋሚ እርምጃ ይራመድ ነበር፡፡
ሌላው ቀርቶ አባቱ እንኳ ሕመምተኛ ነው ብሎ ስለሚያምን፣ የጥርጣሬ በሽታ በዘር የሚተላለፍ እንደሆነና ከናቱ ቤተሰቦች ወደርሱ የተላለፈ መሆኑን እፊቱ ደጋግሞ እየተናገረ ካላቆመ መጨረሻው የአእምሮ ሕሙማን መታከሚያ ማእከል እንዳይሆን ይመክረው ነበር! የሥራ አለቃው ይሁዳዊው ካኽም እንዲሁ ብዙ ጊዜ ይስቅበታል፡፡ አዘኔታና ፌዝ በተቀላቀለበት ቅላጼ ፡-
-ወዳጄ ጆርጅ፣እኔ በጣም ነው የማዝንልህ፡፡ ፋይዳ በሌለው ነገር ራስህን ታሽቸግራለህ፡፡ የሚያስጨንቅህና የምታሰላስለው ነገር ሀብትህን አይጨምረውም፣ይብሱንም በሕይወት እንዳትደሰት ነው የሚያደርግህ፣ይለዋል፡፡
ጆርጅ የሰላሳ ስምንት ዓመት ጎልማሳ ሲሆን እንደሱው እንግሊዛዊት የሆነችውን ካትሪናን ነው ያገባው፡፡ እሷ ግን በዘር ግንዷ ትውልደ ሕንዳዊ ነች፡፡ ከተጋቡ አስር ዓመታቸው ሲሆን ሦስት ልጆች ወልደዋል፡፡ ትልቋ ማሪ (ዛሬ ዕድሜዋ አስር ዓመት ይሆን የነበረና በሰባት ዓመቷ የሞተች)፣ ማይክል (ስምንት ዓመት)፣ ሳሊ (ስድስት ዓመት) ናቸው፡፡ ትልቋ ልጁ ማሪ በመኪና አደጋ ከሞተች ወዲህ፣ስለ ሕይወትና ሞት ምንነት በማያቋርጥ ሁኔታ የሚያስብና ሁሌም የሚያሰላስል በመሆኑና ለፍልስፍና ባለው ፍቅርና በብሩህ አእምሮው ምክንያት እውስጡ የሚጉላሉ ጥያቄዎች በእጅጉ በዝተዋል፡፡ ጆርጅ የመጽሐፍ ቀበኛ የሆነ አንባቢ ሲሆን ፍልስፍናን፣ታሪክንና ሃይማኖቶችን የሚመለከቱ ርእሰ ጉዳዮችን ማንበብ ይወዳል፡፡ ምናልባትም የስነ መለኮት አስተማሪ የሆነቸውን ካቶሊኳን ካትሪና እንዲያገባ የገፋፋው ይኸው ሳይሆን አይቀርም፡፡
ጆርጅ ፕሮቴስታንት ቢሆንም ያጣውን እምነትና እርግጠኝነት እርሷ ዘንድ መኖሩን ያውቅ ነበር፡፡ እርሱ ከሞላ ጎደል ሁሉንም ነገር የሚጠራጠርና
ጥያቄ የሚያበዛ ሲሆን
ጥርጣሬዎቹን አሜን ብላ መቀበሏ
በጣም ይገርመዋል፡፡ ይሁን እንጂ አማኟ ካትሪና ሊኖራት የማይችል ብሩህ አእምሮ፣ንቁ ሕሊናና ሎጂክ ስላለኝ ነው ይህን የምታደርገው ብሎ ነው ሁሌም የሚያስበው፡፡ ከርሷ ጋር ብዙ ጊዜ ተወያይቷል፡፡ ውይይቶቹ በርሱ በሚወከለው አእምሮና በርሷ በሚወከለው እምነትና አሜን ብሎ መቀበል መካከከል፣ አሊያም በርሱ በሚወከለው ተጨባጭ እውነታና በርሷ ተምሳሌታዊ ተምኔት መካከል የሚደረጉ ውይይቶች ሆነው ነው የሚታዩት፡፡ ለካቲሪና ግን ወይይቶቹ በርሷ በሚወከለው አምኖ የመቀበል እርግጠኝነትና በርሱ በሚወከለው የጥርጣሬ በሽታ መካከል የሚደረጉ ሆነው ነው የሚወሰዱት፡፡ ውይይቶቹ ብዙውን ጊዜ የሚያበቁት በረዥም ዝምታ ሲሆን ሁለቱን የሚያስተሳስራቸው ፍቅር በመካከላቸው ባይኖር ኖሮ ገና ድሮ ነበር የሚፋቱት፡፡
ዳሩ ግና ልጁ ከሞተች በኋላ ጆርጅ ዘንድ እየጨመረ የመጣው ጥርጣሬ፣በመካከላቸው የሚደርጉትን እነዚያ ውይይቶች የበለጠ ጠጣርና ጠባብ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ታላላቆቹ ጥያቄዎችም ‹‹ለምን
ዓለማ ተፈጠርን?
፣ ‹‹ለምንድነው የምንኖረው››?
« መጨረሻችንስ ወዴት ነው?››
የሚሉ ሆነዋል፡፡ ሀሳቡ በሙሉ በዚህ ተይዞ እእምሮው ተወጥሯል፡፡ ጥያቄዎቹ ተራና ቀላል ቢመስሉም ከባድና በጣም የተወሳሰቡ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የሕይወትንና የፍጥረተ ዓለም ጽንሰ ሀሳቦችን የቀመሩ ባለ ብሩህ አእምሮ ፈላስፎች ብዙ ትኩረት የሰጧቸው፡፡ ለጆርጅ እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ አገኙ ማለት የሰው ልጅ የሕሊና እርጋታ፣የመንፈስ እርካታና ደስተኝነትን አገኘ ማለት ነው፡፡
ራሱን ለመግደል በሚሄድበት ጊዜ ብዙ የሕይወቱ ትእይንቶች ከፊቱ ይደቀኑ ነበር፡፡ ትልቋ ልጁ በሆስፒታሉ የድንገተኛ አደጋ ክፍል ውስጥ ሞትን ስትታገል፣ተሸንፋ ውበቷን፣ ሕይወቷንና ነፍሷንም በሞት ስትነጠቅ ታወሰው፡፡ ከለታት አንድ ቀን በሥራ ጫና ድክምክም ብሎት በተቀመጠበት ልጁ ማይክል እንዲህ ሲል የጠየቀውም ትዝ አለው ፡-
-አባዬ በየቀኑ ወደ ሥራ የምትሄደው ለምንድነው?
-ሕይወቴ ተልእኮና ዓለማ እንዲኖረውና ላንተም የሚያስፈልግህንና የምትወደውን ነገር ለማሟላት ነው፡፡
-የሕይወቴ ተልእኮና ዓለማ ስትል ምን ማለትህ ነው ?!
-ሰዎችን ማገልገልና የሰውን ልጅ መጥቀም ማለቴ ነው፡፡
-ለምን ?!
ጥያቄው ውስጡን እያራደው መሆኑ የተሰማው ጆርጅ ብድግ አለና ፡-
-ነገሩ ከባድ ነው፣ምናልባት አንተም እኔም አናውቀውም !
-አባዬ አንተ ትልቅ ሆነህ ይህን አታውቅም ! እኔ ግን ትልቅ ስሆን ሁሉንም ነገር አውቃለሁ፣ሳላውቀው የምተወው ምንም ዓይነት ትልቅ ነገር አይኖርም፡፡
-ውድ ልጄ ማይክል . . በቃ እርሳው . .
ከዚያም ስቆ ‹‹እነኚን ጥያቄዎች እርሳቸውና በሕይወትህ ተደሰት›› ይህማ ዘውትር በየቀኑ የሚነገረኝ ምክር ነው አለ ለራሱ፡፡ ቀጠለናም እንዲህ አለው ፡-
-አይዞህ፣ አንድ ቀን መልሱን እነግረሃለሁ፡፡
-አባዬ አንተ ትምህርትህን ጨርሰሃለህ፣ብዙ ታነባለህ፣ ግን አታውቅም !
-ውዴ የቤት ሥራህን ጨርሰሃል ?
-አዎ፡፡
-እሺ ደህና እደር፡፡
እርምጃዎቹ እየከበዱት
በመሄድ ላይ
እያለ ከራሱ ጋር ማውራቱን ቀጠለ፡፡ ካትሪና እንደምትለው ሁሉ ሕመምተኛ ሳልሆን አልቀረሁም፣ወይም ካኽ እንደሚለው ሕይወቴን በከንቱ የማባክን ሞኝ ተላላ ነኝ፣አሊያም አባቴ እንደሚለኝ የተወሰወስኩ ነኝ፡፡ . . ወይም ደግሞ . . ወይም ማይክል እንዳለው ማይም ነኝ
! ምናልባት ማይክል ትክክለኛ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚያስቀው ግን ሌሎች ለኔ የሚሰጡኝን የ‹‹በቃ እርሳው›› መልስ ለርሱም የሰጠሁት መሆኔ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ እኔም ወደፊት መሸሽን ሳልማር አለቀረሁም !
ሕይወቱን ለማጥፋት ወደሚፈልግበት ቦታ እያመራ ከባድ የጭንቀትና የመደበት ስሜት ተጠናውቶት እሰኪሰክር ድረስ የጠጣበትን ዕለት አስታወሰ፡፡ በዚያ ቀን መኪናውን እየነዳ መጥቶ ከግድግዳ ጋር ተላተመ፡፡ ይዞት የነበረውንና ‹‹የደስተኝነት ፍልስፍና›› የሚል ርእስ ያለው መጽሐፍ በእጁ ይዞ እየተንገዳገደ ከመኪናው ወረደ፡፡ የትራፊክ ፖሊሱ ያዘውና እንዲህ አለው ፡-
-ይኸ የደስተኝነት ፍልስፍና ነው ወይስ ራስን የማጥፋት ፍልስፍና ነው?! ሰክሮ መንዳት ሕገ ወጥ መሆኑን አታውቅም?!
ካትሪና ከትራፊክ ፖሊስ በዋስትና አስለቀቀችውና እንዲህ አለችው ፡-
-ሰክረህ መንዳት አይገባህም ነበር፡፡
በማፌዝ መለሰላት ፡-
-ሁሌ የምትመክሪኝ ‹‹በቃ እርሳው›› እያልሽ አይደል?!
-በዚህ ዓይነቱ አይደለማ፡፡
-አንቺ በየቀኑ እያመሸሽ ለምን ትጠጭያለሽ ?
-እኔ የምጠጣው ኢየሱስን ለማገልገል በቤተክርስቲያን የሚፈጸመውን ስነ ስርዓት ለማክበር ነው፡፡
በሴረኝነት ስሜት እንዲህ አላት ፡-
-ቅዱስ የመጠጥ ጽዋና የተባረከ ስካር ነው፣ ወይስ ሽሽት በሌላ መልኩ ነው?!
-ካንቺ ጋር መከራከር አድካሚ ሆኗል፡፡ ማሰብና ማስተንተንን ስለምትፈሪና ልክ እኔ እንዳደረኩት ሁሉ በመጠጥና በማምሸት ትሸሸጊያለሽ፡፡ ልዩነቱ አንቺ ለድርጊቱ የቅድስና ካባ መደረብሽ ብቻ ነው፡፡
የጆርጅ ቃላት በጣም ጠጣር ነበሩ፡፡ በሀዘንና በተጎዳ ስሜት ተነሳችና ፡-
-ቢያንስ እንዳንተ የአእምሮ ሕሙማን ሐኪም አያስፈልገኝም ! አለችው፡፡
-ምናልባት! ማን የውቃል?!
(2)
በዚህ በጣም ረዥም መስሎ በታየው ጉዞው፣ በመከታተል አእምሮውን በሚያጨናንቁ ሀሳቦችና ትውስታዎቹ ምክንያት ጭንቅላቱ ሊፈነዳ ምንም
ያህል
ባልቀረበት
ጊዜ፣ የማመንታትና ግራ የመጋባት ሁኔታው አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዙሪያው ያለውን የሰዎች እንቅስቃሴ ሲመለከት ሕይወትም ሆነ ትርጉም የሌላቸው ዕቃዎች የሚንቀሳቀሱ ሆኖ ይታየዋል፡፡ የሰው ልጆች ወደ ሕይወት አልባ እቃዎች መለወጥን እንዴት በጀ ብለው ይቀበላሉ ብሎ ራሱን ጠየቀ፡፡ ድል በተመታ መንፈስ ጉዞውን እንደቀጠለ ዕድሜው በሰባዎቹ ውስጥ የሚገኝ አንድ አረጋዊ ሽማግሌ ደስተኝነት በተሞላው መንፈስ ከልጅ ልጁ ጋር ሲጫወት ተመለከተ፡፡ የሽማግሌው የዋህነት፣ፈገግታውና ሳቅታነቱ ትኩረቱን ሳበውና ቀረብ ብሎ እንዲህ አለው ፡-
-በማቋረጤ ይቅርታ፣ደስተኛ ነዎት?
ሸማግሌው በአግራሞት አየውና ፡-
-አዎ . . ብሎ ከልጅ ልጁ ጋር ወደ መጫወቱ ተመለሰ፡፡
ጆርጅ እንደገና አቋረጣቸውና ፡-
-እንዴት? ማለቴ ለምን ደስተኛ ሆኑ? ለምንድነው የሚኖሩት?
ሽማግሌው ትኩር ብሎ ተመለከተውና ፡-
-ጥያቄህን አንተው ራስህ መልሰሃል አለው፡፡
-እንዴት?
-ለምን እንደምኖር ስለማውቅ ደስተኛ ነኝ፣በአጭሩ ይኸው ነው፡፡
-ለምንድነው እምኖረው? እባክዎን ይንገሩኝ፡፡
-ራስህን ጠይቅ! ይህን ጥያቄ እኔ ልመልስልህ አልችልም፡፡ ያንተው መንፈስና ያንተው ሕይወት እንጂ ማንም አይመልሰውም፡፡
-አደራ ብይዎታለሁ፣እባክዎን ይንገሩኝ፡፡
-ነገርኩህ እኮ ይህን ጥያቄ በቀላሉ የሚመልሰው መንፈስና ሕይወት ነው፡፡ መንፈስህና ሕይወትህ አምነው የማይቀበሉትን ነገር ልነግርህ አልችልም፡፡
በቁርጠኝነት ስሜት ቀጠለና ፡-
-ስለ ሕይወትና ስለ ፍጥረተ ዓለም ያለኝን አመለካከት ባንተ ላይ እንድጭን የምትፈልገው አንተ ልጅ ሆነህ ነው? ወይስ በሌሎች ላይ የመመርኮዝ የጥገኝነት ልማድ የተጠናወተህ ሰው ነህ? መልካም ፈቃድህ ይሁንና ከልጄ ጋር እንዳልጫወት አታውከኝ?
-በድጋሜ ይቅርታ ያድርጉልኝና መንፈሴና ሕይወቴ እንዴት አድርገው ነው ምላሽ የሚሰጡኝ ?
-አነጋገርህ ከልብ መሆኑ ይሰመኛል፣አንድ ነገር ልንገርህ ፡- የአንገት ጌጥን ብትመለከት ውብ ሐብል ለመሆን እርስ በርሱ መሰናሰል ይኖርበታል፡፡ የኛ ሕይወትም እንዲሁ በእውቀት ሰንሰለት የተሰናሰለ መሆን ይኖርበታል፡፡ የምንኖርበትና . . ደስተኛ የምንሆንበት ምክንያትም ይኸው ነው፡፡
-እንዴት ነው? እባክዎን ይንገሩኝ !
-እውነተኛ ከሆንክ የመልሱን መክፈቻ ቁልፍ የምታገኘው በምርምር በጽናት፣በፍለጋና በቁጠኝነትና ወደ ግቡ ለመድረስ ጥረት በማድረግ ነው፡፡
-ወደ የትኛው ግብ ለመድረስ ?
-ወደ ደስተኝነት!
-እንዴት?
-ወደ ደስተኝነት የሚያደርሰውን መንገድ ፈልግ ! ነፍስህ ትጽናናለችና፣ያንተ ሕይወትና ፍጥረተ ዓለሙም ትርጉም ይኖራቸዋልና! ይቅርታ ጊዜዬን አታቃጥልብኝ፣ከአያቴ ጋር መጫወት እፈልጋለሁ፡፡
-እሺ . . ደግ ነው፡፡ እኔ የደስታን መንገድ አላውቅም፡፡ ይሁንና ቀድሞ ነገር መኖሩ እውነት ከሆነ፣ምናልባት እርስዎ እንደሚሉት በጥረትና በትጋት ወደ ደስታ መንገድ እደርስ ይሆናል!
-መኖሩማ እርግጥ ነው፡፡ ባይኖርማ ኖሮ ሕይወት ትርጉም የለሽ በሆነች ነበር፡፡ ለማንኛውም መልሱን በምታገኝበት ጊዜ የምስራቹን ንገረኝ፡፡ ጽናትና ቁርጠኝነት ካለህ ታገኘዋለህ፡፡ መንፈስህና ሕይወትህ ምላሽ ይሰጡሃል ማለት ምን ማለት እንደሆነም ትረዳለህ፡፡ ለያንዳንዱ የሕይወትህ ነጠላ ጉዳዮች ትርጉም የሚሰጥህን ገመድ ጫፍም ደርሰህ ትጨብጣለህ፡፡
-እንዳሉት እንዲሆን ምኞቴ ነው፣ ግን ስምዎን ማን ልበል? የሚኖሩትስ የት ነው?
-በሕይወት ከቆየሁ በየሳምንቱ ዐርብ በዚህ ሰዓት እዚህ ቦታ ላይ ታገኘኛለህ፡፡ አድራሻህን ስጠኝና አድራሻዬን በኋላ እልክልሃለሁ፡፡
ሽማግሌው ቀጠሉና ወደ ልጅ ልጃቸው ዞር ብለው ኳሱን ወረወሩ፡፡ ጆርጅ በአድናቆት ተሞልቶ ፡-
-በጣም አመሰግናለሁ ይኸውና አድራሻዬ፣አላቸው፡፡
ትቷቸውም ሄደ . .
ትንሽ ሄደት እንዳለ፣ የሥራ ጫና በሚበዛበት ጊዜ እንኳ ተሰምቶት በማያውቅ ሁኔታ ከባድ ድካም ይሰማው ጀመር፡፡ ንቃትና ጥንካሬውን በጥቂቱም ቢሆን ለማስመለስ ትንሽ ለመጠጣት ወሰነ፡፡ ጭንቅላቱ ሊፈነዳ ምንም ያህል እንዳልቀረው እየተሰማው ብሶበት መንገዳገድ ጀመረ፡፡ በዙሪያው ያሉ ነገሮች ምንነት መለየት እስኪያቅተው አዞረው፡፡ በመጓዝ ላይ እያለ አጥወለወለውና ጎዳናው ላይ ራሱን ስቶ ወደቀ፡፡፡
ሰዎች በዙሪያው ተሰበሰቡና አንስተው ሲሸከሙት እንደ ምንም ብሎ ቀና ብሎ የቤቱ አድራሻ ነገራቸው፡፡
በራፉ ላይ ካትሪናን እያለቀሰችና እየጮኸች አገኛት፡፡ ገና ስታየው እያለቀሰች ሮጣ ደረቱ ላይ ስትወድቅ ፡-
-ይኸው አለሁ አልሞትኩም አላት፡፡
-ጌታ የተመሰገነ ይሁን፣እንኳን ተረፍክ፡፡ በጣም ነበር የፈራሁት፡፡ ራስህን ለመግደል ለምን ታስባለህ?
-ጆርጅ ከሚባለው ተንቀሳቃሽ እቃ ራሴን ለመገላገል ! የመኖር ትርጉምና የሕይወትን ዓለማ ምንነት ከማያውቀው፣ በየሰከንዱ መንፈሱ ሞቶ ነፍሱ ከሚድነው ከዚያ እቃ፣ከዚያ የመገልገያ መሳሪያ ለመገላገል ነበር፡፡ መንገድ ላይ ያገኘሁት ሽማግሌ ባይኖር ኖሮ፣መጠጥ ባልጠጣ ኖሮ ከሕይወት ተገላግዬ ነበር !
-ሽማግሌው ደግሞ ማነው?
-አላውቀውም፣ግና ደስተኛ ነበር! (በማፌዝ ቀጠለና) ለምን እንደሚኖርም ያውቃል ?!
-ስለምን እንደምታወራ አልገባኝም፣ለማንኛውም ግን በሰላም የመለሰህ ጌታ የተመሰገነ ይሁን፡፡
-ለኔ ለራሴም አልገባኝም፣ የገባኝ ነገር ቢኖር ወደ ደስታ መንገድ ለመድረስ ቁርጠኝነት ፍለጋና ጽናት የሚያስፈልግ መሆኑን ብቻ ነው፡፡
-የደስታ መንገድ ! የኔ ፍቅር ወደዚያ ትደርሳለህ፡፡ ዋናው ነገር ለኛ ታስፈልገናለህና ለሕይወትህ ግድየለሽ አትሁን፡፡
-አህ፣ለሕይወቴ ግድየለሽ ላለመሆን እሞክራለሁ፡፡ መልሱን እስከማገኝ ድረስ ፍለጋውንና ምርምሩን ለመቀጠልም ስል፣ያኔ እንደ ሽማግሌው ደስተኛ እሆናለሁ፡፡
ካትሪና በገጽታው ላይ በጣም እንደ ደከመው አስተውላ እጁን ይዛ ወደራሷ አስደገፈቸው፡፡ ወደ መኝታ ክፍሉ ሲደርሱ አልጋው ላይ ተዘረገፈ፡፡ የዕለቱ ገጠመኝ ዝርዝሮች እንደ አስበርጋጊ ጽላሎቶች ጭንቅላቱ ውስጥ እየተወራጩ እንቅልፍ አሸንፎት ጭልጥ ሳተ፡፡