- የት ነህ? አሳሰብከኝ፣ደጋግሜ ደውዬ ስልኩ አይነሳም።
- ይቅርታ፣ረስቼ ስልኬን ሳልይዝ ለቁርስ ወጥቼ ነበር።
- ከቀጠሮ መዘግየት ልማድህ አይደለም ብዬ ነው።
- ሳያመኝ አልቀረም፣ሌሊቱን በደንብ መተኛት አልቻልኩም ነበር።
- ጌታ ይፈውስህ፣ሐኪም ቤት እንድወስድህ ትፈልጋለህ?
- የለም አመሰግናለሁ፤ቀጠሮ በማሳለፌም ይቅርታ እጠይቃለሁ። አሁን በጎ ነኝ፣ሻል እያለኝ ነው።
- ሐኪም ቤት መሄድ አለብህ፣እንዲህ ሆነህ እያየን ዝም ማለት አይገባም።
- ሌቪ አመሰግናለሁ። አሁን ጥሩ ተሸሎኛል፣ቅዱሳን ስፍራዎቹን ለመጎብኘት ብንሄድ ደስተኛ ነኝ።
- እንደ ፈቃድህ ይሁን፤ዋነው ነገር ያንተ ደስተኝነት ነው . . ዛሬ ሁለት ወይም ሦስት ቦታዎችን ትጎበኛል፣ምን ይመስለሃል?
- ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው እንጀመር፣ሁለቱን ካደረስን በቂ ነው። ይበልጥ የሚያስፈልገኝ ጉብኝቱ ብቻ ሳይሆን ካንቺ ጋር ቁጭ ብሎ መወያየት ነው።
- ለኔም ዋነኛው ነገር ያ ነው። መጀመሪያ የምናመራው ወደ ማልቀሻ ግንብና ወደ ዮራ ተራራ ነው። ከዚያ በጽዮን ተራራ የሚገኘውን የንጉሥ ዳዊትን መቃብር ትጎበኛለህ። በቂ ጊዜ ከተገኘ ደግሞ በወይራ ተራራ የሚገኙ ጥንታዊ መቃብሮችን ትጎበኛል።
- ተስማሚ ነው፤ድካሙ ሳይመለስብኝ ጉብኝቱን በጊዜ ለማጠናቅቅ ተስፋ አደርጋለሁ።
- ከሐቢብ ጋር የነበረህ ቆይታ እንዴት ነበር?
- ምርጫሽ ግሩም ነው፤በሚገባ የተረዳሽኝ ይመስለኛል።
- ኣ . . ምናልባት በመጠኑ፣ሐቢብ ምሁር ነው፣አእምሮው ብሩህና ክፍት ነው።
- ልክ ነሽ፣በእውቀቱ ብዙ ተጠቅሜያለሁ።
- እሱም ሰለ አንተ እንዲዚሁ ነው የሚለው።
- እንዴትና መቼ ነው እንደዚህ ያለሽ?
- ማታ ወደ ሆቴል ካደረስህ በኋላ ወዲያውኑ ነበር የደወለልኝ፤ካንተ ጋር ባሳለፈው ቆይታ ብዙ መጠቀሙን በአድናቆት ነገረኝ . . ማንንም ሲያደንቅ ባልሰማሁት ሁኔታ ነው ላንተ ያለውን አድናቆት የገለጸልኝ።
- ይህ መቼም የርሱ ትሕትና ነው እንጂ ሙሉ ጊዘውን ከርሱ ጋር ያሳለፍኩት በውይይት በክርክርና በቃለ ምልልስ ነበር።
- ከኔ ጋር የምታደርገው ዓይነት ውይይትና ምልልስ ከሆነ እጹብ ድንቅ ውይይት ነው!
- እህ፣ትንሽ ይለያያል፤አንቺ ረቀቅ ያልሽ ውብ ቆንጆ ነሽ፣እሱ ግን አይደለም፤እርሱን ስለ መረጥሽልኝ ግን በጣም አመሰግንሻለሁ፣ላደረግሽልኝ እንክብካቤና ከኔ ጋር በመድከምሽም ምሳጋናዬ የላቀ ነው። ዋናው ጉዳይ መሰረታዊዎቹ የጉብኝቴ ዓላማዎች ማለትም ስምምነቱን መፈራረምና የደስተኝነት መንገድ ፍለጋውም በስኬት እየተካሄደ መሆኑ ነው።
- ምስጋና የሚገባህ አንተ ነህ፣የውሉን ጉዳይ አሁንም ታስታውሳለህ? እኔ ጭራሽ ረስቼዋለሁ። በነገራችን ላይ ከቤንያሚን ጋር ያደረከው ቆይታ አእምሮው ውስጥ ዝብርቅርቅ ሁኔታ ሳይፈጥርበት አልቀረም።
- እንዴት?
- እኔ እንጃ፣አንተ ወጥተህ ከሄድክ በኋላ አስጠራኝና ‹‹ይህ ሰው በሕይወቴ ውስጥ ካጋጠሙኝ ሁሉ በጣም አስገራሚው ነው›› አለኝና እንዴት? አልኩት፤‹‹ወይ እብድ ነው፣ወይ ደግሞ ቅዱስ ነው›› አለኝ።
- እህህ፣ሦስተኛ አማራጭ የለም ! እብድ መሆን እንኳ አልፈልግም፤አዝናለሁ ለርሱ ጉቦ እያቀበልኩ ግን ቅዱስ መሆን አልችልም።
- ያልከው ነገር ለምን ተጽእኖ እንዳሳደረበት አላውቅም፣ደጋግሞ ሕይወት ገንዘብ ብቻ ናት ብለን ስናስብ ስህተት እንሰራለን ይለኝ ነበር። በሕይወቴ እንዲህ ያለውን አነጋገር ከቤንያሚን ስሰማ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
- ግልጽ ልሁንና . . የማይመቸኝ ሰው ቢሆንም እርሱም በአነጋገሩ ትልቅ ተጽእኖ አሳድሮብኛል። እውን የአካል ደስታ የመንፈስ ስቃይ ነው? የአካልና የመንፈስ ደስታን አንድ ላይ ማጣጣም የሚቻልበትና ስቃይ የሚወገድበት መንገድ አይኖርም?
- እንዲህ ያለውን መንገድ ማግኘት የዘውትር ጉጉቴ ነው።
- እናም ሐቢብ እንደነገረኝ ሁሉ አንቺም በደስተኝነት መንገድ ፍለጋ ላይ ነሽ ማለት ነው?
- በጣም ውብ አባባል ነው፤ግና የደስተኝነት መንገድ ምንድነው?
- አሁን ለማግኘት ስትመኚው የነበረውና እኔም ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ፈልጌ ለማግኘት የተሰማራሁበት መንገድ ነው።
- እኔም ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ በፍላጋ ላይ ነኝ . . (ፈገግ ብላ ዓይን ዓይኑን እያየች) ፦ በሁለታችን መንፈስ መካከል እንዴት ያለ መቀራረብ ይሆን ያለው?!
- ሐቢብ ነግሮኛል፣ካቶሊካዊነትን ለምን አልተቀበልሽም?
- ሀሳቤ ከአይሁዳዊነት ውስብስብነትና ከመዛነፎቹ ለመሸሽ እንጂ ውስብስብነትን በሌላ ውስብስብነት፣መዛነፍን በሌላ መዛነፍ ለመለወጥ አልነበረም። ለዚህ ለዚህማ አይሁዳዊነት ይበልጥ ጥንታዊና ይበልጥ የተቀደሰ ነው።
- እንዳስለመድሽኝ በግልጽነት ንግሪኝ፣ምክንያትሽ ይኸው ብቻ ነው ወይስ ሌሎች ምክንያቶች አሉሽ?!
- እውነቱን ለመናገር ሃይማኖትን መለወጥ ፈጽሞ ቀላል ነገር አይደለም። ሃይማኖቱን የሚቀይር ሰው በዙሪያው ካሉት ሰዎች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ስታስብ ከቤንያሚን ጋር የሚኖረኝ ግንኙነት እንዴት ይሆናል? በሠራዬ ላይ ለአንድ ቀን እንኳ የምቆይ ይመስለሃል?
- እናም ከርሱ በኩል ስጋት አለብሽ ማለት ነው?
- ከመጀመሪያውም በካቶሊካዊነት አልረካሁበትም ብየሃለሁ፣ደግሞም ግልጽ ለመሆን ሃይማኖቴን መለወጥ ያስፈራኛል . . ነጻነት ውድ ዋጋ ያስከፍላል . . እጅግ ውድ የሆነ ዋጋ !
- ነጻነታችንን ለማግኘት ግን ይህን ዋጋ መክፈል ግድ ይለናል፣ነጻነትን የሚመስል ምንም ነገር የለም።
- አሁንም ድረስ ትክክለኛውን ውሳኔ ወይም የደስተኝነትን መንገድ በመፈለግ ላይ ነኝ። ያንን በአሳማኝ መልኩ ሳገኝ ምናልባት በድፍረት መወሰን እችል ይሆናል፣ወይም መወሰን እፈራም ይሆናል . . አላውቅም !
- ቤንያሚንን ትፈሪዋለሽ?
- በትክክል ! . . ድፍረት የተሞላበት ትክክለኛው ውሳኔ ወይም በአንተ አገላለጽ የደስተኝነት መንገድ ወደ ክርስትና የሚወስድ ነው ብለህ ታምናለህ?
- በተከራካሪሽ ላይ መንገድ የመዝጋት ልዩ አቅምና ብቃት አለሽ፣ለምን አንደሆነ አላውቅም?
- መንፈሳችን አብሮ ነው የሚንሳፈፈው ብየህ የለ? ምናልባት በሆነ አፍታ ላይ ተዋህዶ ሊሆን ይችላል።
- አንቺ ቆንጂት ፍጡር እነሆማ ወደ ፈላስፋነት ተለወጥሽ፣መንፈስና መንፈስ እንዴት ነው የሚዋሀደው?
- ኣህ፣አላውቅም፣የማውቀው ነገር ቢኖር አካል እንደሚዋሐድ ሁሉ መንፈስም የሚዋሐድ መሆኑንና የኔ መንፈስና ያንተ መንፈስ አብረው የሚንሳፈፉ መሆናቸውን ብቻ ነው።
- የሚመረጠው ግን በግርታና በጥርጣሬ ከመሆን ፈንታ በተድላና በደስተኝነት አብረው እንዲንሳፈፉ ነው።
- ልክ ነህ፣አሁን ይህን እንተውና ወደ ማልቀሻው ግንብ ወይም ሙስሊሞች እንደሚጠሩት የቡራቅ ግንብ ለመድረስ ጥቂት ደቂቃዎች ይቀሩናል። ከሰሎሞን ቤተ መቅደስ የተረፈ ብቸኛው ቅርስ ነው። በብዙኃኑ የአይሁድ ሃኻሞች አመለካከት ቤተ መቅደሱ ከወደመ በኋላ ወደ ቁድስ ቅጽረ ግቢ መግባት በአይሁዶች ላይ እርም ተደርጓል፣በመሆኑም በዘመነኛው አይሁዳዊ ሕግ መሰረት ግንቡ ለቤተመቅደሱ ቦታ ቅርብ የሆነ አይሁዶች መጸለይ የሚችሉበት ነጥብ ነው። ‹‹የማልቀሻ ግንብ›› የተባለው በግንቡ አጠገብና በትይዩው በሚደረገው የለቅሶና የሀዘን የጸሎት ስርዓት ምክንያት ነው።
- ከመቼ ጀምሮ ነው?
- ከአስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት አይሁዶች ጸሎቶቻቸውን የሚያደርሱትና ለሰሎሞን ቤተ መቅደስ መውደም የሚያከናውኑትን የለቅሶ ሥርዓት ይፈጽሙ የነበሩት በቁድስ ግቢ አካባቢ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ነበር። ከዚያ በኋላ በየዓመቱ ቁድስን ከሚከልለው አጥር አቅራቢያ ከሚገኘው ድንጋይ ፊትለፊት መሰባሰብ ጀመሩ። እነሱ የማልቀሻ ግንብ ሲሉት ሙስሊሞች ደግሞ የቡራቅ ግንብ ይሉታል።
- ታድያ የቡራቅ ግንብ ምንድነው?
- ቦታው በሙስሊሞች ዘንድም የተቀደሰ ቦታ ነው። ነቢያቸው ከመካ ወደ ቁድስ ቡራቅ በሚባል እንስሳ ላይ ተቀምጦ የሌሊት ጉዞ ባደረገ ጊዜ ቡራቅን እዚህ ግንብ ዘንድ እንዳቆመው ይናገራሉ።
- ሙስሊሞች በዚህ ቦታ ላይ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንዲያከናውኑ ትፈቅዳላችሁ?
- ሙሉውን የቁድስ ግቢ ትተንላቸውም ይህን ግንብም ከኛ ጋር ይሻማሉ ! ደግሞም ሙስሊሞች በቅርሶች ዘንድ አምልኮ አያካሄዱም፣ሐውልትና ቅርጻ ቅርጾች ጉዳያቸው አይደሉም።
- ሐቢብ፣ፕሮቴስታንቶች እንደ ሙስሊሞች ናችሁ፣ቅርጻቅርጽና ሥልሎችን አትወዱም እያለ ያሾፍብኝ ነበር።
- ከወደመው ቤተ መቅደሳችን የተረፈልን ይኸው ብቻ ነው፣ይህንን የሚያረጋግጡ የቅርስ ማስረጃዎችን ለዓለም ሁሉ ወደፊት እናሳያለን።
- ይህን ሁሉ ዓመታት የምትሉትን አስረጅ ቅርስ ማግኘት አልቻላችሁም፣ካሁን በኋላ እናገኛለን ብለሽ ተስፋ ታደርጊያለሽ?
- አሃ፣ባናገኘው እንኳ እንፈጥረዋለን !
- እናም አንቺ በዚህ አታምኚም ማለት ነው?
- አምንበታለሁ ወይም አላምንበትም አልልም፣በጥርጣሬ ሁኔታ ውስጥ ነኝ። አንዳንድ ጥናቶች የሚያመለክቱት አይሁዶች ግንቡ አጠገብ መጸለይ የጀመሩት በኦትማን ኢምፓይር ዘመን መሆኑን ነው። ቅድም እንዳልኩህ ከአስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት አይደለም። ሙስሊሞች ይህን ግልጽ ውሸት አድርገው ይቆጥሩታል። ለማንኛውም ቦታው እኛ ዘንድ ከሁሉም በላይ የተቀደሰ ቦታ ነው። (ወደ ጆርጅ ዞር አለችና) ፦ መንፈስህን መግራት፣ማንቃትና ደስተኛ ማድረግ የግድ ነው፤እናም ያለ አምልኮ እንድንቀር ነው የምትፈልገው?
- ዛሬ ደግሞ ከትናንቱ ይበልጥ አስደናቂ ትመስልያለሽ።
- ዛሬ የአምልኮ ቀን ነው፣ወደ ማልቀሻ ግንብ እየደረስን ነው። አሁን ከመኪና ወርደን የቀረውን በእግር መጓዝ ይኖርብናል።
- በዚህ ጸሐይ ውስጥ በእግር የምንጓዘው አጭር ርቀት ብቻ እንዲሆን ምኞቴ ነው፤የድካም ስሜቱ እየተመለሰብኝ ነው።
- አይሁዳዊ አለመሆንህ እንዳይታወቅብህ ይሁን።
- እንዴት?
- ይህን በርኔጣ ወስደህ አድርገው።
- ግዴለም ይሁን፣እህህ፣ግን ይህን አድርጌ ፎቶግራፍ እንዳታነሽኝ፣አለዚያ ካትሪና መቆጣቷ ነው።
- ካትሪናን በጣም የምትወዳት ትመስላለህ !
- አዎ፣ሃይማኖተኛ የሆነች ምሁር ናት፣ልቧም እንዳንቺው የጸዳ ነጭ ነው።
- እንዳንተ ለሃይማኖት፣ለዕውቀትና ለፍካሬ . . አክብሮት የሚሰጥ ሰው ማግኘት እመኛለሁ . . አሁን ወደ ቀኝ ከዚያም እንደገና ወደ ቀኝ እንታጠፍና ሰዎች ተሰብስበው ግንቡ አጠገብ ሲያለቅሱ እናገኛቸዋለን።
- በርኔጣውን ለብሻለሁ፣ለቅሶውን አስመስዬ መተወን ግን አልችልም።
- ችግር የለውም፣ብዙዎች እንዳንተው አስመስለው መተወን አይችሉበትም። ሌሎች በርካታ ሰዎች ግን ሲያለቅሱ ወይም በሚገባ አስመስልው ሲተውኑ ታገኛቸዋለህ . . የቀረው ያንተ ነው ለሴቶች መግባት የተከለከለ ነው።
- እንዴት? አንቺ ካልገባሽ እኔ አልገባም።
- በል እኔ እዚህ እጠብቀሃለሁ፣ገብቼ እንደውሻ እንድባረር ነው የምትፈልገው? እባክህን በል ግባ።
- ቶሎ ተመለስክ !
- በጣም ደክሞኛል፣ቶሎ ወደ መኪናው መሄድ እንችላለን?
- ጥሩ ደስ እንዳለህ።
- ወይም መኪናውን እዚህ ማምጣት ትችያለሽ?
- በጣም የተዳከምክ ትመስላለህ . . አዝናለሁ መኪናውን እዚህ ማምጣት የሚቻል አይደለም፣በርታ እኔ ላይ መደገፍ ትችላለህ . .
- አዝናለሁ፣አስቀድሜም አደከምኩሽ፣አሁንም እንደገና እያስቸገርኩሽ ነው . . እንደ ሕጻን እየቀበጥኩ ነው መሰለኝ።
- ግዴለም . . ዋናው ነገር ወደ መኪና ቶሎ መድረሳችን ነው . . በቅርብ ሆስፒታል ስለሚገኝ ወደዚያ እንሄዳለን፤ጤንነትህ አስተማማኝ ከሆነ በኋላ መቅበጡና እሽሩሩው ሊቀጥል ይችላል።
- ምን ሆኖ ነው?
- አይዞሽ አትስጊ . . እረፍት እንዲያገኝ የሚያስተኛ ማስታገሻ ሰጥቼዋለሁ። በሽታውን ከአንድ ሰዓት በኋላ ከምርመራ ውጤቶቹ የምናውቅ ይሆናል . . (ፈገግ አለና) ፦ በጣም የተጨነቅሽለት ትመስያለሽ፣ባለቤቱ ወይስ ጓደኛው ነሽ?
- ወዳጁ ብቻ ነኝ።
- ለማንኛውም በአንድ ሰዓት ውስጥ የምርመራ ውጤቶቹ ይደርሳሉ፣ከዚያ በፊት የሚነቃ የሚስለኛል።
- ዬት ነኝ?
- በመንቃትህ ጌታ የተመሰገነ ይሁን፣ሆስፒታል ነው የምንገኘው፣አንተም ደህና ነህ።
- ሐኪሙ የታለ?
- በደቂቃዎች ውስጥ የምርመራ ውጤቱን ይዞ ይመጣል። ጆርጅ እረፍት ውሰድ፣ ራስህን አታድክም።
- ሌቪ በጣም ነው የማመሰግንሽ፣እንዲህ አስቸግርሻለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር . .
- እንዲህ አትበል፣ጆርጅ አንተን ለመርዳት ነው እዚህ ያለሁት።
- ጆርጅ ነቃህ? ፍቅረኛህ . . ይቅርታ ወዳጅህ በጣም ተጨንቃልህ ነበር።
- ዶክተር ምን ይሆን የነካኝ?
- የመጀመሪያው የምርመራ ውጤት ሀይለኛ የቫይረስ ኢንፈክሽን መኖሩን ነው የሚያሳየው፡፡ ሌሎቹ የምርመራ ውጤቶች ነገ ነው የሚደርሱት።
- መቼ ነው መውጣት እምችለው?
- በሚገባ ማገገምህ ከተሰማህ ካንድ ሰዓት በኋላ ወይም ነገ፣እንዳፈለክ። ስትወጣ ነርሷ መድኃኒቶችን ትሰጠሃለች። በሉ እኔ ልሂድ . .
- ለጤንነትህ አስተማማኝ ስለሚሆን፣ ጆርጅ እባክህን እስከ ነገ ድረስ እዚህ ቆይ።
- ሌቪ አመሰግናለሁ፣ወደ ሆቴሉ መሄድ እፈልጋለሁ፣ጉብኝቱን ባለ ማሟላቴ ይቅርታ . .
- ይቅርታ አድርጊልኝ።
- የምን ይቅርታ ነው የምትጠይቀው? አትጠይቅ፣ዋናው ነገር ያንተ በጥሩ ጤንነት ላይ መገኘት ነው።
- እርሱም መምጣት ይኖርበታል? ወይስ እኔ መጥቼ የምርመራ ውጤቱን ልውሰድለት?
- ሕመሙ ከተመለሰበት አብራችሁ ኑ፣ደህና ከሆነ ግን አንቺ ብቻ መጥተሸ ቀሪዎቹን የምርመራ ውጤቶች መቀበል ትችያለሽ።
- እንግዲያውስ ነገ መጥቼ ውጤቱን እወስዳለሁ። በአንቡላንስ መኪና ነው ወይስ በኔ መኪና ነው የሚወጣው?
- በራስሽ መኪና ውጡ፣በእግሩ ተራምዶ መሄድ ይችላል . . (ወደ ጆርጅ ዞር አለና) ፦ በል አሁን መሄድ ትችላልህ አለው።
- እንግዲያውስ ጠብቀኝ መኪናዋን ወደዚህ ላቅርብ።
- ሌቪ አመሰግናለሁ፣እንዴት ብዬ እንደማመሰግንሽም አላውቅም . .
- ይቅርታ ዛሬ ቀኑ ሰንበት ነው፣የአምልኮ ብቻ ነው። እኔን ማመስገን አያሰፈልግህም። የማደርገው ሁሉ ለሕሊናዬ ብዬ ነው።
- አዝናለሁ፣ችግር ውስጥ ከትቼሽ ይሆናል፤ምስጋናዬንና ላንቺ ያለኝን አክብሮት የሚገልጽበት መንገድ ስለጠፋኝ ነው የሳምኩሽ።
- አሁን ጊዜው አይደለም . . አሁን ዕረፍት ለመውሰድ ሞክር . . (ፈገግ አለችና) ፦ ካኽ ብዙ ጊዜ ስሞኝ ይቅርታ አልጠየቀም ነበር ! እንዴት እጠላው መሰለህ።
- ይቅርታ፣አንቺን ማስከፋት ፈልጌ አይደለም፤ይህን እንዴት እንዳደረግኩ አላቅውም። ምናልባት በበሽታው ምክንያት የሞራል ድክመት አፍታ ውስጥ ሆኜ ይሆናል፣ወይ ደግሞ ሐቢብ እንዳለው ሁሉ ፦ የውብ መንፈስ አድናቆት ከውብ ገላ አድናቆት ጋር ተደበላልቆብኝ ሊሆን ችላል።
- ወይ ደግሞ ስንነጋገርበት የነበረው የመንፈስ ጥምረት ሊሆን ይችላል፤ለማንኛውም ይህን እርሳውና አሁን እንዴት ነህ?
- አንቺንና ራሴንም እያፈርኩ ነኝ፤በሥጋዊ ፍላጎቴ ፊት ድክመቴን አየሁ። የልቤን ለመገግለጽ እንጂ እመኒኝ አንቺን ማስቀየም ፈልጌ አይደለም።
- እባክህን ይህን ርእስ ዝጋው። ካኽ ሳመኝ ብቻ ሳይሆን ካንድ ጊዜ በላይ ደፍሮኝ ይቅርታ እንኳ አልጠየቀኝም ብየህ የለ? የባሰ ውርደቴ ደግሞ ከቆሻሻው ካኽ ጋር ወሲብ ስፈጽም አንዳንድ ጊዜ የደስታ ስሜት ይሰማኝ የነበረ መሆኑ ነው። ይታይህ መርሆዬን እንድጥስ በመገደዴ እደሰት ነበር ማለት ነው። ምናልባት ቤንያሚን እውነቱን ይሆናል ስጋዊ ፍላጎታችንን የምናረካው መንፈሳችንን በመበደል ነው።
- ምናልባትም መንፈሳችንና ሥጋችን የሚጣጣሙበትን፣መንፈሳችን አካላችንን አካላችን ደግሞ መንፈሳችንን የሚያረካበትን መንገድ ባለማግኘታችን ሊሆን ይችላል።
- ምናልባት የደስተኝነት ጎዳና ፍለጋ ፕሮጄክትህ ወደዚያ ሊያደርስህ ይችል ይሆናልና ከደረስክበት ለኔም መንገሩን እንዳትረሳ። ባታደርገው ይቅርታ አላደርግልህም።
- መቼ ይሆን ይህን መንገድ የምጨርሰው? የሚየገኘኝ ሰው ሁሉ ውጤቱን እየተጠባበቀ ነው። ሌቪ በሆነው ነገር ማዘኔንና ላንቺ ያለኝን አክብሮት ደጋግሜ እገልጽልሻለሁ።
- ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወደ ሆቴሉ እንደርሳለን፤ዛሬ ክፍልህ ውስጥ የተሟላ ዕረፍት መውሰድ ይገባሃል። የምሳ ሰዓቱን አሳልፈናል፣እራት ክፍልህ ድረስ እንዲመጣልህ አመቻችልሃለሁ። ቁርስም ጧት እዚያው ይመጣልሃል . . እኔ የምርመራ ውጤቱን ለማምጣት ወደ ሆስፒታሉ ሄጄ ወዳንተ እመጣለሁ፤መቼ ነው የምትሳፈረው?
- አንደበቴን ለጎምሽኝ፣መቼም አመሰግናለሁ፣ጉዞዬ ማታ አስራ ሁለት ሰዓት ነው።
- ካንተ ጋር ብቀመጥ ደስ ይለኝ ነበር፣ከቆየሁ ወደ ውይይቱ ገብተህ እንዳይደክምህ ስለምፈራ እሄዳለሁ።
- ካንቺ ጋር ሀሳብ ስለዋወጥ የምሰማኝን እርካታ ልነግርሽ አልችልም፣ግና ብዙ አድክሜሻለሁና አንቺም ሄደሽ ማረፍ አለብሽ።
- አሁን የሰንበት ጸሐይ ጠልቃለች፣ለምን እንደሆነ የማላውቀውን ነገር መስራት እፈልጋለሁ፤ባሻህ መንገድ ልትተረጉመው ትችላለህ።
- አልገባኝም !
- የኛ ሰንበት አሁን አብቅቷል፤ያደረኩትን ነገር ምንነት የመተርጎሙን ነገር ላንተ ትቻለሁ፤እኔ ግን ለምን እንዳደረኩት አላውቅም፣ደህና ሁን።
- የኔ ፍቅር ጤንነትህ አሁን እንዴት ነው?
- እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ፣ከሆስፒታል ወጥቻለሁ። መታመሜን ማን ነገረሽ?
- መታመምህን? የምን መታመም? የማውቀው ነገር ቢኖር ቶም ትናንት በቤተክርስቲያን ስነ ሥርዓት ላይ በላክለት ኢ-ሜይል ትንሽ ድካም እንደሚሰማህ የገለጽክለት መሆኑን የነገረኝን ብቻ ነው።
- አሁንም በድጋሜ ቶም?
- የኔ ፍቅር አሁንም እየጠረጠርከኝ ነው ማለት ነው?
- ፈጽሞ፣አሁን ደህና ነኝ ነገ መምጣቴ ነው፣አይሮፕላኑ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ ከዚህ ይነሳል።
- በአንቡላንስ መኪና እንጠብቀሃለን።
- ኣይ፣አስፈላጊ አይደለም።
- ግዴለም ለጤንነትህ ጥንቃቄ ሲባል አስፈላጊ ነው . . አላራዝምብህም፣አሁን በደንብ እረፍት ለማድረግ ሞክር፣ጌታ ይጠብቅህ።
- የኔ ፍቅር አንቺንም ጌታ ይጠብቅሽ።
- ሴትየዋ በጣም የምትወድህና የምትጨነቅልህ ትመስላለች። የምግቡን ጥራት ራሷ ነች ያረጋገጠችው፤መድኃኒትህን መውሰድ እንዳትረሳ እንድንነግርህ አሳስባናለች። ምግቡን ይዤ ወዳንተ ስመጣ ነው የሄደቸው።
- መልካም፣ አመሰግናለሁ።
- ይህ ከፍቅረኛህ የተሰጠን መመሪያ ነው፣ቁርስ ማዘጋጀታችንን ለማረጋገጥ ከግማሽ ሰዓት በፊት ደውላ ነበር። ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይም መድኃኒትህን እንድትወስድ ደውለን እንድናስታውስህ ለመጠየቅ ደውላ ነበር . . አንተ ዕድለኛ ሰው ነህ፣እንዲህ ያለችውን ማራኪ ቆንጆ ፍቅረኛ ማን ይታደላል?
- መልካም ፈቃድህ ከሆነ ወደ ክፍልህ እንምጣ?
- በደስታ፣ግቢ።
- እንግዳ አለኝ፣ይግባ?
- በመካከላችን መለያ አታድርጊ፣እንግዳሽ የኔም እንግዳ ነው፣እባክሽን አስገቢው።
- የታመምከው በኔ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፣ሕመሙ የጀመረህ ከኔ ጋር ሆነህ ነበር፣ሌቪ ከዚህ ነጻ ነች።
- ሌቪማ ከማንኛውም እንከን ንጹሕ ነች፣ከራሱ ከንጽሕናም በላይ ንጹሕ ነች።
- እኔ ፊት ይህ ሁሉ ማሽኮርመም ምንድነው?
- ኦህ፣ጠባቂ ዘበኛችን መሆንህን ረስቼ።
- አልገባኝም ሐቢብ ዘበኛችን ነው ስትል ከምን የሚጠብቅ ዘበኛ ነው?
- ዝም በይው . . ጆርጅ ሊያጣላን ፈልጎ ነው . . (ወደ ጆርጅ ፊቱን አዞረና) ፦ ለጤንነትህ አሁን እንዴት ነህ?
- እንደምታየሁ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነኝ፣አሁን በጣም ተሸሎኛል . . ትናንት በጣም ደክሜ ሌቪም ከኔ ጋር ስትደክም ዋለች።
- ፈጽሞ አልደከምኩም፣ምን እንደማደርግም አላወኩም ነበር። እኔ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙኝ ሁሌም እርበተበታለሁ። እንዲያውም አንተን አስቸግሬህ እንዳልሆን እሰጋለሁ። ድካም እንደሚሰማህ በነገርከኝ ጊዜ ጉብኝቱን መሰረዝ ይገባን ነበር፣ምናልባት ምክንያቱ የኔ አለማስተዋል ሳይሆን አይቀርም።
- ፈጽሞ አልተሳሳትሽም፣ያጋጠመኝ ድንገተኛ ሁኔታ ነበር።
- ሐኪሙ ተመልሰህ ለሁለት ሦስት ቀን እነሱ ዘንድ እንድትቆይ ይፈልጋል፣ምን ታስባለህ?
- አይሮፕላኑ የሚነሳው አስራ ሁለት ሰዓት ላይ ነው፣ማለትም ከሁለት ሰዓት በኋላ ወደ አይሮፕላን ማረፊያ መንቀሳቀስ ይኖርብኛል፤ሁለት ሦስት ቀን ትይኛለሽ !
- ጆርጅ እባክህን ጤንነትህ አስተማማኝ መሆኑን እስክናረጋግጥ ሁለት ሦስት ቀናት ብቻ !
- አሁን ደህና ነኝ፣የመጨረሻው የሐኪም ውሳኔ እንዴት ሆነ?
- ሌቪ ስጭው፣ውጤቱ ጥሩ ነው፤ ሐኪሙ ግን የበለጠ እርግጠኛ መሆን ይገልጋል።
- ጆርጅ ለንደን ሰትደርስ በቀጥታ ወደ ሆስፒታል በመሄድ እንድንረጋጋ አድርገን።
- ባለቤቴ ካትሪና መታመሜን አውቃ አንቡላስ መኪና ይዛ አይሮፕላን ማረፊያ እጠብቃለሁ ብላለች፣እንዳታደርገው ብለምናትም እምቢ ብላለች፣ሌቪ እሷም እንዳንቺው ሀይለኛ ናት።
- ካትሪና በጣም ጥሩ ነው ያደረገችው። ሁለት ሰዓት ያህል ስላለን ምሳህን መብላት አለብህ፣ከዚያ ለመጓዝ እቃህን ታዘጋጃለህ።
- ምሳውን ከአንድ ሰዓት በኋላ አብረን እዚሁ ሆቴሉ ሬስቶራንት እንመገባለን፣ተጋብዛችኋልና እምቢ አትበሉ። ከምሳ በኋላ ለመታጠብና ሸንጣዎቼን ለማዘጋጀት ከሩብ ሰዓት በላይ አያስፈልገኝም።
- በሬስቶራንቱ ሳይሆን እንዳትደክም እዚህ አንተ ክፍል ውስጥ ከሆነ ተስማምተናል።
- ኣይ ሌቪ . . ትንሽ መንቀሳቀስ እፈልጋለሁ፣በሬስቶራንቱ ቢሆን ፈጽሞ አያስቸግረኝም።
- ቀሪ ጊዜያችንን ለመጠቀም ያህል የደስተኝነት መንገድ ፍለጋው ጉዳይ እንዴት ሆነ?
- ሐቢብ፣ይህ የደስተኝነት መንገድ ፍለጋ ሁለተኛው ጉዞዬ ነው። ከተለያዩ ሰዎች ጋር ካደረኳቸው ግንኙነቶች፣ ውይይቶችና ስብሰባዎች ሌላ ማለት ነው። ይህ ጉዳይ ረዥም ጊዜና ጥረት ጠይቆኛል፣ጥረቶቼ በድልና በስኬት እንደሚጠናቀቁ ነው ተስፋ የማደርገው።
- ሌቪ ፦ ያንተ ስኬት የሁላችንም ድልና ስኬት ነው። የምተትደርስበትን ውጤት በጉጉት እንጠባበቃለን።
- ሐቢብ ፦ የመጀመሪያ ጉዞህ ወዴት ነበር?
- ቅደም ተከተሉን ካትሪና እንዳስቀመጠቸው ላስቀምጥላችሁና ፦ መጀመሪያ ወደ ድንቃ ድንቆች አገር፣ከዚያ ወደ ፍጥጫዎች አገር፣ ቀጥሎም ወደ አብያተ ክርስቲያናት አገር ነው።
- የድንቃ ድንቅ አገር ሕንድ መሆኗንና የፍጥጫዎች አገር አንተ አሁን ያለህበት መሆኑን አወቅን፤የአብያተ ክርስቲያናት አገር ደግሞ የትኛው ነው?
- ሮምና ቫቲካን ነው። ቀጣዩ የጉዞዬ መዳረሻ ወደዚያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
- ሐቢብ ፦ ቁድስ የሃይማኖቶች መገኛና ማጣቀሻ፣የእምነት ፍጥጫዎች ማስተናገጃ በመሆኗ ጠቃሚ ተደርጋ መታሰብ ትችላለች። ቫቲካንም በተለያዩ የክርስትና ጎራዎች ዘንድ ከዋነኞቹ የክርስትና ስፍራዎች አንዷ ከመሆኗ አንጻር ለምን እንደምትጎበኝ መገመት ይቻላል። የሚገርመው ሕንድ ለምንና እንዴት የመጀመሪያ ሆነች? የሚለው ነው።
- የመጀመሪያ ጥያቄዬ መለኮታዊ ሃይማኖቶች ይሻላሉ ወይስ ሰው ሰራሽ ምድራዊ ሃይማኖቶች? የሚል ነበር። ለዚያ ብዬ ነው ወደ ሕንድ የተጓዝኩት። ቀጣዩ ጥያቄ ደግሞ . .
- ሌቪ ፦ በማቋረጤ ይቅርታ አድርግልኝና የመጀመሪያ ጥያቄ ‹‹ሃይማኖት ነው ወይስ ኤቲዝም ነው የሚሻለው?›› የሚል መሆን የነበረበት።
- ልክ ነሽ፣ይሁን እንጂ ፊትም ሆነ አሁን ኤቲዝም የማመካኛ ፍልስፍናን የሚያስከትል የስነ ልቦና በሽታ ነው የሚል እምነት አለኝ። ኤቲስቶች በውስጣቸው የአምላክን መኖር ያምናሉ። ከነሱ የበለጠ በመንፈስ ቀውስና በጭንቀት የሚጠቃ ፍጡር የለም።
- ልክ ነህ፣ግና ይህ በገለልተኝነትና በሳይንሳዊ መንገድ መጠናት ይገባው ነበር።
- አጥንቻለሁ፣በእውነት መርምሬያለሁ ! ግና ያንን በአካል ለማየት ወዴት መሳፈር ነበረብህ ብለህ ታስባለህ?
- እህህ፣በማንኛውም ኤቲስት የአእምሮ ጓዳ ውስጥ ተጓዝ፣የምትናገረው እርግጠኛ መሆኑን ትረዳለህ ! ! እነሱ ራሳቸው እንዴት ችለው እንደሚሸከሙት እኔ እንጃ ! !
- ሌቪ ፦ ለዚህ ነው ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ በጭንቀት የሚጠቁና ራሳቸውን የሚያጠፉ የሆኑት።
- ፍቀጂልኝና ልቀጥል፣ሰው ሰራሽ ምድራዊ ሃይማኖቶች አፈተረትና ማጭበርበር መሆናቸውን አረጋግጠን ካበቃን በኋላ ሁለተኛው ጥያቄ፣ ከመለኮታዊ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚሻለው የትኛው ነው? የሚል ነበር። ወደ ቅድስት አገር የተደረገው ጉብኝት አይሁዳዊነትን በቅርበትና በጥልቀት ለመመርመር ነበር . . (ወደ ሌቪ ዞር ብሎ) ፦ ጉብኝቱ ባንቺ ባልዳረባነት በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ።
- እናም ከትናንት ወዲያ ክርስትናንና የተለያዩ ጎራዎቹን፣የርስ በርስ ጦርነቶቹንም አስመልክተን ያደረግናቸው ውይቶች ከሦስተኛው ጉዞ የቀደመ ችኮላ ነበር ማለት ነዋ? !
- አዎ፣ይሁን እንጂ ተገቢ የሆነ ችኮላ ነው። ወደ ቫቲካን የሚደረገው ጉዞ ክርስትናን በተለይም ካቶሊክን በይበልጥ ከቅርበት ለማወቅ ነው።
- የእስላም ሃይማኖትን ማወቅ ብቻ ነው የሚቀርህ።
- (ሌቪ ፊቷ ላይ የመከፋት ስሜት በግልጽ እየተስተዋለ) ፦ የአረመኔዎቹን ሃይማኖት፣እንግዲያውስ ወደ መካ ሂድና እወቀው፤ግና ያሻህን ብታደርግ አያስገቡህም።
- አህ፣አትቆጭ ተረጋጊ፣እውነቱን ለመናገር ቁድስ ውስጥ ከሙስሊሞች ጋር ለመገናኘት ተስፋ አድርጌ ነበር። እዚህ አብዛኞቹ ነዋሪዎች ሙስሊሞች መሆናቸውን አንዘንጋ፤ይሁንና ጉብኝቱ አጭር በመሆኑና በመታመሜም ምክንያት አልተሳካልኝም። በአጠቃላይ ግን ወደ ሙስሊሞች አገር መሄድ ላያስፈልገኝ ይችላል።
- ሙስሊም ያልሆነን ሰው ወደ መካ እንዳይገባ ማድረጉ አይሁዶች ሙስሊሞችን፣ወይም አይሁድ ሴቶችን ወደ ማልቀሻ ግንብ እንዳይገቡ በማገድ እንደሚጥሉት ክልከላ ዓይነት ነው። ወይም ወጣት ሙስሊሞች ዓርብ ቀን በአልአቅሳ መስጊድ ተገኝተው እንዳይሰግዱ በአይሁዶች እንደሚከለከሉት ነው . .
- ጆርጅ ፦ ነገሩን ቀለል አድርገው፤ቀድሞውኑም አንተ የካቶሊክ ጭንብል ያጠለቅህ ሙስሊም ነህ ብየሃለሁ !
- ሌቪ ፦ እህህ፣እርሱ ሁሌም እንደዚህ ነው፤ዶክተር ዛሬ የራስህ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ግለሰብ አንተን ተጻርሮ ለኔ ወግኗል።
- በኔ ላይ የጆርጅን እገዛ አትጠይቂ፣እሱ ዛሬ መሳፈሩ ነው፣እኔና አንቺ ግን ክርክራችን የሚቀጠል ይሆናል። ይሁንና አንተ ጆርጅ አይሁዳዊነትንና ክርስትናን እንደመረመርክ ሁሉ እስላምንም ማጥናትና መመርመር ፍትሐዊነትና ሚዘናዊነት ነው። ኤቲዝምን እንኳ እንድትመረምረው ጠይቄህ የለ? እናንተ ዘንድ ኤቲዝም ከእስላም የተሻለ ነው ማለት ነው?
- እህህ፣ምናልባት።
- ጊዜው ሄዷል፣እኛ ቀድመን ሄደን እንጠብቅህ? ወይስ ከኛ ጋር ትወጣለህ?
- ስለሚደክመው ሲወጣ ሊናግዘው ይገባል።
- ሌቪ አመሰግናለሁ፣እናንተ ቀድማችሁ ሂዱ፤መጸዳጃ ቤት ገብቼ እወጣና ቶሎ እደርስባችኋለሁ።
- ለርሱ ያለሽ አድናቆት ከሚገባው በላይ እንዳይሆን ስጋት አለኝ።
- ለምን?
- ጣልቃ በመግባቴ ይቅርታ፤ግና የምትለዋወጡት እይታ ጥርጣሬን የሚጭር፣አነጋገራችሁም ልክ የፍቀረኞች አነጋገር ዓይነት ነው።
- እዚህ ደረጃ ላይ ለምን እንደ ደረስን አላውቅም ! እንደ ነገርኩህ ሁሉ ከመጀመሪያው አንስቶ ወሲባዊ ግንኙትን እምቢ ብሎ ባለቤቱን እንደሚወዳትና ይህን ማድረግ ክህደት መሆኑን ነበር የነገረኝ።
- የመንፈስና የስነ ምግባር አድናቆት ከጾታዊ ሥጋዊ ስሜታዊ ፍላጎት አድናቆት ጋር አይምታታብሽ ብየሻለሁ።
- ትናንት እጅግ አስደናቂ የሆነ ነገር ተከስቶ ነበር። በሕመሙ ምክንያት ተዝለፍልፎ ሲወድቅ ደግፌ ካነሳሁት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከንፈሬን ሳመኝ፤ወደ ክፍሎ ደርሰን አልጋው ላይ ሳስተኛው ደግሞ እኔም መልሼ ሳምኩት።
- በጣም ያሳዝናል፣መሳሳም በሁለታችሁም ባህሎች ውስጥ በጣም የተለመደ ተራ ጉዳይ ነው። መርሆዎቻችሁን መጣስ ግን ተራ ጉዳይ መሆን የለበትም።
- ለሆነው ነገር ይህ ነው የምለው ትንተና የለኝም። አንተ እንደምትለው ሊሆን ይችላል፣ወይም ሰብአዊ ድክመት ይመስለኛል።
- የሬስቶራንቱ ምግብ ክፍት ቡፌ ነውና መልካም ፈቃዳችሁ ከሆነ ተነስተን ምግባችንን እንውሰድ።
- ካቆምንበት እንቀጥላለን፤እኔ እስላምን ለማወቅና ለማጥናት ወደ አንድ ሙስሊም አገር መጓዝ እንዳለብህ ነው የሚታየኝ።
- ብዙ ጊዜ ከርሱ ጋር የማልስማማ ቢሆንም ለእስላም እንደ ሞገተ ሁሉ ለኤቲዝም በመሞገቱ አሁን እኔም ሀሳቡን ተቀብያለሁ።
- እህህ፣ለኤቲዝም ሆነ ለእስላም አልተሟገትኩም፣ የተናገርኩት ወደ እውነት ለመድረስ መከተል ስላለበት ሳይንሳዊ የምርምርና የጥናት ዘዴ ነው።
- ያደረኳቸው ጉዞዎች ሁሉ አሁን የምናደርገውን በመሳሰሉ በርከታ ረዣዥም ውይይቶችና ክርክሮች የታጀቡ፣በብዙ ንባቦች የተደገፉ፣ስመለስም ጥልቅ እሳቤና ምክክሮችን ያስተናገዱ ነበሩ። በአሁኑ ዙር ግን ጉዞው በጣም የተሳካና የበለጸገ በመሆኑ የመረጃው መጠንና ብዛት ለማስተንተን ካለኝ ጊዜ አንጻር እጅግ የበዛ ነው። ከተመለስኩ በኋላ ለማስተንተን ተስፋ አደርጋለሁ።
- አፋጣጭ እንደማይሆን ተስፋ እያደረኩ አንድ ጥያቄ መጠየቅ ይፈቀድልኛል?
- ጠይቂ።
- አይሁዳዊነት፣ካቶሊካዊነት፣ኦርቶዶክስ ወይም ሌላው ቀርቶ እስላም የምታስሰው የደስተኝነት መንገድ መሆኑን ካረጋገጥክ በቀጥታ እምነቱን ተቀብለህ ተከታዩ ትሆናለህ? ወይስ ትርፍና ኪሳራን ማስላት ትጀምራለህ?
- የደስተኝነትን መንገድ ካወቅሁ የተጣራው ትርፍ ያ በመሆኑ ሁሉም የትርፍና ኪሳራ ስሌት ያከትማል የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ መንገድ ይበልጥ ደስታን የሚሰጥና ይበልጥ ትርፋማ የሆነ ምን ይኖራል? . . ዋናው ነገር መንገዱን ላግኘው።
- ታገኘዋለህ፣በእርግጠኝነት ታገኘዋለህ፤ይሁን እንጂ ባልከው ነገር ላይ ጥርጣሬ አለኝ . .
- ምኑን ነው የምትጠራጠረው?
- ያን ማድረግ እንዲሁ በቀላሉ የሚሆን መሆኑን። የትርፍና ኪሳራ ስሌት የማይኖር ስለ መሆኑ እጠራጠራለሁ። አንዳንድ ውሳኔዎች ሁሌም ለመወሰን በጣም አስቸጋሪ ይሆናሉ . . ! !
- እንዴት?
- ሀሳቤን ግልጽ ላደርግልህ፣የስኳር ሕመም ያለባቸው ሰዎች ሁሉ ስኳር መውሰድ ጎጂ መሆኑን ያውቁታል ግን ይወስዳሉ። ትርፍ ክብደት ያለው ሰው ሁሉ አንዳንድ የአመጋገብ ልማዶች ጎጂ መሆናቸው ያውቃል ግን ምግቡን መብላት አያቋርጥም።
- ይህን ካልኩት ጋር ምን ያገናኘዋል?
- ሃይማኖትን መለወጥ የአመጋገብ ልማድን ከመለወጥ ይበልጥ አስቸጋሪ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ሃይማኖትን መለወጥ የሕወትን ትርጉምና መንስኤውንና አንቀሳቃሽ ሞተሩን የመለወጥ ያህል ነው። (ወደ ሌቪ ዞረና) ፦ ሌቪ ይህን በሚገባ ትረዳለች ብዬ አምናለሁ። ለማንኛውም በእርግጠኝነት መንገዱን ታገኛለህ።
- እንዴት እንዲህ እርግጠኛ መሆን ቻልክ? ታድያ ሁለታችሁም መንገዱን እየፈለጋችሁት ስትሆኑ እስካሁን እንዴት አላገኛችሁም?
- አንተ ይህን ያህል ጽናትና ቁርጠኝነት ሰንቀህ እየፈለከውን ልታጣው አትችልም። በተጨማሪም የፈጣሪ አምላክ ቸርነት ወደ እውነት ለመድረስ የሚጥረውን ሰው አያግዝም ብሎ ማሰብ የማይቻል ነው።
- አንድ ወቅት ላይ አግኝቸው አሁን አንተ ያልከውን ያለኝን ደስተኛ ሽማግሌ እንዳስታውስ አደረከኝ።
- ሽማግሌው ምን አለ?
- በምናገረው ትገረሙ ይሆናል፤ራሴን ለመግደል እየሄድኩ ነበር፣የደስተኝነት መንፈስ ፊቱ ላይ በግልጽ ይነበብ የነበረውን ሽማግሌ መንገድ ላይ አገኘሁትና ደስተኛ ነህ? ብዬ ጠየኩት። አዎ አለኝ፤ደስተኛ መሆን የምችለው እንዴት እንደ ሆነ ጠየኩት። ለማንኛውም ‹‹የደስተኝነት መንገድ›› የሚለውን ብሂል የሰማሁት ከርሱ ነበር።
- መልሱ ምን ነበር?
- ቀጥተኛ መልስ አልሰጠኝም፣ጽናትና ቁርጠኝነት ካለህ ትደርስበታለህ ነበር ያለኝ።
- ከዚያ በኋላ ከርሱ ጋር ግንኙነት አልቀጠልክም?
- አዝናለሁ፣ቁጥሩ ወይም አድራሻውን . . አልወሰድኩም ነበር። ቁጥሬንና አድራሻዬን የወሰደው እርሱ ነው ግን አልደወለልኝም።
- ይቅርታ ጆርጅ ጊዜው እየሄደብህ ነው፣ምሳውን ቶሎ በልተህ ሸንጣዎችህን ማዘጋጀት ይኖርብሃል።
- አልዘገይም . . በሩብ ሰዓት ውስጥ ከናንተ ጋር እሆናለሁ . . ወደ ክፍሉ ሄደ።
- የጆርጅ ድፍረትና ነገሮችን አቅልሎ በጥልቀት የማየት ብቃቱ በጣም ያስደንቀኛል።
- እኔም እንደዚሁ እደነቃለሁ።
- እኔን በተመለከተ እኔ ወንድ ነኝና እንዳሻኝ አደንቃለሁ፣አንቺ ግን ራስሽን ያዝ አድርጊ።
- እናንተ ዐረቦች በወንድና በሴት መካከል ልዩነት ታደርጋላችሁ !
- ዐረቦች ወይስ አይሁዶች? በዚህ ጉዳይ ላይ ክርክራችንን የቋጨን ይመስለኛል፤ይሁንና መካድ የማትችያቸው አንዳንድ ልዩነቶች መኖራቸው የግድ ነው
- ምን የመሳሰሉ?
- እህህ፣እኔ እንዳንቺ ቆንጆ አለመሆኔን፣አንቺ ወንድ እኔ ሴት አለመሆኔን . . የመሳሰሉ። የነገሮችን ተፈጥሮ መለወጥ ትፈልጊያለሽ? የፈለግነውን ብናደርግ መብላት ከመጠጣት የተለየ ነገር መሆኑ ይቀጥላል። ሁለቱም የየራሳቸው የሆነ የተለየ ሚና ይጫወታሉ። አንቺ ውብ ተከራካሪ ኮረዳ እንደሆንሽ ትቀጥያለሽ፣እኔም ወንድ ተከራካሪ ሆኜ እቀጥላለሁ። ሴቶችን እንደ ውሾች፣ቆሻሻዎች ወይም እርኩሶች . . አድርጎ ማቅረብ ግን ተከታዮቹን ከሚያከብር ግለሰብ ወይም ሃይማኖት ሊሰማ የማይገባ እኩይ ነገር ነው።
- ማለት የፈለከውን በሚገባ እረዳለሁ፣ማንጓጠቱጡን ግን ተወት አድርገው።
- ይቅርታ፣ዋናው ነገር አድናቆትሽ ለገላው ሳይሆን ለአመለካከቱ፣ለጽናቱ፣ለመንፈሱና ለመልካም ስነ ምግባሩ ብቻ ሊሆን ይገባል። ለርሱም አስቀድሜ እንዲህ ብየዋለሁ፤የሁለታችሁ ጠባቂ ዘበኛነቴ ትርጉምም ይህ ነው።
- አሃ . . የዘበኛ ትርጉም ገና አሁን ገባኝ . . እንግዲያውስ እጠነቀቃለሁ፣ትናንት የሆነው ይበቃል።
- ጊዘው እየተጣደፈ መሰለኝ . . እንነሳ እንዴ?
- አዎ፣የትራፊክ መጨናነቅ ወይ ፍተሻ ኬላዎች እንዳይኖሩ ፍርሃት አለኝ።
- ጌታ ይጠብቅህ፣ይቅርታ አድርግልኝ ሌቪ ታደርሰሃለች፣ እኔ ቀጠሮ አለኝ። የደስተኝነት መንገድ ፍለጋው ከምን እንደደረሰ ለኛ ማሳወቁን ግን አደራ እንዳትረሳ።
- የዘበኝነት ሥራህን ከጫፍ አታደርሰውም?
- እህህ፣አላደርስም የሚጠብቃችሁ እግዚአብሔር ነው፤ከመርሁ ይበልጥ የሰውን ልጅ የሚጠብቅ ምንም ዘበኛ የለም።
- ሻንጣዎቹን ለመጫን መኪናውን ወደ ሆቴሉ በር ላስጠጋ።
- ጆርጅ አርክተህናልና አመሰግናለሁ፤ስላንተ ለመስማትም እጓጓለሁ፤ጌታ ይጠብቅህ። ለንደን እንደደረስክ በአቅራቢያህ ወደሚገኝ ሆስፒታል መሄዱን እንዳተረሳ፣ሌቪ ዘንድ ያለውን መርፌ መውሰድም እንዳትዘነጋ።
- የምን መርፌ ነው?
- አይሮፕላን ውስጥ ሕመሙ ቢቀሰቀስብህ እንድትወስደው ሐኪሙ የሰጠን መርፌ ነው።
- ሁለታችሁንም አመሰግናለሁ።
- ጆርጅ ስትለየን በጣም ቅር ይለናል፤ጥቂት ቀናት ብቻ ነው ከኛ ጋር የቆየኸው፤ሆኖም ግን የማይረሳ ጉልህ አሻራ ትተህልናል።
- የሚፍለቀለቅ ፈገግታሽ፣ዕውቀትሽና አስተሳሰብሽን ናቸው እንጂ የማይረሱት። ካንቺ በብዙ ነገር ተጠቅሜያለሁ፣ብዙም አስቸግሬሻለሁ፣እናም ምስጋናዬ ይድረስሽ።
- ክርክሮችህንና ውይይቶችህን . . እይታህንም አጣለሁ፤ወደኖርኩበት የጭቆና አዙሪትም መመለሴ ነው።
- እንደ ቤንያሚን ላለ ሰው ይህ እንባ ተገቢ አይደለም።
- ችግሩ ቤንያሚን ወይም ሁሉም አይሁዶች ሳይሆኑ እውስጤ ያለው እውነታ ነው። የደስተኝነትን መንገድ አላውቅም፤ካንተ ጋር ስንወያይ የበዛ ደስተኝነት ይሰማኝ ነበር።
- የጋራ ውይይቶቻችን ይቀጥላሉ፤ከሐቢብ ጋር የሚኖርሽ ውይይትም ይቀጥላል . . አንቺ እውነት አለሽ ! እኔ በደስተኝነት ፍለጋ መንገድ መጓዝ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ቀደም ሲል ተለይቶኝ የማያውቀው ጭንቀት ጎብኝቶኝ አያውቅም።
- ይህን በደስተኝነት መንገድ ፍለጋህ የምትደርስበትን ውጤት እንደምታስታውቀኝ የሰጠኸኝ ቃል ኪዳን አድርጌ ነው የምቆጥረው። እኔና ሐቢብም የምንደርስበትን ውጤት እናሳውቀሃለን።
- ቃል ኪዳን ነው . . ግን ከግዴታ ጋር ነው።
- ግዴታው ምንድነው?
- እንባሽን አብሰሽ ፈገግ ማለት ነው፣በፈገግታ የበራ ፊትሽን ማየት ደስ ይለኛል።
- ተስማምተናል፤ትናንት ስሰናበትህ ለሆነው ነገር ይቅርታ አድርግልኝ፤እመነኝ ለምን እንዳደረኩት አላውቅም።
- በሚገባ እረዳሻለሁ፣እኔም እንዳንቺው ሁሉ ከማልቀሻው ግንብ ለቀን ስንወጣ ያንኑ ዓይነት ለምን እንደ ፈጸምኩ አላውቅም . . እህህ፣ምናልባት በማልቀሻው ግንብ አጠገብ ማልቀስ ባለ መቻሌ ሊሆን ይችላል።
- ለምን አላለቀስክም?
- ለምን አላቅሳለሁ? የሚችሉትን ሁሉ አድርገው ስለመኖሩ እስካሁን አንድ ማስረጃ ማግኘት ላልቻሉት ቤተመቅደስ ውድመት አለቅሳለሁ !
- ስለ ሃይማኖቴ ስትናገር ቀይ መስመር እያለፍክ መሆንህ አይሰማህም?
- እህህ፣አዝናለሁ፣የተናገርኩትን ለማካካስ የፐሮቴስታንትን ቀይ መስመር ረግጬ አልፋለሁ፤በአውሮፓ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ካቶሊኮችን የገደሉ ወንጀለኞች ናቸው . . የኔ እመቤት ደስ ብሎሽ ይቅር አልሽኝ?
- የኔ ጌታ ይቅር ብየሃለሁ . . ግን ከግዴታ ጋር ነው።
- ወደኔ መለስሽው፣ግዴታው ምን ይሆን?
- ነገ በኢ-ሜይል ቢሆን እንኳ ስለ ጤንነትህ ሁኔታ እንዳናስብ ታስታውቀናለህ።
- ተስማምተናል።
- እነሆ ደረስን፤ይህ በመጀመሪያው የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ስም የተሰየመ የቤንጎሪዮን አይሮፕላን ማረፊያ ነው። ለመረጃ ያህል ይህ አይሮፕላን ማረፊያ በመካከለኛው ምስራቅ ከሁሉም የተሸለ በመሆን የተሸለመ ነው።
- አመሰግናለሁ ።
- ደህና ሁኚ፣ኢየሱስ ይተጠብቅሽ ።
- ደህና ሁን፣ጌታ አምላክ ይጠብቅህ።