በቀጠሮው መሰረት ከተገናኙ በኋላ ማይክል ውይይቱን ለመጀመር ጠየቀ፦
ዛሬ በአንድ የኦሪየንታሊስት ሙያተኛ የተጻፈና እስላማዊ ሕግና ሸሪዓን አስመልክቶ አያሌ ጉዳዮች የተነሱበትን አነጋጋሪ መጽሐፍ አንብቤያለሁ። በዚህ ላይ ከናንተ ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ።
ራጂቭ፦ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ ርእስ ነው።
ራሽድ፦ ለውይይት ያመቸን ዘንድ ከተቻለ ያልካቸውን ነገሮች አንድ በአንድ ብታስቀምጣቸው ጥሩ ይሆናል።
ማይክል፦ መልካም፣ትኩረቴን ይበልጥ የሳበውን እጠቅሳለሁ። ራጂቭም ከመጽሐፉ ውጭ ከርእሱ ጋር ተያያዥነት ያለው ጥያቄ ካለው ማቅረብ ይችላል።
ራሽድ፦ እሽ ቀጥል።
ማይክል፦ መጽሐፉ የእስላም ሸሪዓ ከሮማውያን ሕግ የተቀዳ መሆኑን፣በውስጡ ያሉት አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችም ተመሳሳይነት እንዳላቸው ይጠቅሳል።
ራሽድ፦ መልካም ፈቃዳችሁ ይሁንና ይህ በጣም የቆየና ዛሬ በሚገኙት ብዙኃኑ ኦሪየንታሊስቶች ዘንድ ተቀባይነት የሌለው አባባል ነው። እኔ ራሴ ከታላላቅ ኦሪንታሊስቶች አንዱና የሕግና የእስላማዊ ሸሪዓ ኤክስፐርት የሆኑትን ሩሲያዊውን ሊዮኔድ ሶኪያኒንን በዚህ ጉዳይ ላይ አነጋገሬያለሁ። ቃል በቃል እንዲህ ነበር ያሉኝ፦ ‹‹ዛሬ እስላማዊው ሸሪዓ ከሮማውያን ሕግ የተቀዳ ነው የሚለውን እሳቤ የሚያራምድ ከምዕራባውያን ተመራማሪዎች መካከል አንድም ሰው የለም። ይህ በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ሲሆን፣እሳቤው በአንዳንድ ምዕራባውያን ተመራማሪዎች ዘንድ ይራመድ ነበር። ዛሬ ግን ምዕራባዊው የሕግ እሳቤ ያለ ምንም ገደብ እሰላማዊው ሸሪዓ ራሱን የቻለ የሕግ ሥርዓት መሆኑንና የሮማዊው ሕግ አሻራ የሌለበት መሆኑን ሙሉ በሙሉ አምኖ ይቀበላል።››
ይህ አንደኛው ነው፤ሁለተኛው ነጥብ የእስላማዊ ሕግ ምንጭ ከተቀሩት ሌሎች ሕጎች ሙሉ በሙሉ የተለየ መሆኑ ነው። ደጋግሜ እንዳልኳችሁ እስላም የተሟላና ሁሉ አቀፍ የሆነ ሥርዓት ነው። የሕግ ሥርዓቱንም በተመለከተ የተፈጠሩበትን ዓላማ እውን ለማድረግ በፍጥረታቱ ላይ ከሚኖረው የፈጣሪ መብትና በግዛቱ ውስጥ የሚኖሩ ተገዥዎች ከመሆናቸው አንጻር ከትእዛዙ ውጭ እንዳይሆኑ ካለው መብቱ ጋር የተሳሰረ ነው። በመሆኑም የእስላም መሰረታዊ የሕግ ምንጭ በቁርኣንና በነቢዩ ﷺ ሱንና የሚወከለው ወሕይ (መለኮታዊ መገለጥ) ነው። ነቢዩ ﷺ የማያነቡና የማይጽፉ ሰው እንደነበሩ ሁላችንም የምናውቀው ነውና በርሳቸው ሁኔታ ላይ ለነበረ ሰው ሕጉን መገልበጥ ቀርቶ መኖሩንም የማወቅ ዕድል በተለይም የተባለው ምንጭ የባዕድ ምንጭ በሚሆንበት ጊዜ ሊኖር እንደማይችል በጣም ግልጽ ነው።
ኦሪየንታሊስቱ ተመራማሪ ዴቪድ ዴ ሳንቲላና በትክክል ያስቀመጠውም ይህንኑ እውነታ ነው፦ ‹‹ሰፍኖ ከቆየው እሳቤ የተነሳ ሁለቱ የምሥራቅና የምዕራብ ]እስላማዊውና ሮማዊው [ሕግ የሚገናኙበትን አንድ ምንጭ ለማግኘት በከንቱ እንለፋለን። እስላማዊው ሕግ ተለይቶ የተወሰነ ገደብና የጸኑ መርሆዎች ያሉት ከመሆኑም በላይ ሃይማኖታዊ ሕግ በመሆኑ ከእኛ እሳቤ ከነአካቴው የሚለይ ነውና ከእኛ ሕጎችና ሥርዓቶች ጋር ማስተሳሰርም ሆነ ወደዚያ ማዛመድ የማይቻል ነው . . ››
በተለያዩ የሕግ ሥርዓቶች መካከል ሊኖር የሚችለውን አንዳንድ ተመሳስሎ በተመለከተ ግን መነሻው፣የሰው ልጆች ችግሮች ተመሳሳይ ከመሆናቸው አኳያ መፍትሔ ማፈላለጊያውም ተመሳሳይ ሊሆን ስለሚችል፣በዚህ ረገድ መሰረቱ ተመሳሳይነት ባላቸው አካባቢዎች ውስጥ ጥቅም ማስገኘትና ችግር ማስወገድ ከሆነ ወይም የሰውን ልጅ ተፈጥሯዊ ጉዳዮች የሚመለከት ተመሳስሎ ሊኖር ይችላል። ይህም ነቢዩ ﷺ ፦ ‹‹ማስረጃ ማቅረብ የከሳሽ ግዴታ ሲሆን መሐላ ደግሞ ያስተባበለ (የተከሳሽ) ሰው ግዴታ ነው።›› እንዳሉት ዓይነት ማለት ነው።
ማይክል፦ ይሁን እንጂ ከእስላም በፊት የነበሩ መለኮታዊ ሃይማኖቶች ከመሆናቸው አንጻር፣እስላማዊው ሕግ ከአይሁድ ወይም ከክርስትና ሕግ ወስዷል የሚል ግምት ሊኖር ይችላል።
ራሽድ፦ በመስኩ አንቱ የተባሉ ታዋቂ ትውልደ ጀርመናዊ ኦሪየንታሊስት ሊቅ ጆዜፍ ሻኸት በተናገሩት ቃል ነው መልስ የምሰጥህ፦ ‹‹እስላማዊ ሸሪዓ ሃይማኖታዊ ሕግ ተብሎ ሊጠራ ለሚችለው የራሱ የሆነ ልዩ መለያ ያለው ተምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል። ይህ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖታዊ ሕግ ሞዴል ተደርገው የሚቆጠሩት የተቀሩት ሁለቱ ቅዱሳን ሕጎች - የአይሁድ ሕግና የቤተክርስቲያን ሕግ - ከታሪክና ከመልክአምድር አኳያ ለእስላማዊው ሸሪዓ የቀረቡ ሲሆኑ፣በይዘታቸው ግን ከእስላማዊው ሕግ ተጨባጭ የሆነ ልዩነት አላቸው። ይህም እስላማዊው ሕግ ከተጠቀሱት ሁለቱ ሕጎች በዓይነት የበዛ ይዘት ያለው በመሆኑና አንድ ገጽታ ብቻ ከመያዝ የራቁ የሕግ ርእሰ ጉዳዮችን ከሃይማኖት አንጻር በጥልቀት በመመልከትና በመመርመር የተገኘ ውጤት በመሆኑ ነው . . ››
ከዚህም አልፎ አንተ ያቀረብከውን ግምት በመጻረር እንዲህ ይላል፦ ‹‹ . . ከሜዲትራኒያን ባሕር ወዲያ ማዶ እስላማዊው ሸሪዓ በሁሉም የሕግ ዘርፎችና ቅርንጫፎች ላይ ጥልቀት ያለው አሻራ አሳርፎ እናገኘዋለን . . እስላማዊው ሕግ በሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮች የእስላም መቻቻልና ገርነቱ አቅፎአቸው በእስላማዊው መንግስት ስር በኖሩት አይሁዶችና ክርስቲያኖች ሕጎች ላይ የራሱን አሻራ አሳርፏል . . የምሥራቅ ቤተክርስቲያን ሁለቱ ትላልቅ ቅርንጫፎች ማለትም ያቆባውያንና ነስጦራውያን ነጻ ሆነው ከእስላማዊው ሸሪዓ መርሆዎችን ለመቅዳት ያላቅማሙ መሆናቸው ጥርጥር የለውም። የተዋሷቸው ነገሮችም አንድ ሰው በሙስሊሙ ዳኛ (ቃዲ) ምልከታ ውስጥ የሚገቡ ናቸው ብሎ ከሚገምታቸው ርእሰ ጉዳዮች ሁሉ ነው . . ››
ራጂቭ፦ እናም በእስላማዊው ሸሪዓና በሌሎች ሕጎች መካከል ያሉትን ልዩነቶች ትነግረናለህ ብለን እንጠብቃለን።
ራሽድ፦ አንድ የተለየ የሕግ ሥርዓትን ጠቅሰህ ለንጽጽር አላቀረብክምና ልዩነቶቹን መንገር ያስቸግራል። አጠቃላዩን የእስላማዊ ሕግ መለያ ባሕርያት እጠቅስልህና አንተ ከሌሎቹ ጋር ታነጻጽራለህ።
ራጂቭ፦ ይሁን።
ራሽድ፦ ዋነኞቹ የእስላማዊ ሸሪዓ መለያ ባሕርያት የሚከተሉት ናቸው፦
1) የምንጩ መለኮታዊነት - እንደ ጠቀስኩላችሁ ሕጉ ከሁለት መሰረታዊ ምንጮች ማለትም ከቅዱስ ቁርኣንና ከነቢዩ ﷺ ሱንና የተቀዳ ነው። በዚህ ውስጥ የሰው ልጅ ሚና ከመሰረቶቹ ሕግጋትና ድንጋጌዎችን በማመንጨትና በመቅረጽ፣ከተጨባጩ የሕይወት ሁኔታ ጋር በማጣጣም የመተግበር ሚና ነው። ከምንጩ መለኮታዊነት መገለጫዎች አንደኛው ሕግጋቱ ሰዎችን ከፈጣሪ አምላካቸው ጋር ማስተሳሰርን ዒላማ የሚያደርጉ መሆናቸው ነው።
2) ጽናትና ልስላሴን የሚያጣምር መሆኑ - የጽናቱ ገጽታ በመሰረታዊ መርሆዎቹ፣በሁለንተናዊ ጎኖቹና ሊለወጡ ሊቀየሩም ሆነ መሻሻል ሊደረግባቸው በማይችሉ ፍጹም በጸኑ ሕጎች የሚወከል ሲሆን፣ይህም በሌሎች የሕግ ሥርዓቶች ውስጥ ከመቅለጥና የቦይ ውሃ ከመሆን ጠብቆ የሚያቆየው ነው። ልስላሴው ደግሞ እንደ ሁኔታው ድንጋጌዎችን የማመንጨት አቅም የሚሰጠውና ዘመኑ ለሚጠይቃቸው አዳዲስ ደራሽ ጉዳዮች ሁሉ ምላሽ መስጠት በሚያስችሉት ቅርንጫፎቹ፣ንኡሳን ክፍሎቹና ግምቶቹ የሚገለጽ ነው።
3) ከጊዜ ከሰፍራ ከሰውና ከድንጋጌ አኳያ ሁለንተናዊ መሆኑ - ከዘመን አንጻር በሁሉም ዘመናት ተፈጻሚነት ያለው ሸሪዓ መሆኑ ሲሆን፣ከስፍራ አኳያ ተፈጻሚነቱና አመቺነቱ በወሰን ክልልና በመልክአ ምድራዊ ድንበር የማይገደብ መሆኑ ነው። ከሰው አኳያ ሕጎቹ ለመላው የሰው ዘር የመጣ ዩኒቨርሳል ሸሪዓ መሆኑን ያመለክታል። ከብያኔና ከድንጋጌ አንጻር ደግሞ ሁሉን አቀፍና ሁሉንም የሕይወት ፈርጆች የሚያጠቃልል፣ጽንስ ሆኖ፣ሕጻን ሆኖ፣ወጣት ሆኖ፣ጎልማሳና አረጋዊ ሆኖም በሁሉም እርከኖች ከሰው ልጅ ጋር መሆኑን ያመለክታል። ሲሞትም ያከብረዋል። በዚህም የሰው ልጅ ከፈጣሪው ከገዛ ራሱና ከሌሎች ጋር ያሉትን ግንኙነትቶች ሁሉ ይገዛል።
4) ተጨባጭነቱ - ድንጋጌዎች ሲወጡ የሰዎችን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባትና በሚያደርግላቸው አያያዝ የሚገለጽ ነው። ሕጎቹን ሲቀርጽ የሰው ልጆችን አካላዊ፣ መንፈሳዊ፣ሕሊናዊ፣ግላዊና ማሕበራዊ . . ሁለንተናዊ ጎኖችን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባል። ሲተገበርም የግለሰቦችንና የማህበረሰቦችን አቅም ችላ አይልም።
5) ሚዘናዊነቱና መካከለኛነቱ - ይህ ደግሞ የሸሪዓ ሕግጋት ሁሌም ከተነጻጻሪ ነገሮች ሁሉ ከመሀል በመሆን የሚዘናዊነትን ነጥቦች የሚጠብቁ በመሆናቸው የሚገለጽ ሲሆን፣ይህም ጥንካሬና ዘላቂነትን ያላብሳቸዋል። ለምሳሌ ያህል ሸሪዓው የግል ሀብት ባለቤትነትን በሚመለከት በኮሙኒዝም ዘንድ እንዳለው ሙሉ በሙሉ ውድቅ ከማድረግም ሆነ በካፐታሊዝም ዘንድ እንዳለው በምንም ያልተገደበ ልቅ ከመሆን በተለየ ሚዘናዊ በሆነ ሁኔታ በሕግ የሚመራ የግል ንብረት ባለቤትነት መብትን ይደነግጋል። በፈሪነትና በጀብደኝነት መካከል ጀግንነትን ያበረታታል። በንፉግነትና በብኩንነት መካከል የሆነውን ለጋስነት ያዛል . . እንዲህ እያለም ይቀጥላል።
6) የዛሬውን ሕይወት ቅጣት ከወዲያኛው ሕይወት ቅጣት ጋር የሚያጣምር መሆኑ - ሸሪዓው ሕጎቹን በሚጥሱት ላይ በዛሬው ሕይወት ቅጣት በመደንገግ ረገድ ከተቀሩት የሕግ ሥርዓቶች ጋር ይስማማል። ሰው ሰራሽ ሕጎች አጥፊውን በወዲያኛው ዘላለማዊ ሕይወቱ የማስቀጣት አቅም የሌላቸው ሲሆን፣የሸሪዓ ሕግ ግን አጥፊዎችን በወዲያኛው ዓለም ቅጣትና ሲቃይ ያስጠነቅቃል፤በዚህም ሁለቱንም ቅጣቶች አንድ ላይ ያጣምራል።
7) ለጥቅሞች ትኩረት የሚሰጥ መሆኑና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ከሳይንስ ጋር የማይጋጭ መሆኑ።
ማይክል፦ አንተ ራሽድ ሁሌም በስልትና በብልጠት የሃይማኖትህን ገጽታ ለማሳመር ትጥራለህ።
ራሽድ፦ ወዳጄ ጉዳዩ ለሃይማኖት የመወገን ጉዳይ አይደለም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ታላቁ ጀርመናዊ ባለቅኔ ጎቴህ፦ ‹‹ከእስላማዊ ትምሕርቶች አንጻር በምዕራቡ ዓለም የሚገኘው ሕግ ጎደሎ ነው። እኛ የአውሮፓ ሰዎች ባሉን ግንዛቤዎቻችን ሁሉ ሙሐመድ ከደረሰበት ገና አልደረስንበትም፤የሚቀድመው ማንም አይኖርም።›› ብሎ ሲናገር ምን ትለዋለህ? ጎቴህ እንደዚህ የሚለው እርሱም ሙስሊም ስለሆነ ነው?!
ራጂቭ፦ ከሸሪዓው መለያ ባሕርያት መካከል የጠቀስከው የመጨረሻው ነጥብ ማብራሪያ ያሸዋል።
ራሽድ፦ ሸሪዓ ከሳይንስ ጋር የማይጋጭ ስለመሆኑ አንድ ምሳሌ ልስጥህ። የእስላም ሸሪዓ ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱ ለምግብ የሚታረዱ እንስሳት በተለየ መንገድ እንዲታረዱ የሚደነግግ መሆኑ ነው። እንስሳቱንም በተለዩ ዓይነቶች ብቻ የተወሰኑ ያደርጋል። ለእርዱ መሟላት ያለባቸውን መስፈርትም ያስቀምጣል። እዚህ ላይ የማነሳው ግን የአስተራረዱን መንገድ ብቻ ይሆናል።
እስላማዊው የአስተራረድ መንገድ እንስሳው ሕያው ሆኖ በአንገቱ በኩል ጉሮሮውና የደም ጋኖቹ ከጎን እስከ ጎን አንገቱ ሳይቆረጥ እንዲታረድ ያዛል። ይህም ከእርዱ በኋላ የእንስሳው ጡንቻዎች በነጻ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ሲሆን፣እንቅስቃሴው ከፍተኛ መጠን ያለው ደም ከገላው ወደ ውጭ እንዲፈስ ያደርጋል። እስላማዊ ባልሆነ አስተራረድ ግን እንስሳው የአላህ ስም ሳይወሳበት በተሳሳተ መንገድ በጋዝ በማፈን ወይም በኤሌክትሪክ ንዝረት፣ወይም በጥይት እንዲገደል ይደረጋል። እነዚህ መንገዶች የእንስሳው የጡንቻዎች እንቅስቃሴ እንዳይኖር በማድረግ ደሙ ወደ ውጭ እንዳይፈስ ምክንያት ይሆናሉ። ውስጥ ታምቆ የቀረው ደምም የተለያዩ ጀርሞችና ተዋሕሲያን መፍለቂያ በመሆን ወደመርዛምነት ይለወጥና ሥጋውን ተመጋቢ ይመርዛል። በተጨማሪም እነዚህ የአስተራረድ መንገዶች የእንስሳውን ስቃይ ይጨምራሉ።
ሌላም ልጨምርልህ። ሲታረድ የአላህን ስም ማውሳት አንዱ መስፈርት ነው። ቁሳዊው አመለካከት ግን እንስሳውን ወደ ምግብነት ከመለወጥ ውጭ የሚታየው ሌላ ነገር የለም። እስላም ዘንድ ግን ሁሉም ነገር ከአላህ ﷻ ተውሒድ ጋር የተያያዘ ነው። ሕግጋትና ድንጋጌዎችም፣‹‹አላህ - ዩኒቨርስ - ሰው - መመለሻው›› እንደሚለው የታላላቆቹ ጥያቄዎች ምላሽ ሁሉ ከሃይማኖቱ ሁለንተናዊ ሥርዓት ጋር የተሳሰሩ ናቸው። በዚህ ሁኔታ የሰው ልጅ ከአላህ ﷻ ፍጥረታት አንዱ ከመሆኑ አንጻር በሌላው ፍጡር ላይ ግፍ መፈጸምና ከፈጣሪው ፈቃድ ውጭ ነፍሱን መግደል የለበትም፤ያን የሚያደርገው የራሱን ሕይወት ለማቆየት ቢሆን እንኳ ተገቢ አይሆንም። ከዚህ ስንነሳም ሲያርዱ የአላህን ﷻ ስም ማውሳት (ብስምላህ) ማለት የአላህን ﷻ ኃያልነትና ልዕልናውን ማወጅ ሲሆን፣ሙስሊሙ ይህን ድርጊት የሚፈጽመው ይህን የተፈቀደ (ሐላል) ባደረገለት ፈጣሪው ፈቃድ ብቻ መሆኑንና ሙስሊሙ ለርሱ ፍጹም ተገዥ መሆኑን ለማመልከት ነው።
ማይክል፦ የእስላምን ሸሪዓ በደንብ ማወቅና ምስጢራቱንና ውስጠቱን መረዳት ሰፊ ጥናትና ጥልቅ ምርምር የሚያስፈልግ መሆኑን አምኜ ተቀብያለሁ።