አላህ (ሱ.ወ.) ኣደምን ሲፈጥር መላእኮችን ለኣደም እንዲሰግዱ አዟል፦
{በእርግጥም ፈጠርናችሁ፤ከዚያም ቀረጽናችሁ፤ከዚያም ለመላእክቶች፣ለአዳም ስገዱ አልን፤ወዲያውም ሰገዱ፤ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ሲቀር፣ከሰጋጆቹ አልኾነም።}[አል አዕራፍ፡11]
አላህ (ሱ.ወ.) ሰውን ፈጥሮት አክብሮታል፤በተቀሩት ብዙ ፍጥረታቱ ላይም ብልጫ ሰጥቶታል፦
{የኣደምንም ልጆች በእርግጥ (ከሌላው ፍጡር) አከበርናቸው፤በየብስና በባሕርም አሳፈርናቸው፤ ከመልካሞችም (ሲሳዮች) ሰጠናቸው፤ከፈጠርናቸውም ፍጡሮች በብዙዎቹ ላይ ማብለጥን አበለጥናቸው።}[አል እስራእ፡70]
የሰው ልጅ ከመነሻው ክቡር የሆነ ልዩ ብልጫ የተቸረው ፍጡር ነው። ጌታው ቀጥሎ በተዘረዘሩ ነገሮች ብልጫና ከበሬታ ሰጥቶታል፦
1-በአፈጣጠሩ ክቡርና ብልጫ ያለው መሆኑ፦ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦
{ሰውንም በጣም በአማረ አቋም ላይ ፈጠርነው።}[አል ቲን፡4]
ሲፈጥረው በተክለ ሰውነቱ ሚዘናዊነትና በአወቃቀሩ ቅንጅት ረገድ፣አእምሮና ማሰብን የተቸረ ከመሆኑ አንጻርም፣መናገርንና መስማትንም የታደለ ከመሆኑም አኳያ በአማረና ውብ በሆነ አቋም ፈጥሮታል።
2- የብስና ባሕርም ለርሱ የተገሩ በመደረጋቸው ክቡርና ብልጫ ያለው መሆኑ፦ በዚህ የመግራት ዝርዝር ውስጥ አየርም ይካተታል። ይህም በአንደኛው ለተገለጸው ከበሬታና ብልጫ ማረጋገጫና ማጠናከሪያ ነው። አላህ (ሱ.ወ.) እነዚህን ሁሉ ለሰው ልጅ በመግራት ከተቀሩት ፍጥረታቱ ልዩ ማድረጉ፣ሰብአዊ ፍጡር በዚህ ዓለም ላይ እንደመሪና ንጉሥ መሆኑንና የተቀሩት ፍጥረታት የርሱ ተከታዮች መሆናቸውን ያመለክታል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦
{የኣደምንም ልጆች በእርግጥ (ከሌላው ፍጡር) አከበርናቸው፤በየብስና በባሕርም አሳፈርናቸው፤}[አል እስራእ፡70]
በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ.) በሰማያትና በምድርም ያለውን ሁሉ ለሰው ልጆች የተገሩ መሆናቸውን ተናግሯል፦
{ለናንተም በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ በመላ ከርሱ ሲኾን የገራላችሁ ነው፤በዚህ ለሚያስተነትኑ ሕዝቦች ታምራት አለበት።}[አል ጃሢያህ፡13]
2-መልካም ሲሳይ የተሰጠው መሆኑ፦ አላህ (ሱ.ወ.) የሰው ልጅ የሚስማማውንና የሚመቸውን ሁሉ የመመገብ ግንዛቤ ሰጥቶታል። በምግቦቹ ውስጥም የጠቀሜታቸውን አመላካች አኑሯል። የሰው ልጅ የሚመገባቸውን ምግቦች፣ከለመዱት ውጭ የማይመገቡት የተቀሩት እንስሳት ከሚመገቡት በዓይነት በጣም የበዙ እንዲሆኑ አድርጓል። ይህን ሁሉ በችሮታው የገራለት በመሆኑም ሰውን ክቡር ፍጡር አድርጎታል፦
{(እርሱ) ያ ለናንተ ምድርን ምንጣፍ፣ሰማይንም ጣሪያ ያደረገ ነው፤ከሰማይም (ከደመና) ውሃን ያወረደ፣በርሱም ከፍሬዎች ለናንተ ሲሳይን ያወጣ ነው፤እናንተም (ፈጣሪነቱን) የምታውቁ ስትኾኑ፣ለአላህ ባላንጣዎችን አታድርጉ።}[አል በቀራህ፡22]
3-በብዙዎቹ ፍጥረታቱ ላይ አላህ (ሱ.ወ.) ብልጫ የሰጠው መሆኑ፦ የሰው ልጅ በዚህ መንገድ ላይ ሲጓዝ ክቡርነቱ፣ታላቅነቱ፣ደረጃውና ከተቸረው መለኮታዊ ከበሬታ የሚመነጨውን ቁመናውን (ልኩን) ይገነዘባል። እናም የሰው ልጅ በሕያው ቁስ አካል ዓለም ምንም ያህል ኢምንት ነጥብ አይደለም ማለት ነው . . ምድር ራሷ በዚያ ቁሳዊ ሚዛን ስትለካ አንድ የአቶሚክ ቦንብ በሂሮሺማ እንደተከሰተው በሰከንዶች ውስጥ ሁለት መቶ ሺህ ሰዎችን መቅሰፍ የሚችልባት ተራ ኢምንት ነጥብ እንጂ ሌላ አይደለችም። በእስላም አመለካከት የሰው ልክና ዲካው የሚመነጨው አላህ (ሱ.ወ.) ከፍጥረታቱ ውስጥ ልዩ ካደረገበትና ከተቸረው መለኮታዊ ከበሬታ ነው። ስለ ኣደም አፈጣጠርና መላእኮች ለርሱ መስገዳቸውን፣እብሊስ ለኣደም የመስገድን ትእዛዝ እምቢ በማለቱ ከአላህ እዝነት መባረሩን የሚተርኩ የቁርኣን ምንባቦችን ስንመለከት፣ይህ ሁሉ የዓለም አቀፍ ሰብአዊነትን ሕንጻ ለማነጽ ምን ያህል አስፈላጊ መሰረት እንደሆነ እንገነዘባለን። ከዚህ ለሰው ልጅ ነጻነቱን፣ሰብአዊ ክብሩንና የምርጫዎቹን ዓይነቶች በመላ ከሚያጎናጽፈው ከዚህ የቁርኣን መንገድ ውጭ፣የኃይል ፍላጎት እንዲዘፍቅበት ካደረገበት አረንቋ መውጣት የሰው ልጅ ባልቻለበት ሁኔታ ውስጥ አስፈላጊነቱ ወሳኝ ነው።
በከበሬታና በልዕልና መንገድ ውስጥ የሰውን ልጅ ክብር ማዋረድ፣ማንቋሸሽም ሆነ በሰብአዊ ፍጡር መሳለቅ ትክክለኛ አይደለም፤አይፈቀድምም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦
{እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ወንዶች ከወንዶች አይቀልዱ፤ከነርሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና፤ሴቶችም ከሴቶች (አይሳለቁ)፤ከነሱ የበለጡ ሊኾኑ ይከጀላልና፤ነፍሶቻችሁንም አታነውሩ (ከፊላችሁ ከፊሉን አይዝለፍ)፤በመጥፎ ስሞችም አትጠራሩ፤ከእምነት በኋላ የማመጥ ስም ከፋ፤ያልተጸጸተም ሰው፣እነዚያ እነሱ በዳዮቹ ናቸው።}[አል ሑጁራት፡11]
በሰብኣዊ ከበሬታ በነጩና በጥቁሩ ሰው መካከል፣በቀዩና በብጫው መካከል፣ዐረብ በሆነውና ዐረብ ባልሆነው መካከል፣በዘርና በጎሳ መካከል፣በአገሮች መካከል፣በሀብታምና በድሃ መካከል . . አላህን በመፍራት ደረጃ (በተቅዋ) ካልሆነ በስተቀር ምንም ዓይነት መበላለጥ ፈጽሞ የለም። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦
{እላንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፤እንድትተዋወቁም ጎሣዎችና ነገዶች አደረግናችሁ፤አላህ ዘንድ በላጫችሁ፣በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው፤አላህ ግልጽን ዐዋቂ፣ውስጥንም ዐዋቂ ነው።}[አል ሑጁራት፡13]
የአላህ መልክተኛ እንዲህ ብለዋል፦ { አላህ ወደ ተክለ ሰውነታችሁና ወደ ገንዘቦቻችሁ አይመለከትም፤ነገር ግን ወደ ልቦቻችሁና ወደ ሥራዎቻችሁ ይመለከታል።} [በሙስሊም የተዘገበ]
በመሆኑም የሰው ልጅ የሚኖረው ከበሬታና ልዕልና ይህን መንገድ በመያዝና በመከተል ደረጃው መጠን ይሆናል፦
{ማሸነፍን የሚፈልግ የኾነ ሰው፣[ሁሉም] አሸናፊነት ለአላህ ብቻ ነው፤}[ፋጢር፡10]
የሚድርስበት ውርደትም ለአላህ ተገዥ የሆኑ ባሕርያትን ሁሉ ከሚያካትተው ከዚህ መንገድ በሚኖረው ርቀት መጠን ይሆናል። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦
{አላህ በሰማያት ያለው ሁሉ፣በምድርም ያለው ሁሉ፣ፀሐይና ጨረቃም፣ከዋክብትም፣ተራሮችም፣ዛፎችም፣ተንቀሳቃሾችም፣ከሰዎች ብዙዎችም፣ለርሱ የሚሰግዱለት መኾኑን አታውቁምን? ብዙውም በርሱ ላይ ቅጣት ተረጋገጠበት፤አላህ የሚያዋርደውም ሰው ለርሱ ምንም አክባሪ የለውም፤አላህ የሻውን ይሠራልና።}[አል ሐጅ፡18]
አላህ (ሱ.ወ.) የሰውን ልጅ ክቡር ያደረገው ቢሆንም፣ብዙዎቹ ሰዎች ግን የውርደትን መንገድ መርጠዋል፦
{አላህ የሚያዋርደውም ሰው ለርሱ ምንም አክባሪ የለውም፤}[አል ሐጅ፡18]
አላህ (ሱ.ወ.) በቸርነቱ ለዚህ ፍጡር የቸረውን ከበሬታ በሚጻረር መልኩ፣የሰው ልጆችን እንደ እንስሳት ወይም ግዑዝ መሳሪያዎች፣እንደ የገንዘብ አኃዞች ወይም ሌሎች ቁሳቁሶች አድርገው መመልከትን መርጠዋል።
የሰው ልጅ ከበሬታ ሰው ከመሆኑ ብቻ የሚመነጭ ነው። እስላም በሁለቱ ጾታዎቹ መካከል ፍልሚያ አይፈጥርምና ከበሬታው ወንዱ በሴቷ ላይ፣ወይም ሴቷ በወንዱ ላይ በተለይ የሚይዙት ከበሬታና ብልጫ አይደለም። ሰዎች ወንድም ሴትም ከአንዲት ነፍስ የተፈጠሩ ናቸውና። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦
{እላንተ ሰዎች ሆይ! ያንን ከአንዲት ነፍስ (ከአዳም) የፈጠራችሁን፣ከርስዋም መቀናጆዋን (ሔዋንን) የፈጠረውን፣ከነርሱም ብዙ ወንዶችንና ሴቶችን የበተነውን ጌታችሁን ፍሩ። ያንንም በርሱ የምትጠየቁበትን አላህንና ዝምድናዎቻችሁንም (ከመቁረጥ) ተጠንቀቁ፤አላህ በእናንተ ላይ ተጠባባቂ ነውና።}[አል ኒሳእ፡1]
ክብርና ልዕልናን የፈለገ ሰው የክብርና የልዕልናን መንገድ ይዞ ይጓዝ። አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፦
{ኃይል ሁሉ በሙሉ፣የአላህ ብቻ ነውና፤}[ዩኑስ፡65]