ራሽድና ማይክል ምሳቸውን በልተው አበቁ . . ራሽድ አንጋጦ እያየ ለወዳጁ እንዲህ አለ፦
ወዳጄ ማይክል፣የሂስ ፍላፃ ነው ያዘነብክብኝ፣የኔን ስልጣኔም ተከሳሽ አድርገሃል።
ማይክል፦ ወዳጄ፣የተሰነዘረ ፍላፃም ሆነ የቀረበ ምንም ውንጀላ የለም። ወደ እውነት ለመድረስ የሚያግዘን ገንቢ ሂስ እንጂ ሌላ አይደለም። በነዚህ ውይይቶችና በቀረቡ ማብራሪያዎች አማካይነት ወደ እውነታው ለመድረስ ረዥም መንገድ የሄድን ይመስለኛል። በተጨማሪም በሆደ ሰፊነትና በክፍት አእምሮ ነው ያስተናገድከኝ። ወዳጄ በቅድሙ አነጋገሬ አስቀይሜህ ይሆን?
ራሽድ፦ የለም፣ፈጽሞ አላስቀየምከኝም። የተሟላ ምስል ለመፍጠር ነገሮችን በሁሉም ገጽታዎቻቸው ማቅረብ የግድ ነው ማለት ፈልጌ ነው። ምስሉን የተሟላ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል በኛ ስልጣኔና በናንተ ስልጣኔ ውስጥ ያለውን የሴቶች ሁኔታ ማነጻጸርና ማወዳደር አንዱ ነው። የሴቶችን ጉዳይ አስመልክተን ቀደም ሲል ያደረግነው ውይይት ጉዳዩ በእስላማዊው ስልጣኔ ውስጥ እንዴት እንደሚታይ እንድናውቅ የማይናቅ ማብራሪያ ሰጥቶናል ብዬ አስባለሁ። አሁን የቀረን ጉዳዩን ከናንተ ስልጣኔ አንጻር መመልከት ነው።
ማይክል (እየሳቀ)፦ ይኸውና ደረቴን ለትችት ጦር ክፍት አድርጌ በሬንም ለሂስ ወለል አድርጌ ከፍቻለሁ።
ራሽድ (ፈገግ ብሎ)፦ ለጦርነት ለምን እንፋጠጣለን? በመካከላችን ያሉ የወል ጉዳዮች፣አንተም እንዳልከው የውይይት ግንኙነቱ ወደ እውነት ለመድረስ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ግንኙነት እንዲሆን ይፈቅዱልናል።
ማይክል፦ ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ። ከየት መጀመር ትፈልጋለህ?
ራሽድ፦ መጀመሪያ ማየት የሚገባን በስልጣኔው መሰረታዊ መርሆዎች ውስጥ ሴቶች የሚይዙትን ስፍራ ነው።
ማይክል፦ ለሴቶች የሚኖረው እይታና የሚሰጣቸው አያያዝ እንደ እያንዳንዱ ግለሰብ አመለካከት ይለያያል። ምዘናውም እንደ ግለሰቦቹ አስተዳደግ፣እንደ ባህላቸውና እንደ ግንዛቤያቸው ይለያያል። እዚህ ላይ ጉዳዩ ሴት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ወይም በዚያኛው እሳቤ ዘንድ ያላትን ስፍራ የሚመለከት አይደለም።
ራሽድ፦ ይህ እውነት ነው። ይሁን እንጂ የዚህን ግለሰብ ግንዛቤ የመሰረቱ፣እሴቶቹን የቀረጹና በአመለካከቱና በእሳቤው ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ መንደርደሪያ መርሆዎችን ችላ ማለት ግን አንችልም። መንደርደሪያ መርሆዎች ስል ግን የሚጠቀሱ መጽሐፎችን ወይም ሳይንሳዊ ዋቢዎችን ብቻ ሳይሆን፣በግለሰቡ ንቃተ ሕሊና እና በማንነቱ ቀረፃ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድረውን ሁሉ ማለቴ ነው። ከነዚህ የመንደርደሪያ ዋቢዎች መካከል አንዳንድ ሕዝባዊ ትውፊት፣ስነቃልና ተረት ሲገኙ፣በተጨማሪም ከወል ስውር አእምሮ ክምችት ወደ ግለሰብ ስውር አእምሮ የሚገቡ ጥበበ ቃላትና ምሳሌዎችም ይኖራሉ። የመንደርደሪያ መርሆዎችና የርእዮተ ዓለም መሰረቶች ከዚህ ግንዛቤ አኳያ በተራቸው በአስተዳደግና በእነጻ ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ።
ማይክል፦ የሴትን ስፍራና ለርሷ ያለውን እሳቤ በሚመለከት ቅዳሳን መጻሕፍት ብዙ አይለያዩም የሚል እምነት አለኝ። በዚህ ረገድ በኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው በናንተ ቁርኣን ውስጥ ካለው ጋር ብዙ ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን፣ይህም ከወንድ ጎድን የተፈጠረች፣ለመጀመሪያው ኃጢአትና ከገነት ለመውጣት ምክንያት መሆኗንና የምትይዘውን ማህበራዊ ስፍራና ኃላፊነት የሚያጠቃልል ነው።
ራሽድ፦ በዚህ አገላለጽ አንዳንድ ይዘቶች ላይ ከአንተ እለያለሁ። የመጀመሪያውን ኃጢአትና የኣደምና የሔዋንን ከጀነት መውጣት ጥያቄን በሚመለከት ቅዱስ ቁርኣን ከናንተ መጽሐፍ ቅዱስ ይለያል። ሰይጣን ኣደምን በማሳሳቱ ቁርኣን ውስጥ ሔዋን ተጠያቂ አይደለችም፤በመሆኑም ከገነት ለመውጣትም ሴት ልጅ ተጠያቂ አይደለችም።
መጽሐፍ ቅዱስ ለሴቶች ያለውን እይታ በተመለከተ እናት ሴት ልጅ ስትወልድ የርክሰቷ ጊዜ የወንዱ እጥፍ እንደሚሆን ሲገልጽ የሚከተለውን ወንጌል ውስጥ እናገኛለን፦ ‹‹ሴት ብታረግዝ ወንድ ልጅም ብትወልድ፣ሰባት ቀን ያህል የረከሰች ናት፤እንደ ህመምዋ መርገም ወራት ትረክሳለች። . . ከደምዋም እስክትነጻ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቀመጥ፤ . . ሴት ልጅም ብትወልድ እንደ መርገምዋ ወራት ሁለት ሳምንት ያህል የረከሰች ናት፤ከደምዋም እስክትነጻ ድረስ ስድሳ ስድስት ቀን ትቀመጥ።›› (ዘሌዋ.12፣1-5)
ከክርስትና አመለካከት አኳያ ሴቶች ሕብረተሰቡ ውስጥ መከተል የሚገባቸውን ስነምግባር በተመለከተ፣ቤተክርስቲያን ውስጥ አፋቸውን መክፈት የማይፈቀድላቸው መሆኑን እንረዳለን። አዲስ ኪዳን እንዲህ ይላል፦ ‹‹ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ፤ሕግ ደግሞ እንደሚል እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውምና። ለሴት በማኅበር መካከል መናገር ነውር ነውና፣ምንም ሊማሩ ቢወዱ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ።›› (ቆሮንቶስ114፣34)። ይህ ሁሉ ቁርኣን ውስጥ ተነጻጻሪ የለውም።
ማይክል፦ ከግሪክና ከሮማውያን ስልጣኔ ስረ መሰረቶች ጋር ከላስተሳስረንና የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ የተሐድሶ ንቅናቄ ያሳደረበትን ተጽእኖ ግምት ውስጥ ካላስገባን በኛ ሕብረተሰብ ውስጥ የተፈጠረውን ዕድገትና ለውጥ መረዳት አይቻልም። በተጨማሪም የዘመነ ህዳሴ አስተሳሰቦች ተጽእኖ፣የፈረንሳይ አብዮት ያስከተለውን ተጽእኖና በእንዱስትሪ አብዮቱ ዘመን የተፈጠሩትን ለውጦች ግምት ውስጥ ማስገባትም የግድ ነው።
ራሽድ፦ የግሪክንና የሮማውያንን ስልጣኔ ካነሳህ ዘንዳ፣አሁን ለአስረጅነት በምናነሳው ዘመንና በዘመናዊው ስልጣኔ ዘንድ ጭምር የሴቶችን ጉዳይ በሚመለከት ትልቅ መደናበር ነው ያለው። የግሪካዊቱን ሴት ታሪክ ስናገላብጥ ነጻነትና ማህበራዊ ክብርን የተነፈገች ሆና እናገኛለን። ሰብአዊነቷን ተክዶ የሚሸጥና የሚገዛ እንስሳ አድርገው ይመለከቷት ነበር። በምንም ነገር ላይ የማዘዝ መብት ነስተዋት በሕግ የውርስ ድርሻ እንዳይኖራት ያደርጉ ነበር። የግሪክ ስልጣኔ መራመድና ማደግ ሲጀምር በግሪክ ሴቶች ሁኔታ ላይ ፈጣን ስርነቀል ለውጥ መከሰቱ ሴቶች በአደባባይ መታየትና ከወንዶች ጋር መቀላቀል ጀመሩ። ይህም በተራው ጋጠወጥነትና ዝሙት እንዲስፋፋ አደረገ። የዘማውያት መሸታ ቤቶችም የፖለቲካና የስነጽሑፍ ማእከሎች ተደርገው ተወሰዱ። በስነ ጥበብ ስም እርቃናቸውን ለሚታዩ ሴቶች ቅርጾች ተጠረቡ።
ከአንዳንድ ዝርዝር ልዩነቶች በስተቀር የሮማውያኑ ስልጣኔ ለሴት ልጅ ያለው አመለካከት በይዘቱ ከዚህ ብዙም የተለየ አልነበረም። ሴቷን በንቀትና በበታችነት ዓይን ሲመለከታት እንዳሻው ሊያደርጋት መብት ካለው ወንድ በደረጃ ያነሰች ፍጡር አድርጎ ይወስዳታል። የሮማውያን ሕግ በተለያዩ የሕይወቷ እርከኖች አብዛኛውን ሰብአዊ መብቶቿን ይነፍጋታል። ከዚያም ሮማውያን በሴቶች ላይ ባላቸው አመለካከት ላይ ለውጥ መከሰት ጀመረ። ለውጡ ቀጥሎ ሥርዓታቸውን፣ቤተሰብን፣ጋብቻንና ፍችን የሚመለከቱ ሕጎቻቸውን ያካተተ ለውጥ ሆነ። ነገሮች ሙሉ በሙሉ ተገለባበጡና ጋብቻ ለሮማውያን ትርጉም የለሽ ሆነ። ሴት የተሟላ የውርስና የስልጣን መብት ባለቤት ሆነች። ከዚያም በወንድና በሴት መካከል ባሉትና ከሕጋዊ ጋብቻ ውጭ የሆኑ ግንኙነቶችንና ትስስሮችን በተመለከተ አመለካከታቸው ተለወጠ።
ማይክል፦ እኔም ልጨምርልህ። በአጠቃላይ አነጋገር በግሪክና በሮማውያን ስልጣኔዎችና አውሮፓ ወደ ክርስትና ከገባች በኋላ ቤተክርስቲያን ሴቶችን አስመልክታ በያዘችው አመለካከት መካከል አንዱ በሌላው ላይ ተጽእኖ የማሳደር መስተጋቢራዊ ሁኔታ በመፈጠሩ፣የሃይማኖት መሪዎች ለሴቶች ያላቸው እይታ በኖሩበት ተጨባጭ ሁኔታ ተጽእኖ ስር ሊውል ችሏል።
ራሽድ፦ ልክ ነህ፤የመጀመሪዎቹ የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች በሮማውያኑ ማህበረሰብ ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን ዝሙትና ጋጠ ወጥነት፣በአስከፊ ሁኔታ የዘቀጠውን ሞራላዊ ስነምግባር . . ለዚህ ሁሉ ሴትዋን ተጠያቂ አድርገው ወሰዱ። ሴት የሰይጣን መግቢያ በር መሆኗንና የሰይጣን የማሳሳቻ መሳሪያ በመሆኑ በውበቷ ልታፍርበት እንደሚገባም አወጁ . . በዚህ መልኩም የምዕራባውያኑ ሴቶችን በንቀት የማየትና መብቶቻቸውን የመንፈግ ሁኔታ በመካከለኞቹ ክፍለ ዘመናት እንደሰፈነ ቀጠለ። ሌላው ቀርቶ ሴት ልጅ የተሻለ ማህበራዊ ስፍራ አግኝታለች ተብሎ በሚገመተው በአርበኝነትና በፈረሰኝነት ዘመን እንኳ ያለ ባልዋ ፈቃድ በገዛ ሀብቷና ንብረቷ ላይ የማዘዝ ስልጣን ተነፍጋ ኖራለች።
ማይክል፦ ግና፣ወዳጄ ውይይታችን ወደ ታሪክ ክፍለ ጊዜነት የተለወጠ አይመስልህም?! ዛሬ ወደምንኖርበት ዘመን ወዳደረሱን የመጀመሪያዎቹ ሽግግሮች ለመድረስ ይህን ዘመን መዝለል እንችላለን። የሕዳሴውን ዘመን፣ከዚያም የፈረንሳይን አብዮትና ከዚያ የሚቀጥለውን ዘመን ማለቴ ነው።
ራሽድ፦ የነገሮችን ስረ መሰረት መመርመር እንጂ የታሪክ ትምህርት አይደለም። አንተ ታሪክ ናቸው በምትላቸው በነዚህ አቋሞችና አመለካከቶች፣አንዳንድ የገጽታ ልዩነቶች ቢኖሩም ዛሬ በምዕራቡ ዓለም ሴት ልጅ በምትኖርበት ተጨባጭ ሁኔታ መካከል ጥብቅ ተያያዥነት መኖሩን ነው የማስተውለው።
በነዚህ የታሪክ እውነታዎችና በምዕራቡ ዓለም በሚታየው የሴቶች መብት ይዘትና አካሄድ መካከል ተመሳሳይነት መኖሩን አታስተውልም?!
ማይክል፦ እንዴት ያሉትን ማለትህ ነው?
ራሽድ፦ ሴትን የመዝናኛና የእርካታ ሸቀጥ አድርገው መጠቀምን የመሳሰለውን ማለቴ ነው። በሁሉም መስክ ከወንድ ጋር እኩል መሆኗን የሚደነግጉ ሕጎች ሲወጡና መብቶቿ የተረጋገጡላት አድርጋ ስትገምት፣ሳታስበው በብዙ ጉዳዮች ላይ የወንዶች መጫወቻ አሻንጉሊት እንደተደረገች ገባት። ለምሳሌ ያህል በቤተሰብ ስም አጠራርና በገንዘብ ነክ ጉዳዮችም ሕልውናዋ ተፍቆ የባልዋ ጥገኛ መደረጓ አንዱ ነው። በገንዘብ ነክ መብቷ ላይ የተጣለው ገደብ በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎች ላይ እንጂ አልተነሳላትም ነበር።
ማይክል፦ ይሁን እንጂ ሴት ልጅ በመጨረሻ መብቷን ተጎናጽፋለች። በተለያዩ የስልጣን ቦታዎች መሾምን ጨምሮ በሁሉም መስኮች ከወንድ ጋር እኩል ተደርጋለች።
ራሽድ፦ የሴት ልጅ ጭቆና እና የመብት ጥሰት በምዕራቡ ዓለም በተወሰነ ደረጃ ወይም በንድፈ ሀሳብ አንዳንድ ሕጎችንና መመሪያዎችን በማውጣት ቆሟል ቢባልም፣የጭቆናው ስም ወይም ምክንያት ቢለዋወጥም፣በተግባር ግን ዛሬም ድረስ በስፋት ቀጥሏል። በዚህ እንቅስቃሴ ስም ወንዶች ሴቶችን ለገንዘብ መሰብሰቢያነት፣ለመደሰቻነትና ለመገልገያነት ይጠቀማሉ። በዚህም በመዝናኛና በጭፈራ ቦታዎች የደንበኞችን ፍላጎት ወደሚያረካ ሸቀጥነት ተለውጣለች፤ገቢ የሚያስገኝ ዕቃ ተደርጋለች። ይህ ለሴት ልጅ ክብርና ለሰብእናዋ የመጨረሻው ውርደት ነው። በዚህ የተነሳ ሴቶች በብዙ አገሮች ውስጥ ሴቷን በንግድ ማስታውቂያነት መጠቀም እንዲቆም የሚጠይቁ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ማካሄድ ጀምረዋል።
ስዊድናዊቱ ዳኛ ብርጊት አውፍ ሃሀር የሴቶችን ነጻነትና እኩልነት አስመልከታ እንዲህ ትላለች፦ ‹‹ስዊድናዊቱ ሴት ግዙፉን ቅዠት - ለሴት ልጅ የተሰጠውን ነጻነት ማለቷ ነው - አስደንጋጭ በሆነ ውድ ዋጋ በእውነተኛው ደስተኝነት የለወጠች መሆኗን የተረዳችው በድንገት ነበር።››
በምዕራብ አገሮች ያለውን የሴቶች ሁኔታ አስመልክቶ ከአውሮፓ ኮሚሽን የወጣው ዘገባ፣የሴት ልጅ ነጻነት ጥሪና ሁሉም መብቶቿ ተከብረውላታል መባሉ ከእውነታ ጋር ያልተዛመደ ትርጉም የለሽ ባዶ መፈክር እንዴት እንደሆነ ይገልጻል። ዘገባው እንዳመለከተው የአውሮፓ ኩባንያዎች ሴቶች ከፍተኛውን የአመራር ቦታ እንዳይይዙ የሚያደርገውን የቅዠት ግድግዳ ለማፍረስ በቂ ጥረት አያደርጉም።
የአውሮፓ ኮሚሽን የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር የሆኑት ኣና ዲያሞንት ፖሎ ፦ ‹‹የንግድና ቢዝነስ ዓለሙ በሁለቱ ጾታዎች መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ያሳያል። አውሮፓ ውስጥ በፐብሊክ ሴክተሩ ሴቶች ከ20% እስከ 30% ያለውን የመንግስትና የአመራር ከፍተኛ ቦታዎች የያዙ ሲሆን፣በግል ኩባንያዎች ውስጥ ያላቸው የከፍተኛ ሥራዎች ድርሻ በፈረንሳይ ከ2% አይበልጥም፤በጀርመን ከ3% አይበልጥም፣በእንግሊዝ ደግሞ ከ 6.3% የማይበልጥ ሲሆን በባንኮች ውስጥ ባሉት ከፍተኛ የሥራ ቦታዎች ያላቸው ድርሻ 5% ብቻ ነው።
ለሴቶች በሚከፈለው ደሞዝና ለወንዶች በሚከፈለው ደሞዝ መካከል፣በተለይም በሥራ አመራር ቦታዎች ላይ ያለው ልዩነት አሁንም አንደቀጠለ መሆኑን ኮሚሽነሯ በአጽንኦት ገልጸው ሴቶች በ16% ከወንዶች ያነሰ ደሞዝ እንደሚከፈላቸው አረጋግጠዋል . . .
ማይክል (በማቋረጥ)፦ ባቡሩ ወደ መጨረሻው ጣቢያ እየገባ ነው . . ሻንጣዎቻችንና እቃዎቻችን አሁን ማሰናዳት ይኖርብናል . . .