ራጂቭ ከወዳጆቹ ጋር እንደተቀላቀለ በቅርቡ ያነሳቸውን ፎቶግራፎች እያሳየ ማብራራት ጀመረ፦
እነዚህ ፎቶዎች አንድ ወዳጄ ባደረገልኝ ግብዣ ቱርክን ስገበኝ ያነሳኋቸው ናቸው። በዚህ ታሪካዊ አገር ያየሁት የስልጣኔ አሻራዎችና ገጽታዎች በጣሙን አስደምሞኛል። ወዳጄ በአገሩ ስለሚገኙት የእስላማዊ ስልጣን ገጽታዎች ያቀረበልኝ መረጃ በአገሬ በሕንድ ካየኋቸው ጋር እንዳነጻጸር አድርጎኛል።
ማይክል፦ እኔ ግን እስላማዊ ስልጣኔን በተመለከተ ሌላ ገጽታውን የሚወክሉ መረጃዎች አሉኝ።
ራሽድ፦ በቅድሚያ የስልጣኔ ጽንሰ ሀሳብ ራሱ ምን እንደሆነ እንወስንና አስፈላጊ ሆኖ ካገኘነው እስላማዊውን ስልጣኔ ገምግመን እንመዝን የሚል ሀሳብ አለኝ።
ማይክል፦ በጽንሰ ሀሳቡ ላይ የተስማማን ይመስለኛል!
ራሽድ፦ ችግር የለውም፤መጀመሪያ የጽንሰ ሀሳቡን ምንነት ለይተን እናስቀምጥና በውል ከተስማማንበት ከዚያ መንደርር እንችላለን።
ማይክል፦ ስልጣኔ አንድ ሕብረተሰብ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ፈጠራዎቹንና እድገቱን የሚገልጽበት የሰው ልጆች ቁሳዊና ርእዮታዊ እንቅስቃሴ ውጤት ነው።
ራጂቭ፦ ማይክል በተናገረው ላይ ጥቂት ማብራሪያ ልጨምር። ስልጣኔ የሰው ልጅ ባህላዊ ምርቱን እንዲያሳድግ የሚረዳ ማሕበረሰባዊ ሥርዓት ሲሆን፣ከአራት ነገሮች ይመሰረታል። እነሱም ኢኮኖሚያዊ ሀብት፣ፖለቲካዊ ሥርዓት፣ስነምግባራዊ ልማዶችና ሳይንስና ስነጥበብን የሚከተል መሆን ናቸው።
ስልጣኔ የሚቆመው በመጀመሪያ ደረጃ በሳይንሳዊና ቴክኒካዊ ምርምርና በቁሳዊ ጥበብ ላይ ሲሆን፣ሳይንሳዊ ጎኑ በቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና በሰብአዊ ሳይንስ ይወከላል . . ቴክኒካዊ ጥበባዊ ጎኑ ደግሞ በኪነ ሕንጻ በቀረጻና ለእድገት አስተዋጽኦ በሚኖራቸው ጥበቦች ይወከላል። እናም ሳይንስና ጥበብ ማንኛውንም ስልጣኔ የሚመሩ ሁለት የማይነጣጠሉ ግብአቶች ናቸው።
ራሽድ፦ መጀመሪያ ወዳጄ ማይክል በተናገረው ላይ አስተያየት ልስጥ። በጽንሰ ሀሳቡ ምንነት ላይ ከተስማማን ስልጣኔ ከሁሉም በፊት የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ውጤት መሆኑን አስምሮ ማለፍ ግድ ይላል። ከዚህ ስንነሳ ደግሞ የሰብአዊነት ግብአቶችን አንዱንም ችላ ሳንል ሁሉንም ገጽታዎቻቸውን አስተውለን መመልከት ይኖርብናል። ይህን ካላደረግን ግን ስልጣኔው ጎደሎ ወይም ጭራሹኑ ስልጣኔ ሊባል የማችል ይሆናል . . ይኸ አንደኛው ነው።
ሁለተኛው - የስልጣኔ መገለጫዎችን በተመለከተ ሕብረተሰቡ የተመሰረተባቸው እሴቶች ነጸብራቅ ከመሆናቸው አንጻር ከሕብረተሰብ ሕብረተሰብ ሊለያዩ ይችላሉ። በመሆኑም እነዚህ እሴቶች ትክክል ወይም ስህተት መሆን አለመሆናቸው፣ከሰው ልጅ ሰብአዊነትት ጋር የሚስማሙ መሆን አለመሆናቸው፣ከሚኖርበት አካባቢ ጋር የሚጣጣሙ መሆን አለመሆናቸው፣ለአንድ ስልጣኔ በጎነት ወይም መጥፎነት . . መለኪያ ሚዛን ነው። ይህም በተለያዩ ስልጣኔዎች መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነትና በተለይም የሰው ልጆች በዘመናዊው የምዕራብ ስልጣኔ ውስጥ የሚመሩትን የመከራና የሰቆቃ ሕይወት በግልጽ የሚያሳየን ነው።
ማይክል፦ ራሽድ የእስላማዊውን ስልጣኔ የጨፈገጉ ጎኖች አንስተን እንዳንነጋገርባቸው እየሸሸ ይመስለኛል።
ራጂቭ፦ አባባልህ የእስላማዊ ስልጣኔ አበይት ባሕርያትንና ከሌሎች ስልጣኔዎች የሚለይባቸውን ገጽታዎች ይነግረን ዘንድ ለራሽድ ጥያቄ እንድናቀርብ ያደርገናል።
ራሽድ፦ መልካም፤እስላማዊ ስልጣኔ እስላማዊ እሳቤ ስለ ሰው ልጅ፣ስለ ዩኒቨርስና ስለ ሕይወት ባለው ግንዛቤ ላይ ይመሰረታል። አበይት መለያ ባሕርያቱን እጠቅስላችኋለሁ። ግና እነዚህን ባሕርያት በዘመናዊው ምዕራባዊ ስልጣኔ ውስጥ ካሉት መሰሎቻቸው ጋር እያነጻጸርኩ እንዳቀርባቸው ፍቀዱልኝ።
የእስላማዊ ስልጣኔ አበይት መለያ ባሕርያት በሚከተሉት ውስጥ ይጠቃለላል፦
•የዚህ ስልጣኔ መሰረት በሆነው እስላማዊ እሳቤ ውስጥ የሰው ልጅ ፈጣሪ ጌታ ያለው፣በዚህ ምድር ላይ ተጠሪነት (ኽላፋ) የተሰጠው፣ለአላህ ﷻ ሕግና ትእዛዛት የታመነ፣ነጻና ምርጫ ያለው ተገዥ የሆነ ፍጡር ነው። ስለዚህም በዚህ የአላህ ﷻ ሕግና መመሪያ ላይ የተንተራሰ መልካም ሥራ እንዲሠራ የታዘዘ ሲሆን፣ፈልጎና አቅዶ በሚፈጽማቸው ነገሮች ሁሉ በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛውም ተጠያቂ ነው።
በዘመናዊው የምዕራብ ስልጣኔ ውስጥ ግን የሰው ልጅ የዩኒቨርስ ጌታ በመሆኑ፣የራሱና የፍጥረተ ዓለሙ ጌታ ከመሆኑ አንጻር እርሱ ራሱ ከሚወስነው ውጭ ምንም የማይገድበው፣ዋነኛ ትከረቱ ከተቀሩት እንስሳት ጋር በሚጋራቸው ቁሳዊ ፍላጎቶቹና እርካታዎቹ ዙሪያ የሚያጠነጥን ፍጡር ነው። በምዕራባዊው ስልጣኔ እይታ የሰው ልጅም እንዲሁ ለከንቱ የተፈጠረ በመሆኑ እርሱ ራሱ ከሚወስነው ማእቀፍ ውጭ ተጠያቂነት የለበትም። በምዕራባውያኑ አመለካከት የሰው ልጅ ዓለማዎች ሁሉ ቅርብና ዓለማዊ የዱንያ ሕይወትን ብቻ የሚመለከቱ ናቸው።
•በእስላማዊ እሳቤ ዩኒቨርስም እንደ ሰው ሁሉ ተገዥና ታዛዥ የሆነ ፍጡር ነው። ይሁን እንጂ ለሰው ልጆች ግልጋሎት የተገራ ነው። ከዚህ በመነሳትም የአላህን ሕግና መመሪያውን የሚከተለው የሰው ልጅ፣ከዚህ ዩኒቨርስ ጋር ይናበባል፣ይጣጣማል፤ከርሱ ጋር በሚኖረው ግንኙነትም ሰላም ይሰማዋል።
የምዕራቡ ስልጣኔ ለዩኒቨርስ ያለው አመለካከት ግን፣በሰውና በፍጥረተ ዓለሙ መካከል ያለው ግንኙነት የመናበብና የመጣጣም ሳይሆን የትግልና የፍጥጫ ግንኙነት ነው በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለዚህም በሁለቱ መካከል የሚካሄደው ፍልሚያ ሁሌም የተፋፋመ ነው።
•በእስላማዊ እሳቤ ሕይወት የሰው ልጅና የዩኒቨርሱ ፈጣሪ ጌታ ንብረት ናት። የዛሬው ሕይወት አሁን ከምናየው እጅግ የገዘፈ የመጪው ሕይወት አንዱ ጣቢያ ሲሆን፣የመጀመሪያው በሁሉም የሰው ልጆች ዓለማዊ ፍጻሜ ያበቃና ቀጣዩ ዘላለማዊ ሕይወት ከሞት በኋላ ይጠብቀናል። የሰው ልጅ ሰውን ዩኒቨርስንና ሕይወትን የፈጠረውን አላህን ﷻ በሚያስደስት መንገድ ይህችን መሬት እንዲያለማና እንዲገነባት ታዟል። ምድራዊ ሕይወት ለወዲያኛው ዘላለማዊ ሕይወቱ የሚያስፈልገውን የሚዘራበት ማሳው ስትሆን፣በዚህች ምድር ላይ ለፈጸማቸው ነገሮች ሁሉ ይጠየቃል፤የሥራውን ዋጋም ከፈጣሪ አምላኩ ያገኛል።
የምዕራቡ ስልጣኔ ግን፣ሕይወትን የሚመለከተው በዚህችው የዱንያ ዓለማዊ በሚወሰን ጠባቧ ጥግ ሲሆን በመጪው ዘላለማዊ የወዲያኛው ሕይወት፣በሠሩት ሥራ መጠየቅ፣መሸለምም ሆነ መቀጣት በመኖሩ አያምንም። በመሆኑም የሰው ልጅ ዕድልና አጋጣሚ በዚህች ዓለም ላይ ብቻ የተወሰነ ነው።
ከዚህ ሁሉ የምንደርስበት ማጠቃለያ የምዕራቡ ስልጣኔ ከእስላማዊው ስልጣኔ ጋር ሊገናኙ የማይችሉና በተቃራኒ ጫፎች ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ነው።
ማይክል፦ ይሁንና ራሽድ በተናገርከው ላይ ሁለት ነጥቦችን እንዳነሳ ፍቀድልኝ፦
አንደኛ - ከምዕራቡ ስልጣኔ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነውን አንድ ጎን የክርስትናን ሃይማኖትና አይሁዳዊነትንም ጭምር ችላ ብለሃል። ለምሳሌ ያህል የምዕራቡ ስልጣኔ ስለ ሕይወት የሚያራምደው እሳቤ በየወዲያኛው ሕይወት፣በሠሩት ሥራ መጠየቅ፣መሸለምም ሆነ መቀጣት በመኖሩ አያምንም ብለሃል። ይህ ግን ስህተት ነው። በእምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ አንዱ ከሌላው የሚለይ ቢሆንም ሁለቱም ሃይማኖቶች በወዲያኛው ሕይወት ያምናሉ።
ሁለተኛ - የነገርከን እስላማዊው ስልጣኔ የቆመባቸውን መሠረቶች ከምዕራባዊው ስልጣኔ ጋር በማነጻጸር ነው። ወዳጃችን ራጂቭ በጠየቀህ መሰረት የእስላማዊውን ስልጣኔ መለያ ባሕርያት አላነሳህም።
ራሽድ፦ በመጀመሪያው አስተያየትህ ከአንተ እለያለሁ። አንድ ስልጣኔ በሚቆምባቸው መሠረቶችና ይህን ስልጣኔ ባመነጨው ሕብረተሰብ ስብጥር መካከል ልዩነት አለ። በምዕራባዊው ስልጣኔ ውስጥ የክርስትና እና የአይሁድ ሃይማኖት አሻራ መኖሩ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ የምዕራቡ ስልጣኔ በነዚህ ሁለት ሃይማኖቶች መሠረት ላይ የታነጸ ነው ማለት ግን ፈጽሞ የሚቻል አይደለም። ይልቁንም ተቃራኒውን ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ እንችላለን። ስልጣኔው የታነጸው በአጠቃላይ ሃይማኖትን በመጻረር፣በተለይ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን የበላይ ተቆጣጣሪነት በመቃወም ላይ ነው። በነጠረ የአእምሮ እሳቤ (rationalism) በዓለማዊ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ስልጣኔ ነው ማለት ነው። ይህም ሃይማኖትን ሙሉ በሙሉ ከሕይወት በሚነጥለው ዓለማዊነት (secularism) ጎልቶ የወጣ ሲሆን፣ ሁለታችሁም በዚህ ላይ ከኔ ጋር ትስማማላችሁ ብዬ አስባለሁ።
ሁለተኛውን አስተያትህን ግን እቀበላለሁ። ግና ከነዚህ የእስላማዊ ስልጣኔ መለያ ባሕርያት የሚከተሉት ነጥቦች ተጨምቀው የሚወጡ መሆናቸውን መጨመር እፈልጋለሁ።
•በእስላማዊ ስልጣኔ ውስጥ ከባድ እንዱስትሪ የሰውን ልጅ አብቅቶ ማምረት ነው። ይህም ለተፈጥሯዊ ስብጥሩ ትኩረት በመስጠት፣ሰብአዊ ፍላጎቶቹን በማርካት፣ከዩኒቨርስ ጋር ያለውን መጣጣም እውን በማድረግ፣የተፈጠረለት ግብና ዓለማ በማሳካት ላይ ያነጣጠረ ቀረጻና እነጻ ነው።
•በአንድ በኩል ሃይማኖትና ዓለማዊ ሕይወትን (ዲንና ዱንያን) ማስተሳሰርና ማሰባጠር፣በሌላ በኩል ደግሞ ሃይማኖትን አእምሮንና ሳይንስን ማጣጣምና ማስተሳሰር ሲሆን፣በዚህ መሠረት ላይ ስነምግባርንና የስልጣኔ ክንዋኔን ማነጽ ነው።
•በሰው ልጅ የዕውቀት ምንጮች ላይ የሚዘናዊነት፣ የወጥነትና የመጣጣም ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ ነው። ከቁሳዊው ጋር የተያያዙም ሆኑ ከዚያ ውጭ ካለው ጋር የተያያዙ እውነታዎች ሁሉ ሰው ሊደርስባቸው የሚችሉ ሲሆኑ፣በተሰጡትና እርስ በርሳቸው በሚደጋገፉ የተለያዩ የግንዛቤ መሳሪያዎቹ ሊደርስባቸው ይችላል . . ከደመነፍሳዊ ግንዛቤው ጀርባ ሕዋሳዊ ግንዛቤ፣ከሕዋሳዊ ግንዛቤው ጀርባ ደግሞ አእምሯዊ ግንዛቤው፣በወሕይ (መለኮታዊ መገለጥ) በኩል የሚመጣውን ዕውቀት ለመቀበል ወደሚያዘጋጁት ከሕዋሳት ግንዛቤ በላይ (ጓይብ) ወደሆኑ የሩቅ ግንዛቤ መቅድሞች ያደርሰውና አምኖ ለመቀበልና ለመታዘዝ ያበቃዋል።
•ተጽእኖ በማሳደርም ሆነ በመቀበል ለሌሎች ስልጣኔዎችና ባህሎች ራሱን ክፍት ማድረግ። ይህም ከሌሎች ሕዝቦች የተገኘውንና ከእስላማዊ ስልጣኔ ጋር የሚጣጣመውን ከራሱ ጋር በማሳለጥ፣ሌሎች ሕዝቦችም ከእስላማዊ ስልጣኔ ውጤቶችና መከሰቻዎች ይቋደሱ ዘንድ በሩን በመክፈት ነው።
ራጂቭ፦ ራሽድ ይቅርታ አድርግልኝ፣ማይክል ቅድም የእስላማዊ ስልጣኔን ጨፍጋጋ ጎን የሚመለከት መረጃ እንዳለው ተናግሯልና ስዕሉ የተሟላ ይሆን ዘንድ ፍቀድለትና እናዳምጠው።
ማይክል፦ በዚህ ላይ የሚቀርበው ዋነኛው ትችት በዚህ ስልጣኔ ላይ የቆመው መንግስት የተመሰረተው በሰይፍ በጎራዴ ነው፣ከማስገደድና ከኃይል እርምጃ ጋር የተሳሰረ ነው የሚለው ነው።
ራሽድ፦ ወዳጄ፣ለስልጣኔ ማበብ አንዱ ዋነኛ መስፈርት ሠላምና መረጋጋት በመሆኑ ጎራዴ ከቶም ስልጣኔን አይመሰርትም። ይህ ደግሞ ከዐረቦች ሁኔታ ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም ነው። ወታደራዊ ድልም እንዲሁ የግድ በእሳቤ በባህልና በስልጣኔ መስክም ድልን መቀዳጀት ማለት አይደለም። የተታሮችን የመንጎላውያንንና የሌሎቹንም ሕዝቦች ታሪክ መለስ ብለህ ብታስተውል፣አከርካሪ የሚሰብር ብርቱ ወታደራዊ አቅም የነበራቸው ሲሆን በዚህ አቅማቸው ግን ስልጣኔን አልመሰረቱም . .
እስላም በጦር በጎራዴ በጅሃድ ነው የተስፋፋው የሚለውን አሉባልታ ማለትህ ከሆነ ግን፣እስላም የሙስሊሞች ጦር ባልደረሰባቸው ሰፋፊ የዓለም ክፍሎች ውስጥም ስልጣኔውን የመሰረተ መሆኑን ብቻ ልጠቅስልህ እፈልጋለሁ። ይህ ርእሰ ጉዳይ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያካትት ነው። ለማንኛውም ግን ብዙ ታላላቅ ምዕራባውያን ሊቃውንት ወደሰጡት ምስክርነት እወስደሃለሁ። The New World of Islam የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት አሜሪካዊው ጸሐፊ ሎሥሮፕ እስቶዳርድ እንዲህ ይላሉ፦ ‹‹ዐረቦች ፈጽሞ ደም ማፍሰስን የሚወድ፣ጥፋትና ውድመትንም የሚፈልግ ሕዝብ ሆነው አያውቁም። የዚህ ሁሉ ተቃራኒ የሆኑ፣የከበረ ስነምግባርና ሰብእና የነበረው፣ዕውቀት መገብየትን የሚናፍቅ፣ከቀደሙት ስልጣኔዎች ለደረሳው የእነጻና የመገራት ጸጋ ግምት የሚሰጡጥና ተሰጥኦ ያለው ሕዝብ ነበሩ። በአሸናፊዎችና በተሸናፊዎች መካከል የእሳቤዎች መጣጣምና መሳለጥ የተንሰራፋ ከሆነ እርስ በርሳቸው በቀላሉና በፍጥነት ይቀላቀላሉ፣ደባለቃሉ። ከዚህ ቅልቅልና መቀያየጥ ነው አዲሱ ስልጣኔ - የዐረቦች ስልጣኔ ያበበው።››
የፈረንሳይ ጦር የቀድሞ መኮንን የሆነው ኮንት ሄንሪ ዴ ካስትሬ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ ‹‹ . . ይህ ሃይማኖት ዛሬ የሚገኝበትን ሁኔታ መፈተሽ፣በጎራዴ ነው የተሰራጨው የሚሉትን ወገኖች አሉባልታ መድረሻ ያሳጣዋል ብለን እናምናለን። የሙሐመድ ﷺ ሃይማኖት በኃይልና በማስገደድ የተስፋፋ ቢሆን ኖሮ፣ስርጭቱ ከድል አድራጊ ሙስሊሞቹ ፍጻሜ ጋር ባከተመ ነበር። የምንመለከተው እውነታ ግን ቁርኣን አሁንም ክንፎቹን በምድሪቱ ጥጎች ሁሉ እንደዘረጋ መቀጠሉን ነው . . ››
እስላማዊው ስልጣኔ በሰው ልጅ ታሪክ ላይ የተወውን አሻራ ከሚገልጹ ከፈረንሳዊው የታሪክ ሊቅ ከጉስታፍ ሊቦን ቃላት የተሻለ እውነተኛ አገላለጽ አላገኝም፤እንዲህ ይላሉ፦
‹‹በታሪክ ውስጥ እንደ ዐረቦች ጉልህ የሆነ አሻራ ያሳረፈ ሌላ ሕዝብ አናገኝም፤ከዐረቦች ጋር ትስስር የነበራቸው ሕዝቦች ሁሉ ለተወሰነ ዘመን ቢሆን እንኳ ስልጣኔያቸውን ወስደዋል . . ››
በመጨረሻም ዛሬ ባለው ስልጣኔ ጥላ ስር፣ሰብአዊ መለያ ባሕርያቱን በማውደም አማካይነት በሰው ልጅ ላይ ያንዣበበው አደጋ ምን እንደሚመስል መመልከት የናንተ ፈንታ ነው። የተጋረጠው አደጋም የእስላማዊ ሕብረተሰብ ምስረታን ሰብአዊና ተፈጥሯዊ ግዴታ የሚያደርግ ነው።