ሕንድ . . የድንቃድንቅ አገር

ሕንድ . . የድንቃድንቅ አገር

ሕንድ . . የድንቃድንቅ አገር (1)

ጆርጅ የአይሮፕላን ማረፊያውን የቪዛ ሂደት ጨርሶ ሲወጣ፣ሊቀበለው የመጣውን ማይክልን አገኘው። በኢሜል አድራሻው ልኮለት ከነበረው ፎቶግራፉ ለይቶ ያወቀው ማይክል ሞቅ ያለ አቀባበል አድርጎለት ወደ ሆቴሉ መሄድ ወይም በከተማው አጭር ጉብኝት ማድረግ ይፈልግ እንደሆነ ጠየቀው።

- አመሰግናለሁ፣በጉዞውና በሰዓት ለውጡ ምክንያት ድካም ስለተሰማኝ ወደ ሆቴሉ ውሰደኝ። ምናልባት ወደ ቢሮ ከመሄዳችን በፊት ነገ ጧት ትንሽ ዞር ዞር ማለት እንችል ይሆናል።

ጆርጅ የማይክልን እስከ መጨነቅ ደረጃ የሚቀርበውን የበዛ ሽቅርቅርነትና የሰለጠነ ምግባሩን አስተውሏል። በውድ መኪናው አብሮት ሲጓዝም በዚህ በድሆች በተጨናነቀች አገር ውስጥ የሀብታም ቱጃሮች መደብ አባል መሆኑን ለማወቅ ጊዜ አልወሰደበትም።
ጆርጅ ሌሊቱን በቂ እንቅልፍና እረፍት ካገኘ በኋላ፣ በቀጣዩ ቀን ጧት ልክ አንድ ሰዓት ላይ ንቁ ሆኖ ከክፍሉ ወጣ። ማይክልን ሆቴሉ እንግዳ መቀበያ ውስጥ ቁጭ ብሎ ሲጠብቀው አገኘው። ትናንት እንዳየው ሁሉ ትኩረት የሚስብ የተሟላ ሽቅቅርነቱን እንደ ጠበቀ ነበር። ሠላምታ አቅርቦለት ወደ መኪናው ገብተው ሄዱ።

- ለአንድ ሰዓት ያህል ዞር ዞር ብለን ብንጎበኝ ምን ይመስለሃል? ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ ወደ ቢሮ እንደርሳለን።

- መልካም ነው፣ሕንድን ማወቅ እፈልጋለሁ።

ማይክል፣ሕንድ
ጥንታዊትና ታሪካዊት አገር በመሆኗ እየተኩራራ ሕንጻዎችንና አብያተክርስቲያናትን ሲያስተዋውቅና ማብራሪያ ሲሰጥ ነበር ሙሉውን ጊዜ ያሳለፈው። ጆርጅ ጥያቄ ቢያቀርብም ማይክል ስለ አንዳንዶቹ ግዙፍ ሕንጻዎች መናገርን ሆን ብሎ የሚሸሽ መሆኑን ጆርጅ አስተውሏል። በየቦታው ስለሚገኙት የቡድሃ ማምለኪያ ሐውልቶችም ምንም ከመናገር ይቆጠብ ነበር። ጆርጅ ካንድ ጊዜ በላይ ጠይቆት፣ሕንድን የክርስትና አገር ብቻ አድርጎ ለማቅረብ የሚፈልግ ይመስል መልስ ሳይሰጠው አድበስብሶ አልፎታል። ጆርጅ ምንም ሀሳብ ሳይሰጥ በመመልከት ብቻ ተወሰነ፣ማይክል አክራሪ ካቶሊክ መሆኑን ካኽ ነግሮት አንደነበረ ትዝ አለው።
ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ ጆርጅና ማይክል ወደ ቢሮው ደርሰው በሥራዎቹ፣በፕሮጄክቶቹና በውል ስምምነቶቹ ላይ በውይይት ተጠምደው እስከ አምስት ሰዓት ቆዩ። በጅርጅ አካሄድ እርካታ የተሰማው ማይክል ድንገት ራሱን ቀና አደረገና እንዲህ አለው፦

- አንተም እንደኔ ክርስቲያን ነህ፣ይሁዲው ካኽ የሁሉንም ተቀጣሪ ውሎች እንዲያጭበረብር ለምን እንፈቅድለታለን። የማዛባቱ ነገር በሕንዱዎች፣በቡድሂስቶችና በሙስሊሞች ላይ ብቻ የተወሰነ እንዲሆንና የክርስቲያኖች ውል ከሁሉም የተሻለ እንዲሆን ብናደርግ ምን ይመስለሃል፣ይህ ይሁዲ እንዲሰርቀን አልፈልግም !

- ሕንዱውን ቡድሂስቱንና ሙስሊሙን መስረቅስ ፍትሐዊ ነው? !

ማይከል ተሸማቆ ዝም አለ . . ያከናውኑት ወደ ነበረው ሥራ ተመልሰው እስከ ሰባት ሰዓት ድረስ ቀጠሉ። ሰባት ሲሞላ በጣም ደክሞት ነበርና ጆርጅ ዕረፍት ጠየቀ።
ወደ ሆቴሉ ለመሄድ በመጡበት መንገድ ተመለሱ። አንድ ትልቅ ሕንጻ ሲመለከት ጆርጅ ሆን ብሎ ለማይክል በድጋሜ ጥያቄ አቀረበ፦
 

- ይህን ውብ ሕንጻ ማነው የገነባው?

- ሙስሊሞቹ ናቸው . . ወራሪዎቹ ሙስሊሞች።

- ይኸኛውስ ምንድነው?

- ኋላ ቀር የሆነ የቡድሂዝም ቤተ መቅደስ ነው . . በድንጋዮችና እንደኛው ባሉ ሰዎች ያመልካሉ ! !

ማይክል በነዚህ ጥያቄዎች ደስተኛ አለመሆኑን ስላወቀ፣ጆርጅ ቀሪውን መንገድ በዝምታ እያዳመጠው መጓዙን መረጠ . .

ሕንድ . . የድንቃድንቅ አገር (2)

ማይክል አስር ሰዓት ላይ ለምሳ አብረው ለመሄድ እንደሚመጣ ለጆርጅ ነግሮት ተስማምተዋል። ቀለል ያለ ግን ለአቀባበሉ በቂ የሆነ ድግስ አዘጋጅቶለታል። ጆርጅ ከመኝታ ክፍሉ ወደ መኪና እንደገባ ማይክል በመገረም ስሜት ጠየቀው፦
 

- ካኽ ወደኛ በሚመጣበት ጊዜ የሚጠይቃቸው የተለመዱ ነገሮች አሉ፤አንተ ግን ስትጠይቅ አላየሁም !

- ምንድን ይሆን?

- ወደ ሬስቶራንቱ እስክንደርስ ድረስ መልሱን እናቆየው፣ በሚጠብቅህ ያልተጠበቀ ነገር ትደሰታለህ ብዬ አምናለሁ !

ወደ ታጅ ኦፍ ኢንዲያ ሬስቶራንት ደረሱ። በሁሉም ገጽታው ታላቅነትንና ታሪካዊነትን የሚያንጸባርቅ ሲሆን፣የቦታው ውበትና አስደናቂነቱ የጆርጅን ትኩረት ስበዋል። ባህላዊ አሠራሩ መስህብነቱን ጨምሯል። ጆርጅ በልማዱ የማይወደው ቢሆንም እንኳ ቦታውን ያወደው የሕንድ ዑድ ሽቶ መዓዛ አስደስቶታል። ማይክል አንዳች መልክት የሚያስተላልፍ ፈገግታ አሳየውና ለርሱ የተያዘለት ልዩ ክንፍ ከዚህ ይበልጥ ውብና ማራኪ እንደሚሆን ነገረው።
በሬስቶራንቱ ልዩ ክንፍ ውስጥ፣ጆርጅ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመት አካባቢ የሚገመት ሁለት ውብ ኮረዶችን አየ።
ወደርሱ እየተመለከቱ ፈገግታ ያሳዩ ነበር። እሱም በአጸፋ ፈገግታ እያሳየ ጨበጣቸው።
ማይክል
በዓይኑ ጠቀስ አድርጎት ደጋግሞ ትከሻውን ቸብ ቸብ አደረገና፦
 

- ያልተጠበቀውን አስደሳች ዱብዳ እንዴት አየኸው? አለው።

- ግሩም ድንቅ ነው።

- ካኽ በመጣ ቁጥር ለምሳ ወደዚህ ቦታ ነው ይዤው የምመጣው። ከዚያም ሁለቱን ኮረዶች ወይም አንደኛዋን አስደሳች ሌሊት በአብሮነት ለማሳለፍ ወደ ሆቴሉ ይዞ ይሄዳል።

የመከፋት ስሜት የሚስተዋልበት የጆርጅ ፊት ጨፍገግ ብሏል፣በቀዘቀዘ አነጋገር መለሰለት፦

- እኔን በተመለከተ ግሩም ድንቁ አስደሳች አጋጣሚ የቦታው ውበት ብቻ ነው ።

- የሚገርም ነው፣ኮረዶቹ አልተመቹህም? !

- በእርግጥ ሁለቱም ውብ ቆነጃጅት ናቸው። የምትገርመው ግን አንተው ነህ ! እኔ ካኽ አይደለሁም !

- እንዴት ማለት?

- ካኽ የሚሰራው ጥሩ ነገር ሆነና ነው እኔም እንደሱ የምሰራው? !

- በዚህ መንገድ እንጅ ካኽ ውሎቹን ጭራሽ አይፈርማቸውም !

- እናም ውሎቹን እንድፈርም የቀረበልኝ ጉቦ ነው ማለት ነዋ !

- ይቅርታ፣ምንድነው የምትፈልገው?

- እኔ ባለትዳር ነኝ፣በባለቤቴ ላይ ክህደት መፈጸም አልፈልግም። የኔማ ማይክል ክርስትና ይህችው ናት? !

- ልክ ነህ . . ልክ ነህ !

አስተናጋጁ የምግብ ሜኖውን አምጥቶ ለማይክል አቀረበና በሕንድኛ ከተነጋገሩ በኋላ ሄደ። ሁለቱ ኮረዶችም ተከትለውት ሄዱ። ፈገግታ ለማሳየት እየሞከረ ወደ ጆርጅ ዞር አለና፦

- በራሴ ምርጫ ልዘዝ ወይስ አንተ ራስህ ትመርጣለህ?

- ምግቡን ከኔ ይበልጥ ስለምታውቀው አንተ ምረጥ።

ጆርጅ የሰፈነውን የውጥረት አየር ለመቀየር ሲፈልግ፣ከሕንድ መስቀል እንዲያመጣላት ደጋግማ የጠየቀችውን ካትሪና አስታወሰ። ከሕንድ የሚመጣላት መስቀል፣ክርስቲያኖች ሕንድ ውስጥ በሙስሊሞች ላይ የተቀዳጁትን ድል፣ፓክስታን ከሕንድ ባንግላዴሽ ከፓኪስታን የተገነጠሉበትን ሁኔታ የሚያስታውሳት ስለመሆኑ የነገረችው ትዝ አለውና ለማይክል እንዲህ አለው፦

- በእጅ ስለሚሰሩት ምርጥ መስቀሎች ከማንም ሰው በላይ ታውቃለህና ለባለቤቴ መስቀል መግዛት የምችልበትን ቦታ ልታመለክተኝ ትችላለህ?

- ሆቴል ክፍልህ ድረስ ይመጣልሃል . . በመቀጠልም ፦ ደሞም ዋጋውን ስለምነግርህ ጉቦ አይደለም ! ሲል አከለ።

- ታውቃለህ፣እኔ ፕሮቴስታንት ክርስቲያን ብሆንም ክርስትናን አላውቅም። እስከገባኝ ድረስ አንተ ሃይማኖተኛ ነህና ስለ ሃይማኖቴ ልታሳምነኝ ትችላለህ? !

- ክርስትና ከእግዚአብሔር የተላለፈ መለኮታዊ ሃይማኖት እንጂ እንደ ሰው ሰራሽ ምድራዊ ሃይማኖት አይደለም።

- የትኞቹን ሃይማኖቶች ማለትህ ነው?

- ቡድሂዝም፣ሕንዱ፣ዞረስትሪያንና የመሳሰሉትን ማለቴ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ መሰል ሃይማኖቶች ሕንድ ውስጥ ይገኛሉ።

ጆርጅ ከአደም ጋር ያደረገው ውይይት ወደ ትውስታው ሲመጣ፣ ስለ ሃይማኖቶች ያለውን አመለካከትና መገኘታቸውን እንዴት እንደሚተነትን ለማወቅ፣ጥያቄዎቹን ለማይክል ማቅረቡን የመቀጠል ፍላጎት አደረበት።

- ክርስትና ወይም ሌላው ምድራዊ ሳይሆን መለኮታዊ ሃይማኖት ስለመሆኑ ማረጋገጫው ምንድነው?

- ይህን የሚያረጋግጠው ታሪክ፣ሲወርድ ሲዋረድ የተላለፈ ማስረጃና ምስክርነት ናቸው። የሕንዱ እምነት ተከታይን ብትጠይቀው ክርስትና መለኮታዊ ሃይማኖት ነው፣ህንዱ ሰዎች በየጊዜው የሚያሻሽሉት ሃይማኖት ነው . . ይለሃል።

- ነገሮችን በማቅለል ስልት መለኮታዊ ሃይማኖቶች ከምድራዊ ሃይማኖቶች ይበልጥ ትክክለኞች መሆናቸው ማወቅ የሚቻል ይመስለኛል።

- ማቅለል የሚለው ውብ ቃል ነው። አዎ ይበልጥ ትክክለኞችም ናቸው፣በዚህ ጥርጣሬ አለ? !

- ይህ የሁሉም ክርስቲያኖች አቋም ነው። እኔ በቀላሉ የምፈልገው ግን ያንን በራሴ ማረጋገጥና በገዛ ዓይኔ ማየት ነው።

 

በሁነቶችና በውይይቶች የተሞላና የተጨናነቀ ቀን ካሳለፈ በኋላ ጆርጅ ወደ ሆቴሉ ሄደ። ገብቶ በጀርባው እንደተዘረረ ያሳለፈውን ሁሉ ማጠንጠን ያዘ። ‹‹ነገሮችን በቅለት እንጂ በውስብስብነት፣ በደስተኝነት እንጂ በትካዜ ላለመመልከትህ እርግጠኛ ሁን›› የሚለውን የአደም አነጋገር ሲደጋግም ራሱን አገኘ።

በሕንድኛ የሚቀርብና የእንግሊዝኛ መግለጫ ያለው ፕሮግራም ለማግኘት ቴሌቪዥን ከፈተ። የሕንዱ ሃይማኖትንና
ሞራላዊ ትምሕርቶቹን አስመልክቶ ይቀርብ የነበረው ፕሮግራም፣የሕንዱ ሃይማኖት ለተፈጥሮ ኃይላት ቅድስናን በመስጠት
ላይ የተመሰረተው የኣርያኖች ሃይማኖትና በአመዛኙ የጥንት ሕንዶች ይወዷቸው በነበሩ ነገሮች ላይ የሚያተኩረው የቀደምት ሕንዶች ሃይማኖት ቅይጥ መሆኑን ያረጋግጣል። ከጊዜ በኋላ ማሻሻያ ተደርጎ አንድ ዓይነት የመዋሐድ ሁኔታ ተከሰተና - ያንዳንድ ማሕበራዊ መደቦች ልዩ መብቶች እንዳይጠፉ በመስጋት - እነዚህን ጉዳዮች የሚመለከቱ እሳቤዎችን በጽሑፍ ማስፈር ጀመሩ። የእሳቤዎቹ ስብስብም ኋላ ላይ ቪዳ ወይም ወይዳ ተብሎ ተሰየመ። ወይዳ የተባለው በሕንዱዎች ዘንድ ዋነኛው ቅዱስ መጽሐፍ ሲሆን ትርጉሙ ሕግ ወይም ጥበብ ማለት ነው። እነዚህን ሕጎች በጽሑፍ አስፍረው ማኖሩን የቀጠሉ ሲሆን፣የሕጎቹ ዓለማ የቆዳ ቀለሙ ነጭ የሆነው አናሳው የኣርያን ዘር መደብ፣የቆዳ ቀለሙ ጥቁር በሆነው የብዙኃኑ መደብ ላይ ልዩ መብቶች እንዳሉት ማረጋገጥና መብቶቹን ማስከበር ነው። ለአናሳው መደብ ማለቂያ የሌላቸው ልዩ መብቶች የሚሰጡ እነዚህ ሕጎች እየበዙና እየገዘፉ በመሄዳቸው በቃል ጠብቆ ማቆየት ከማይቻልበት ደረጃ ሲደረስ ጽፈው ማኖር ጀመሩ። የመጻፉ ሂደትም ለአስር ምእተ ዓመታት ማለትም ለአንድ ሺ ዓመት የቆየ ሲሆን፣ካሁን በኋላ ምንም ነገር አይጨመርበት የሚል የሕንዱ ካህናት ጠቅላይ ጉባኤ ውሳኔ እሰካስተላለፈበት ጊዜ ድረስ ቀጥሏል። ውሳኔው ባይተላለፍ ኖሮ ጭማሬው እንደቀጠለ ይቆይ ነበር። መጽሐፉ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ጥራዞች ያሉት ግዙፍ መጽሐፍ ነው። ከሁሉም በላይ የጆርጅን ትኩረት የሳበው የሕንዱ ሃይማኖት ሕንድ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ብቻ የሚያገለግል፣ሕንዱዎች በሃይማኖት መሪዎቻቸው ጉባኤ ላይ እምነቱ የሕንዶች ብቻ መሆኑንና የሕንዱ አማኝ ከሕንድ አገር ውጭ በሚሆንበት ጊዜ ሕንዱ መሆኑ እንደሚቀር መወሰናቸውን የሚያመለክተው የቲቪ ፕሮግራሙ ክፍል ነበር። ለቦታ ሳይቀር ጠባብ ወገንተኛ በሆነው በዚህ አስገራሚ ሃይማኖት የፌዝ ሳቅ ሳቀ፤ሆኖም ራሱን ያዝ አደረገና፦

- ለማንኛውም ይህ የሰብአዊ ፍጡራን ገዳይ እንጂ መለኮታዊ አይደለም። በቀላሉ ይኸው ነው! . . የፍለጋየን ውጤት ማየት የጀመርኩ ያህል ነው የተሰማኝ። ይሁን እንጂ ይህ ብቻ በቂ አይደለም . .

ሕንድ . . የድንቃድንቅ አገር (3)

ጧት ሁለት ሰዓት ላይ ማይክል በቀጠሮው መሰረት ጆርጅን በእንግዳ መቀበያ ሳሎን ሆኖ በመጠባበቅ ላይ ነበር። ገና ጆርጅን ሲያይ ፈገግ እያለ ሰላምታ አቀረበለትና በቁርጠኝነት ቅላጼ፦

- ዛሬም ልክ እንደ ትናንቱ የተራዘመ ሥራ እየጠበቀን ነው፣ዝግጁ ነህ?

- በትክክል፣ የመጣሁት ለዚህ ነውና።

ወደ ቢሮ በመጓዝ ላይ እያሉ የቡድሃን ሐውልት የማይመስል እንግዳ የሆነ ሐውልት ተመለከተና አትኩሮ ለማየት ራሱን ዘንበል አደረገ። ማይክል ቀድሞት ሳቀና፦

- ምን ሆንክ? ይኸ ከአማልክቱ ውስጥ አንዱ አምላክ ነው። ምድራዊ ሃይማኖቶች በየቀኑ አዲስ አምላክ ይቀረጽላቸዋል አላልኩህም ነበር?

- የነዚህ ምድራዊ ሃይማኖቶች አማኝ ከሆነ ሰው ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ።

- አሃ፣ዛሬ ከኩባንያችን የኦፕሬሽን መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ጋር ነው ምሳ የምትበላው፣አጥባቂ የቡድሂዝም ሃይማኖት ተከታይ ናት።

ወደ ኩባንያው መሥሪያ ቤት ደረሱና በሥራ ተጠመዱ። ጆርጅ ሙሉ በሙሉ ከካኽ እንደሚለይ ማይክል እያስተዋለ መጥቷል። ጆርጅ ለሃይማኖት ትኩረት የሚሰጥ ስለ እምነቶች የሚጠይቅና የማወቅ ጉጉት ያለው ሲሆን፣በተጨማሪም የሚያከብረውና የሚመራበት መርህ ያለው ሰው ነው። ካኽ ግን በተቃራኒው ከገንዘብና ከወሲብ ውጭ የሚያሳስበው ምንም ነገር የለም። ስድስት ሰዓት አካባቢ ሥራውን ሲያጠናቅቁ ማይክል ወደ ጆርጅ ትንሽ ቀረብ ብሎ ለስለስ ባለ ቅላጼ፦

- ከጨርሰን ዘንዳ፣አእምሮዬ ውስጥ የሚመላለስ አንድ ነገር ልነግርህ እፈልጋለሁ፣አለው።

- በል ንገረኝ።

- ሁለታችሁም ካንድ ኩባንያ ብትሆኑም፣አንተ ካኽን ፈጽሞ አትመስለውም።

- አሃ፣የሬስቶራንቱን ኮረዶች ማለትህ ነው?

- ይኸኛው አንዱ ብቻ ነው፣ሌሎችም ብዙ አሉ።

- መልካም፣የነዚህ ልዩነቶች መንስኤ በአንተ አስተያየት ምንድነው?

- መንስኤው በቀላሉ ሃይማኖት ነው።

- አንተ ሃይማኖተኛ እየሆንክ የካኽን ፍላጎት ታስፈጽም የለ?

- ምናልባት፣ይሁን እንጂ . . እኔ የምፈጽመው ነገር ሁሉ የግድ ትክክለኛ ነው ማለት አይደለም።

ማይክል ለመሄድ ተነስቶ እንደ ቆመ ፊቱን ወደ ጆርጅ መለሰና፦
 

- ጂዮስቲናን ማግኘት አትፈልግም?

- ጂዮስቲና ማን ነች?

- ቡድሂስቷ የኦፕሬሽን መምሪያ ሥራ አስኪያጅ ነች . . ጂዮስቲና ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?

- አላውቅም።

- ትርጉሙ የጨረቃ ብርሃን ማለት ነው። ፈገግ አለና ፦ እህህ፣ግና ዕድሜዋ አሁን ወደ ስልሳ ዓመት ነውና ጉቦ አይደለችም።

- ልክ ነህ፣ላገኛት እፈልጋለሁ፣ዛሬ አስር ሰዓት ላይ በሆቴል ከኔ ጋር ምሳ መብላት ትችላለች ?

- ይቻላል፣ከርሷ ጋር ከተገናኘህ በኋላ የክርስትናን ጸጋ ትረዳለህ . .

ጆርጅ ለምሳ ቀጠሮው ከክፍሉ ሲወጣ ዕድሜዋ ትንሽ ገፋ ያለ፣ የሕንድና የቻይና ዝርያ ቅልቅል ገጽታ ያላት፣ወይም እንደዚያ የመሰለችው ሴት ቁጭ ብላ እየጠበቀችው ነበር። ጠጋ ብሎ ሰላምታ አቀረበላት፦

- ወይዘሮ ጂዮስቲና እንኳን ደህና መጣሽ።

- እንኳን ደህና መጣاህ፣ካንተ ጋር በመገናኘቴ ደስተኛ ነኝ።

በሆቴል ቤቱ ሬስቶራንት ክፍት ቡፌ ለምሳ ጋበዛት። አመሰገነችው። ትሁትና በጣም ጨዋ ሴት መሆኗ በግልጽ ይታይ ነበር።
ጆርጅ ለመቀመጫ ወደ ጥግ ያለውን ጠረጴዛ መረጠ። በድጋሜ እንኳን ደህና መጣሽ አላትና፦
 

- ማይክል ስላንቺ ብዙ ብዙ ነግሮኛል።

- ስላንተም እንዲሁ ማይክል ብዙ ነግሮኛል። ስለ ቡድሂዝም ማወቅ ስለምትፈልግ ከኔ ጋር ምሳ ለመብላት መጠየቅህንም ነግሮኛል!

- ልክ ነው።

- ወደ ውይይቱ ከመግባታችን በፊት አንድ ነገርህ ትኩረቴን ስቧል፣እኔ ብቻ ሳልሆን መላው የኩባንያው ሠራተኞች ይህንኑ ነው የሚናገሩት።

- ምንድን ይሆን?

- እንደ ካኽ አለመሆንህ ነው።

- እንዴት አወቁ?

- በክርስቲያኖች፣በቡድሂስቶች፣በሕንዱዎችና በሙስሊሞች መካከል በቅጥር ውል ስምምነት ልዩነት ማድረግንና ኮንተራቶቹን ማጭበርበርን እምቢ አልቀበልም የማለትህ ወሬ በስፋት ተሰራጭቷል። ሁለቱን ቆነጃጅት ኮረዶች አለመቀበልህና ሌሎችም ሰራተኛው ዘንድ ተዳርሰዋል።

- ይህ ያስደስታቸዋል ማለት ነው?

- ቢያንስ ለኔ እንደ ቡድሂስት፣ . . እጅግ በጣም ያስደስተኛል።

- ውሎችን ማጭበርበርና ማዛባትን መቃወም ግልጽ ነው፣ በትዳር ላይ ክህደት መፈጸም ግን እንዴት ይታያል?

- እኛ ቡድሂስቶች ክህደትንና ለሥጋዊ ፍላጎት መረታትን እንጠላለን። ይህ ብቻ ሳይሆን የእኩይ ነገሮች ሁሉ መሰረት ሦስት ነገሮች መሆናቸውን እናምናለን። የመጀመሪያው ፦ ለሥጋዊ ፍላጎት መንበርከክና ተገዥ መሆን ነው። ከቡድሃ ትእዛዛት መካከል የሚከተሉትን እናገኛለን ፦ ‹‹ሕይወት ያለውን ነገር አታጥፋ፣አትስረቅ፣አትናደድ፣አትዋሽ፣አስካሪ መጠጥ አትጠጣ፣ዝሙት አትፈጽም፣ያለ ጊዜው የበሰለውን ምግብ አትብላ፣አትጨፍር፣በጭፈራም ሆነ በዘፈን ድግስ ላይ አትገኝ፣ሐኪም አትጠቀም፣ፍራሽም ሆነ ምንጣፍ አይኑርህ፣ ወርቅም ሆነ ብር አትውሰድ››።

- እጅግ በጣም ድንቅ የሆኑ ትእዛዛት ናቸው፣መልካም ፈቃድሽ ከሆነ ግን አንዳንድ ጥያቄዎች አሉኝ ፦ በሐኪም የማትጠቀሙት፣ ወይም ወርቅም ሆነ ብር የማትወስዱት ለምንድነው? ፍራሽም ሆነ ምንጣፍ የማይኖራችሁስ ለምን ይሆን? ሶሻሊዝም ነው ወይስ ምንድነው ?

- ዓለማዊ ሕይወትን ችላ ማለትና ምናኔ ከዋነኞቹ የቡድሂዝም መገለጫዎች አንዱ ነው። ይህም ከጋብቻ መራቅ፣ሀብት ማካበትን መተው፣ራስን ችላ ማለትንና የሰማሃቸውን የመሳሰሉ ሌሎች ጉዳዮችን ያካትታል። ዓለማዊ ሕይወት የክፋት ሁሉ እናት ነውና።

- የቡድሂዝም ሃይማኖት ዋነኛ መገለጫ ይህን ዓለማዊ ሕይወት እንዳንኖርና እንዳንደሰት ማድረግ መሆኑ አስገርሞኛል። ገንዘብ መውደድና ወደ ተቃራኒ ጾታ መሳብ የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው . . ለመሆኑ ቡድሃ ማነው?

- ዓለማዊ ሕይወት የክፋት ሁሉ እናት ነው ብየሃለሁ። ምናኔና ዓለማዊ ሕይወትን ችላ ማለት የመልካም ነገሮች ሁሉ እናት ነች። ቡድሃ ማነው? ለሚለው ይህ ለመመለስ የሚያስቸግር ጥያቄ ነው !

- ቡድሃ ማነው የሚለውን መመለስ እንዴት ነው አስቸጋሪ የሚሆነው? አምላካችሁ፣ወይም መልክተኛችሁ፣ወይም የምትጠሩበት አዳኛችሁ አይደለም ወይ? !

- አስቸጋሪ ከሆነው ግማሹን አግኝተሃል። ነብይ ነው፣አዳኝ ነው፣አምላክ ነው ወይስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፣መምህር ነው ወይስ ሌላ ? . . በሚለው ላይ ከስምምነት የተደረሰበት አንድ አቋም የለንም።

- አይታመንም፣እንዴት ሊሆን ይችላል? !

- በዚህ ጉዳይ ላይ ሰሜን ቻይና ከደቡቡ፣በርማና ሲሪላንካ ፈጽሞ የተለያየ አቋም ነው ያላቸው። ለማንኛው ዋናው ጉዳይ ይህ አይደለም። ዋነኛው ጉዳይ ቡድሂስት ለመሆን መንፈሳዊ ምጥቀትና ልቀት እንዲኖርህ ነው።

- ነፍስን ማጥራትና መንፈስን ማላቅ ጋብቻና ሀብትን በመተው፣በአለባበስ ራስን በማስቸገር ነው? !

- አዎ፣አትሰርቅም፣አትዋሽም፣አትሰክርም፣አትገድልም።

ጆርጅ ከጂዮስቲና ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ ውድና ማራኪ የሆነው ልብሷ ከእይታው ውጭ አልነበረምና ሳሪዋን በትኩረት እየተመለከተ ሆን ብሎ ጥያቄ አቀረበላት፦

- ቡድሂስቶች በዚህ ተገዥዎች ናቸው?

- አዎ . . ፈገግ አለችና ፦ በተወሰነ ደረጃ፣የሕይወት ውጣ ውረድ በነዚህ ጥበባዊ ትእዛዛት መሰረት እንድንኖር አያስችሉንም።

- እናም ሞራላዊ ምክሮች ብቻ እንጂ ሌላ አይደሉም፣ ለአብዛኛው ሕዝብ ሕይወት የተመቹ አይደሉም ማለት ነዋ? !

- አሁንም በተወሰነ ደረጃ አዎ . . እናንተም ብትሆኑ እንደዚያው ናችሁ።

- ምን እያልሽ ነው?

- ግልጽ ልሁንና ማይክል በጣም ሃይማኖተኛ ነው፤ሆኖም ግን በየጉብኝቱ ቆነጃጅት ኮረዶችን ራሱ ለካኽ ያቀርብና የኮንትራት ስምምነቶችን ያጭበረብራል! አስካሪ መጠጥ የሚጠጡ ብዙ ክርስቲያኖችንም አውቃለሁ። እነዚህ ስህተቶች እናንተ ዘንድም ይገኙ የለም ወይ?

- ትክክል ነሽ፣ግን የኔ ትኩረት በራሱ በሃይማኖት ላይ ነው።

- ለኔ ልዩነቱ ብዙ አይደለም፣ሁላችንም የምንመሳሰል ይመስለኛል።

በመቀጠል ተመግባ ማብቃቷን ለማመልከት አፏን ማበስ ያዘች። ጆርጅ አስተናጋጁን ጠርቶ የሕንድ ጣፋጭ እንዲያቀርብላት አዘዘና ውይይቱን ቀጠለ፦

- በአምላካችሁ ወይም በነብያችሁ ወይም በ . . ላይ ስምምነትና የጋራ አቋም የላችሁም። በሕግጋት፣ በድንጋጌዎችና በትእዛዛት ላይ ስምምነት አላችሁ?

- እኛ እነዚህን ትእዛዛት በየጊዘው፣በየዘመኑና በየአገሩ እናሻሽላቸዋለን . .

- ታሻሽላላችሁ !!

- አዎ፣ቡድሂዝም ከጊዜ ጋር የሚሻሻል ሃይማኖት ነው። ክርስትናን በተመለከተ እናንተ እንደምትሉት መለኮታዊ ሳይሆን የኛ የእጅ ሥራ ውጤት ነው። አንዳንዶች መለኮታዊ መሰረት ነበረው የሚሉ ቢሆንም እኔ ግን እጠራጠራለሁ።

- ትንሽ የሚያሸማቅቅ ቢሆን እንኳ ቀጥተኛና ቀላል የሆነ ጥያቄ እንዳቀርብልሽ ትፈቅጂያለሽ?

- ቡድሂስቶች ሁሌም ማቅለልን ያፈቅራሉ፣አቅርብ።

- መለኮታዊ ሃይማኖት ከሰው ሰራሽ ምድራዊ ሃይማኖት የተሻለ ነው ብለሽ ታምኚያለሽ?

ጂዮስቲና ራሷን ትንሽ አቀርቅራ ለጥቂት ጊዜ ዝም ካለች በኋላ ራሷን ቀና አድርጋ መናገር ያዘች

- ላለመዋሸት ስል . . መለኮታዊ የሆነው በላጭ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም . . ይህ ከመርህ አኳያ ነው። በስተቀር ብዙ ቁጥራቸው የበዛ የመለኮታዊ ሃይማኖቶች ተከታዮች በጣም እኩይ ሰዎች ናቸው . . ፈገግ ብላ አከለች ፦ ለምሳሌ ያህል ይሁዲውን ካኽን፣ ከርሱ አነስ ባለ ደረጃ ደግሞ ክርስቲያኑን ማይክልን ውሰድ። ሁለቱ የሰዎችን ገንዘብ ያጭበረብራሉ፣ ይሰርቋቸዋልም !

- አውነት ነው . . ትክክል ነሽ፤ግን መለኮታዊ ሃይማኖትን ተቀብለሽ ጥሩ ለምን አልሆንሽም?

- ቡድሂስት ከሆኑ ወላጆች ነው የተወለድኩት፣በመሆኑም እኔ ቡድሂስት ነኝ። ግን ማን ያውቃል !! ምናልባት ከሞትኩ በኋላ ይሁዲ፣ሙስሊም ወይም ክርስቲያን እሆን ይሆናል።

- ከሞትሽ በኋላ? !

- አዎ . . እኔ ከሞትኩ በኋላ መንፈሴ ወደ ሌላ ግለሰብ ትዛወራለች፣አሁን እድሜዬ ስልሳ ነው።

- የሙታን መንፈስ ለአዲስ ሕይወት ወደ ሌሎች ተሸጋግሮ ይወለዳል ብለሽ ታምኚያለሽ?

- አላምንም፣ግን ሃይማኖታችን ውስጥ አለ።

በውይይቱና በእሰጣ አገባው ምክንያት ጂዮስቲና ድካም እንደተሰማት ፊቷ ያሳብቃል። በተለይ ደግሞ ሳታርፍ ከሥራ እንደወጣች በቀጥታ የመጣች በመሆኗ ከዚህ በላይ መቀመጥ ስለሚሳናት ውይይቱን የመቋጨት ፍላጎት አሳየች።

- ሌሎች ጥያቄዎች ወይም የማቀርብልህ አገልግሎት አለ?

- የለኝም፣አመሰግናለሁ። ብዙ ነው ያገለገልሽኝ፣ካንቺ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ።

ተሰናብቷት ሄደች።
ማይክል በቀኑ መጨረሻ ላይ ለጆርጅ ደውሎ፣የጠየቀው መስቀል እንግዳ መቀበያ ያለው ሰራተኛ ዘንድ የተቀመጠለት መሆኑን ነገረው። ትንሽ ቀልድ ብጤም አስከተለና

ደሞም ጉቦ ነው ብለህ እንዳትጠራጠር በሆቴሉ ቢል ላይ ተሞልቷል!
ጆርጅ አመሰገነውና አብረው ሳቁ።

- ንገረኝማ፣ከጂዮስቲና ጋር ከተገናኘህ በኋላ የክርስትናን ጸጋ አወቅህ አይደል?

- ከሞላ ጎደል።

- ውይይታችሁ ቢራዘም ኖሮ ጸጉር የሚያሸብቱ ጉዳጉዶችን በሰማህ ነበር። ስለ ምናባዊ እሳቤዎቻቸውና ስለ ፍልስፍናዎቻቸው ነግራሃለች?

- ምናባዊ እሳቤዎቻቸው ! . . አልነገረችኝም።

- አሀ፣ይሻላል፣ክርስትና የተሻለ መሆኑን ለማወቅ የነገረችህ ብቻ በቂ እንደሚሆን ብገምትም፣ያንን ብትነግርህ ኖሮ ሁለተኛ ወደ ሕንድ አትመለስም ነበር።

- ሁሉንም መለኮታዊ ሃይማኖቶች ማላትህ ነው?

- እንደዚያ ነው የሚታየኝ፣ወዳጄ በል ደህና ሁን፣በቸር እንገናኝ።

ጆርጅ እንቅልፍ እስኪወስደው ድረስ፣አልጋው ላይ ተንጋሎ የኢንተርኔት ድረ ገጾችን እየጎበኘና ቲቪ እየተመለከተ በሆቴል ክፍሉ ውስጥ አሳለፈ። ለርሱ አድካሚ የሆነ ቀን ነበር። አካላዊ ድካም ሳይሆን በተልእኮውና በሚፈጽማቸው ዝርዝር ጉዳዮች ጎን ለጎን ወደ ሕንድ እንዲመጣ በዋናነት በገፋፉት የግል ጥያቄዎቹ አእምሮው ተወጥሯል። በዚህ ሁሉ ማዕበል መሀል ‹‹ነገሮችን የምትወስዳቸው ቀለል አድርገህ ስለመሆኑ እርግጠኛ ሁን›› የሚለው የአደም ማሳሰቢያ ከትውስታው አልተለየም። ዛሬ የሰው ሰራሽ ምድራዊ ሃይማኖቶች መደናበርና ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የመጻረራቸው ሁኔታ በከፊል ግልጽ ሆኖለታል። እምነቱም ይኸው ነበርና እንደኛ ያለ ሰብአዊ ፍጡር ለምን ዓለማ እንደተፈጠርን እንዴት ልነግረን ይችላል?! በመሆኑም ብዙም ሳይቆይ ትልቅ እፎይታና ውስጣዊ እርካታ ተሰማው።

ሕንድ . . የድንቃድንቅ አገር (4)

በቀጣዩ ቀን ጧት ጆርጅ ወደ ትልቁ የዴልሂ የኮምፕዩተር ገበያ አመራ። በሕንድ የትልቁ የኮምፕዩተርና የሶፍት ዌር መሸጫ መረብ ባለቤት ወደ ሆነው የሙጢዕ ቢሮ ለመሄድ በአሳንሰር ወደ አምስተኛው ፎቅ ወጣ።
ቢሮው የተለመደ ዓይነት ሆኖ አገኘው። ግና ከውበቱና ከማራኪነቱ ጋር ቀለል ያለ ነው። አካባቢው በሕንድ የዑድ ሽቶ መዓዛ ተሞልቷል። የሙጢዕ ቢሮ የት እንደሆነ እንግዳ ተቀባይ ሠራተኛውን ሲጠይቅ፦
 

- ሸይኽ ሙጢዕ፣በቀኝ በኩል ነው። በቀኝ በኩል የመጨረሻው በር ላይ የጸሐፊውን ቢሮ ታገኛለህ፣አለው።

ሸይኽ ሙጢዕ፣ሸይኽ
! ምን ማለት ይሆን?
! ብሎ በመገረም ራሱን እየጠየቀ ወደፊት ቀጠለ። ኮምፕዩተር ላይ ይሰራ ለነበረው ጸሐፊ ሰላምታ አቅርቦለት ራሱን አስተዋወቀና ቢዝነስ ካርዱን ሰጠው። ከሙጢዕ ጋር ቀጠሮ እንዳለውም ነገረው።

- ይግቡ፣ሸይኹ ከአምስት ደቂቃ ጀምሮ እርስዎን እየጠበቁ ነው።

ጆርጅ ሰዓቱን ሲመለከት በእርግጥም ከሁለት ተኩል አምስት ደቂቃ አልፏል። ጆርጅ ከትልቅነቱ ጋር ዝብርቅርቅ መስሎ ወደሚታየው ቢሮ ሲገባ መጢዕ ብድግ ብሎ ተቀበለው። ስለ ትሕትናው አመስግኖ የሥራ ጉዳዩን ወደ መነጋገር ገቡ።

- መመስረት የምንችለው የትብብርና የአጋርነት አድማስ እስከ ምን ድረስ ሊሆን እንደሚችል ብታብራራልኝ?

- በቀላሉ ለኔና ለናንተም ጥቅም ሊያስገኝ በሚችል በማንኛውም ነገር ሊሆን ይችላል።

ጆርጅ በዚህ ቀለል ያለ ግን ጥልቀት ባለው አነጋገር ተደስቶ ሙጢዕን ጨበጠው። እየሳቀም ቀጠለ፦

- ተስማምተናል . . ይህ በታሪክ እጅግ ፈጣኑ ስምምነት ነው። ይሁንና ሁላችንንም የሚያረካ መንገድ የቱ እንደሆነ ማወቅ ይገባናል።

- እነዚህን ዝርዝር ጉዳዮች ወንድሜ ከሪሙሏህ ከኔ ይበልጥ የሚያውቃቸውና የተሻለ የሚገነዘባቸው ስለሚመስለኝ፣ከርሱ ጋር መነጋገር ትችላላችሁ። ለጊዜው እርሱ ስለሌለ ነገ ጧት ሦስት ሰዓት ተገናኙና የውል ስምምነት ዝርዝሩን አብራችሁ አዘጋጁ . .

- ደልሂንና አካባቢውን ጎብኝተሃል? ካልሆነ አንደ እንግድነትህ የማስተናገድ ግዴታ ስላለብን የጉብኝት ፕሮግራም አመቻችልሃለሁ።

- ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል አጭር ጉብኝት አድርጌያለሁ።

- አይ፣ምንም አላየህም ማለት ነው፤ሕንድ በጣም ሰፊ ታሪክ ያላት ጥንታዊት አገር ነች . . እንድናስተናግድህ ትፈቅድልናለህ?

- በጣም ደስ እያለኝ።

- መልካም እንግዳውስ ተዘጋጅ፣በአላህ ላይ ተወከል።

- ወዴት ነው?

- የጉብኝት ጉዞ ነው፣በታጅ መሐል እንጀምራለን።

ጆርጅ ከሙጢዕ ጋር ከግል ሾፌሩ ጋር ወደሚጠብቃቸው የሙጢዕ ባለምቾት መኪና አመሩ። ሙጢዕ ከኋላ ከጆርጅ ጋር ተቀመጠ።

- ወደ ታጅ መሐል የሚወስደው መንገድ አንድ ሰዓት ተኩል ያህል የሚፈጅ ሲሆን በዚህ ጊዜ የትራፊክ መጨናነቅ የለበትም። መንዱ በራሱ አንድ ሽርሽር ነው፣ታጅ መሐል ደግሞ ከዓለማችን ድንቅ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ቅርሶች አንዱ ነው። ራስህ ስለምታየው በኔ ገለጻ አላበላሽብህም።

- ማነው የገነባው?

- ንጉሥ ሻህ ጅሃን ነው። በአገረ ሕንድ የእስላማዊ ኪነ ሕንጻ ድንቅ ሞዴል ነው።

- እስላማዊ? !

- አዎ።

- ይቅርታ፣ግና ሙስሊሞች የሕንድ መሬት በጉልበት የነጠቁ፣ አጥፊ አረመኔ ሕዝቦች አይደሉም እንዴ? !

ሙጢዕ ፈገግ አለ . .

- አዎ . . ሕንድን ሰርቀናታል፣ሕዝቡንም ገድለናል፣ሀብቷንም ዘርፈናል !

- ኦ ይቅርታ፣አንተ ሙስሊም ነህ?

- አዎ ነኝ፣የምታውቅ መስሎኛል።

- ለጥያቄዬ ይቅርታ አድርግልኝ፣ስለሙስሊሞች የምንሰማው ግን ይኸው ነው።

- ምንም አይደለም፣እኔም ሆንኩ የተቀሩት ሙስሊሞች ሀብቷን ለመዝረፍ ከውጭ የመጣን ሰዎች አይደለንም . . እኔ ከነዘር ምንዛሬ ሕንዳዊ የሕንድ ልጅ ነኝ። ሕንድን ማን እንደሰረቃት ለማወቅ ከፈለግህ ወደ ታጅ መሐል ስትደርስ የሕንጻውን የከበሩ እንቁዎች ቆራርጦ የወሰደው ማን እንደሆነ ጠይቅ።

- ማነው?

- ስንደርስ የቱሪስት አስጎብኚውን ጠይቀው . . የምትሰማው መልስ እንደማያሸማቅቅህ ተስፋ አድርጋለሁ። በሙስሊሞች ላይ የሚወራውን ቅጥፈት ሁሉ ስለማውቀው ምላሽ ለመስጠት ግድ የለኝም። በሕንድ ታሪክ ላይ አጭር ንባብ ማድረግ ብቻ፣ ማለት የፈለኩትን ነገር ግልጽ የሚያደርግ ይመስለኛል።

 

- እንዴት?

- ኢንተርኔት ላይ በየትኛውም ሰርች ኢንጂን ‹‹የሕንድ ታሪክ›› ብለህ በመጻፍ ሕንድን ማን ወሮ እንደያዛትና ማን እንደ ሰረቃት፣ሙስሊሞች የአገሪቱ ነባር ወይም መጤ ሕዝብ መሆን አለመሆናቸውን ማወቅ ትችላለህ። በሙስሊሞች አገዛዝ ስር ሌሎች መደቦች እንዴት እንደኖሩም ግንዛቤ ታገኛለህ . . እየሳቀ ቀጠለና ፦ በእርግጥ ብዙ የተሳሳቱ ነገሮችም ነበሩ፣ከነዚህ ውስጥ አሁን የምንሄድበት ታጅ መሐል የታነጸው ለንጉስ ሻህ ጂሃን ሚስት መካነ መቃብርነት መሆኑ አንዱ ነው።

- በጣም ቀለል ባለ መንገድ ነው የምትናገረው !

- ሕይወትን ቀለል ባለ መንገድ ማየት አንዱ የደስተኝነትና የእርካታ ምልክት ነው።

ጆርጅ በጉዞው በጣም ተደስቷል። የከበሩ ዕንቁዎች የቅርስ ስርቆት በሕንጻው ላይ የተፈጸመው በእንግሊዞች የቅኝ አገዛዝ ዘመን መሆኑን ሲያውቅ መደንገጡ ባይቀርም ሙጢዕ የእንግዳውን ስሜት መጉዳት ባለመፈለጉ ሊነግረው አልፈገም ነበር። ጆርጅ በሙጢዕ ፈገግታና በቅን ልቦናው እጅግ የተማረከ ቢሆንም ያስተዋለበት አንድ ነገር ግን ብዙም አልተዋጠለትም። በዚህ ጉዞ ላይ ሙጢዕ ሦስት ጊዜ ‹‹ጠብቀኝ ሰግጄ እመለሳለሁ›› እያለው ትቶት ሄዷል። ለሥርዓት አለመጨነቅና ነገሮችን እንደመጡ የማስኬድ ባህሪም በሁሉም ነገሩ ውስጥ ጎልተው ይታያሉ።
የሙጢዕ የጉብኝት ፕሮግራም አብቅቶ ጆርጅ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ ወደ ሆቴሉ ደረሰ። በጣም ደክሞት ነበርና ሙቅ ሻወር ወስዶ ወደ መኝታው ሄደ። አልጋው ላይ እንደ ተዘረጋ ከሙጢዕ ጋር የሚደረገው ስምምነት ምን መልክ መያዝ እንዳለበት ማይክልን የማማካር ሀሳብ መጣለት።

- ሃሎ . . ደህና አመሸህ . . ትንሽ ነገር ላማክርህ ነው። ሙጢዕ ለስምምነት በጣም ገር ይመስላል። የማታለያ ገርነት ይሆን?

- ሙጢዕ ለኔ የሚመቸኝ ባይሆንም ሐቀኝነት ያለው እውነተኛ ሰው ይመስለኛል። በሥራዎቹ ላይ ቅንጅት ያንሰዋል፣ራሱን በሥርዓት ቢያቀናጅ የተሻለ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የሚችል ሰው ነው።

- ካኽ ግን ውስብስብና አስቸጋሪ ሰው ነው ይለኝ ነበር። ሆኖ ያገኘሁት ግን ተቃራኒውን ነው።

- አዎ፣በሃይማኖቱ ውስብስብ ነው። በበይነ ሰባዊ ግንኙነቱና በሥራ ግንኙነቶች ላይ ገር፣ቀለል የሚያደርግና የሚመች ሰው ነው። ሳቀና ቀጠለ ፦ በሥጋዊ ፍላጎቶቹና በኮረዶቹ ለካኽ ታዛዥ ባለመሆኑ ውስብስብ ነው። ለዚህ ነው ብዙ ረዣዥም ስብሰባዎች አብረው ቢቀመጡም ካኽ ከርሱ ጋር መስማማት የተሳነው። እንደኔ ሃይማኖተኛ የሆነ ሰው ቆነጃጅት ኮረዶችን ለካኽ የሚያቀርብበትን ምክንያት አሁን የተረዳህ ይመስለኛል !

- ነገ ከርሱ ጋር ውሉን ለመፈራረም ስለምሄድ የምትሰጠኝ የተለየ ምክር ይኖራል?

- ፈጽሞ . . ምንም ነገር የለም። መንፈስ ቅዱስ ይጠብቅህ። ነገ እንዳደርስህ ወይም ለጉብኝት እንድወስድህ ትፈልጋለህ?

- አመሰግናለሁ . . የሚያስፈልገኝ ነገር ካለ እደውልልሃለሁ።

- በቸር ያገናኘን።

ሕንድ . . የድንቃድንቅ አገር (5)

•ጧት በሆቴሉ ምግብ ቤት ውስጥ ቁርሱን በመብላት ላይ እያለ፣የተሰባበረ እንግሊዝኛ ከሚነገረው አስተናጋጅ ጋር ምልልስ አካሄደ፦

- ስምህ ማነው?

- ካቡር።

- ሕንድ የብዙ ሃይማኖቶች አገር ነች ይባላል፣ሃይማኖትህ ምንድነው?

- ሕንዱ ነኝ።

- ግሩም፣ሞራላዊ ሃይማኖት ነው።

- ልክ ነው፣ እንደዚያ ነው።

- በሃይማኖቱ መሪዎች ዘንድ፣ሕንድ ውስጥ ለሚገኝ ሰው እንጂ ለሌላው ሃይማኖቱን መከተል ትክክለኛ አለመሆኑና በዚህ ምክንያት ህንዱ ተብሎ መሰየሙ እውነት ነው?

- አዎ፣እውነት ነው፣ለሕንድ ነዋሪዎች እንዲስማማ አድርገን ነው ይህን ሃይማኖት የሰራነው።

- ሃይማኖት ሰራችሁ !!

- አዎ፣ለኛ እንዲስማማ አድርገን ሰራነው !

- የምታመልኩት አምላካችሁ ማነው?

- እኛ በዓለም ላይ ካሉት እምነቶች ሁሉ በአማልክት ብዛት የበለጸግን ነን !! ቁጥራቸው እጅግ በጣም የበዙ አማልክት አሉን። ስሞቻቸውን ዘርዝረን ለማስፈር ምናልባት ብዙ ጥራዝ መዛግብት ሊያስፈልግ ይችላል። ‹‹የስልጣኔ ትረካ›› መጽሐፍ ደራሲ ዎል ዲዮራንት እንዳለው ሁሉ እነኚህን አማልክት ለመመዝገብ የሚያስፈልገው ምናልባት እስከ አንድ መቶ ጥራዝ ይደርሳል።

- በጣም የሚያስደንቅ ነው !

- እንደ ጸሐይ ያሉ ጠፈራዊ አካላትን አማልክት አድርገን እናመልክባቸዋለን። አንዳንዶቹን አማልክት በመላእክት ባሕርያት አንዳንዶቹን ደግሞ በሰይጣናት ባሕርያት እንገልጻቸዋለን።

- ለሰይጣን ይበልጥ የቀረበ አምላክ !

- አንዳንድ ጠልሰሞች አማልክት ናቸው፤አንዳንድ አእዋፍም አማልክት ናቸው፤አንዳንድ እንስሳትም እንዲሁ አማልክት ናቸው።

- እንስሳ አምላክ !

- ዝሆን ለምሳሌ የሰው ልጅ እንስሳዊ ባህሪ መገለጫ የሆነው ‹‹ጃኒሻ›› አምላክ ነው። አንድ ጊዜ በመንደፍ ጋዳይ የሆነው እባብም ‹‹ናጃ›› አምላክ ነው። ለእባቦቹ ወተትና ለውዝ እናቀርብላቸዋለን፤የአምልኮት በዓላትም እናዘጋጅላቸዋለን።

- ለነዚህ ሁሉ አማልክት እንዴት ነው አምልኮት የምታከናውኑት?

- በአማልክቱ ቁጥር ብዛት የተነሳ በሦስት ወይም ሦስት በህርያት ባሉት አንድ አምላክ ውስጥ እናጠቃልላቸዋለን።

- አንድም ሶስትም የሆነ . . ልክ እንደ ክርስትና !

- ሃይማኖታችን በኛው በራሳችን እጅ የሚሻሻል ስለሆነ፣ ምናልባት ይህን ከክርስትና ወስድነው ይሆናል። ምናልባትም እናንተ ከኛ ወስዳችሁ ይሆናል።

- እህህ፣ቀጥልበትና አሟላው . .

- ለማንኛውም ሦስቱ አማልክት፣ወይም ሦስት በአንድ ወይም ሦስት አምላክ ፦ ፈጣሪ የሆነው ‹‹በራህማ››፣ዓለምን የሚጠብቀው ‹‹ቪሽኖ›› እና የውድመትና የጥፋትና አምላክ የሆነው ‹‹ሺቫ›› ናቸው።

- በድንቃድንቅ የተሞላ አስደናቂ ሃይማኖት ! ነገር ግን ስለ ላም ምንም አላልክም? ! . . ችሁ የምታደርጉ መሆኑን ሰምቻለሁ።

- አሃ፣ጋንዲ እንዳለው ሁሉ ላም አምላካችን ናት፣ከእናቶቻችን ይበልጥ እንወዳታለን፣እለሃለሁ። እናቴ አንድ ወይም ሁለት ዓመት ጡት አጥብታኝ ዕድሜ ልኬን አገለግላታለሁ። ላም ግን እድሜ ልኬን ወተት አጠጥታኝ ከኔ የምትፈልገው መኖዋን ብቻ ነው። እናቴ ስትሞት የቀብር ስነ ስርዓት ወጭ የምታስወጣኝ ሲሆን፣ላም ስትሞት ግን አጥንቷ እንኳ ሳይቀር ከሁለመናዋ ጥቅም እናገኛለን።

- ይህ የላም አምልኳችሁ ከሞት በኋላ ወደ ገነት ያደርሳችኋል ማለት ነው?

- እኛ ዘንድ ገነትም ሆነ ገሀነም የለም።

- ታዲያ በጎ ሰሪ የሚሸለመውና ክፉ ሠሪ የሚቀጣው እንዴት ነው? ወይስ ሁለቱም እኩልና ተመሳሳይ ናቸው?

- ጥሩ የሰራው ከሞተ በኋላ መንፈሱ ወደ ጥሩ ሰው በመዘዋወር ይሸለማል። ከዚያም ከመነሻ ጉዞው ከበራህማ አምላክ ጋር ሊዋሐድም ይችላል። ክፉ የሰራው ሰው ደግሞ ተኮንኖ መንፈሱ ወደ ተኮነነ ክፉ ሰው ይዘዋወራል።

- በዚህ ዓለም ላይ በደጉና በክፉ ሰው መካከል ልዩነት ታደርጋላችሁ?

- አዎ፣አንዳንዶቻችን ከአምላክነት ደረጃ የተወሰነ ድርሻ ይኖረዋል።

- እንዴት?

- ፈጣሪው ‹‹በራህማ›› እያንዳንዱን መደብ ከአካል ክፍሉ ውስጥ ከአንዱ ነው የፈጠረው። በራህማዎችን ከፊቱ ነው የፈጠራቸው። ስለዚህም የፍካሬና የጥበብ ሰዎች ናቸው። ከሽተሪዎችን ከክንዱ ነው የፈጠራቸው፣ስለዚህም የኃይል፣ የማጥቃት፣የጥበቃና የውትድርና ሰዎች ናቸው። ዌሽን ደግሞ ከጭኑ ነው የፈጠራቸው፣በመሆኑም የሚሰማሩት በንግድ፣ በእንዱስትሪና በምግብ ዋስትና ላይ ነው። ሾደርን ከሁለቱ ጫማዎቹ ነው የፈጠራቸው፣ስለሆነም አገልጋዮችና ባሮች ሲሆኑ ማገልገል ግዴታቸው ነው፤አምልኳቸውም የመጀመሪያዎቹን ሦስት መደቦች ማገልገል ነው። ካስቶችን በተመለከተ ግን በነዚህ አራቱ መደቦች ውስጥ አይገቡም፤ በሕንዱ ስብጥር ውስጥም አይካተቱም።

- ሾደር ብሆን ወደ በራህማዎች መደብ ከፍ ማለት እችላለሁ? ከካስቶች ወገን ብሆንስ ወደ ሕንዱ ሃይማኖት መግባት እችላለሁ?

- ፈጽሞ አይቻልም . . የሾደር ሃይማኖትና አምልኮ ሌሎቹን መደቦች ማገልገል ነው፤ካስቶች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከኛ ስብጥር ውጭ ናቸው።

ከመገረም ብዛት የጆርጅ ምላስ ተሳሰረ። ውስጡ ይህን እኩይ እምነት ክፉኛ ተጠየፈው፤ይሁን እንጂ ለማስመሰል ያህል ፈገግ አለና ጥቂት ገንዘብ ሰጥቶት ካቡርን አሰናበተው። ከከሪሙሏህ ጋር ካለው ቀጠሮ እንዳይዘገይ ተቻኩሎ ሄደ።
በመጓዝ ላይ እያለ የምድራዊ ሃይማኖቶችን አስከፊነት በመጥቀስ ማይክል ከጂዮስቲና ጋር የበለጠ ጊዜ አሳልፎ ቢሆን ኖሮ ሕንድን ይጠላ እንደነበርና ሁለተኛም ወደዚህ እንደማይመለስ የነገረውን አስታወሰ። በእርግጥም እነዚህ ሃይማኖቶች ከሰብአዊ አእምሮና ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው ተቃርኖ የትየሌለ ነው። ለመሆኑ ይህ የምድራዊ ሃማኖቶች አስከፊ ገጽታ ብቻ ነው? ወይስ ሐኪሙ ቶም
‹‹ሃማኖት የሚባለውን ሁሉ የጠላህ ሆነህ ነው የምትመለሰው›› እንዳለው የሁሉም ሃይማኖቶች የወል መገለጫ ነው? የሃይማኖተኛው ማይክል ባህሪም ያው የካኽ ባህሪ ነው፣ሙጢዕም ቢሆን በሥርዓተ አልበኝነት ጎኑ ከሁለቱ የተሻለ አይደለም
! አውነተኛ ሃይማኖት ከሰው አእምሮ፣ከተፈጥሮም ሆነ ከሎጂክ ጋር ፈጽሞ መቃረን እንደማይችል እርግጠኛ ነው። ይሁንና እንዲህ ያለ ሃይማኖት አለ ወይስ የለም . . ?

ሕንድ . . የድንቃድንቅ አገር (6)

ጆርጅ ልክ ሦስት ሰዓት ላይ ወደ ሙጢዕ ጸሐፊ ቢሮ ደረሰ። ከከሪሙሏህ ጋር ለመገናኘት እንደሚፈልግ ሲነግረው በሸይኹ ቢሮ ውስጥ እየጠበቀው መሆኑን ነገረው። ሲገባ ሁለቱ ወንድማማቾች ሙጢዕና ከሪሙሏህ ሲነጋገሩ አገኛቸው። ተነስተው ሰላምታ ተለዋውጠው ተቀበሉት። ከሪሙሏህን ሲያይ ገጽታው ብዙ ደስ አላሰኘውም። ለምን የመሸማቀቅ ስሜት እንደተሰማው ግን አላወቀም!

- ወደኔ ቢሮ እንሄድ፣ውሉን ለመጻፍ ተዘጋጅቻለሁ።

ሙጢዕ አቋረጣቸውና፦

- ከጨረሳችሁ በኋላ፣ጆርጅ ከመሄድህ በፊት ላገኝህ እፈልጋለሁ።

- እኔም ሳልሰናበትህ መሄድ አልፈልግም፡፡

ጆርጅ ከከሪም ጋር ወደ ቢሮው አመራ። ሰፋ ያለና ቀለል ያለ ቢሮ ነበር።

- ለሁለቱ ወገኖች ጥቅም በሚሰጥ ማንኛውም ውል ላይ እንደምንስማማ ወንድሜ ነግሮሃል።

- አዎ ልክ ነው . . ግን አንተ የሆነ ሰው ትመስላለህ . . !

- ኡሳማ ብን ላዲንን ነው የምመስለው ! አሀሃ፣አንተ እንዲህ ያለኝ የመጀመሪያው ሰው አይደለህም።

- እንደሱ እንደማትሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

- እኔም እንደሱ ሙስሊም ነኝ። እርሱ ዐረብ እኔ ሕንዳዊ በመሆኔ ከርሱ እለያለሁ።

- ማለቴ እንደርሱ ገዳይ አሸባሪ አይደለህም ማለቴ ነው።

- ይህን ርእስ ወዲያ በለው፣እናንተን ስለማያስደስትና ከናንተ ጋር ስለማይስማማ ነው አሸባሪ የሆነው።

- እንዴት ? እርሱና ተከታዮቹ አይደሉም ወይ የኛን ባቡሮች ሕንጻዎችና ተቋማት የሚያፈነዱት? !

- አንዳንዶቹ መሪዎቻችሁ እብን ላዲን የገደላቸውን በብዙ እጥፍ የሚበልጡ ሰዎችን ገድለዋል፣ግን አሸባሪዎች አድርጋችሁ አትስዷቸውም። ምዕራባውያን በወረራ በያዟቸው አገሮች ውስጥ ከዚህ በሺ እጥፍ የሚበልጥ ሕዝብ ፈጅተዋል፣አሸባሪዎች ሲባሉ ግን ሰምተን አናውቅም። ከዚያም ፈገግ አለና ፦ ጠላታችሁን ሩሲያን ይዋጋ በነበረበት ጊዜ ጀግና እንጂ አሸባሪ አልተባለም ነበር . . መልካም ፈቃድህ ሆኖ ይህን ተወንና ወደ ሥራችን እንግባ።

ጆርጅ በርሱና በከሪሙሏህ መካከል ክፍተት እየጨመረ መሆኑ ተሰማውና ከሥራው ውጭ ሌላ ምልልስ ውስጥ ላለመግባት ወሰነ። ማድረግ ያለበት ሥራውን በተቻለ መጠን በፍጥነት ማጠናቀቅ መሆኑን እያሰላሰለ፣ቶም እንዳለው ሁሉ እነዚህ ሙስሊሞች በታሪክ ትልቁ አሸባሪ ለሆነው ግለሰብ ይሟገታሉ ልበል
! ሲል ከራሱ ጋር ይነጋገር ነበር።

- መልካም፣ይሀ የኛ ርእሰ ጉዳይ አይደለም።

- ያዘጋጀህ የስምምነት ረቂቅ አለህ፣ወይስ የኛን ረቂቅ ልስጥህ ?

- ረቂቅ አለኝ፣ግን ያንተን ረቂቅ ስጠኝና ላንብበው።

- ይኸው እንካ።

- አመሰግናለሁ . . እንዳነበው ጥቂት ደቂቃዎች ስጠኝ።

ጆርጅ ረቂቁን ማንበብ ጀመረ። አንቀጾቹ ገርና ቀለል ያሉ መሆናቸውንና በራሱ ረቂቅ ውስጥ ለፍቶባቸው ከጻፈው የተሻሉ ሆነው አገኛቸው። ሆኖም ግን ረቂቁ ለኩባንያቸው ሰፊ ነጻነት ይሰጣል። የሆነ መጽሐፍ በማንበብ ተጠምዶ ወደነበረው ከሪሙሏህ ፊቱን አዞረና፦

- ተስማሚና ባጣም ግሩም ሆኖ ነው ያገኘሁት፣ግን አነስተኛ ማሳሰቢያ ግን አለኝ።

- በል አቅርበው፣ምን ይሆን ?

- ለናንተ ኩባንያ ትልቅ ነጻነት የሚሰጥና ለኛ የሚከፈለውን ገንዘብ የሚያዘገይብን አይመስልህም ?

- ሁለት ነጥቦች ናቸው ማለት ነው። ነጻነትን በተመለከተ ማሰራጨቱን በስፋት ማካሄድ እንዲያስችለኝ ነው፤ በተጨማሪም እያዘንኩኝ አኛ በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀን አይደለንም። የገንዘብ ክፍያ የመዘግየቱ ነገር ደግሞ ከናንተ ጋር ከተስማማን በኋላ መዋሸት ስለማንፈልግ ነው።

- መዋሸት አትፈልግም፣እንዴት ?

- ቃል ገብቼ ቃሌን ማፍረስ ነው። ነጻ ባልሆን በሀሰተኛና ተራ ምክንያቶች ባለመከፈሉ በተደጋጋሚ ይቅርታ ለመጠየቅ እገደዳለሁ፣ይህ ደግሞ እኔም እናንተም የማንፈልገው ነገር ነው። በተጨማሪም እነዚህ መስፈርቶች የናንተን የሽያጭ መጠን ከፍ ስለሚያደርጉ የበለጠ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ። ለክፍያው የተሟላ የባንክ ዋስትና ውሉ ውስጥ ተካቷል።

- ክፍያው በየሦስት ወሩ እንዲፈጸም በማድረጉ ላይ መስማማት እንችላለን ?

- ተስማምተናል። በሚቀጥለው ጊዜ ካኽ ወደኛ እንዳይመጣ ካንተ ጋር ገር መሆን እፈልጋለሁ።

- ካኽን ለምንድነው የማትፈልገው ?

- ይቅርታ አድርግልኝ፣አንተን ላለማስከፋት ስል መልስ አልሰጥህም።

- ፈጽሞ አታስከፋኝም፣ለምን እንደሆነ ንገረኝ ?

- እኛንና አሱንም ለኪሳራ በሚዳርግ ያልተገራ አቀራረብ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ብቻ የሚያስብ ሰው ነው። የኔ እምነት በመርህ መመራት ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ ያደርጋል። በተጨማሪም እኛ ልንቀበለው የማንችል ወሲብ ነክ ቃላትን ብዙ ጊዜ ይደጋግማል። ይቅርታ አድርግልኝና እኛ የምስራቅ ሕዝቦች ወግ አጥባቂዎች ነን።

- ምንም አይደለም፣ከተናገርከው ውስጥ እኔም በብዙው እስማማለሁ፣በውሉ ተስማምቻለሁ። ውሉ እዚህ ባለው የእንግሊዝ ኤምባሲ ይረጋገጥና ወደ ለንደን ስመለስ እዚያ በሚገኘው የሕንድ ኤምባሲ እንዲረጋገጥ አደርጋለሁ።

- አመሰግናለሁ፣ስለ አለቃህ በተናገርኩት ይቅርታ አድርግልኝ።

- ምንም አይደለም፣ከመሄዴ በፊት ሙጢዕን ሰላም ማለት እፈልጋለሁ

- በል እንሂድ።

ጆርጅና ከሪሙሏህ ወደ ሙጢዕ አርረሕማን ቢሮ ሲገቡ ለጆርጅ የተለየ ሞቅ ያለ አቀባበል አድርጎለት ጥያቄ አቀረበለት፦

- ውሉን አጠናቀቃችሁ ?

- አዎ።

- እንዳልኩህ ገር ቀላልና ያልተንዛዛ ነበር ?

- በጣም ገርና ቀለል ያለ ነው።

- ገርና ቀለል ያለ ነገር ሁሉ ስኬታማ ነው። የተወሳሰበና የተንዛዛ ነገር ሁሉ የሰውን አእምሮ ተፈጥሮንና ሃይማኖትን ይቃረናል . . ቀጠለና ፦ ካጠናቀቃችሁ ዘንዳ፣ጆርጅ ከሕንድ ማየት የምትፈልገውና የምንወስድህ ቦታ አለ ? መቼም የድንቃድንቅ አገር በሆነችው ሕንድ ቱሪዝም ማራኪ ነው።

- አመሰግናለሁ . . ዛሬ በጊዜ ወደ ሆቴል መመለስ እፈልጋለሁ፣ኢንተርኔት ላይ ማከናወን ያለብኝ ብዙ ሥራ ይተብቀኛል።

- እንግዲያውስ እንደ ፍላጎትህ ይሁን፣ አለና ከመሳቢያው ውስጥ ውድ የሆኑ ሁለት የሕንድ ዑድ ሽቶ እሽጎችን አወጣ። ይህ የኔ ስጦታ ነው፣ ብሎ በውብ ኪስ ውስጥ አደረጋቸው። ወደ ሆቴል ሊያደርስህ ሾፌሩ እየጠበቀህ ነው አለው።

- የትም የማይገኝ ምስራቃዊ መስተንግዶ ነው። እጅግ በጣም አመሰግነሃለሁ አለና ኪሱን ተቀብሎ ተሰናብቷቸው ወጣ።

ሕንድ . . የድንቃድንቅ አገር (7)

ጆርጅ፣ መምጣቱን የሚጠባበቀውን ሾፌር አገኘ። መምጣቱን ሲያይ ወደርሱ አመራና ወደ መኪናው ይዞት በመሄድ በሩን ከፈተለት።

- ጌታዬ ይግቡ።

- አመሰግናለሁ፣ስምህ ማነው ?

- እስቲቨን።

- ኦ፣የምዕራባውያን ስም !

- እኔ ክርስቲያን ነኝ፣ለዚህ ነው ስሜ የምዕራባውያን ስም የመሰለው።

- ከመቼ ጀምሮ ነው ክርስትና ሕንድ ውስጥ የኖረው ?

- ለረዥም ዓመታት ነው።

- ቅኝ አገዛዝና የክርስትና ሚሽናሪዎች በዚህ ውስጥ ሚና ነበራቸው ?

- ያለ ጥርጥር፣ባይሆን ኖሮማ ሙስሊሞች ሕንድን ባጥለቀለቁ ነበር።

- ሙስሊሞች ! በሽብራቸው ሕንድን ያጥለቀልቁ ነበር ማለትህ ነው ?

- አይደለም፣አንተ የምድራዊ ሃይማኖቶችን ዝቅጠት አታውቅም። የዘቀጡ አስቂኝ ሃይማኖቶች ናቸው። ሚስዮናዊ ዘመቻዎች ባይኖሩ ኖሮ ሰዎች ሁሉ በገዛ ፈቃዳቸው ወደ እስላም በገቡ ነበር።

- አንዳንዶቹን አውቅአቸዋለሁ፣መለኮታዊ ሃይማኖቶችም ከነሱ አይለዩም !

- ይገርማል ! ክርስቲያን ሆነህ እንዴት እንዲህ ትላለህ ? ይህማ የኤቲስቶች አነጋገር ነው !

- ኤቲዝም እርስበርሱ የሚቃረን በመሆኑ እጠለዋለሁ፣ይሁን እንጂ መለኮታዊ ሃይማኖቶችም ከምድራዊ ሃይማኖቶች ብዙ አይለዩም።

- እኛ ክርስቲያኖች ግን የሰው ልጅ ከጥፋት እንዲድን ነው የምንፈልገው። በንጽሕና በሞራል ላይ እናተኩራለን። ስለዚህም በምንም ዓይነት ክርስትናን መተቸት አልቀበልም። ከአንድ ክርስቲያን በኩል ሲመጣ ቀርቶ፣ የግል ሾፌሩ ከመሆኔና አድርጎት የማያውቅ ከመሆኑም ጋር ከሙስሊሙ ከሙጢዕ አርረሕማንም ቢመጣ እንኳ ይህን አልቀበልም። ምናልባት ፕሮቴስታንት ስለሆንክ ይሆናል፣ያም ቢሆን አልቀበለውም !

- ክርስትናን መተቸት አላሰብኩም ! ክርስትያን ሆኜ እንዴት እተቸዋለሁ ! ማለት የፈለኩት በተግባራዊ አፈጻጸም ከምድራዊ ሃይማኖቶች ጋር ይመሳሰላል ነው። እውር መደናበሩም ካንዳንድ ምድራዊ ሃይማኖቶች መደናበር ጋር ይመሳሰላል።

- አልገባኝም !

- ርእሱን ብንቀይርና ቀሪውን መንገድ ስለ ሕንድ ታሪክ ብትነግረኝስ?

- ለመድረስ ብዙ መንገድ አልቀረንም፤በጥቅሉ ፓኪስታን ባንግላዴሽና ሕንድ አንድ አገር ነበሩ፣ፓኪስታን ከሕንድ ተገነጠለች።

- ለምንድነው የተለያዩት ?

- ሙስሊሞች ከሕንዱዎች በኩል ይደርስብናል ባሉት ጭቆና ሲሆን ሳያስተውሉት ከሕንድ እንዲገነጠሉ ተገፋፉ። ያ ባይሆን ኖሮ ሕንድ ዛሬ እስላማዊት አገር በሆነች ነበር።

- ከነሱ ወገን ሳትሆን አንተ ብዙ ጊዜ ለሙስሊሞች ትከራከራለህ ! . . እነሱ ዘንድ ስለምትሠራ ነው ወይስ ስለምትፈራቸው ነው?

- እህ፣ ምናልባት !