ሁለት ሰዓት ከሩብ ከወሰደ ጉዞ በኋላ ሁለቱ ጓደኛሞች ራሽድ ከዚህ ቀደም ጎብኝቷት ወደማያውቃት ፓሪስ ደረሱ። የባቡር ጣቢያውን ለቀው ሲወጡ ማይክል ፓሪስን በሚገባ የሚያውቃትና በርሱና በከተማዋ መካከል የጸና ትስስር እንዳለው ሁኔታው ያሳብቅ ነበር።
ማይክል፦ ራሽድ! ይህች ፓሪስ ናት። ፓሪስ የብርሃን መዲና . . ከዚህ ስፍራ ነው ዓለም ‹‹ነጻነት - ወንድማማችነት - እኩልነት›› የሚለውን መፈክር ያወቀውና የሰብአዊ መብት መርሆዎች ለዓለም ያፈነጠቁት።
ራሽድ፦ ተመልከት! ማይክል ተመልከት! . . ይህችን ሴት ፖሊስ አስቆሟታል፣ጥፋት ወይም ወንጀል የሠራች አትመስልም!
ማይክል፦ ኦ፣ንቃብ ለብሳለቻ! ፈረንሳይ ውስጥ በአደባባይ ስፍራዎች ንቃብ መልበስን የሚከለክለው ሕግ ከሁለት ቀን በፊት ተግባራዊ ሆኗል። ፖሊሱ ያስቆማት ሕጉ የሚጥለውን የመቀጫ ገንዘብ የሚያስከፍል ካርኒ ሊቆርጥላት ይሆናል፤ለእስርም ትዳረግ ይሆናል።
ራሽድ፦ በአደባባይ ቦታዎች?! ሕጉ እቤቷ ውስጥ ንቃብ እንድትለብስ ይፈቅድላታል ማለት ነው . . ማ ሻአልሏህ! . . . ለሴት ልጅና ለሙስሊሞች ጫፍ የነካ ነጻነት ይሰጣላ! ድንቄም ነጻነት! አዎ ሕጉን አስታወስኩት። በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በቤልጂየም ተመሳሳይ ሕግ አለ፤በሰሜን ጣሊያንም አንዲት ከተማ ተግባራዊ አድርጋለች። በሆላንድ በእስፔንና በሌሎች የአውሮፓ አገሮችም ተመሳሳይ ሕግ ለማውጣት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። በአውስትራሊያ ደግሞ መንግስት ንቃብ የለበሱ ሴቶችን ፊት ገልጦ የማየትና ማንነታቸውን የማረጋገጥ መብት ለፖሊስ ሰጥቷል።
ማይክል፦ እኔ በግሌ ይህ እገዳ ሴት ያሻትን ነገር የመልበስ መብቷን እንዳትጠቀም ያደርጋታል የሚል እምነት አለኝ። የዚህ ሕግ መውጣት ፈረንሳይ ውስጥ መብትና ነጻነትን የሚሸራርፍ የኋልዮሽ ጉዞ ተደርጎ ይቆጠራል። የሌሎች መብቶች እንዲከበሩ የሚጠይቁ ከመቶ የሚበልጡ የሕግ አንቀጾች ባሉበት አገር ውስጥ ይህ ሕግ በቀጥታ የግለሰብ መብትን የሚጥስ ነው።
ይሁን እንጂ እነሱ የሚሉት እገዳው የሃይማኖት ምልክቶችን መጠቀም ከሚከለክለው የሪፐብሊካቸው መርሆ ጋር የሚጣጣም ነው። በተጨማሪም የፈረንሳይ መንግስት ንቃብ አዲስ ዓይነት ባርነት በመሆኑ የፈረንሳይ ሪፐብሊክ በግዛቱ ውስጥ አይቀበለውም ባይ ነው።
ራሽድ፦ የሴኩላሪዝም መርህ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን መጠቀም የሚከለክለው ለመንግስትና ለመንግስታዊ ተቋማት ብቻ እንጂ ለግለሰቦች አይደለም። ደግሞስ እገዳው ለምንድነው በሙስሊሞች ላይ ብቻ የሚጣለው?! አንገቷ ላይ መስቀል ያንጠለጠለችውን ወይም የመነኩሴ ዩኒፎርም የለበሰችውን ሴትስ ለምን አላጠቃለለም?! እነዚህ ሰዎች ለባርነት ጽንሰ ሀሳብ ያላቸው አመንክዮም አስገራሚ ነው። ሴት ራቆቷን እንድትሄድ መገፋፋትና የወንዶች ልቅ ስሜት ማርኪያ እንድትሆን ማጋለጥ ነው እውነተኛው ባርነት፣ወይስ በገዛ ፍላጎቷ ሴቲቱ ገላዋን የሚሸፍን ጨዋ ልብስ መልበሷ ነው ባርነት?! አዎ፣በእርግጥ ባርነት ነው፣ግና ለዓለማት ጌታ ለአላህ የሚደረግ ተገዥነትና ባርነት ነው . .
ወዳጄ፣የፈረንሳይ አብዮትን የነጻነት መፈክር ምንነት አሁን በደንብ ተረዳሁት . . ከፈጣሪ አምላክ ጋር ካለው ትስስር ነጻ መሆን፣ከርሱ ተገዥነት ራስን ማላቀቅ እንጂ ከሰብአዊ ፍጡራን ባርነትና ተገዥነት ነጻ መውጣት አይደለም። ከሰብአዊ ፍጡራን ነጻ የመውጣት መብት ራሳቸውን በፈጣሪ አምላክ ቦታ ያስቀመጡት የሴኩላር መንግስት ባለስልጣናት በሞኖፖሊ ይዘውት ለአሻቸው ሰውና በአሻቸው መንገድ የሚቸሩት መብት ሆኗል። የግለሰብ ነጻነት ገደብ እስከምን እንደሆነ ሲናገሩ ‹‹ያንተ ነጻነት የሚያበቃው የሌሎች ነጻነት በሚጀምርበት ቦታ ላይ ነው›› ይሉ ነበር። የሌሎች ሰዎችን የተራቆተ የሴት ገላ የመመልከት ፍላጎት፣የሙስሊሟን ሴት ነጻነት እንዲገደብ ማድረግ ያለበት ነጻነትና መብት አድርገው ይመለከታሉ ማለት ነው?! ነገሩማ የሕጃብ ችግር ሳይሆን አውሮፓ ለእስላም ያላት ስጋት ነው።
ማይክል፦ ወዳጄ ራሽድ፣ጉዳዩን በጣም አታካብደው። ብዙ ሙስሊሞች እንደ ሌላው ሁሉ መብታቸው ተከብሮ አውሮፓ ውስጥ ይኖራሉ። በአገሮቻቸው የማያገኙትን የትምህርትና የሥራ ዕድልም ያገኛሉ።
ራሽድ፦ እኔ ነገሩን አላካበድኩም። እስላምን በስጋት ዓይን መመልከታቸው ነው ለሚለው አባባሌ ብዙ ማሳያዎች ይገኛሉ።
ማይክል፦ እንዴት ያሉ ማሳያዎች?
ራሽድ፦ ለምሳሌ ያህል የሰብአዊ መብት ዘበኛ ነኝ በምትለው፣የገለልተኝነትና የጄኔቫ ስምምነቶች አገር በሆነችው ስዊዘርላንድ ውስጥ መስጊዶች ሚናሬት እንዳይኖራቸው መከልከሉ አንዱ ማሳያ ነው። የሙስሊሞች ቁጥር ከ4% በማይበልጥበትና አራት ሚናሬቶች ብቻ ባሉበት አገር ውስጥ የመስጊድ ሚናራዎች ምን ችግርና ጉዳት ያስከትላሉ?! እንዲህ ዓይነቱ እገዳ በውስጡ ለእስላም ያላቸውን ጥላቻና ጤናማ ያልሆነ ስጋት (እስላሞፎቢያ) ያዘለ መሆኑ በጣም ግልጽ ነው።
ማይክል፦ እኔ በግሌ ይህን እገዳ የማልደግፍ ቢሆንም፣እነዚህ ሚናሬቶች ከመንግስታቸው እሴቶች ጋር የሚጋጩና በአገራቸው ማንነት ላይ የተጋረጠ አደጋ አድርገው መመልከታቸውን ግን እረዳለሁ።
ራሽድ፦ እገዳው ቤተክርስቲያኖችንና የአይሁድ ቤተ አምልኮዎችን፣ጉልላትና የደወል ቤቶችን የማያካትት መሆኑን በአእምሮዬ ሳሰላስል፣መንግስታችን የታነጸበት መሰረት ነው የሚሉት ሴኩላሪዝም ወሰኑ እስከምን ድረስ እንደሆነ እገነዘባለሁ። የሚያራግቡት የመብትና የእኩልነት መፈክር እውነተኛ ገጽታው ምን እንደሆነም እረዳለሁ . . ነገሩ በዚህ ብቻ ሳያበቃ የእስላምን ነብይ እንኳ ሳይቀር ሁሉንም የእስላም ተምሳሌት የሚነካ ሆኗል። ይህንንም በዴንማርክና በጉዳዩ ላይ ከርሷ ጋር በተባበሩት ሌሎች አገሮች ውስጥ በታዩትና ነብያችንን በሚወርፉ የካርቱን መስሎች ቀውስ ወቅት ተመልክተናል።
ማይክል፦ ወዳጄ ይህ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ነው። በኛ አገር ሀሳብን በነጻ በመግለጽ መብት ውስጥ የተቀደሰ ወይም የተከለከለ የሚባል ነገር የለም። ኢየሱስ እራሱና ሌሎች የሃይማኖት ተምሳሌቶችም ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ የትችትና የስላቅ ሰለባ ሆነዋል።
ራሽድ፦ የለም፣ሀሳብን በነጻ በመግለጽ መብትም ሆነ በሳይንሳዊ ምርምር መብት እንኳ ሊተች የማይችል የተቀደሰና በማንኛውም ሁኔታ አይነኬ የሆነ ነገር አላችሁ። የዴንማርክ ጋዜጦች ነብዩን የሚዘልፉ ካርቱኖችን አትመው ካወጡና ቅሌቱ ወደተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ተጋብቶ፣ብዙ የአውሮፓ መንግስታት የአንድ ቢሊዮን ተኩል ሙስሊሞች ታላቁ ሃይማኖታዊ ተምሳሌት የሆኑትን ነብይ ለሚዘልፍ ካርቱን ጥብቅና ቆመው ሀሳብን በነጻ በመግለጽ መብት በማሳበብ ይቅርታ አንጠይቅም ካሉ በኋላ . . አንድ የሆላንድ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሆሎኮስት የይሁዲዎች ፈጠራ ነው ወይም ከእውነታው ጋር በማይገናኝ ሁኔታ የሰለባዎቹን ቁጥር አግዝፈውታል የሚል መልክት ያለው የካርቶን ስዕል ባሳተመ አንድ የሆላንድ ሙስሊሞች ማህበር ላይ የ2500 ዩሮ መቀጫ ጥሏል . . ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብያኔ ሲያብራራ፣ሀሳብን በነጻ ለመግለጽ መብት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውና ለመብቱ መከበር ብርቱ ጥረት የሚያደርገው የአውሮፓ ህብረት የሰብአዊ መብት ፍርድ ቤት ሆሎኮስትን ማስተባበል ወይም አሳንሶ ማየትን ከዚህ ውጭ አድርጓል ነው ያለው።
አንድ የፈረንሳይ ፍርድ ቤት በ1998 በፈረንሳዊው ፈላስፋ ጃሩዲ ላይ የአይሁዶችን ሆሎኮስት ተጠራጥሯል በሚል ክስ የጥፋተኘነት ብይን አስተላልፏል። የጃሩዲ ብቸኛ ጥፋት በናዚዎች እጅ አውሮፓ ውስጥ በግፍ ተፈጅተዋል ተብሎ የሚነገረውን የሰለባዎች ቁጥር ትክክለኛነት እጠራጠራለሁ ማለቱ ነበር።
በ2006 አንድ የነምሳ ፍርድ ቤት በእንግሊዛዊው የታሪክ ሊቅ ዴቪድ ኤይርቪንግ ላይ የአይሁዶችን ሆሎኮስት አስመልክቶ የሚወሩትን ዝርዝር ጉዳዮች በማስተባበሉ ምክንያት የሦስት ዓመት እስራት ፈርዶበታል።
በ2009 የጀርመን ፍርድ ቤት በእንግሊዛዊው የካቶሊክ ኤጲስ ቆጶስ በሪቻርድ ዊልያምሰን ላይ የ10 ሺህ ዩሮ መቀጫ ወስኗል። ጥፋታቸው በናዚዎች የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የተፈጁት አይሁዶች ቁጥር ከ200 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብቻ መሆኑን መናገራቸው ነበር።
ከዚህ አይነኬ ቅዱስ ነገር የምርምር ነጻነትም ሆነ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተብዬው ሊያድናቸው ያልቻለ ሰዎች ቁጥር በጣም ብዙ ነው።
ማይክል፦ በአውሮፓ ክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከል የነበረው የተራዘመ የጠላትነት ታሪክ፣ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚስተዋለው የሙስሊሞች የሽብር ጥቃቶች ጋር፣ለምሳሌ ያህል ለሕንዱዎችና ለቡድሂስቶች . . ካላቸው አመለካከት በተለየ ብዙ ሰዎች እስላምን በስጋት እንዲመለከቱትና እስላሞፎቢያ በስፋት እንዲሰራጭ ማድረጉ የማይካድ እውነት ነው። የአንዳንድ ሙስሊሞች ድርጊት ለእስላሞፎቢያ መፈጠር ዐቢይ ምክንያት መሆኑን ማስተባበል ትችላለህ?
ራሽድ፦ እነሆ ወደ እውነታው እየተቃረብን ነው። የአንዳንድ ሙስሊም ግለሰቦችና ቡድኖች ድርጊት ለሚቀናቀኗቸው ወገኖች በእስላምና በሙስሊሞች ላይ ያላቸውን ጥላቻ ለማቀጣጠልና እስላሞፎቢያን ለመንዛት የሚጠቀሙበትን ማመካኛ ያስገኙላቸው መሆኑን አላስተባብልም . . በተመሳሳይ ወቅት ግን ነገሮችን በተገቢ ቦታቸውና በትክክለኛ መጠናቸው ልናስቀምጣቸው ይገባል። በእስላምና በሙስሊሞች ላይ የሚካሄደው የማጥላላት ዘመቻ ሌሎች ገጽታዎች እንዳለትም መዘንጋት አንችልም። አንተ የጠቀስካቸው ክስተቶች፣ለእስላምና ለሙስሊሞች የከረረ ጥላቻ ላላቸው ዘረኛ ቡድኖች የሚያራምዱትን የነዚህን ሌሎች ገጽታዎች ዓላማ እውን ለማድረግ አገልግሎት ላይ ይውላሉ . . አለዚያማ ከወገንተኝነት ስሜት ነጻ ሆነን ነገሮችን ብንከታተል፣ከተከታዮቹ መካከል እንዲህ ዓይነቱን የወንጀል ወይም የጥላቻ ተግባራት ሊፈጽም የሚችል ተከታይ የሌለበት አንድም ሃይማኖታዊም ሆነ ጎሳዊ ቡድን አለመኖሩን እንገነዘባለን። የሚፈጽሙት እኩይ ተግባር በሚዲያ መቅረቡ ወይም ተድበስብሶ መቅረቱ አንደኛውን የትኩረትና የክትትል ዒላማ ሲያደርግ ሌላውን በቸልታ እንዲታለፍና ስሙ ሳይነሳ ተድበስብሶ እንዲቀር ያደርጋል።
ማይክል፦ ሌሎች ገጽታዎች አሉት ስትል ምን ለማለት ነው?
ራሽድ፦ እነዚህን ገጽታዎች ሁሉንም ሳይሆን አንዳንዶቹን እጠቅስልሃለሁ፦
አውሮፓ ቀደም ሲል ለተወሰኑ ዓላማዎች የስደት በሯን ለዐረቦችና ለሙስሊሞች ከፍታለች። ከዐበይት ዓላማዎቹ አንዱ በምዕራቡ ማህበረሰብ ውስጥ በተከሰተው የቤተሰብ መፈረካከስና መበታተን ምክንያት አውሮፓውያን ልጅ መውለድ በመተዋቸው የተፈጠረውን የሕዝብ ብዛት ሚዛን መዛባት ማካካስ ነበር። በእርግጥ በሩን ሲከፍቱ ታሳቢ ያደረጉት በእስላማዊ ወግና ልማድ ታንጸው ያደጉትን ጎልማሳ ስደተኞች ሳይሆን፣ከሃምሳ ዓመት በኋላ በአውሮፓዊ ሕብረተሰብ ውስጥ ሰርጾ መዋሐድ እንዲችል በአውሮፓ ባህልና ስልጣኔ ተቀርጾ የሚያድገውንና እዚያ የሚወለደውን ሁለተኛውን የስደተኞች ትውልድ ነበር . . የምዕራባውያኑ እስትራቴጂስቶች እቅድ ይህ ነበር።
ዳሩ ግና እስትራቴጂስቶቹ በሙስሊሙ ዓለም የተጀመረው እስላማዊ ተሐድሶ ወደ ምዕራቡ ዓለም መዛመቱንና ሙስሊም ስደተኞችንና ልጆቻውን በአውሮፓዊው ባህል ውስጥ የማስረጽና ከሕብረተሰቡ ጋር የማዋሀድ ሂደቱን ማሰናከሉን ተመለከቱ። በመሆኑም ሕጃብ የምትለብስ ሴት ልጆች ወይም ሃይማኖታቸውን የሚተገብሩ ሙስሊም ቤተሰቦች፣ሃይማኖታዊ እሴቶቻቸውንና እስላማዊ መርሆዎቻቸውን አጥብቀው የሚይዙ ወግ አጥባቂዎች ሆነው የመገኘታቸው እውነታ፣በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰርጸው እንዲዋሀዱና አውሮፓዊ ማንነት እንዲላበሱ የማድረጉ ሂደት እንዳይሳካ እንቅፋ የፈጠሩ ተደርገው እንዲወሰዱ አደረጋቸው።
እናም ይህ የሙስሊም ስደተኞች ልጆች ትውልድ ለምዕራቡ ዓለም የስርጸትና የውህደት ፕሮጄክት የስጋት ምንጭ ሆኖ ተገኘ። በዚህ ምክንያትም ምዕራባውያን ተጨባጭ የሆነ ችግር ከፊታቸው ተደቀነ። ያም ከአውሮፓዊው ባህልና ማንነት የተለየ ባህልና ማንንት የያዘ፣እያደገና እየተስፋፋ የሚሄድ ክፍለ ሕዝብ በመካከላቸው ተፈጥሮ የመገኘቱ እውነታ ነበር።
በመሆኑም የዚህ ዘረኛ ዘመቻ ዋነኛ ምክንያት ምዕራቡ ዓለም ማንነትን የማጣት አደጋ መራራ ስሜት የተሰማው መሆኑ ነው። እስላማዊ በሆነ ማንኛውም ገጽታ ወይም ተምሳሌት እንዲበረግጉ የሚያደርጋቸውም ይኸው ነው። እነዚህን ቀላል እስላማዊ ገጽታዎች በዝምታ ቢያልፉ የተቀረው እስላማዊ ሥርዓት ይዘምትብናል ብለው ይሰጋሉ . . ስለዚህም በእንጭጩ ለመቅጨት ወሰኑ። የተቀሩት ርእዮተ ዓለሞች ከመድረኩ ገለል ካሉ በኋላ የሥልጣኔዎች ፍጥጫና ትግል ከእስላም ጋር ሆኗል ማለት ይቻላል። ይህም በምዕራቡ ዓለም ያለውን ርእዮታዊ ፖለቲካዊ እሳቤ ለመግለጽ፣አሜሪካዊው ርእዮተኛ ሳሙኤል ሃንግቶን ‹‹የስልጣኔዎች ፍጥጫ›› በሚል ርእስ በለቀቀው ጥሪ የተገለጸው ነው።
ማይክል፦ ወደ ሆቴሉ ደርሰናል። አንተ የከፈትከው ርእስ ብዙ ውይይቶችን የሚፈለግ ነው።