ራሽድ በንቁ መንፈስና ስሜት በጉያው መጽሐፍ እንደ ሸጎጠ ላፕቶፑን ተሸክሞ ወደ ወዳጆቹ አቀና . . ቀረብ እንዳለም በችኮላ ሠላምታ አቀረበላቸውና ምላሽ ሳይጠብቅ መናገር ጀመረ፦
ዛሬ ለወዳጄ ለማይክል ጥያቄ ምላሽ መስጠት እጀምራለሁ . . እነሆ የእስላምን አበይት መገለጫዎች አብራራላችኋለሁ። ከነዚህ አበይት መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል አንደኛው በእስላም ነቢይና መልእክተኛ በሙሐመድ ﷺ ማመን መሆኑን ማንም አለ አይልም . . አንድ ምዕራባዊ ርእዮተኛ ስለ ሙሐመድ የጻፈውን ታነቡት ዘንድ መጽሐፉን አምጥቼላችኋለሁ . . ጸሐፊው የሚለውን ስሙት . .
ማይክል፦ ውድ ወዳጄ ራሽድ ተረጋጋማ . . እስላም በተለይ የሚታወቅበት ዋነኛው መገለጫ ስለ አምላክ ያለው እሳቤ ነው ብዬ እገምት ነበር።
ራሽድ፦ በአጠቃላይ አነጋገር ያልከው ትክክል ነው . . ያንን ትቼ ያለፍኩት በብዙ ምክንያቶች ሲሆን ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፦
እስላም የመልእክተኛው ﷺ መልእክት ከመሆኑ አንጻር፣አምላክን አስመልክቶ የሚያራምደውን እሳቤ የእስላም ነቢይ ያመጡት አዲስ ግኝት ነው አይልም። እሳቤው ከኣደም ጀምሮ እስከ አልመሲሕ እና ሙሐመድ ]በሁሉም ላይ የአላህ እዝነትና ሠላም ይውረድ [ድረስ የሁሉም ነቢያት ሃይማኖት መሆኑን ነው እስላም የሚያረጋግጠው። ይልቁንም እሳቤው የመላው የሰው ልጆች ሃይማኖት ስረ መሰረት ነው . . የሃይማኖት ስረ መሰረት ይህ ሆኖ ሳለ ግን የሰው ልጆች ናቸው ከዚህ ሃይማኖት የተዛነፉትና እሳቤውንም እንዲዛባ ያደረጉት። እስላም ሲመጣ የተዛባውን እሳቤ በማረም በአላህ ማመንን መልሶ፣መላው የሰው ልጅ ወደ አላህ ﷻ ተውሒድ ተመልሶ እንዲመጣና በአምልኮ ከርሱ ጋር ማንንም ምንንም እንዳያሻርኩ ጥሪ አደረገ . . በአላህ ማመንና ተውሒድ እስላም ውስጥ፣ከሰው ልጅ መፈጠር ጋር የጀመረና በዓለም ፍጻሜ ምድሪቱን እስኪሰናበት ድረስ የሚቀጥል፣በመላው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ተያይዞ በተዘረጋ ሰንሰለት ውስጥ የሕዳሴ ዘለበት ነው . . የእስላም ነቢይ ﷺ ከመወለዳቸው በፊት የነበረ ሃይማኖት ነው።
ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ባለፉት ውይይቶች የተስማማንባቸው ነገሮች፣ይህን ነጥብ ተራምደን ለማለፍ በቂ ያደርጋሉ የሚል እሳቤ ማሳደሬ ነው።
ራጂቭ፦ ቀደም ሲል የተነጋገርንበትን የእውነተኛው ሃይማኖት መስፈርት የሚያሟላው እስላም ነው ማለት ነወ የፈለግኸው?
ራሽድ፦ አዎ፣ትክክል ነው!
ራጂቭ፦ እንግዲያውስ ማቅረብ ወደምትፈለገው ከመሸጋገርህ በፊት፣እስላም ስለ አምላክ ያለውን እሳቤ አጠር አድርገህ ብትነግረን መልካም ነው።
ራሽድ፦ ጥሩ . . በእስላም አመለካከት የሰውን ልጅና ዓለማትን ሁሉ ካለመኖር አውጥቶ የፈጠረው አንድ አምላክ ብቻ ነው። በዓለማትና በፍጥረታት ውስጥ ካሉት እርሱን የሚመስል ምንም ነገር የለም። ‹‹የተፈጥሮ ሕግጋት›› ብለን የምንጠራቸውን የዩኒቨርስ ሕግጋትን ያኖረው እርሱ ነው። ነገሮችን ሁሉ በልካቸውና በመጠናቸው ወስኖ፣ነገሮችን ሁሉ በልካቸውና በመጠናቸው አቀናጅቶና አቀናባብሮ የዘረጋው እርሱ ነው። እርሱ ከሁሉም በላይ ኃያል፣ከሁሉም በላይ ታላቅና ከሁሉም ነገር በላይ ነው . .
በእርሱነቱ፣በባሕርያቱና በተግባሮቹ እርሱን የሚመስለው ምንም ነገር የለም። የፍጹማዊ ምሉእነት ባለቤት ሲሆን፣በየትኛውም በኩል ፈጽሞ እንከን ወይም ጉድለት አይጠናወተውም። ጥራት ይገባውና አልወለደም፣ አልተወለደምም፤አንድም ብጤ ሆነ አቻ የለውም። የሚያኖርና የሚገድል እርሱ ብቻ ነው። በማንምና በምንም ፍጥረታቱ ውስጥ አይሰርጽም፤ማንምና ምንም ነገር ፈጽሞ በእርሱነቱ ውስጥ አይሰርጽም . .
ይህ ፈጣሪ ጌታ ከርሱ በስተቀር ሌላ ፈጽሞ ሊመለክ የማይገባ አንድያ ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ነው። በንግሥናው ምንም ሸሪክ፣ተጋሪም ሆነ ተጠሪ፣አጋዥም ሆነ አማካሪ የሌለው፣ከርሱ ፈቃድ ውጭ እርሱ ዘንድ ማንም አገናኝም ሆነ አማላጅ ተቀባይነት የሌለው፣አምልኮት (ዕባዳ) በሁሉም መልኮቹና መገለጫዎቹ ሙሉ በሙሉ ለርሱ ብቻ የሆነ አንድ አምላክ ነው።
ማይክል፦ ያመጣኸው መጽሐፍ ስለምን የሚያወራ ነው?
ራሽድ፦ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ስለታዩት ታላላቅ ሰዎች ነው የሚናገረው። የተጻፈው በአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ ውስጥ ይሠራ በነበረ የስነፈለክና የማቴማቲክስ ሊቅ በዶክተር ማይክል ሃርት ነው።
ማይክል፦ ታድያ በታሪክ ጥናት ውስጥ ምን ዶለው?
ራሽድ፦ የታሪክ ጥናት የዚህ ምሁር ተወዳጅ ሆቢ ነው። ምሁሩ ከብዙ ሺህ ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ ኢንሳይክሎፔዲያዎች ውስጥ ስማቸው የተወሳው ሃያ ሺህ ግለሰቦች ብቻ መሆናቸውን አስተውሎ፣ከነዚህ መካከል የታላቆች ታላቅ የሆነ አንድ ሕያው ሰብእና ለመምረጥ መስፈርቶችን አስቀመጠ። ከመስፈርቱ ውስጥ ዋነኞቹ፦ ግለሰቡ ተረታዊ ወይም የማይታወቅ ሳይሆን ተጨባጭ ታሪካዊ ሰው መሆን፣ገንቢም ይሁን አፍራሽ ጥልቅ የሆነ ተጽእኖ ያሳደረ፣ተጽእኖውና አሻራውም ዓለም አቀፋዊ የሆነ፣የተጽእኖው አሻራ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሁሌ የማቋርጥና ቀጣይነት ያለው . . የሚሉ ናቸው። ለርእሱ የሚመጥን ግሩም መስፈርት ይመስለኛል።
ራጂቭ፦ በዚህ ጸሐፊ አመለካከት የታላላቆች ታላቅ ሆኖ ያገኘው ታሪካዊው ሕያው ግለሰብ ማነው?!
ራሽድ፦ ጸሐፊው በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ታላቆቹ አድርጎ ከመረጣቸው አንድ መቶ ሕያው ባለ ታሪኮች መካከል የእስላም ነቢይ የሆኑትን ሙሐመድን ﷺ ቁጥር አንድ የታላቆች ታላቅ አድርጓቸዋል። ለዚህ ምርጫው እርሱ ራሱ ያብራራቸው ምክንያቶች አሉት . .
በመቀጠል ራሽድ መጽሐፉን ይከፍትና ያነባል፦
‹‹በዚህ ዝርዝር ውስጥ ሙሐመድን ቁጥር አንድ አድርጌ መርጫለሁ። ብዙዎች በዚህ ምርጫ እንደሚገረሙ እሙን ነው፤ለዚህም እውነት አላቸው። ዳሩ ግና ሙሐመድ ﷺ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በሃይማኖታዊም ሆነ በዓለማዊው መስክ ፍጹም የሆነ ስኬታማነትን ያስመዘገበ ብቸኛው ሰው ነው።
ወደ እስላም ጥሪ አድርጎ ከታላላቅ ሃይማኖቶች ውስጥ አንዱ እስኪሆን ድረስ አሰራጭቶታል። ፖለቲካዊ፣ወታደራዊ እና ሃይማኖታዊ መሪ ሆኗል . . ከሕልፈቱ ከ13 ምእተ ዓመታት በኋላ የሙሐመድ ﷺ ተጽእኖና አሻራው ዛሬም ጠንካራና ታዳሽ ሆኖ ቀጥሏል።››
‹‹ . . የክርስቲያኖች ቁጥር የሙስሊሞች ቁጥር እጥፍ ቢሆንም፣የሙሐመድ በዚህ ዝርዝር ቁንጮ ላይ መቀመጥ ምናልባት እንግዳ ነገር መስሎ ሊታይ ይችል ይሆናል። ምናልባትም ዒሳ ቁጥር 3 ላይ፣ሙሳ ደግሞ ቁጥር 16 ላይ ሲቀመጥ፣በዚህ ዝርዝር ውስጥ ነብዩ ሙሐመድ ﷺ ቁጥር አንድ መሆኑ አስገራሚ መስሎ ታይቶ ይሆናል።
ይህ ግን የራሱ ምክንያቶች አሉት። ዋነኞቹ እስላምን በማሰራጨት፣በማጠናከርና የሸሪዓውን መሠረቶች በመትከል ላይ የመልእክተኛው የሙሐመድ ሚና፣በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ኢየሱስ ከነበረው ሚና ይበልጥ ከባድና ይበልጥ ታላቅ የነበረ መሆኑ ነው። በክርስትና ውስጥ ኢየሱስ የስነምግባር መርሆዎች መሪ ቢሆንም፣ለክርስትና ሕግና ሥርዓት መሠረቶችን ያነጸው ቅዱስ ጳውሎስ ነው። በተጨማሪም በአዲስ ኪዳን መጽሐፎች ውስጥ ለቀረቡት ብዙ ጉዳዮች መጻፍም ኃላፊነቱ የርሱ ነው።
መልእክተኛው ነቢዩ ሙሐመድን በተመለከተ ግን፣የእስላምን መሠረቶች ለማቆም፣የሸሪዓውን ሕግጋት ለመደንገግ፣ማሕበራዊና ሞራላዊ ስነምግባራትን ለማነጽ፣የሰዎችን ሃይማኖታዊና ዓለማዊ ሕይወት የሚያደራጁና የሚመሩ የበይነሰባዊ ግንኙነት መርሆዎችን ለማኖር የመጀመሪያውና ብቸኛው ኃላፊነት የነቢዩ ﷺ ነበር። ቅዱስ ቁርኣንም የወረደው በነቢዩ ላይ ብቻ ሲሆን፣ሙስሊሞች ለዓለማዊ ሕይወታቸውም ሆነ ለወዲያኛው የኣኽራ ሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያገኙት ከርሱ ]ከቁርኣን [ነው። . . ›› በዚህ አነጋገር አልተገረማችሁም?!
ራጂቭ፦ በእርግጥ ቆም ተብሎ ሊስተዋል የሚገባ አነጋገር ነው። መልካም ፈቃድህ ይሁንና፣ይህ ጸሐፊ ግን የሰብአዊ ሳይንሶች ጥናት ባለሞያ አይደለም።
ራሽድ፦ የሰብአዊ ሳይንሶች ጥናት ባለሞያ ባይሆን እንኳ፣አነጋገሩ አሳማኝና በተጨባጭ መሠረቶች ላይ የተንተራሰ ነው። ይሁዲ በመሆኑ ለሙሐመድ ﷺ የሚያዳላ ወገንተኛ ነው ተብሎ የሚታማም አይደለም። የሌሎችን ምስክርነት የምትፈልግ ከሆነም ፍቀድልኝና የአንዳንዶቹን ልደርድርልህ . .
ራሽድ ላፕቶፑን አውጥቶ ፋይሎቹን እያነበበ እንዲህ አለ፦
የኔ ወንድም ተመልከት፦
ፈረንሳዊው ባለቅኔ ላ ማርቲን እንዲህ ይላል፦ ‹‹ከሰው ልጅ ታላቅነት ደረጃ ሙሐመድ ከደረሰበት የደረሰ የትኛው ሰው ነው?! እርሱ ከደረሰበት የመጠቀ የምሉእነት ደረጃ የትኛው የሰው ልጅ ነው የደረሰው?! በፈጣሪና በፍጡር መካከል አገኛኝና አማላጅ የሚይዙ የተሳሳቱ እምነቶችን መልእክተኛው ደምስሷቸዋል።››
ተቀዳሚው ጀርመናዊ ባለቅኔ ጎቴህ ደግሞ ፦ ‹‹ለሰው ልጅ ምጡቅ የሆነ ምሉእ ተምሳሌት የሚሆን ሰብእና ለማግኘት ታሪክን ፈትሼ፣ዐረባዊውን ነቢይ ሙሐመድን ﷺ አገኘሁ›› ይላል።
ሩሲያዊው ዓለም አቀፍ የጥበብ ሰው ሊዮ ቶልስቶይ ፦ ‹‹የመለኮታዊ መልክቶች ማጠቃላያ የርሱ መልክት እንዲሆንና እርሱ ራሱም የነቢያት መደምደሚያ ይሆን ዘንድ አላህ በመረጠው በነቢዩ ሙሐመድ በእጅጉ ከተደመሙ ሰዎች መካከል እኔ አንዱ ነኝ›› ይላል።
የኖቤል የስነጽሑፍ ሽልማትን አልቀበልም ያለው፣ አይርላንዳዊው ጸሐፊና ፈላስፋ ጆርጅ ቤርናንድ ሾው ደገሞ ፦
‹‹የእስላምን ነቢይ የሕይወት ታሪክ በሚገባና ደጋግሜ አንብቤያለሁ። መሆን የሚገባውን ታላቅ ስነምግባር እንጂ ሌላ አላገኘሁበትም። እስላም የዓለም መንገድ ይሆን ዘንድም በጽኑ ተመኘሁ። እጅግ አሰደናቂ ሰው ከመሆኑ አንጻር ሙሐመድን አጥንቻለሁ። ኢየሱስን ከመቀናቀን በጣም የራቀ ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ይልቅዬም ‹የሰው ልጆች መድህን› ተብሎ መጠራት ይገባዋል›› ብሏል።
ማይክል፦ አሁን የምትናገረው በሙሐመድ ታላቅነት ላይ ያጠነጠነ ነው። ይሁንና ሙሐመድ በተጨባጭ የአላህ መልእክተኛ ስለመሆኑ ማረጋገጫው ምንድነው?
ራሽድ፦ ወዳጄ፣ስዊዘርላንዳዊው የስነመለኮት ሊቅ ሃንዝ ኮንግ የሚናገሩትን አዳምጥ፦ ‹‹ሙሐመድ በትክክለኛው የቃሉ ትርጉም እውነተኛው ነቢይ ነው። ወደ መድህን መንገድ የሚያደርስ መሪ እርሱ መሆኑን ማስተባበል የምንችልበት መንገድም ፈጽሞ የለም።››
ሙሐመድ ﷺ በእውነት የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች ይገኛሉ።
ማይክል፦ የምታስታውሳቸው ከሆነ ቢያንስ አንዳንዶቹን ጥቀስልን።
ራሽድ በኮምፒውተሩ ላይ ያሉትን ፋይሎች እያገላበጠ መናገር ቀጠለ፦
ሙሐመድ ﷺበእውነት የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን ከሚያረጋግጡት ማስረጃዎች መካከል፣ወደፊት እንደሚመጡ በቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት ውስጥ የሰፈረው ብሥራት አንዱ ነው። ኦሪት ዘዳግም ውስጥ እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ ብሏል፦ ((ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፣ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ።)) [ዘዳግም 18፣15-30] እንደሚታወቀው ሁሉ የእስራኤላውያን ወንድሞች የእስማዒል ልጆች (ዐረቦች) ናቸው። በተጨማሪም በሙሴ እና በሙሐመድ ﷺ መካከል ያለው ተመሳስሎ ከሌላ ማንኛውም መልእክተኛ ነቢይ ጋር ካለው ተመሳስሎ በጣም የበዛ ነው። ‹‹ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ›› የሚለው አባባልም ነቢዩ ሙሐመድ ﷺ የማያነቡና የማይጽፉ ነቢይ መሆናቸውን የሚጠቁም ነው።
አዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ ሚከተለውን እናገኛለን፦ ((ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለም ከናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ]ጰራቅሊጦስ[ ይሰጣችኋል፤)) [ዮሐ. 4፣15] PERIQLYTOS የሚለው የግሪክ ቃል ብዙ የተመሰገነ፣ምስጉኑ የሚል ትርጉም ያለው አበላላጭ ቅጽል ሲሆን፣ትርጉሙ ‹‹አሕመድ›› ከሚለው የዐረብኛው የነቢዩ ሙሐመድ ስም ጋር ተመሳሳይ ነው።
በተጨማሪም ‹‹እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ። (ዮሐ.15፣26) (( የሚለውንና ‹‹ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይናገርምና፤የሚመጣውንም ይነግራችኋል።)) [ዮሐ. 16፣13-14] የሚለውንም እናገኛለን።
ነቢዩ ﷺ ራሳቸው በተግባር የተፈጸሙ ብዙ ትንቢቶችን መናገራቸው፣የመልእክታቸው ሳይንሳዊ ታምራት፣ጽናት ያላቸው ሕግጋቱ . . ተጨማሪ ማስረጃዎች ናቸው።
ማይክል፦ የት አለ? . . ይህ ሁሉ ወዴት ነው ያለው?! ምሳሌዎችን አቅርብልን።
ራሽድ፦ ከአላህ ወደ ሙሐመድ ﷺ በተላለፈውና የነቢዩ ታላቁ ተአምር በሆነው ቁርኣን ውስጥ በብዛት ቀርበዋል።
ራጂቭ፦ እንግዲያውስ ከዚህ ቁርኣን ጋር መተዋወቅ በጣም አስፈላጊ ይሆናል ማለት ነው። በርሱ አማካይነት የነቢያችሁ እውነተኛነት እስከምን እንደሆነና የዚህ ሃይማኖት መሰረታዊ መርሆዎች ምን እንደሆኑ ማወቅ እንችላለን።
ራሽድ፦ ይህ ትክክል ነው፤ይሁን እንጂ ርእሰ ጉዳዩን ለሚቀጥለው ውይይታችን እንድናቆየው ሀሳብ አቀርባለሁ።
ማይክል፦ ከመለያየታችን በፊት የያዝከውን መጽሐፍ እንዴት ማግኘት እንደምችል ባውቅ ደስ ይለኛል።
ራሽድ፦ ይህ መጽሐፍ አብሮኝ ብዙ የኖረ የቆየ እትም ነው። ካረፍንበት ማእከል በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ አንድ መጽሐፍ መሸጣ ውስጥ የመጽሐፉን አዲስ እትም አይቻለሁና ከሚቀጥለው ውይይት በፊት መጎብኘት እንችላለን።